ምዕራፍ 2 · 23 ደቂቃ ንባብ · 30 ደቂቃ ማዳመጥ
የጃንዋሪ ወር
ጃንዋሪ 1
የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ተስፋ
«በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።» ዘፍጥረት 3:15
ይህ ለወደቀው ሰው የተሰጠ የመጀመሪያው ተስፋ ነው። ወንጌልን ሁሉ፥ የጸጋ ኪዳንንም ዋና ነገር ይዞአል። በብዙ መጠን ተፈጽሞአል። የሴቲቱ ዘር፥ ማለትም ጌታችን ኢየሱስ፥ በሰኮናው ተቀጠቀጠ፤ ያም መቀጥቀጥ አስፈሪ ነበር። የእባቡ ራስ የመጨረሻው መቀጥቀጥ ምንኛ አስፈሪ ይሆን! ኢየሱስ ኃጢአትን ባስወገደ፥ ሞትን ድል በነሣና የሰይጣንን ኃይል በሰበረ ጊዜ ይህ በእውነቱ ተፈጽሞአል፤ ነገር ግን በጌታችን ዳግም ምጽአትና በፍርድ ቀን ገና የበለጠ ፍጻሜን ይጠብቃል። ለእኛ ይህ ተስፋ በታችኛው ተፈጥሮአችን በክፋት ኃይሎች እንደምንጨነቅ፥ በዚህም በሰኮናችን እንደምንቀጠቀጥ የሚናገር ትንቢት ነው፤ ነገር ግን እግሩን በአሮጌው እባብ ራስ ላይ በሚያኖረው በክርስቶስ ድል እንነሣለን። በዚህ ዓመት ሁሉ በዲያብሎስ ፈተናዎችና ዘሩ በሆኑት በኃጢአተኞች ክፋት የዚህን ተስፋ የመጀመሪያ ክፍል በልምድ መማር ይኖርብን ይሆናል። በቈሰለው ሰኮናችን እስክናነክስ ድረስ ሊቀጠቅጡን ይችላሉ፤ ነገር ግን የጥቅሱን ሁለተኛ ክፍል አጥብቀን እንያዝ፤ አንደነግጥምም። በሴቲቱ ዘር በክርስቶስ ኢየሱስ ገና እንደምንነግሥ በእምነት ደስ ይበለን።
ጃንዋሪ 2
ከድል ወደ ድል
«የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል።» ሮሜ 16:20
ይህ ተስፋ የትላንትናውን ተስፋ በሚገባ ይከተላል። በሰኮናው በመቀጥቀጡ ብቻ ሳይሆን ክፉውን ድል በማድረጉም የኪዳን ራሳችንን እንድንመስል መወሰኑ ግልጽ ነው። አሮጌው ዘንዶ ከእግራችን በታች እንኳ ይቀጠቀጣል። በሮሜ የነበሩ አማኞች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነበረው ክርክር ተጨንቀው ነበር፤ አምላካቸው ግን «የሰላም አምላክ» ነበረ፤ ለነፍሳቸውም ዕረፍትን ሰጣቸው። ታላቁ ጠላት የዘናጮችን እግር አሰናከለ፥ የየዋሆችንም ልብ አሳተ፤ ነገር ግን ተሸናፊ ሊሆንና ባስጨነቃቸው ሰዎች ሊረገጥ ነበረ። ይህ ድል ለእግዚአብሔር ሕዝብ በራሳቸው ብልሃት ወይም ኃይል የሚመጣ አልነበረም፤ እግዚአብሔር ራሱ ሰይጣንን ይቀጠቅጠዋል። ከእግራቸው በታች ቢሆንም መቀጥቀጡ የጌታ ብቻ ነው።
ፈታኙን በድፍረት እንርገጠው! ታናናሽ መናፍስት ብቻ ሳይሆኑ የጨለማው አለቃ ራሱ በፊታችን መውደቅ አለበት። በእግዚአብሔር ላይ በማያወላውል መታመን ፈጣን ድልን እንጠብቅ። «ፈጥኖ»። ደስ የሚያሰኝ ቃል! በቅርቡ እግራችንን በአሮጌው እባብ ላይ እናኖራለን! ክፉን መቀጥቀጥ ምንኛ ደስታ ነው! ራሱ በሰው እግር መቀጥቀጡ ለሰይጣን ምንኛ ውርደት ነው! በኢየሱስ በማመን ፈታኙን እንርገጠው።
ጃንዋሪ 3
በተስፋ ላይ ማረፍ
«የተኛህባትን ምድር ለአንተ እሰጣታለሁ።» ዘፍጥረት 28:13
ማንኛውም ተስፋ በግል የሚተረጎም አይደለም፤ ለአንድ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ለአማኞች ሁሉ ነው። ወንድሜ ሆይ፥ በእምነት በተስፋ ላይ ተጋድመህ በላዩ ብታርፍ የአንተ ነው። ያዕቆብ «በደረሰበትና» ባደረበት፥ ባረፈበትም ስፍራ ርስቱን ወሰደ። የደከመ ሰውነቱን በምድር ላይ ዘርግቶ የዚያን ስፍራ ድንጋዮች ተንተርሶ ሳለ በዚህ መንገድ የምድሪቱ ባለቤት እየሆነ እንደ ነበረ አላሰበም፤ ሆኖም እንዲሁ ነበረ። ለእውነተኛ አማኞች ሁሉ ምድርንና ሰማይን የሚያገናኘውን ያን ድንቅ መሰላል በሕልሙ አየ፤ በእርግጥም የመሰላሉ እግር በቆመበት ስፍራ በምድሩ ላይ መብት ሊኖረው ይገባ ነበር፤ አለዚያ ወደ መለኮታዊው ደረጃ ሊደርስ አይችልም ነበርና። የእግዚአብሔር ተስፋዎች ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ አዎንና አሜን ናቸው፤ እርሱም የእኛ ስለ ሆነ በዕረፍት እምነት በላዩ ብንተኛ ብቻ እያንዳንዱ ተስፋ የእኛ ነው።
አንተ የደከምህ ሆይ፥ ና፤ የጌታህን ቃላት ትራስ አድርጋቸው። በሰላም ተኛ። ስለ እርሱ ብቻ አልም። ኢየሱስ የብርሃን መሰላልህ ነው። መላእክት በነፍስህና በአምላክህ መካከል በእርሱ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ እይ፤ ተስፋውም ከእግዚአብሔር የተሰጠህ የራስህ ድርሻ እንደ ሆነ፥ ለአንተም በተለይ እንደ ተነገረ አድርገህ ለራስህ መውሰድህ ዝርፊያ እንዳልሆነ እርግጠኛ ሁን።
ጃንዋሪ 4
በጸጥታ ዕረፍት
«ተማምነውም እንዲተኙ አደርጋቸዋለሁ።» ሆሴዕ 2:18
አዎን፥ ቅዱሳን ሰላም ይኖራቸዋል። ይህ የጸጋ ቃል የተወሰደበት ክፍል «ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ከምድርም ተንቀሳቃሾች ጋር» ስለሚሆን ሰላም ይናገራል። ይህ ከምድራዊ ጠላቶች፥ ከምሥጢራዊ ክፋቶችና ከትናንሽ ችግሮች ጋር ያለ ሰላም ነው! ከእነዚህ ማናቸውም ከመተኛት ሊከለክሉን ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን አንዳቸውም አይከለክሉንም። ጌታ ሕዝቡን የሚያስፈራሩትን ነገሮች ፈጽሞ ያጠፋል፤ «ቀስትንና ሰይፍን ሰልፍንም ከምድር እሰብራለሁ።» የሁከት መሣሪያዎች ሁሉ ተሰባብረው ሲደቅቁ ሰላሙ በእውነት ጥልቅ ይሆናል።
ከዚህ ሰላም ጋር ዕረፍት ይመጣል። «ለወዳጆቹ እንቅልፍን ይሰጣልና።» በሙላት ተሰጥቷቸውና በመለኮት ጸጥ ብለው አማኞች በጸጥታ ዕረፍት ይተኛሉ።
ይህ ዕረፍት በሰላም የሆነ ነው። መተኛት አንድ ነገር ነው፤ «ተማምኖ መተኛት» ግን ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው። ወደ ተስፋው ምድር፥ ወደ አብ ቤት፥ ወደ ፍቅር እልፍኝ፥ ወደ ክርስቶስም እቅፍ ገብተናል፤ በእርግጥ አሁን «ተማምነን መተኛት» እንችላለን። ለአማኝ ተቀምጦ ከመጨነቅ ይልቅ በሰላም መተኛት ይበልጥ ደኅንነት ነው።
«በለመለመ መስክ ያሳድረኛል።» አጽናኙ እስኪያስተኛን ድረስ ከቶ አናርፍም።
ጃንዋሪ 5
ድንቅ ዋስትና
«አበረታሃለሁ።» ኢሳይያስ 41:10
ለማገልገል ወይም መከራ ለመቀበል በተጠራን ጊዜ ኃይላችንን እንመረምራለን፤ ካሰብነውም ሆነ ከሚያስፈልገን ያነሰ ሆኖ እናገኘዋለን። ነገር ግን እንዲህ ያለ የምንደገፍበት ቃል ሳለን ልባችን በውስጣችን አይዝል፤ የሚያስፈልገንን ሁሉ ዋስትና ይሰጠናልና። እግዚአብሔር ሁሉን የሚችል ኃይል አለው፤ ያንንም ኃይል ሊሰጠን ይችላል፤ እንደሚሰጠንም ተስፋው ነው። እርሱ የነፍሳችን ምግብ የልባችንም ጤንነት ይሆናል፤ በዚህም ኃይልን ይሰጠናል። እግዚአብሔር በአንድ ሰው ውስጥ ምን ያህል ኃይል ሊያኖር እንደሚችል የሚናገር የለም። መለኮታዊ ኃይል ሲመጣ የሰው ድካም ከዚያ በኋላ እንቅፋት አይሆንም።
ራሳችንን እስክንደነቅ ድረስ ልዩ ኃይል የተቀበልንባቸውን የድካምና የፈተና ወቅቶች አናስታውስምን? በአደጋ መካከል ተረጋጋን፥ በሐዘን ጊዜ ተገዛን፥ በሐሜት ራሳችንን ገዛን፥ በሕመምም ታገሥን። እውነቱ ይህ ነው፤ ያልተለመደ መከራ ሲመጣብን እግዚአብሔር ያልተጠበቀ ኃይል ይሰጣል። ከደካማው ማንነታችን በላይ እንነሣለን። ፈሪዎች እንደ ወንድ ይቆማሉ፥ ሰነፎች ጥበብ ይሰጣቸዋል፥ ዝምተኞችም የሚናገሩትን በዚያው ሰዓት ይቀበላሉ። የራሴ ድካም ወደ ኋላ እንድል ያደርገኛል፤ የእግዚአብሔር ተስፋ ግን ደፋር ያደርገኛል። ጌታ ሆይ፥ «እንደ ቃልህ» አበርታኝ።
ጃንዋሪ 6
ከውጭ የሚመጣ እርዳታ
«እረዳሃለሁም።» ኢሳይያስ 41:10
የትላንትናው ተስፋ ለምንሠራው ሥራ ኃይልን አረጋገጠልን፤ ይህ ደግሞ ብቻችንን መሥራት በማንችልበት ጊዜ እርዳታን ያረጋግጥልናል። ጌታ «እረዳሃለሁ» ይላል። በውስጥ ያለው ኃይል ከውጭ በሚመጣ እርዳታ ይሟላል። በፊቱ መልካም ቢመስለው እግዚአብሔር በጦርነታችን አጋሮችን ሊያስነሣልን ይችላል፤ የሰው እርዳታ ባይልክልን እንኳ እርሱ ራሱ ከጎናችን ይሆናል፤ ይህም ይበልጥ መልካም ነው። «ክቡሩ አጋራችን» ከብዙ ሟች ረዳቶች ሠራዊት ይሻላል።
እርዳታው በጊዜው ነው፤ በመከራ ጊዜ ቅርብ ረዳት ነው። እርዳታው እጅግ ጥበበኛ ነው፤ ለእያንዳንዱ ሰው የሚገባውንና የሚስማማውን እርዳታ እንዴት እንደሚሰጥ ያውቃል። የሰው እርዳታ ከንቱ ቢሆንም የእርሱ እርዳታ እጅግ የሚሠራ ነው። እርዳታው ከእርዳታ በላይ ነው፤ ሸክሙን ሁሉ ይሸከማል፥ ጕድለቱንም ሁሉ ይሞላልና። «ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?»
እርሱ አስቀድሞ ረዳታችን ስለ ሆነ ለአሁኑና ለወደፊቱ በእርሱ እንታመናለን። ጸሎታችን «አቤቱ፥ ረዳቴ ሁን» የሚል ነው፤ ልምዳችን «መንፈስ ድካማችንን ያግዛል» የሚል ነው፤ ተስፋችን «ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከዚያ ይመጣል» የሚል ነው፤ በቅርቡም ዝማሬያችን «አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛል» የሚል ይሆናል።
ጃንዋሪ 7
ሁልጊዜ ማደግ
«ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ።» ዮሐንስ 1:50
ይህ የተነገረው በአንድ አሳማኝ ማስረጃ ብቻ ኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅ፥ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ ለመቀበል ዝግጁ ለነበረ እንደ ሕፃን ላለ አማኝ ነው። ለማየት የሚፈቅዱ ያያሉ፤ እንዲህ በሚያሳዝን ሁኔታ የምንታወረው ዓይናችንን ስለምንጨፍን ነው።
እስከ አሁን ብዙ አይተናል። ጌታ ታላቅና የማይመረመር ነገር አሳይቶናል፤ ስለዚህም ስሙን እናመሰግናለን፤ ነገር ግን በቃሉ ውስጥ የሚበልጡ እውነቶች፥ የሚበልጡ የልምድ ጥልቀቶች፥ የሚበልጡ የኅብረት ከፍታዎች፥ የሚበልጡ የጥቅም ሥራዎች፥ የሚበልጡ የኃይልና የፍቅር የጥበብም መገለጦች አሉ። በጌታችን ለማመን ፈቃደኞች ብንሆን እነዚህን ገና እናያለን። የሐሰት ትምህርት የመፍጠር ችሎታ የሚያጠፋ ነው፤ እውነትን የማየት ኃይል ግን በረከት ነው። ሰማይ ይከፈትልናል፤ ወደዚያ የሚወስደው መንገድ በሰው ልጅ ግልጽ ይሆንልናል፤ በላይኛውና በታችኛው መንግሥታት መካከል የሚካሄደው የመላእክት ምልልስ ይበልጥ ይገለጥልናል። ዓይኖቻችንን ወደ መንፈሳዊ ነገሮች እንክፈት፤ ከዚህም የበለጠ ለማየት እንጠብቅ። ሕይወታችን ወደ ምንም እንደማይዝል፥ ታላቁን አምላክ ራሱን እስክናይና ከዚያ በኋላ ከቶ ማየቱን እስከማናጣ ድረስ የሚበልጡትንና ይበልጥ የሚበልጡትን ነገሮች እያየን ሁልጊዜ በማደግ ላይ እንደምንሆን እንመን።
ጃንዋሪ 8
የልብና የሕይወት ንጽሕና
«ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።» ማቴዎስ 5:8
ንጽሕና፥ የልብ ንጽሕና እንኳ፥ ልንመኘው የሚገባ ዋና ነገር ነው። በመንፈስና በቃሉ በውስጣችን መንጻት ያስፈልገናል፤ ከዚያም በመቀደስና በመታዘዝ በውጭ ንጹሓን እንሆናለን። በስሜትና በማስተዋል መካከል የቀረበ ግንኙነት አለ፤ ክፉን ብንወድ መልካሙን ልናስተውል አንችልም። ልብ ቢረክስ ዓይን ይደበዝዛል። ርኩስ ነገርን የሚወዱ ሰዎች ቅዱሱን አምላክ እንዴት ሊያዩ ይችላሉ?
እግዚአብሔርን እዚህ ማየት ምንኛ ታላቅ መብት ነው! እርሱን በጨረፍታ ማየት በምድር ላይ ያለ ሰማይ ነው! በክርስቶስ ኢየሱስ ልበ ንጹሖች አብን ያያሉ። እርሱን፥ እውነቱን፥ ፍቅሩን፥ ዓላማውን፥ ሉዓላዊነቱን፥ የኪዳን ባሕርዩን እናያለን፤ አዎን፥ በክርስቶስ እርሱን ራሱን እናያለን። ነገር ግን ይህ የሚገኘው ኃጢአት ከልብ እንዲወጣ ሲደረግ ብቻ ነው። «ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው» ብለው መጮኽ የሚችሉት እግዚአብሔርን መምሰል የሚሹ ብቻ ናቸው። «ክብርህን አሳየኝ» የሚለው የሙሴ ምኞት በእኛ ሊፈጸም የሚችለው ከኃጢአት ሁሉ ራሳችንን ስናነጻ ብቻ ነው። «እርሱ እንዳለ እናየዋለን»፤ «በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።» የአሁኑ ኅብረት ደስታና የብፁዕ ራእዩ ተስፋ ለልብና ለሕይወት ንጽሕና አጣዳፊ ምክንያቶች ናቸው። ጌታ ሆይ፥ አንተን እናይ ዘንድ ልበ ንጹሖች አድርገን!
ጃንዋሪ 9
በመስጠት ማትረፍ
«የምትመጸውት ነፍስ ትጠግባለች።» ምሳሌ 11:25
በነፍሴ ለመለምለም ብመኝ ሀብቴን ማከማቸት የለብኝም፤ ለድሆች ማካፈል አለብኝ እንጂ። ንፉግና ቈጣቢ መሆን ወደ ብልጽግና የሚወስድ የዓለም መንገድ ነው፤ የእግዚአብሔር መንገድ ግን አይደለም፤ እርሱ «የሚበትን ሰው አለ፥ ይጨመርለትማል፤ ከሚገባውም በላይ የሚነፍግ ሰው አለ፥ ነገር ግን ይደኸያል» ብሎአልና። የእምነት የማትረፊያ መንገድ መስጠት ነው። ይህን ደጋግሜ መሞከር አለብኝ፤ ለእኔ የሚጠቅመኝ ያህል ብልጽግና ለለጋስ አካሄድ የጸጋ ዋጋ ሆኖ ወደ እኔ እንደሚመጣ ልጠብቅ እችላለሁ።
እርግጥ ነው፥ ሀብታም እንደምሆን እርግጠኛ ላልሆን እችላለሁ። እወፍራለሁ፤ ከመጠን በላይ ግን አይደለም። ብዙ ሀብት እንደ ወፍራም ሰዎች መንቀሳቀስ ያስቸግረኝ፥ የዓለማዊነትን የሆድ ሕመም ያመጣብኝ፥ ምናልባትም የልብ ስብ መበስበስን ያስከትልብኝ ነበር። አይደለም፤ ጤነኛ ለመሆን የሚበቃ ያህል ብወፍር ልረካ ይገባኛል፤ ጌታም የሚበቃኝን ቢሰጠኝ ፈጽሞ ልረካ እችላለሁ።
ነገር ግን እጅግ የምመኘው የአእምሮና የመንፈስ ውፍረት አለ፤ ይህም ለአምላኬ፥ ለቤተ ክርስቲያኑና ለባልንጀሮቼ ከሚኖረኝ ለጋስ አሳብ የሚመጣ ውጤት ነው። ልቤን እንዳላስርብ አልቈጥብ። ለጋስና ቸር ልሁን፤ እንዲህ ሳደርግ ጌታዬን እመስላለሁና። እርሱ ራሱን ስለ እኔ ሰጠ፤ እኔ አንዳች ነገር እነፍገዋለሁን?
ጃንዋሪ 10
መለኮታዊ ብድራት
«የሚያረካም ራሱ ደግሞ ይረካል።» ምሳሌ 11:25
ሌሎችን በጥንቃቄ ባስብ እግዚአብሔር ያስበኛል፤ በአንድ መንገድም ብድራቴን ይከፍለኛል። ድሆችን ላስብ፤ ጌታም ያስበኛል። ትናንሽ ልጆችን ልንከባከብ፤ ጌታም እንደ ልጁ ይይዘኛል። መንጋውን ልመግብ፤ እርሱም ይመግበኛል። አትክልቱን ላጠጣ፤ እርሱም ነፍሴን የሚጠጣ ገነት ያደርጋታል። ይህ የጌታ የራሱ ተስፋ ነው፤ ቅድመ ሁኔታውን መፈጸም፥ ከዚያም ፍጻሜውን መጠበቅ የእኔ ድርሻ ይሁን።
ስለ ራሴ እስክታመም ድረስ ልጨነቅ እችላለሁ፤ ምንም እስከማይሰማኝ ድረስ ስሜቶቼን ልጠብቅ እችላለሁ፤ ለማልቀስ እንኳ እስክደክም ድረስ ስለ ድካሜ ላለቅስ እችላለሁ። ራስ ወዳድ ያለመሆንና ለጌታዬ ለኢየሱስ ካለኝ ፍቅር የተነሣ በዙሪያዬ ስላሉት ሰዎች ነፍስ መጨነቅ መጀመር ለእኔ እጅግ የበለጠ ይጠቅመኛል። ማጠራቀሚያዬ እጅግ እየጎደለ ነው፤ የሚሞላው አዲስ ዝናብ አይመጣም፤ ምን ላድርግ? መክደኛውን አንሥቼ በዙሪያዬ ያሉትን የሚጠወልጉ ተክሎች ለማጠጣት ውኃው እንዲፈስ እለቃለሁ። ምን አያለሁ? ጕድጓዴ እየፈሰሰ የሚሞላ ይመስላል። የተሰወረ ምንጭ እየሠራ ነው። ሁሉ ቆሞ ሳለ አዲሱ ምንጭ ታትሞ ነበር፤ ያለኝ ግን ሌሎችን ለማጠጣት ሲፈስ ጌታ ያስበኛል። ሃሌ ሉያ!
ጃንዋሪ 11
እምነት ቀስቱን ታያለች
«በምድር ላይ ደመናን ባመጣሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመና ትታያለች።» ዘፍጥረት 9:14
አሁን ደመናዎች በብዛት አሉ፤ ነገር ግን ዓለም በጥፋት ውኃ እንድትጠፋ አንፈራም። እንዲህ ያለ ፍርሃት እንዳይኖረን ቀስተ ደመናውን በበቂ ሁኔታ አዘውትረን እናያለን። ጌታ ከኖኅ ጋር ያደረገው ኪዳን ጸንቶ ይቆማል፤ ስለ እርሱም ጥርጥር የለንም። ታዲያ አሁን ሰማያችንን የሚያጨልሙት የመከራ ደመናዎች በጥፋታችን ያበቃሉ ብለን ለምን እናስባለን? እንደዚህ ያሉትን መሠረት የሌላቸውንና እግዚአብሔርን የሚያዋርዱ ፍርሃቶችን እናስወግድ።
ስሜት የመከራን ደመና በሚያይበት ጊዜ ሁሉ እምነት የኪዳኑን ተስፋ ቀስት ሁልጊዜ ታያለች። እግዚአብሔር የጥፋት ፍላጾቹን የሚወረውርበት ቀስት አለው፤ ነገር ግን እዩ! ወደ ላይ ተመልሶአል። ፍላጻም አውታርም የሌለው ቀስት ነው፤ ለጦርነት ሳይሆን ለማሳያ የተሰቀለ ቀስት ነው። ደስታንና ሐሴትን የሚገልጥ ብዙ ቀለም ያለው ቀስት ነው እንጂ በእልቂት በደም የቀላ ወይም በቍጣ የጠቆረ ቀስት አይደለም። አይዞአችሁ። እግዚአብሔር ኪዳኑን ያለ ምስክር እስኪተው ድረስ ሰማያችንን ከቶ አያጨልምም፤ ቢያደርገውም እንኳ እንታመንበታለን፤ ሊለወጥ፥ ሊዋሽ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ የሰላም ኪዳኑን ሳይጠብቅ ሊቀር አይችልምና። ውኃዎች እንደ ገና ምድርን እስኪሸፍኑ ድረስ አምላካችንን የምንጠራጠርበት ምክንያት አይኖረንም።
ጃንዋሪ 12
«እስከ መጨረሻ የሚዘልቅ ፍቅር»
«ጌታ ለዘላለም አይጥልምና።» ሰቆቃው ኤርምያስ 3:31
እርሱ ለጊዜው ሊገፋ ይችላል፤ ለዘላለም ግን አይደለም። አንዲት ሴት ጌጣጌጦቿን ለጥቂት ቀናት ሳታደርግ ልትቀር ትችላለች፤ ነገር ግን አትረሳቸውም፥ ወደ ጕድፍም አትጥላቸውም። የሚወዳቸውን መጣል የጌታ ጠባይ አይደለም፤ «በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው»። አንዳንዶች ወደ ጉድጓዳቸው እንደሚገቡና እንደሚወጡ ጥንቸሎች ሆነን፥ አንድ ጊዜ በጸጋ ውስጥ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጸጋ ውጭ እንደምንሆን ይናገራሉ፤ በእውነት ግን እንዲህ አይደለም። የጌታ ፍቅር ከዚህ እጅግ የከበደና ጸንቶ የሚኖር ነገር ነው።
ከዘላለም መረጠን፥ እስከ ዘላለምም ይወደናል። ስለ እኛ እስኪሞት ድረስ ወደደን፤ ስለዚህም ፍቅሩ ፈጽሞ እንደማይሞት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ክብሩ ከአማኙ መዳን ጋር እጅግ የተቈራኘ ነው፤ ስለዚህ የክብር ንጉሥ ሆኖ የለበሰውን የሹመት ልብሱን ሊጥል እንደማይችል ሁሉ፥ አማኙንም ሊጥለው አይችልም። አይደለም፥ አይደለም! ጌታ ኢየሱስ ራስ እንደ መሆኑ ብልቶቹን ፈጽሞ አይጥልም፤ ባል እንደ መሆኑም ሙሽራውን ፈጽሞ አይጥልም።
የተጣልህ መስሎህ ነበርን? ለራሱ ያጨህን ጌታ ስለ ምን እንዲህ በክፉ አሰብኸው? እንዲህ ያለውን አሳብ ጣለው፤ ዳግመኛም በነፍስህ እንዲያድር አትፍቀድለት። «እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝብ አልጣላቸውም» (ሮሜ 11:2)። «መፋታትን እጠላለሁ» (ሚልክያስ 2:16)።
ጃንዋሪ 13
ከቶ ወደ ውጭ አያወጣም
«ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም።» ዮሐንስ 6:37
ጌታችን ወደ እርሱ የመጣውን ወደ ውጭ ያወጣበት አንድ ምሳሌ እንኳ አለን? ቢኖር ልናውቀው በወደድን ነበር፤ ነገር ግን አንድም አልተገኘም፥ ወደ ፊትም ፈጽሞ አይገኝም። በገሃነም ካሉ ከጠፉት ነፍሳት መካከል «ወደ ኢየሱስ ሄድሁ፥ እርሱም አልተቀበለኝም» ማለት የሚችል አንድ እንኳ የለም። ኢየሱስ ቃሉን የሚያጥፍበት የመጀመሪያው ሰው አንተ ወይም እኔ መሆናችን የማይቻል ነው። እንዲህ ያለውን የጨለመ ጥርጣሬ በልባችን አናስተናግድ።
ስለ ዛሬው መከራችን አሁን ወደ ኢየሱስ እንሂድ እንበል። ይህን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን — እርሱ ሊሰማን እምቢ አይልም፥ ወደ ውጭም አያወጣንም። ብዙ ጊዜ ወደ እርሱ የሄድነውም ከዚህ በፊት ፈጽሞ ያልሄዱትም — አብረን እንሂድ፤ የጸጋውንም ደጅ በማናችንም ፊት እንደማይዘጋ እናያለን።
«ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል»፤ ማንንም ግን አይገፋም። በድካምና በኃጢአት፥ በሚንቀጠቀጥ እምነት፥ በጥቂት እውቀትና በቀጭን ተስፋ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ እርሱ ግን ወደ ውጭ አያወጣንም። በጸሎት እንመጣለን፥ ያም ጸሎት የተሰባበረ ነው፤ በኑዛዜ እንመጣለን፥ ያም ኑዛዜ ጕድለት ያለበት ነው፤ በምስጋና እንመጣለን፥ ያም ምስጋና ከሚገባው እጅግ ያነሰ ነው፤ ቢሆንም ይቀበለናል። ታምመን፥ ረክሰን፥ ዝለንና ዋጋ ቢሶች ሆነን እንመጣለን፤ እርሱ ግን ከቶ ወደ ውጭ አያወጣንም። ፈጽሞ ወደ ውጭ ወደማያወጣን ወደ እርሱ ዛሬም ደግሞ እንምጣ።
ጃንዋሪ 14
ዕረፍት ስጦታ ነው
«እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።» ማቴዎስ 11:28
የዳንን እኛ በኢየሱስ ዕረፍትን እናገኛለን። ያልዳኑትም ወደ እርሱ ቢመጡ ዕረፍትን ይቀበላሉ፤ በዚህ ስፍራ ዕረፍትን «ሊሰጥ» ተስፋ ሰጥቶአልና። ከስጦታ ይበልጥ ነጻ የሆነ ምንም የለም፤ እርሱ በደስታ የሚሰጠውን እኛም በደስታ እንቀበል። ልትገዛው ወይም ልትበደረው አይገባህም፤ እንደ ስጦታ ልትቀበለው ይገባሃል እንጂ። በምኞት፥ በስግብግብነት፥ በፍትወት ወይም በጭንቀት ጅራፍ ሥር ትደክማለህ፤ እርሱ ከዚህ የብረት ባርነት ነጻ ያወጣሃል፥ ዕረፍትንም ይሰጥሃል። «ሸክም» ተሸክመሃል — አዎን፥ በኃጢአት፥ በፍርሃት፥ በጭንቀት፥ በጸጸትና በሞት ፍርሃት «ሸክምህ ከብዶአል»፤ ወደ እርሱ ብትመጣ ግን ሸክምህን ያራግፍልሃል። እኛ ከእንግዲህ እንዳንሸከመው፥ የሚያደቅቀውን የኃጢአታችንን ክምር እርሱ ተሸከመ። ሸክሙ የከበደ ሁሉ ከዚያ ታላቅ ጫና በታች ከማጐንበስ እንዲያርፍ፥ ራሱን ታላቅ ሸክም ተሸካሚ አደረገ።
ኢየሱስ ዕረፍትን ይሰጣል። እንዲህ ነው። ታምናለህን? ልትፈትነውስ ትወዳለህን? አሁኑኑ ታደርገዋለህን? ሌላውን ተስፋ ሁሉ በመተው፥ እርሱን በማሰብ፥ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የሰጠውን ምስክርነት በማመንና ሁሉን ለእርሱ አደራ በመስጠት ወደ ኢየሱስ ና። እንዲህ ወደ እርሱ ብትመጣ፥ የሚሰጥህ ዕረፍት ጥልቅ፥ አስተማማኝ፥ ቅዱስና ዘላለማዊ ይሆናል። ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያድግ ዕረፍትን ይሰጣል፤ ወደ እርሱ ለሚመጡ ሁሉም ዛሬውኑ ይሰጣቸዋል።
ጃንዋሪ 15
በእምነት ባለ ጠጎች መሆን
«ችግረኛ ለዘወትር አይረሳምና፤ የድሆችም ተስፋ ለዘላለም አይጠፋም።» መዝሙር 9:18
ድህነት ከባድ ርስት ነው፤ በጌታ የሚታመኑ ግን በእምነት ባለ ጠጎች ይሆናሉ። በእግዚአብሔር እንዳልተረሱ ያውቃሉ፤ እርሱ በመግቦቱ መልካም ነገሮችን ሲያከፋፍል የተዘነጉ ቢመስሉም፥ ይህ ሁሉ የሚቃናበትን ጊዜ ይጠባበቃሉ። አልዓዛር ሁልጊዜ በባለ ጠጋው ደጅ ከውሾች መካከል አይተኛም፤ በአብርሃም እቅፍ ዋጋውን ይቀበላል እንጂ።
አሁንም እንኳ ጌታ ድሆች ነገር ግን ውድ የሆኑትን ልጆቹን ያስባል። ከጥንት አንዱ «እኔ ድሀና ችግረኛ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል» አለ፤ እንዲሁም ነው። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ድሆች ታላቅ ተስፋ አላቸው። ጌታ ለዚህ ሕይወትና ለአምልኮ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንዲሰጣቸው ይጠብቃሉ፤ ሁሉ ነገር ለበጎ አብሮ ሲሠራላቸው ለማየት ይጠብቃሉ፤ ራሱን የሚያስጠጋበት ስፍራ ካልነበረው ከጌታቸው ጋር ይበልጥ የቀረበ ኅብረት እንዲኖራቸው ይጠብቃሉ፤ ዳግመኛ መምጣቱንም፥ በክብሩም ተካፋዮች መሆንን ይጠብቃሉ። ይህ ተስፋ ሊጠፋ አይችልም፤ ለዘላለም ሕያው በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ተከማችቶአልና፤ እርሱ ሕያው ስለ ሆነም ተስፋው ደግሞ ሕያው ሆኖ ይኖራል። ድሀው ቅዱስ ባለ ጠጋው ኃጢአተኛ ሊረዳው የማይችለውን ብዙ መዝሙር ይዘምራል። ስለዚህ በምድር ላይ ምግባችን ሲያንስ፥ በላይ ያለውን የንጉሥ ማዕድ እናስብ።
ጃንዋሪ 16
እጅግ የደከመውን ጥሪ እንኳ
«እንዲህም ይሆናል፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።» ኢዩኤል 2:32
ስሙን የማልጠራው ስለ ምንድር ነው? እግዚአብሔር እንዲህ ቅርብ ሆኖ እጅግ የደከመውን ጥሪዬን እንኳ የሚሰማ ሆኖ ሳለ፥ ወደዚህና ወደዚያ ጎረቤት የምሮጠው ስለ ምንድር ነው? ተቀምጬ ዘዴ የምቀይሰውና ዕቅድ የምፈጥረው ስለ ምንድር ነው? ራሴንና ሸክሜን ወዲያውኑ በጌታ ላይ የማልጥለው ስለ ምንድር ነው? ቀጥ ብሎ የሚሮጥ ከሁሉ የሚሻል ሯጭ ነው — ታዲያ ወዲያውኑ ወደ ሕያው እግዚአብሔር የማልሮጠው ስለ ምንድር ነው? ከሌላ ስፍራ መዳንን ብፈልግ በከንቱ ነው፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ግን አገኘዋለሁ፤ በዚህ ስፍራ ያረጋግጠው ዘንድ ንጉሣዊው «ይድናል» የሚለው ቃሉ አለኝና።
እርሱን ልጠራው ይፈቀድልኛል ወይስ አይፈቀድልኝም ብዬ መጠየቅ አያስፈልገኝም፤ ያ «የሚጠራ ሁሉ» የሚለው ቃል እጅግ ሰፊና ሁሉን የሚያቅፍ ነውና። «ሁሉ» እኔንም ያመለክታል፤ እግዚአብሔርን የሚጠራ ማንኛውንም ሰውና ሁሉንም ያመለክታልና። ስለዚህ የጥቅሱን መሪነት እከተላለሁ፥ ይህን ያህል ታላቅ ተስፋ የሰጠውንም ክቡር ጌታ ወዲያውኑ እጠራለሁ።
ጉዳዬ አስቸኳይ ነው፤ እንዴት እንደምድንም አላይም፤ ይህ ግን የእኔ ሥራ አይደለም። ተስፋውን የሰጠው እርሱ የሚጠብቅበትን መንገድና ዘዴ ያገኛል። ትእዛዛቱን መታዘዝ የእኔ ድርሻ ነው፤ ምክሩን መምራት ግን የእኔ አይደለም። እኔ ባሪያው ነኝ እንጂ ጠበቃው አይደለሁም። እርሱን እጠራለሁ፥ እርሱም ያድነኛል።
ጃንዋሪ 17
ፍርሃት የሌለበት ሰው
«እርሱም፦ በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ አለ።» ዘጸአት 3:12
እርግጥ ነው፥ ጌታ ሙሴን ለአንድ መልእክት ቢልከው ብቻውን እንዲሄድ አይተወውም ነበር። ጉዳዩ የሚያስከትለው ታላቅ አደጋና የሚጠይቀው ታላቅ ኃይል፥ እግዚአብሔር አንድን ምስኪን ብቸኛ ዕብራዊ በዓለም ሁሉ ካሉ ነገሥታት እጅግ ኃያል የሆነውን እንዲጋፈጥ ልኮ ለራሱ ቢተወው አስቂኝ ያደርገው ነበር። ጥበበኛ አምላክ ምስኪኑን ሙሴ ከፈርዖንና ከግብፅ ታላቅ ሠራዊት ጋር ብቻውን ያጋጥመዋል ተብሎ ሊታሰብ አይቻልም። ስለዚህ ብቻውን ይልከዋል የሚለው ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር እንደ ሆነ፥ «በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ» ይላል።
በእኔም ጉዳይ ይኸው ሥርዓት ይጸናል። በኃይሉ በቅንነት ተደግፌና ለክብሩ ብቻ ዓይኔን አድርጌ በጌታ መልእክት ብሄድ፥ እርሱ ከእኔ ጋር እንደሚሆን እርግጥ ነው። እኔን መላኩ እኔን እንዲደግፍ ያስገድደዋል። ይህ አይበቃምን? ከዚህ የበለጠ ምን እፈልጋለሁ? መላእክትና የመላእክት አለቆች ሁሉ ከእኔ ጋር ቢሆኑ ልወድቅ እችል ነበር፤ እርሱ ግን ከእኔ ጋር ቢሆን ማሸነፌ የግድ ነው። ብቻ ለዚህ ተስፋ በሚገባ እንድመላለስ ልጠንቀቅ። በፍርሃት፥ በግማሽ ልብ፥ በግዴለሽነት ወይም በትዕቢት አልሂድ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያለ ሰው እንዴት ያለ ሰው ሊሆን ይገባዋል! በእንዲህ ያለ ጓደኝነት ውስጥ ሆኜ እንደ ወንድ ልቆም፥ እንደ ሙሴም ያለ ፍርሃት ወደ ፈርዖን ልገባ ይገባኛል።
ጃንዋሪ 18
ክርስቶስና ልጆቹ
«ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ዘሩን ያያል።» ኢሳይያስ 53:10
ጌታችን ኢየሱስ በከንቱ አልሞተም። ሞቱ መሥዋዕታዊ ነበር፤ ሞት የኃጢአታችን ቅጣት ስለ ነበረ በእኛ ፋንታ ሞተ፤ በእኛ ፋንታ መቆሙም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ፥ ነፍሱን መሥዋዕት ያደረገላቸውን አዳናቸው። በሞቱ ብዙ ፍሬ እንደምታፈራ የስንዴ ቅንጣት ሆነ። ለኢየሱስ የሚቀጥሉ የልጆች ትውልድ መኖር አለበት፤ እርሱ «የዘላለም አባት» ነውና። «እነሆኝ እኔና የሰጠኸኝ ልጆች» ይላል።
ሰው በልጆቹ ይከበራል፤ ኢየሱስም በእነዚህ የኃያላን ፍላጾች የተሞላ ሰገባ አለው። ሰው በልጆቹ ይወከላል፤ እንዲሁም ክርስቶስ በክርስቲያኖች ይወከላል። የሰው ሕይወት በዘሩ የሚራዘምና የሚሰፋ ይመስላል፤ እንዲሁም የኢየሱስ ሕይወት በአማኞች ይቀጥላል።
ኢየሱስ ሕያው ነው፤ ዘሩን ያያልና። ዓይኑን በእኛ ላይ ያደርጋል፥ በእኛ ደስ ይለዋል፥ የነፍሱ ምጥ ፍሬ እንደ ሆንንም ያውቀናል። ጌታችን ከአስፈሪው መሥዋዕቱ ውጤት ደስታን ሳያገኝ እንደማይቀር፥ ዓይኖቹንም በሞቱ መከር ማርካቱን ፈጽሞ እንደማያቋርጥ ደስ ይበለን። በአንድ ወቅት ስለ እኛ ያለቀሱት ዓይኖች አሁን በደስታ ይመለከቱናል። አዎን፥ ወደ እርሱ የሚመለከቱትን ይመለከታቸዋል። ዓይኖቻችን ይገናኛሉ! ይህ እንዴት ያለ ደስታ ነው!
ጃንዋሪ 19
በአፍ መመስከር፤ በልብ ማመን
«ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ።» ሮሜ 10:9
በአፍ መመስከር ያስፈልጋል። መስክሬአለሁን? እግዚአብሔር ከሙታን ባስነሣው አዳኝ በኢየሱስ ያለኝን እምነት በግልጥ ተናግሬአለሁን? ይህንስ በእግዚአብሔር መንገድ አድርጌአለሁን? ይህን ጥያቄ በቅንነት ልመልስ።
በልብ ማመንም ደግሞ ያስፈልጋል። ከሙታን በተነሣው በጌታ ኢየሱስ በእውነት አምናለሁን? ብቸኛ የመዳን ተስፋዬ አድርጌ በእርሱ እታመናለሁን? ይህ መታመን ከልቤ ነውን? በእግዚአብሔር ፊት እንዳለሁ ሆኜ ልመልስ።
ክርስቶስን እንደ መሰከርሁና በእርሱም እንዳመንሁ በእውነት መናገር ከቻልሁ፥ እንግዲያስ ድኛለሁ። ጥቅሱ ምናልባት ይሆናል አይልም፤ ነገር ግን እንደ ቀን ብርሃን የተገለጠ፥ በሰማያትም እንዳለች ፀሐይ የጠራ ነው፤ «ትድናለህ»። አማኝና መስካሪ እንደ መሆኔ፥ በዚህ ተስፋ ላይ እጄን ልጭንና በዚህች ቅጽበት፥ በሕይወቴም ዘመን ሁሉ፥ በሞት ሰዓትና በፍርድ ቀን በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ልማጸንበት እችላለሁ።
ከኃጢአት በደል፥ ከኃጢአት ኃይል፥ ከኃጢአት ቅጣት፥ በመጨረሻም ከኃጢአት ህልውና ራሱ መዳን አለብኝ። እግዚአብሔር ተናግሮታል — «ትድናለህ»። አምነዋለሁ። እድናለሁ፤ ድኛለሁ። ለእግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን!
ጃንዋሪ 20
ድል የሚነሣው
«ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ።» ራእይ 2:7
በጦርነት ቀን ማንም ጀርባውን ሊያዞር ወይም ወደ ቅዱሱ ጦርነት ለመሄድ እምቢ ሊል አይገባውም። ልንነግሥ ብንወድ መዋጋት አለብን፤ ጠላትንም ሁሉ እስክናሸንፍ ድረስ ውጊያውን መቀጠል አለብን፤ አለዚያ ይህ ተስፋ ለእኛ አይደለም፤ «ድል ለነሣው» ብቻ ነውና። ወደ ዓለም የመጡትን ሐሰተኞች ነቢያትንና ትምህርታቸውን የሚከተሉትን ክፉ ነገሮች ሁሉ ልናሸንፍ ይገባናል። የገዛ ልባችንን መዛልና ከመጀመሪያው ፍቅራችን የማሽቈልቈል ዝንባሌያችንን ልናሸንፍ ይገባናል። መንፈስ በኤፌሶን ላለችው ቤተ ክርስቲያን የተናገረውን ቃል ሁሉ አንብብ።
ድል አድራጊ መሪያችንን በእውነት ብንከተል እንደምንነሣው፥ በጸጋ ድል ብንነሣ፥ ወደ እግዚአብሔር ገነት ማዕከል እንገባለን፤ ኪሩቡንና የሚንበለበለውን ሰይፉን አልፈን ሰው ቢበላው ለዘላለም ወደሚኖርበት ወደዚያ የተጠበቀ ዛፍ እንድንደርስ ይፈቀድልናል። እንዲህም የኃጢአት ፍርድ ከሆነው ማለቂያ ከሌለው ሞት እናመልጣለን፥ የንጽሕና ማኅተም የሆነውንና እግዚአብሔርን ከመሰለ ቅድስና የማይሞቱ መሠረቶች የሚያድገውን የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። ልቤ ሆይ፥ ና፥ አይዞህ! ከውጊያው መሸሽ የአዲሲቱንና የተሻለችውን ኤደን ደስታ ማጣት ነው፤ እስከ ድል መዋጋት ግን በገነት ከእግዚአብሔር ጋር መመላለስ ነው።
ጃንዋሪ 21
የእግዚአብሔር ጠላቶች ይሰግዳሉ
«ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።» ዘጸአት 7:5
እግዚአብሔርን የማይፈራውን ዓለም ማስተማር ከባድ ነው። ግብፅ እግዚአብሔርን አታውቅም፤ ስለዚህም ጣዖቶቿን ለማቆም ትደፍራለች፥ «እግዚአብሔር ማን ነው?» ብላ ለመጠየቅም እንኳ ትደፍራለች። ቢሆንም ጌታ ቢወዱም ባይወዱም የትዕቢተኞችን ልብ ሊሰብር አስቦአል። ፍርዶቹ በራሳቸው ላይ ሲያንጐደጕዱ፥ ሰማያቸውን ሲያጨልሙ፥ አዝመራቸውን ሲያጠፉና ልጆቻቸውን ሲገድሉ፥ የእግዚአብሔርን ኃይል በጥቂቱ መገንዘብ ይጀምራሉ። ተጠራጣሪዎችን በጉልበታቸው የሚያንበረክኩ እንዲህ ያሉ ነገሮች ገና በምድር ላይ ይደረጋሉ። ስለ ስድባቸው አንደንግጥ፤ ጌታ ለገዛ ስሙ ሊጠነቀቅ ይችላልና፥ እጅግም በሚያሠራ መንገድ ይጠነቀቅለታል።
የገዛ ሕዝቡ መዳን ደግሞ የእስራኤል አምላክ ሕያውና እውነተኛ አምላክ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ግብፅ እንድታውቅ ያደረገ ሌላ ብርቱ መንገድ ነበር። ከአሥሩ መቅሠፍቶች በአንዱም አንድ እስራኤላዊ እንኳ አልሞተም። ከተመረጠው ዘር አንድም በቀይ ባሕር አልሰጠመም። እንዲሁም የተመረጡት መዳንና የእውነተኛ አማኞች ሁሉ የተረጋገጠ መክበር፥ ከእግዚአብሔር ጠላቶች እጅግ እልከኞች የሆኑትን እንኳ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል።
ወይ፥ አሕዛብ ሁሉ በኢየሱስ ስም እስኪሰግዱና ጌታ ብለው እስኪጠሩት ድረስ፥ የሚያሳምነው ኃይሉ በወንጌል ስብከት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ምነው በወጣ!
ጃንዋሪ 22
ክርስቲያናዊ ልግስና
«ለድሀ የሚያስብ ብፁዕ ነው፤ በክፉ ቀን እግዚአብሔር ያድነዋል።» መዝሙር 41:1
ስለ ድሆች ማሰብና በልባችን ላይ እንዲያርፉ ማድረግ የክርስቲያን ሰው ግዴታ ነው፤ ኢየሱስ «ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉ» ባለ ጊዜ ከእኛ ጋርና በአጠገባችን አኑሮአቸዋልና።
ብዙዎች ሳያስቡ በችኮላ ገንዘባቸውን ለድሆች ይሰጣሉ፤ ከዚያ የሚበዙትም ምንም አይሰጡም። ይህ የከበረ ተስፋ ለድሆች «ለሚያስቡ»፥ ጉዳያቸውን ለሚመረምሩ፥ ለጥቅማቸው ዕቅድ ለሚያወጡና በአሳቢነት ለሚፈጽሙት ነው። ከገንዘብ ይልቅ በእንክብካቤ ብዙ ማድረግ እንችላለን፤ ሁለቱን አንድ ላይ ብናደርግ ደግሞ ከሁሉ የበለጠ እናደርጋለን። ለድሆች ለሚያስቡ ጌታ በጭንቅ ጊዜ የራሱን አሳቢነት ተስፋ ይሰጣል። ሌሎች በመከራ ሳሉ ብንረዳቸው እርሱ ከመከራ ያወጣናል። ጌታ ለሌሎች ለማቅረብ እንደምንጥር ቢያይ እጅግ ልዩ የሆነ የመግቦት እርዳታ እንቀበላለን። ምንም ያህል ለጋሶች ብንሆን የመከራ ጊዜ ይመጣብናል፤ ርኅሩኆች ብንሆን ግን ልዩ ማዳንን ለመጠየቅ መብት አለን፤ ጌታም የገዛ ቃሉንና ውሉን አይክድም። ንፉጋን ስስታሞች ራሳቸውን ይርዱ፤ አሳቢዎችንና ለጋሶችን አማኞች ግን ጌታ ይረዳቸዋል። ለሌሎች እንዳደረግህ ጌታም እንዲሁ ያደርግልሃል። ኪስህን ባዶ አድርግ።
ጃንዋሪ 23
የተፈጸመ መሥዋዕት
«እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ የተወደደ ይሆንለታል።» ዘሌዋውያን 1:4
ወይፈኑ እጁን በመጫኑ የአቅራቢው መሥዋዕት ከሆነ፥ በእምነት እጅ መጫን ኢየሱስ እንዴት አብልጦ የእኛ አይሆንም?
«እምነቴ እጇን ትጭናለች
በዚያ በውዱ ራስህ ላይ፥
እንደ ንስሐ ገቢ ቆሜ፥
በዚያም ኃጢአቴን እናዘዛለሁ።»
ወይፈን ያስተሰርይለት ዘንድ የተወደደ ሊሆንለት ከቻለ፥ ጌታ ኢየሱስ እንዴት አብልጦ ሙሉና ሁሉን የሚበቃ ማስተስረያችን አይሆንም? አንዳንዶች ስለ ምትክነት ታላቅ እውነት ይከራከራሉ፤ ለእኛ ግን እርሱ ተስፋችን፥ ደስታችን፥ ትምክህታችንና ሁሉ ነገራችን ነው። ኢየሱስ ያስተሰርይልን ዘንድ ስለ እኛ ተቀባይነት አግኝቶአል፤ እኛም «በውድ ልጁ» ተቀባይነት አግኝተናል።
አንባቢው የጌታን የተፈጸመ መሥዋዕት በመቀበል ጥቅሙን ያገኝ ዘንድ፥ ወዲያውኑ እጁን በእርሱ ላይ ለመጫን ይጠንቀቅ። አንድ ጊዜ አድርጎት ከሆነ ደግሞ ያድርገው። ፈጽሞ አድርጎት የማያውቅ ከሆነ ግን ለአንዲት ቅጽበት እንኳ ሳይዘገይ እጁን ይዘርጋ። ብትፈልገው ኢየሱስ አሁን የአንተ ነው። በእርሱ ተደገፍ፤ አጥብቀህ ተደገፍበት፤ ያለ አንዳች ጥርጥርም የአንተ ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀሃል፥ ኃጢአትህ ተደምስሶአል፥ አንተም የጌታ ነህ።
ጃንዋሪ 24
እግሮቻችንን መጠበቅ
«የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል።» 1ኛ ሳሙኤል 2:9
መንገዱ የሚያዳልጥ ነው፥ እግሮቻችንም ደካሞች ናቸው፤ ጌታ ግን እግሮቻችንን ይጠብቃል። ቅዱሳኑ እንሆን ዘንድ ራሳችንን በታዛዥ እምነት አሳልፈን ብንሰጥ፥ እርሱ ራሱ ጠባቂያችን ይሆናል። እኛን እንዲጠብቁ መላእክቱን ማዘዝ ብቻ ሳይሆን፥ እርሱ ራሱ አካሄዳችንን ይጠብቃል።
ልብሳችንን እንዳናረክስ፥ ነፍሳችንን እንዳናቆስልና ጠላት እንዲሳደብ እንዳናደርግ እግሮቻችንን ከመውደቅ ይጠብቃል።
ወደ ስሕተት ጎዳና፥ ወደ ስንፍና መንገድ ወይም ወደ ዓለም ልማድ አካሄድ እንዳንሄድ እግሮቻችንን ከመቅበዝበዝ ይጠብቃል።
እግሮቻችንን በድካም ከማበጥ፥ ወይም ከመንገዱ ሸካራነትና ርዝመት የተነሣ ከመላጥ ይጠብቃል።
እግሮቻችንን ከመቍሰል ይጠብቃል፤ ጫማችን ብረትና ናስ ይሆናል፤ ስለዚህ በሰይፍ ስለት ወይም በገዳይ እባቦች ላይ ብንረግጥ እንኳ ደም አይፈስብንም፥ መርዝም አይገድለንም።
ደግሞም እግሮቻችንን ከወጥመድ ያወጣል። በክፉና በተንኰለኛ ጠላቶቻችን ማታለል አንጠመድም።
እንዲህ ያለ ተስፋ ስላለን ሳንደክም እንሩጥ፥ ሳንፈራም እንመላለስ። እግሮቻችንን የሚጠብቅ እርሱ በሚገባ ይጠብቃቸዋል።
ጃንዋሪ 25
በቅን ኑዛዜ ላይ ይሠራል
«ሰዎችን ይመለከታል፤ ማንም፦ ኃጢአት ሠርቻለሁ፥ ቅን የሆነውንም አጣምሜአለሁ፥ አልጠቀመኝምም ቢል፥ ነፍሱን ወደ ጕድጓድ ከመውረድ ያድናታል፥ ሕይወቱም ብርሃንን ታያለች።» ኢዮብ 33:27, 28
ይህ ከእግዚአብሔር ሰው ተሞክሮ የተሰበሰበ የእውነት ቃል ነው፤ ከተስፋም አይለይም። ጌታ ያደረገውንና የሚያደርገውን ዓለም እስካለች ድረስ ማድረጉን ይቀጥላል። ጌታ ኃጢአታቸውን በቅንነት እየተናዘዙ ወደ እርሱ የሚመጡትን ሁሉ ወደ እቅፉ ይቀበላል፤ እንዲያውም ስለ በደላቸው በጭንቅ ያሉትን ያገኝ ዘንድ ሁልጊዜ ይጠባበቃል።
እዚህ የተነገረውን ቃል የራሳችን ልናደርገው አንችልምን? «ኃጢአት ሠርቻለሁ» እስክንል ድረስ በግላችን ኃጢአት አልሠራንምን? ቅን የሆነውን አጣምመን በፈቃዳችን ኃጢአት አልሠራንምን? ጥቅም እንደሌለበት ይልቁንም የዘላለም ኪሳራ እንዳለበት እስክናውቅ ድረስ ኃጢአት አልሠራንምን? እንግዲያስ በዚህ ቅን ምስክርነት ወደ እግዚአብሔር እንሂድ። ከዚህ የበለጠ አይጠይቅም። ከዚህ ያነሰ ልናደርግ አንችልም።
በኢየሱስ ስም በተስፋው እንማጸን። ለእኛ ከተከፈተው ከሲኦል ጉድጓድ ያድነናል፤ ሕይወትንና ብርሃንን ይሰጠናል። ስለ ምን ተስፋ እንቈርጣለን? ስለ ምንስ እንጠራጠራለን? ጌታ በትሑታን ነፍሳት አይሣለቅም። የሚናገረውን በእውነት ማለቱ ነው። በደለኞች ይቅር ሊባሉ ይችላሉ። ሞት የሚገባቸው የነጻ ምሕረት ይቅርታን ሊቀበሉ ይችላሉ። ጌታ ሆይ፥ እንናዘዛለን፤ ይቅር እንድትለንም እንለምንሃለን!
ጃንዋሪ 26
እግዚአብሔር ፍርሃትን ያባርራል
«በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም።» ዘኍልቍ 23:23
ይህ የሞኝነትንና የአጉል እምነትን ፍርሃት ሁሉ ከሥሩና ከቅርንጫፉ እንዴት ሊቈርጠው ይገባል! በጥንቈላና በምልክቶች አንዳች እውነት ቢኖር እንኳ በጌታ ሕዝብ ላይ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም። እግዚአብሔር የባረካቸውን አጋንንት ሊረግሙ አይችሉም።
እግዚአብሔርን የማይፈሩ ሰዎች እንደ በለዓም የጌታን እስራኤል ውድቀት በተንኰል ያሤሩ ይሆናል፤ ነገር ግን በምሥጢራቸውና በብልሃታቸው ሁሉ ሊወድቁ ተፈርዶባቸዋል። ባሩዳቸው ረጥቦአል፥ የሰይፋቸውም ስለት ደንዝዞአል። ይሰበሰባሉ፤ ጌታ ግን ከእነርሱ ጋር ስላልሆነ በከንቱ ይሰበሰባሉ። ዝም ብለን ተቀምጠን መረባቸውን እንዲጐነጕኑ ልንተዋቸው እንችላለን፤ በእርሱ አንያዝምና። የብዔልዜቡልን እርዳታ ቢጠሩና የእባብ ተንኰሉን ሁሉ ቢጠቀሙ እንኳ ምንም አይጠቅማቸውም፤ ድግምቱ አይሠራም፥ ምዋርቱም እነርሱን ራሳቸውን ያታልላቸዋል። ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው! ልብን እንዴት ያሳርፋል! የእግዚአብሔር ያዕቆቦች ከእግዚአብሔር ጋር ይታገላሉ፤ ነገር ግን ማንም ከእነርሱ ጋር ታግሎ አያሸንፍም። የእግዚአብሔር እስራኤሎች ከእግዚአብሔር ጋር ኃይል አግኝተው ያሸንፋሉ፤ ማንም ግን እነርሱን ለማሸነፍ ኃይል አያገኝም። ዲያብሎስን ራሱንም ሆነ፥ ቃላቸው ተንኰል የሞላበትና ዕቅዳቸው ጥልቅና የማይመረመር የሆኑትን ስውር ጠላቶች መፍራት አያስፈልገንም። በሕያው እግዚአብሔር የሚታመኑትን ሊጐዱ አይችሉም። ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ሁሉ እንገዳደራለን።
ጃንዋሪ 27
የከበረ ንስሐ
«በዚያም መንገዳችሁንና የረከሳችሁበትን ሥራችሁን ሁሉ ታስባላችሁ፤ ስለ ሠራችሁትም ክፋት ሁሉ በዓይናችሁ ፊት ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።» ሕዝቅኤል 20:43
በጌታ ተቀባይነት አግኝተን በሞገስ፥ በሰላምና በደኅንነት ስፍራ ስንቆም፥ በዚያን ጊዜ በቸሩ አምላካችን ላይ ስለ ፈጸምነው ውድቀትና ስሕተት ሁሉ ንስሐ እንድንገባ እንመራለን። ንስሐ እጅግ የከበረ ከመሆኑ የተነሣ እንከን የሌለበት አልማዝ ልንለው እንችላለን፤ ይህም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ከመዳን እጅግ ከሚቀድሱ ፍሬዎች አንዱ ሆኖ በጣፋጭ ቃል ተስፋ ተሰጥቶአል። ንስሐን የሚቀበል እርሱ ንስሐን ደግሞ ይሰጣል፤ የሚሰጠውም ከ«መራራው ሣጥን» ሳይሆን ሕዝቡን ከሚመግብበት «በማር ከተሠሩ እንጎቻዎች» መካከል ነው። በደም የተገዛ ይቅርታና የማይገባ ምሕረት ስሜት የድንጋይን ልብ ለማቅለጥ ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። ልባችን እንደ ደነደነ ይሰማናልን? የኪዳንን ፍቅር እናስብ፤ በዚያን ጊዜ ኃጢአትን እንተዋለን፥ ስለ ኃጢአት እናለቅሳለን፥ ኃጢአትንም እንጸየፋለን፤ አዎን፥ እንዲህ ያለውን ወሰን የሌለውን ፍቅር በመበደላችን ራሳችንን እንጸየፋለን። በዚህ የንስሐ ተስፋ ወደ እግዚአብሔር እንምጣ፤ እንድናስብ፥ ንስሐ እንድንገባ፥ እንድንጸጸትና እንድንመለስም እንዲረዳን እንለምነው። ወይ፥ የቅዱስ ኀዘንን መቅለጥ ብናጣጥም! የእንባ ጐርፍ እንዴት ያለ እፎይታ በሆነ ነበር! ጌታ ሆይ፥ ዓለቱን ምታው፥ ወይም ለዓለቱ ተናገር፥ ውኃውንም አፍስስ!
ጃንዋሪ 28
እንባ ያከትማል
«እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል።» ራእይ 21:4
አዎን፥ አማኞች ከሆንን ወደዚህ እንደርሳለን። ኀዘን ያከትማል፥ እንባም ይታበሳል። ይህ የልቅሶ ዓለም ነው፤ ነገር ግን ያልፋል። የዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያው ቍጥር እንደሚለው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይሆናል፤ ስለዚህም ስለ ውድቀቱና ስለሚያስከትለው መከራ የሚያስለቅስ ምንም ነገር አይኖርም። ሁለተኛውን ቍጥር አንብብ፥ ስለ ሙሽራይቱና ስለ ሰርግዋም እንዴት እንደሚናገር አስተውል። የበጉ ሰርግ ወሰን የሌለው የደስታ ጊዜ ነው፤ እንባም በዚያ ስፍራ የለውም። ሦስተኛው ቍጥር እግዚአብሔር ራሱ በሰዎች መካከል እንደሚያድር ይናገራል፤ በእርግጥም በቀኙ ለዘላለም ደስታ አለ፤ እንባም ከእንግዲህ ሊፈስ አይችልም።
ኀዘንም ጩኸትም ሥቃይም ከእንግዲህ ወዲህ በማይኖርበት ጊዜ ሁኔታችን ምን ይመስል ይሆን? ይህ አሁን ልናስበው ከምንችለው በላይ የከበረ ይሆናል። በልቅሶ የቀላችሁ ዓይኖች ሆይ፥ የሚያቃጥለውን ፈሳሻችሁን አቁሙ፤ በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንባን ከቶ አታውቁምና! እንደ ፍቅር አምላክ እንባን የሚያብስ ማንም የለም፤ እርሱም ይህን ሊያደርግ ይመጣል። «ልቅሶ ማታ ይመጣል፤ ደስታ ግን በማለዳ ይሆናል።» ጌታ ሆይ፥ ና፥ አትዘግይ፤ አሁን ወንዶችም ሴቶችም ያለቅሳሉና!
ጃንዋሪ 29
መታዘዝ በረከትን ያመጣል
«በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምንና ቅን ነገርን ስታደርግ፥ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘላለም መልካም ይሆን ዘንድ፥ ይህን የማዝዝህን ቃል ሁሉ ጠብቀህ ስማ።» ዘዳግም 12:28
መዳን በሕግ ሥራ ባይሆንም፥ ለመታዘዝ ተስፋ የተሰጡት በረከቶች ግን ለታማኝ የእግዚአብሔር ባሪያዎች አይከለከሉም። ጌታችን ስለ እኛ እርግማን በሆነ ጊዜ እርግማኖቹን አስወገደ፤ ከበረከቱ አንቀጾች ግን አንዱ እንኳ አልተሻረም።
የጌታን የተገለጠ ፈቃድ ልናስተውልና ልንሰማ፥ ትኵረታችንንም ለከፊሉ ሳይሆን «ለዚህ ቃል ሁሉ» ልንሰጥ ይገባናል። መምረጥና መለየት የለም፤ እግዚአብሔር ላዘዘው ሁሉ ያለ አድልዎ ማክበር እንጂ። ይህ ለአባትና ለልጆቹ የብፅዕና መንገድ ነው። የጌታ በረከት በመረጣቸው ላይ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ነው። በፊቱ በቅንነት ቢመላለሱ፥ ጌታ የባረካቸው ዘር እንደ ሆኑ ሰዎችን ሁሉ እንዲያውቁ ያደርጋል።
በማጭበርበር ወይም በሁለት ልብ ሥራ ለእኛም ሆነ ለእኛ ለሆኑት ምንም በረከት ሊመጣ አይችልም። ዓለምን የመምሰልና የርኵሰት መንገዶች ለእኛም ሆነ ለእኛ ለሆኑት መልካም ነገር ሊያመጡ አይችሉም። በእግዚአብሔር ፊት በመልካም ስንሄድ ለእኛ መልካም ይሆንልናል። ቅንነት ካላበለጸገን ተንኰል አያበለጽገንም። እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው እኛንም ደስ ያሰኘናል።
ጃንዋሪ 30
ሰማያዊ አጃቢ
«እነሆም፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድበትም ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ።» ዘፍጥረት 28:15
የጉዞ ምሕረት ያስፈልገናልን? የተመረጡት እነሆ — የእግዚአብሔር መገኘትና ጥበቃ። በስፍራ ሁሉ ሁለቱም ያስፈልጉናል፤ በገዛ ምኞታችን ብቻ ሳይሆን በግዴታ ጥሪ ብንሄድ በስፍራ ሁሉ እናገኛቸዋለን። በመለኮታዊ ፈቃድ በላያችን በተጣለ ጊዜ ወደ ሌላ አገር መዛወርን እንደ አሳዛኝ ግዴታ ስለ ምን እንመለከተዋለን? በአገር ሁሉ አማኝ እኩል መጻተኛና እንግዳ ነው፤ ነገር ግን በየትኛውም ክፍለ ምድር ለቅዱሳኑ በትውልድ ሁሉ እንደ ሆነላቸው ጌታ ማደሪያው ነው። የምድራዊ ንጉሥ ጥበቃ ሊቀርብን ይችላል፤ እግዚአብሔር ግን «እጠብቅሃለሁ» ሲል በምንም እውነተኛ አደጋ ውስጥ አይደለንም። ይህ ለመንገደኛ የተባረከ የይለፍ ፈቃድ፥ ለስደተኛም ሰማያዊ አጃቢ ነው።
ያዕቆብ ከዚያ ቀደም ከአባቱ ቤት ወጥቶ አያውቅም ነበር፤ የእናቱ ልጅ ነበረ እንጂ እንደ ወንድሙ ጀብደኛ አልነበረም። ቢሆንም ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ሄደ። ጓዙ ጥቂት ነበረ፥ አገልጋዮችም አልነበሩትም፤ ሆኖም ከዚህ የከበረ ጠባቂ ጋር የተጓዘ አንድም ልዑል የለም። በሜዳ ላይ ተኝቶ ሳለ እንኳ መላእክት ይጠብቁት ነበር፥ ጌታ እግዚአብሔርም ተናገረው። ጌታ ሂዱ ቢለን፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ጋር «ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ» እንበል።
ጃንዋሪ 31
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይሰማል
«አምላኬ ይሰማኛል።» ሚክያስ 7:7
ወዳጆች ታማኝ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ጌታ ግን ከጸጋ ከተሞላች ነፍስ ፊቱን አይመልስም፤ ይልቁንም ምኞቷን ሁሉ ይሰማል። ነቢዩ «በብብትህ ከምትተኛው ሴት የአፍህን ደጅ ጠብቅ። የሰው ጠላቶቹ የቤቱ ሰዎች ናቸው» ይላል። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ነው፤ ነገር ግን በእንዲህ ያለ ጊዜ እንኳ ከሁሉ የሚበልጠው ወዳጅ ታማኝ ሆኖ ይኖራል፥ ኀዘናችንንም ሁሉ ልንነግረው እንችላለን።
ጥበባችን ከወንዶችም ሆነ ከሴቶች ጋር መጣላት ሳይሆን ወደ ጌታ መመልከት ነው። የፍቅር ልመናችን በገዛ ዘመዶቻችን ቸል ቢባል፥ የመዳናችንን አምላክ እንጠባበቅ፤ እርሱ ይሰማናልና። ከሌሎች ጭካኔና ግፍ የተነሣ እንዲያውም አብልጦ ይሰማናል፤ እኛም «ጠላቴ ሆይ፥ በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ!» ብለን የምንጮኽበት ምክንያት በቅርቡ ይኖረናል።
እግዚአብሔር ሕያው አምላክ ስለ ሆነ ሊሰማ ይችላል፤ አፍቃሪ አምላክ ስለ ሆነ ይሰማል፤ የኪዳን አምላካችን ስለ ሆነ እኛን ለመስማት ራሱን አስሮአል። እያንዳንዳችን ስለ እርሱ «አምላኬ» ብለን መናገር ብንችል፥ በፍጹም እርግጠኝነት «አምላኬ ይሰማኛል» ልንል እንችላለን። እንግዲያስ፥ የምትደማ ልብ ሆይ፥ ና፤ ኀዘንህም ለአምላክህ ለጌታ ራሱን ይንገር! በስውር ተንበርክኬ በውስጤ «አምላኬ ይሰማኛል» ብዬ በሹክሹክታ እናገራለሁ።