ሁሉም በጸጋ
ለአንተ

ምዕራፍ 1 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

ለአንተ

ይህን መልእክት የተናገረውና የጻፈው ሰው ብዙዎችን ወደ ጌታ ኢየሱስ ባይመራ እጅግ ያዝናል። ይህ መልእክት የሚላከው፣ ፈቃዱ ቢሆን ሚሊዮኖችን ለመለወጥ እንዲጠቀምበት፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ እንደ ሕፃን በመደገፍ ነው። ብዙ ድሆች ወንዶችና ሴቶች ይህን ትንሽ መጽሐፍ እንደሚያነሡ፣ ጌታም በጸጋ እንደሚጎበኛቸው አያጠራጥርም። ለዚህም ዓላማ እጅግ ቀላል የሆነ ቋንቋ ተመርጦአል፤ ብዙ የዕለት ተዕለት አነጋገሮችም ጥቅም ላይ ውለዋል። ነገር ግን ባለ ጠጎችና ባለ ማዕረጎች ይህን መጽሐፍ በጨረፍታ ቢመለከቱት፣ መንፈስ ቅዱስ እነርሱንም ሊነካቸው ይችላል፤ ያልተማሩ ሊረዱት የሚችሉት ነገር ለተማሩትም ማራኪነቱ አይቀንስምና። ኦ፣ ብዙ ነፍሳትን የሚማርኩ ታላላቅ ሰዎች የሚሆኑ አንዳንዶች ምነው ባነበቡት!

እዚህ በሚያነቡት ነገር ወደ ሰላም መንገዳቸውን የሚያገኙ ስንት እንደ ሆኑ ማን ያውቃል? ውድ አንባቢ ሆይ፣ ለአንተ ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ጥያቄ ይህ ነው፦ አንተ ከእነርሱ አንዱ ትሆናለህን?

አንድ ሰው በመንገድ ዳር የውኃ ምንጭ አቆመ፤ በአጠገቡም አንድ ጽዋ በትንሽ ሰንሰለት አንጠለጠለ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ታላቅ የጥበብ ሐያሲ የምንጩን ቅርጽ እጅግ እንደ ነቀፈው ተነገረው። እርሱም፦ «ነገር ግን» አለ፣ «ብዙ የተጠሙ ሰዎች ከእርሱ ይጠጣሉን?» ከዚያም በሺዎች የሚቈጠሩ ድሆች — ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች — በዚህ ምንጭ ጥማቸውን እንደሚያረኩ ነገሩት፤ እርሱም ፈገግ ብሎ በሐያሲው አስተያየት ብዙም እንዳልተጨነቀ ተናገረ፤ ብቻ በአንድ በሚያቃጥል የበጋ ቀን ሐያሲው ራሱ ጽዋውን ሞልቶ እንዲጠጣ፣ እንዲታደስም፣ የጌታንም ስም እንዲያመሰግን ተስፋ አደረገ።

እነሆ ምንጬ፣ እነሆም ጽዋዬ፤ ከፈለግህ ንቀፍ፤ ነገር ግን ከሕይወት ውኃ ግድ ጠጣ። እኔ ግድ የሚለኝ ይህ ብቻ ነው። የንጉሣዊ ደም ያለውን ልዑል ደስ አሰኝቼ ወደ እግዚአብሔር ሳልመልሰው ከምቀር፣ ከመንገድ ጠራጊዎች ወይም ከቡትቶ ለቃሚዎች እጅግ ድሃ የሆነውን ሰው ነፍስ ብባርክ እመርጣለሁ።

አንባቢ ሆይ፣ እነዚህን ገጾች በቁም ነገር ልታነብ አስበሃልን? እንዲህ ከሆነ ከመጀመሪያው ተስማምተናል፤ ነገር ግን እዚህ የታለመው ቁም ነገር ክርስቶስንና መንግሥተ ሰማያትን ከማግኘትህ ያነሰ አይደለም። ኦ፣ ይህን አብረን ብንፈልግ! እኔ ይህን ትንሽ መጽሐፍ በጸሎት በመቀደስ እፈልገዋለሁ። አንተስ ወደ እግዚአብሔር ቀና ብለህ በመመልከትና በምታነብበት ጊዜ እንዲባርክህ በመለመን አትተባበረኝምን? የእግዚአብሔር መግቦት እነዚህን ገጾች በመንገድህ ላይ አስቀምጦአቸዋል፤ የምታነብበት ጥቂት ትርፍ ጊዜ አለህ፤ ትኩረትህንም ልትሰጣቸው ፈቃደኛ እንደ ሆንህ ይሰማሃል። እነዚህ መልካም ምልክቶች ናቸው። የተወሰነው የበረከት ጊዜ ለአንተ ደርሶ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ያም ሆነ ይህ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፦ «ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ።»

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀጣይ