በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ
አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀቶች፣ ወይም በመንፈስ ቅዱስ እንደ ገና መሞላት

ምዕራፍ 4 · 2 ደቂቃ ንባብ

አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀቶች፣ ወይም በመንፈስ ቅዱስ እንደ ገና መሞላት

በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለት ቁጥር አራት ላይ፦ «በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ ... ይናገሩ ጀመር» ወዘተ ብለን እናነባለን። ይህም የሐዋርያት ሥራ 1:5 ፍጻሜ ነበር፦ «እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ»። በዚያን ጊዜ «መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው» (የሐዋርያት ሥራ 2:4)፣ ወይም «በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ» (የሐዋርያት ሥራ 1:5) ተብሎ ከተነገረላቸው ሰዎች መካከል በስም ከተጠቀሱት አንዱ ጴጥሮስ ነበር። ወደ ምዕራፍ አራት ቁጥር ስምንት ስንሻገር ደግሞ፦ «በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ እንዲህ አላቸው» ወዘተ ብለን እናነባለን። እዚህ ላይ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ አዲስ መሞላትን ተለማመደ።

ደግሞም በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር ሠላሳ አንድ ላይ፦ «ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው» ብለን እናነባለን።

ጴጥሮስ በዚህ ጉባኤ ውስጥ ከነበሩት አንዱ እንደ ሆነ ተጠቅሷል (ቁጥር 19 እና 23)፤ ስለዚህ ጴጥሮስ እዚህ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላ እናያለን። አንድ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ «በመንፈስ ቅዱስ መጠመቁ» በቂ እንዳልሆነ ግልጥ ነው። አዳዲስ የአገልግሎት ፈተናዎችና ችግሮች በተነሡ ቁጥር በመንፈስ አዲስ መሞላት ያስፈልጋል። ይህን አለመገንዘብ በብዙ ሰዎች አገልግሎት ላይ እጅግ አሳዛኝና ከባድ ውጤት አስከትሏል። እንዲህ ያለው ሰው በሕይወቱ በአንድ ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቋል፤ ከዚያም በዚያው በአንዱ ልምምድ ኃይል ቀሪ ሕይወቱን ሁሉ ለመዝለቅ ይታገላል።

በአንድ ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያለ ጥርጥር ይሠሩ የነበሩ፣ ዛሬ ግን ያን ኃይል ስለ መያዛቸው የሚያሳዩት ምልክት እጅግ ጥቂት የሆነ ብዙ ሰዎችን የምናየው በአብዛኛው በዚህ ምክንያት ነው።

ለሚመራው ለእያንዳንዱ አዲስ አገልግሎት፣ ለምንቀርባት ለእያንዳንዷ አዲስ ነፍስ፣ ለክርስቶስ ለሚፈጸመው ለእያንዳንዱ አዲስ ተግባር፣ ለእያንዳንዱ አዲስ ቀንና በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ውስጥ ለሚያጋጥመው ለእያንዳንዱ አዲስ ችግር በመንፈስ ቅዱስ አዲስ መሞላትን በግልጥ ልንፈልግ ይገባናል። «የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል» (1ኛ ዮሐንስ 2:27) የሚለውን፣ ወይም መንፈስ ቅዱስ የሚሰጣቸው ስጦታዎች ጸንተው የሚኖሩ መሆናቸውን አልክድም፤ እኔ የምለው ግን፣ ከልምምድና ከምልከታ የሚገኘውን ማስረጃ እንኳ ሳንጠቅስ፣ ግልጥና የበዛ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ይዤ፣ ስለዚህ ስጦታ «ቸል አትበል» እንደ ተባለ (1ኛ ጢሞቴዎስ 4:14)፣ ይልቁንም «እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው» እንደ ገና ሊነሣሣ እንደሚገባ (2ኛ ጢሞቴዎስ 1:6)፣ እንዲሁም ኃይል እንዲቀጥልና እንዲጨምር በመንፈስ ቅዱስ ደጋግሞ መሞላት አስፈላጊ እንደ ሆነ ብቻ ነው።

እንግዲህ ጥያቄው ይነሣል፦ እነዚህ በመንፈስ ቅዱስ አዳዲስ መሞላቶች «አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀቶች» ተብለው ሊጠሩ ይገባቸዋልን? በአንድ በኩል፣ በሐዋርያት ሥራ 2:4 ላይ «መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው» የሚለው አገላለጽ በሐዋርያት ሥራ 1:5 «በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ» በሚሉት ቃላት ተስፋ የተሰጠበትን ልምምድ ለመግለጥ እንደ ዋለ፣ ስለዚህም ሁለቱ አገላለጾች እስከዚህ ድረስ አንድ ትርጉም እንዳላቸው መቀበል ግድ ነው፤ በሌላ በኩል ግን «በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ» የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመጀመሪያው ልምምድ በቀር ለሌላ ለየትኛውም ልምምድ እንዳልዋለ፣ ከዚህም በላይ «መጠመቅ» የሚለው ቃል በራሱ የመጀመሪያን ልምምድ እንደሚያመለክት ልብ ሊባል ይገባል።

ስለዚህ «አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀቶች» ብለው የሚናገሩ ሰዎች ሊያመለክቱት ለሚፈልጉት እውነት ጸንተን ብንቆምም፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ወጥ አጠቃቀም ተከትሎ ከመጀመሪያው በኋላ የሚመጡትን ልምምዶች «በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ» ሳይሆን «በመንፈስ ቅዱስ መሞላት» ብሎ መጥራት እጅግ ጥበብ ያለበት ይመስላል።

ምዕራፍ 4 ተጠናቋል

አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀቶች፣ ወይም በመንፈስ ቅዱስ እንደ ገና መሞላት

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል