ምዕራፍ 1 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
መቅድም
ለዕለት ጥቅም የተዘጋጁ
ውድ ተስፋዎች
ከአጭር የልምድ ማብራሪያዎች ጋር
ደራሲ
ሲ. ኤች. ስፐርጀን
መቅድምከእግዚአብሔር የተሰጠ ተስፋ ለተቀባዩ ከሚከፈል ቼክ ጋር ቢነጻጸር እጅግ አስተማሪ ነው። ለአማኙ የሚሰጠው አንዳች መልካም ነገር እንዲያገኝ ብሎ ነው። በምቾት አንብቦት ከዚያም እንዲተወው አይደለም። አይደለም፤ ሰው ቼክን እንደሚይዝ ተስፋውንም እንደ እውነተኛ ነገር ሊይዘው ይገባዋል።
ተስፋውን ወስዶ እውነት እንደ ሆነ በግሉ በመቀበል በራሱ ስም ይፈርምበታል። በእምነት የራሱ አድርጎ ይቀበለዋል። እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ፥ በተለይም በዚህ የተስፋ ቃል እውነተኛ እንደ ሆነ ማኅተሙን ያትማል። ከዚህም አልፎ፥ የበረከቱ የታመነ ተስፋ ስላለው በረከቱን እንዳገኘ ያምናል፤ ስለዚህም በረከቱን መቀበሉን ለመመስከር ስሙን ይፈርምበታል።
ይህን ካደረገ በኋላ፥ ሰው ቼክን በባንኩ ቆጣሪ ላይ እንደሚያቀርብ፥ ተስፋውንም በእምነት ለጌታ ማቅረብ አለበት። ፍጻሜውን እየጠበቀ በጸሎት ሊማጸንበት ይገባዋል። ወደ ሰማይ ባንክ በትክክለኛው ቀን ከመጣ፥ የተገባለትን ገንዘብ ወዲያው ይቀበላል። ቀኑ ገና ወደ ፊት ከሆነ ግን እስኪደርስ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ አለበት፤ እስከዚያው ግን ተስፋውን እንደ ጥሬ ገንዘብ ሊቈጥረው ይችላል፤ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ባንኩ በእርግጥ ይከፍላልና።
አንዳንዶች በቼኩ ላይ የእምነትን ፊርማ ሳያኖሩ ይቀራሉ፤ ስለዚህም ምንም አያገኙም፤ ሌሎችም ለማቅረብ ይዘገያሉ፤ እነርሱም ደግሞ ምንም አይቀበሉም። ይህ የተስፋው ጥፋት አይደለም፤ በአስተዋይነትና እንደ ነጋዴ በሥርዓት በእርሱ የማይሠሩ ሰዎች ጥፋት ነው እንጂ።
እግዚአብሔር የማይከፍለውን መያዣ አልሰጠም፤ የማይፈጽመውንም ተስፋ አላበረታታም። ወንድሞቼ ይህን እንዲያምኑ ለመርዳት ይህችን ትንሽ መጽሐፍ አዘጋጀሁ። ተስፋዎቹን ራሳቸውን ማየት ለእምነት ዓይኖች መልካም ነው፤ የጸጋን ቃላት ባጠናን መጠን ከቃላቱ የበለጠ ጸጋ እናገኛለን። በሚያጽናኑት መጻሕፍት ላይ ከመከራና ከልምድ የተገኘ ፍሬ የሆነውን የራሴን ምስክርነት ጨምሬአለሁ። የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ሁሉ አምናለሁ፤ ብዙዎቹን ግን በግሌ ፈትኜ አረጋግጫቸዋለሁ። በእኔ ላይ ስለ ተፈጸሙ እውነት እንደ ሆኑ አይቻለሁ። ይህ ለወጣቶች የሚያበረታታ፥ ለአረጋውያንም መጽናናት የማይጎድለው እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። የአንድ ሰው ልምድ ለሌላው እጅግ ሊጠቅም ይችላል፤ ስለዚህም ነው በቀድሞ ዘመን የነበረው የእግዚአብሔር ሰው «እግዚአብሔርን ፈለግሁት፥ ሰማኝም»፤ ደግሞም «ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው» ብሎ የጻፈው።
እነዚህን የዕለት ንባቦች መጻፍ የጀመርሁት በክርክር ማዕበል ውስጥ እየተንገላታሁ ሳለሁ ነበር። ከዚያ ወዲህ ደግሞ «የሚዋኙበት ውኃ» ውስጥ ተጣልሁ፤ የእግዚአብሔር ደጋፊ እጅ ባይኖር ኖሮ የሚያሰጥም ውኃ በሆነ ነበር። ከብዙ መውቂያዎች መከራን ታገሥሁ። ከአእምሮ ጭንቀት በኋላ ብርቱ የአካል ሕመም ተከተለ፤ ከዚህም ጋር ሞት ያመጣው ሐዘንና እንደ ሕይወቴ በምወዳት ሰው ላይ የደረሰ መከራ ተጨመረ። ውኃው ማዕበል በማዕበል ላይ ሳያቋርጥ ይጎርፍ ነበር። ይህን የምጠቅሰው ርኅራኄን ለመጠየቅ አይደለም፤ አንባቢው የየብስ መርከበኛ እንዳልሆንሁ እንዲያይ ብቻ ነው። ሰላማዊ ያልሆኑትን ውቅያኖሶች ብዙ ጊዜ አቋርጫለሁ፤ የሞገዱን መናወጥና የነፋሱን ጩኸት አውቃለሁ። የእግዚአብሔር ተስፋዎች እንደ አሁኑ ሰዓት ውድ ሆነውልኝ አያውቁም። አንዳንዶቹን እስከ አሁን ድረስ አልተረዳኋቸውም ነበር፤ የሚበስሉበት ቀን ገና አልደረሰም ነበርና፤ ትርጉማቸውን ለማስተዋል እኔ ራሴ ገና አልበሰልሁም ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው ይልቅ አሁን ለእኔ እንዴት እጅግ ድንቅ ሆኖአል! ጌታን በመታዘዝና ከሰፈር ውጭ ነቀፌታውን በመሸከም አዲስ ተስፋዎችን አልተቀበልሁም፤ ነገር ግን ውጤቱ ለእኔ የተቀበልሁ ያህል ነው፤ አሮጌዎቹ ተስፋዎች በበለጸገ ሀብት ተከፍተውልኛልና። በተለይ ጌታ ለባሪያው ለኤርምያስ የተናገረው ቃል በጆሮዬ እጅግ ጣፋጭ ሆኖ ተሰምቶአል። የማይሰሙትን፥ ወይም ሰምተውም የማያምኑትን ሰዎች መናገር ዕጣው ነበረ። የተከፋ ፍቅርና የጸና ታማኝነት የሚያመጣው ሐዘን የእርሱ ነበረ፤ ሕዝቡን ከስሕተታቸው ሊመልሳቸው ይወድ ነበር፤ እርሱ ራሱ ግን የጌታን መንገድ አይተውም ነበር። ተፈጥሮ ብቻዋን ብትሆን በምትወድቅበት ስፍራ አእምሮው እንዳይዝል የጠበቁት ጥልቅ የሚያጸና ኃይል ያላቸው ቃላት ለእርሱ ነበሩ። እነዚህንና እንደነዚህ ያሉትን የጸጋ ወርቃማ ዓረፍተ ነገሮች ከሚያስፈልገኝ ምግብ ይልቅ ወደድኋቸው፤ በእነርሱም እነዚህን ገጾች አበለጸግሁ።
ኦ፥ ከጌታዬ ባሪያዎች አንዳንዶቹን ማጽናናት ብችል! ልባቸውን ለማጽናናት ብዬ ከራሴ ልብ ጽፌአለሁ። በመከራቸው እንዲህ እላቸዋለሁ — ወንድሞቼ፥ እግዚአብሔር ቸር ነው። አይተዋችሁም፤ እስከ መጨረሻ ያሻግራችኋል። አሁን ላለባችሁ ችግር የተዘጋጀ ተስፋ አለ፤ ብታምኑና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በምሕረት ዙፋን ፊት ብትማጸኑበት፥ እናንተን ለመርዳት የተዘረጋውን የጌታን እጅ ታያላችሁ። ሌላው ሁሉ ይወድቃል፤ ቃሉ ግን ከቶ አይወድቅም። ቍጥር በሌላቸው ጊዜያት ለእኔ እጅግ ታማኝ ሆኖልኛልና በእርሱ እንድትታመኑ ላበረታታችሁ ይገባኛል። ይህን ባላደርግ ለእግዚአብሔር ምስጋና ቢስ፥ ለእናንተም ጨካኝ እሆን ነበር።
አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ የጌታን ሕዝብ በአዲስ እምነት ያነሣሣ! ያለ እርሱ መለኮታዊ ኃይል የምናገረው ሁሉ ከንቱ እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ ሕያው በሚያደርገው አሠራሩ ግን እጅግ ትሑት የሆነው ምስክርነት እንኳ የሚብረከረኩትን ጉልበቶች ያጸናል፥ የደከሙትንም እጆች ያበረታል። ባሪያዎቹ ያለ ጥርጥር ሲታመኑበት እግዚአብሔር ይከበራል። ከሰማያዊ አባታችን ጋር ከመጠን በላይ ሕፃናት ልንሆን አንችልም። ልጆቻችን ስለ ፈቃዳችንም ሆነ ስለ ችሎታችን አይጠይቁም፤ ከአባታቸው አንድ ጊዜ ተስፋ ከተቀበሉ በኋላ እንደ ፀሐይ የተረጋገጠ እንደ ሆነ ሳይጠራጠሩ በፍጻሜው ተስፋ ደስ ይላቸዋል። በዓመቱ ውስጥ ለእያንዳንዱ ቀን ያዘጋጀኋትን ትንሽ ክፍል ሲያነቡ፥ ምናልባት ከቶ የማላያቸው ብዙ አንባቢዎች በእግዚአብሔር ላይ እንዲህ ያለውን የሕፃን መታመን ግዴታና ደስታ ያግኙ።
ለረጅም ዓመታት በሺህ የሚቈጠሩ የእግዚአብሔር ሕዝብ «ማለዳ በማለዳ» እና «ማታ በማታ» የተሰኙትን መጻሕፍቶቼን አንብበዋል፤ ብዙዎቹም ጽፈውልኝ ከንባቡ ያገኙትን ጥቅም ለመመስከር ደግነት አድርገዋል። ይህች ትንሽ መጽሐፍ በእነዚያ መጻሕፍት ላይ ጣልቃ እንደማትገባ ተስፋ አደርጋለሁ። የእነዚያ የዕለት ክፍሎች ከብዙ ዓይነት ርዕሶች የተሰበሰቡ ናቸው፤ ስለ ትምህርት፥ ስለ ልምድ፥ ስለ ተግባርና ስለ ሌላውም ሁሉ ስለሚናገሩም ይበልጥ ጠቃሚዎች ናቸው። ይህች ግን የተስፋ ጣፋጭ ምግብ ብቻ ናት፤ ሙሉዎቹን ማዕዶች ልታስቀር አይገባትም፤ እንዲያውም ለእነርሱ ፍላጎትን እንድታነሣሣ ተስፋ አደርጋለሁ።
ጌታችን ኢየሱስ ለበጎቹና ለጠቦቶቹ ያቀረብሁትን ይህን አገልግሎቴን ይቀበል፤ ከ
የማይገባው ባሪያው፥
ሲ. ኤች. ስፐርጀን