የታደሰው እረኛ
ክፍል 1 – ራስን የማዋረድ ተግባራዊ ትምህርት

ምዕራፍ 9 · 51 ደቂቃ ንባብ · 1 ሰዓት 6 ደቂቃ ማዳመጥ

ክፍል 1 – ራስን የማዋረድ ተግባራዊ ትምህርት

የተከበራችሁና የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ዛሬ በዚህ ስፍራ የተሰበሰብንበት ጉዳይ ስላለፈው ቸልተኝነታችን ነፍሳችንን በጌታ ፊት ለማዋረድ፣ ወደፊትም በሥራችን የእግዚአብሔርን እርዳታ ለመለመን ነው። በእርግጥም ያለ መጀመሪያው ሁለተኛውን ልንጠብቅ አንችልም ማለት ይቻላል። እግዚአብሔር ወደፊት በምናደርገው ግዴታችን ሊረዳን ከወደደ፣ አስቀድሞ ስላለፈው ኃጢአታችን ያዋርደናል። ከልብ እስኪያለቅስባቸው ድረስ ጥፋቶቹ የማይሰሙት ሰው፣ እነርሱን ለማረም የሚያነሣሣው የበለጠ ስሜት ሊኖረው አይችልም። የንስሐ ኀዘን የልብና የሕይወት ለውጥ ሳይኖር ሊገኝ ይችላል፤ ስሜትን ማነሣሣት ከእውነተኛ መለወጥ ይልቅ ይቀላልና። ለውጡ ግን በቂ መጠን ያለው ኀዘን ሳይኖር ሊሆን አይችልም። በእርግጥም ኑዛዜያችንን ከዚህ መጀመራችን ተገቢ ነው፤ እኛ ራሳችን ምንም ወይም ጥቂት ብቻ የምናደርገውን ነገር ከሕዝባችን መጠበቅ በእኛ ዘንድ እጅግ የተለመደ ነውና። እኛ ራሳችን ሳንዋረድ እነርሱን ለማዋረድ ምንኛ እንደክማለን! የገዛ ዓይኖቻችን ደረቆች ሆነው ሳሉ ጥቂት የንስሐ እንባ (ያውም እጅግ ጥቂት) ከእነርሱ ለማውጣት ምንኛ አጥብቀን እንሟገታቸዋለን! ወዮ! በቃላችን ልባቸውን ለማቅለጥና ለማለዘብ እየጣርን ሳለ የልብ ድንዳኔ ምሳሌ ምንኛ እንሆናቸዋለን! ኧረ የአድማጮቻችንን ልብ ለመንካትና ለማቅናት እንደምንተጋው እኩሌታውን ያህል እንኳ የገዛ ልባችንን ለመንካትና ለማቅናት ብንተጋ ኖሮ፣ የብዙዎቻችን ሁኔታ አሁን እንዳለው ባልሆነ ነበር! እነርሱን ለማዋረድ የምናደርገው እጅግ ጥቂት ነው፤ ነገር ግን አንዳንዶቻችን ራሳችንን ለማዋረድ የምናደርገው ከዚያ እጅግ ያነሰ እንደ ሆነ እፈራለሁ። ብዙዎች ለሌሎች ሰዎች ነፍስ አንዳች ነገር ያደርጋሉ፤ ሊጠነቀቁላት የሚገባ የገዛ ነፍስ እንዳላቸው ግን የረሱ ይመስላሉ። ነገሩን የሚይዙት እንዲህ አድርገው ነው፦ የሥራው ድርሻቸው ወደ ንስሐ መጥራት፣ የአድማጮቹ ድርሻ ደግሞ ንስሐ መግባት፤ የእነርሱ ድርሻ እንባንና ኀዘንን መጠየቅ፣ የሌሎች ሰዎች ድርሻ ደግሞ ማልቀስና ማዘን፤ የእነርሱ ድርሻ በኃጢአት ላይ መጮኽ፣ የሕዝቡ ድርሻ ደግሞ ኃጢአትን መተው፤ የእነርሱ ድርሻ ግዴታን መስበክ፣ የአድማጮቹ ድርሻ ደግሞ ግዴታን በተግባር መፈጸም እንደ ሆነ አድርገው።

ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሕዝቡን ኃጢአት ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ኃጢአት እንደ ተናዘዙ እናገኛለን። ዕዝራ እያለቀሰና በእግዚአብሔር ቤት ፊት ራሱን እየጣለ የሕዝቡን ብቻ ሳይሆን የካህናቱንም ኃጢአት ተናዘዘ። ዳንኤልም የሕዝቡን ብቻ ሳይሆን የራሱንም ኃጢአት ተናዘዘ። ቀደም ብለው የተገለጹትን ግዴታዎች፣ እኛም ምን ያህል ባልተሟላ ሁኔታ እንደ ፈጸምናቸው በሚገባ ብናስብ፣ ራሳችንን የምናዋርድበት ምክንያት አለን ወይ በሚለው ጥያቄ ላይ ማመንታት የሚያስፈልገን አይመስለኝም። ስናገርም ራሴን ብኰንንም ይህን ማለት ግድ ይለኛል፦ ጳውሎስ በኤፌሶን ላሉት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሰጠውን ይህን አንድ ምክር ብቻ አንብቦ ሕይወቱን ከእርሱ ጋር የሚያነጻጽር ሰው፣ ቸልተኝነቱ ተሰምቶት ልቡ ካልቀለጠ፣ በእግዚአብሔር ፊት በትቢያ ላይ ካልወደቀ፣ ታላቁንም ጕድለቱን እንዲያለቅስበትና ወደ ክርስቶስ ደምና ወደ ይቅር ባዩ ጸጋው መጠጊያ ፍለጋ እንዲሸሽ ካልተገደደ፣ የደነዘዘና ልበ ደንዳና መሆን አለበት። ወንድሞች ሆይ፣ ከእናንተ ማንም የኑዛዜን፣ የጸጸትንና ራስን የማዋረድን አስፈላጊነት፣ ያውም ለኃጢአት ስርየት የሚያስፈልግ መሆኑን የሚያቃልለውን የልቅነት ትምህርት በአእምሮው እንደማይቀበል እርግጠኛ ነኝ! እንግዲያስ ልባችን እንደ አእምሮአችን ቀና አማኝ አለመሆኑ የሚያሳዝን አይደለምን? ነገር ግን ትምህርታችንን ስናውቀውና ልንናገረው ስንችል እኩሌታውን ብቻ እንደ ተማርነው አያለሁ። አእምሮ ከተማረው በኋላ ፈቃዳችንንና ስሜታችንን፣ ዓይናችንን፣ አንደበታችንንና እጃችንን ለማስተማር የበለጠ ድካም ይቀራል። ከእኛ ብዙዎቻችን አድማጮቻችንን በስብከታችን ማስተኛታችን የሚያሳዝን ነገር ነው፤ ነገር ግን እኛ ራሳችን አጥንተንና ሰብከን ራሳችንን አስተኝተን፣ በልብ ድንዳኔ ላይ ይህን ያህል ረጅም ጊዜ ተናግረን የገዛ ልባችን በገዛ ተግሣጻችን ድምፅ መካከል ደንድኖ ከሆነ፣ ይህ ይበልጥ የሚያሳዝን ነው። እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ኀዘን ያለ ምክንያት እንዳልሆነ ታዩ ዘንድ፣ ብዙ ዓይነት ኃጢአቶቻችንን አሳስባችኋለሁ፤ በፊታችሁም በቅደም ተከተል አቀርባቸዋለሁ፤ ይህም በነጻ ኑዛዜ በግልጽና በታማኝነት እንድንይዛቸው፣ «ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ» የሆነው እግዚአብሔርም ይቅር እንዲለንና እንዲያነጻን ነው። በዚህ ጉዳይ ከልብ እንደምትስማሙኝ እገምታለሁ፤ የእናንተን ማንነትና በዚህ ሹመት ያሉትን ሌሎችን ባዋርድ እንኳ፣ በእኔ ከመቀየም ይልቅ ክሱን በፈቃደኝነት ፈርማችሁ በትሕትና ራሳችሁን የምትከሱ እንደምትሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እኔም ሌሎችን በመክሰስ ራሴን ከማጽደቅ እጅግ የራቅሁ ነኝ፤ እንዲያውም በክሱ ሰነድ ላይ ስሜን ከመጀመሪያዎቹ ጋር ከልብ አስፍራለሁ። በብዙና በታላላቅ መተላለፎች የሚጠየቅ ጐስቋላ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን ሊያጸድቅ እንዴት ይደፍራል? ወይስ ሕሊናው በእርሱ ላይ ብዙ የሚናገርበት ሰው እንዴት ንጹሕ ነኝ ብሎ ሊሟገት ይችላል? በአገልግሎቱ ላይ ኀፍረት የማመጣ ከሆነ፣ ኀፍረታችን የሆነውን ኃጢአት በመግለጥ የማመጣው በሹመቱ ላይ ሳይሆን በእኛ ማንነት ላይ ነው። የከፍተኛው ሥራችን ክብር ለኃጢአታችን ምንም ክብር አያጋራውም፤ «ኃጢአት ለወገን ውርደት ነው»ና። መጋቢዎችም ሆኑ ሕዝብ፣ ምሕረትን የሚያገኙት «የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል» የተባለላቸው ብቻ ናቸው፤ «ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ላይ ይወድቃል»።

ጥፋተኛ የሆንባቸውን ታላላቅ ኃጢአቶች ሁሉ ለመዘርዘር አልሞክርም፤ ስለዚህ አንዱን ኃጢአት ለይቼ ሳልጠቅሰው ብተወው፣ ይህ ኃጢአቱን እንደ መካድ ወይም እንደ ማጽደቅ ሊቈጠር አይገባም። ነገር ግን ራስን ለማዋረድና ፈጥኖ ለመታረም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚጮኹትን ጥቂቶቹን ለምሳሌ ማቅረብ ግዴታዬ እንደ ሆነ እቈጥራለሁ።

ብቻ በመጀመሪያ ይህን ምስክርነት አስቀድሜ መናገር ግድ ይለኛል፦ አሁን በመካከላችን ያሉት ጥፋቶች ሁሉ ቢኖሩም፣ እንግሊዝ አገር ከሆነች ጀምሮ እንደ ዛሬው ያሉ ብቁና ታማኝ አገልጋዮች ኖረዋት ያውቃሉ ብዬ አላምንም፤ በምድር ላይ ካሉት አሕዛብም እንዲህ ያሉ አገልጋዮች ያሏቸው ጥቂቶች፣ ምናልባትም አንድም የሌለ እንደ ሆነ እፈራለሁ። በእነዚህ ዐሥራ ሁለት ዓመታት ውስጥ የመጣው ለውጥ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ ማየቴ በዓለም ላይ ካገኘኋቸው ታላላቅ ደስታዎች አንዱ እንደ ሆነ እርግጠኛ ነኝ። ኦ፣ በዚያን ጊዜ በታላቅ ጨለማ ይኖሩ የነበሩ ስንት ጉባኤዎች አሁን በግልጽና በተደጋጋሚ ይማራሉ! በዚያን ጊዜ ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር አሁን በአንድ አውራጃ ውስጥ ስንት ብቁና ታማኝ ሰዎች አሉ! ባለፈው ሁከት መጀመሪያ ላይ ትናንሽ ልጆች የነበሩትን የብዙ ወጣቶችን ጥናት እግዚአብሔር እንዴት በቸርነቱ አከናወነላቸው፤ ስለዚህም አሁን አብዛኞቹን ታላላቆቻቸውን ይጋርዷቸዋል! ከሃያ ዓመት በፊት፣ እንዲያውም ከዚያ ባነሰ ጊዜ፣ ከእነዚያ ጥንታውያን የተከበሩ የሥነ መለኮት ሰዎች አንዱን ለመስማት ስንት ማይል በሄድሁ ነበር፤ አሁን ግን ታናናሾቻቸው በግልጽ በመሻሻላቸው ምክንያት ጉባኤዎቻቸው ቀንሰዋል፤ ችሎታቸውም እንደ ተራ ይቈጠራል! በተለይም ጌታ ለቅዱሱ ሹመት ክብር የሚሆኑ፣ ራሳቸውንም ክደው በነጻ፣ በቅንዓትና ሳይታክቱ ለነፍሳት መልካም ራሳቸውን የሚሰጡ ብዙ ሰዎችን በማስነሣት ለዚህች ድሃ የዎርስተር አውራጃ እንዴት ያለ ምሕረት አደረገላት! እጅግ ብዙ ብቁ፣ ታማኝ፣ ትሑት፣ በአንድ ልብ የሚስማሙና ሰላማውያን ሰዎችን የወንድማማች ኅብረት የማገኝበት እንዲህ ባለ ጉርብትና ያኖረኝን ጌታ እባርካለሁ። ኦ፣ ጌታ ይህን ድንቅ ምሕረት ለዚህች የማይገባት አውራጃ ለረጅም ጊዜ ቢያጸናላት! በሌሎችም ስፍራዎች ለማየት ለበቃሁት አጠቃላይ ለውጥ፣ በሕይወት እስካለሁ ድረስ በእግዚአብሔር ደስ እንደምሰኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ይኸውም ጠላት ቢያጕረመርምና ጥርሱን ቢያፋጭም፣ እጅግ ብዙ መቶ ታማኝ ሰዎች ነፍሳትን ለማዳን በትጋት እየሠሩ መሆናቸው፣ ሌሎችም በፍጥነት እየተነሡ መሆናቸው ነው። ችሎታቸውን የማከብራቸው አንዳንድ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጉዳይ ከእነዚህ የተለየ አሳብ ስላላቸው፣ ይህን የደስታ ለውጥ መጥቀሴ ብቻ እንደሚያስቀይማቸው አውቃለሁ፤ ነገር ግን ልቤን የማውቅ ከሆነ፣ እኔ ፈጽሞ የኤጲስ ቆጶሳት አስተዳደር ደጋፊ ብሆን እንኳ፣ ይህ ሁሉ ቢሆንም ደስ ከመሰኘት በቀር ሌላ ልመርጥ እንደማልችል መመስከር ይገባኛል። ምን! ሰዎቹ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በአንድ አሳብ ስለ ተለያዩ በቤተ ክርስቲያን መበልጸግ ደስ አለመሰኘት? የጌታን ምሕረት እንዳላይ ዓይኖቼን ልጨፍን ይገባኛልን? የሰዎች ነፍሳት በእኔ ዘንድ ይህን ያህል የተናቁ አይደሉም፤ የሕይወት እንጀራ የኤጲስ ቆጶሳትን ይሁንታ ባላገኘ እጅ ስለ ተቈረሰላቸው እንጀራውን የምቀናባቸው አይደለሁም። ኦ፣ እያንዳንዱ ጉባኤ እንዲህ ቢሟላለት! ነገር ግን ሁሉ ነገር በአንድ ጊዜ ሊሠራ አይችልም። የተበላሹ አገልጋዮችን ለማደላደል ረጅም ጊዜ ነበራቸው፤ አላዋቂዎቹና አሰናካዮቹ ሲወገዱም፣ ቦታቸውን ለመሙላት በሌሎች ላይ ችሎታ ልንፈጥር አንችልም፤ ተዘጋጅተውና አድገው እስኪደርሱ ድረስ መጠበቅ አለብን፤ ከዚያም እንግሊዝ ወንጌልን አላግባብ በመጠቀም፣ ማለትም ሆን ብላ ባለመታረሟና ብርሃንን በመጥላቷ ካላባረረችው፣ ከሰማይ በታች ካሉት አሕዛብ ሁሉ እጅግ ደስተኛዋ ሕዝብ ልትሆን ትችላለች። ሾልከው እየገቡ በየዕለቱ ስለሚያውኩን ኑፋቄዎችና ክህደቶች ሁሉ ግን፣ ብቁና ራሳቸውን በሚክዱ አገልጋዮች የሚካሄድ ወንጌል ሁሉንም በውጤታማነት እንደሚበትናቸውና እንደሚያሳፍራቸው አልጠራጠርም።

ነገር ግን፦ ይህ ኃጢአትን መናዘዝ ሳይሆን፣ ኃጢአታቸውን እናዘዛለሁ የምትለውን ሰዎች ማሞገስ ነው፤ ትሉ ይሆናል። ለዚህም እመልሳለሁ፦ ይህ የእግዚአብሔርን ቸርነት በሚገባ መቀበልና ስለ ድንቅ ምሕረቱ ማመስገን ነው፤ ይኸውም በኑዛዜዬ የማላመሰግን እንዳልመስል፣ ይልቁንም በብዙዎች ዘንድ ከእግዚአብሔር ጸጋዎች ጋር አብረው የሚገኙትን ድካሞች ስገልጥ ጸጋዎቹን የምጋርድ ወይም የማቃልል እንዳልመስል ነው፤ ከሚከተሉት ዝርዝሮች እንደሚታየው፣ በምርጦቹ ዘንድ እንኳ ብዙ ነገሮች እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ከሥርዓት ውጭ ናቸውና።

1. ከኃጢአቶቻችን እጅግ ከባዱና ግልጹ አንዱ ትዕቢት ነው። ይህ ኃጢአት በእኛ በምርጦቹ ዘንድ እንኳ እጅግ ብዙ ስፍራ ያለው ነው፤ ነገር ግን በእኛ ዘንድ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ይበልጥ የሚያስጠላና ይቅርታ የማይገባው ነው። ሆኖም በአንዳንዶቻችን ዘንድ እጅግ ከመንሰራፋቱ የተነሣ ንግግራችንን ያረቅቃል፣ ባልንጀሮቻችንን ይመርጣል፣ የፊታችንን ገጽታ ይቀርጻል፣ በቃላችንም ላይ ቅላጼንና ትኵረትን ያኖራል። የአንዳንድ ሰዎችን አእምሮ ከፍ ከፍ የማለት ምኞትንና ዕቅድን ይሞላል፤ በብርሃናቸው ፊት በሚቆሙት ወይም በማናቸውም መንገድ ክብራቸውን በሚጋርዱ ወይም የዝናቸውን መስፋፋት በሚያደናቅፉ ሰዎች ላይ የቅናትና የምሬት አሳብ ያሳድርባቸዋል። ኦ፣ ይህ የትዕቢት ኃጢአት እንዴት ያለ የማይለይ ባልንጀራ፣ እንዴት ያለ ጨካኝ አዛዥ፣ እንዴት ያለ ተንኰለኛና ሾልኮ የሚገባ ስውር ጠላት ነው! ከሰዎች ጋር ወደ ጨርቅ ሻጩ፣ ወደ ሐር ነጋዴው፣ ወደ ልብስ ሰፊው ይሄዳል፤ ጨርቃቸውን፣ ጌጣቸውንና የልብሳቸውን ቅድ ይመርጥላቸዋል። ይህ ጨቋኝ ክፉ ልማድ ባያዝዝ ኖሮ በጠጕርና በአለባበስ የዘመኑን ቅድ ተከትለው የሚንቀባረሩ አገልጋዮች ጥቂቶች በሆኑ ነበር። ይህ ብቻ ወይም ይህ የከፋው ቢሆን ምነው! ነገር ግን ወዮ! ምን ያህል ጊዜ ከእኛ ጋር ወደ ጥናት ክፍላችን ይሄዳል፤ በዚያም ከእኛ ጋር ተቀምጦ ሥራችንን ይሠራል! ምን ያህል ጊዜ ርእሳችንን፣ ከዚያም በበለጠ ቃላችንንና ጌጦቻችንን ይመርጣል! እግዚአብሔር አላዋቂዎችን እናስተምር ዘንድ በተቻለን መጠን ግልጽ እንድንሆን፣ የደነደነውንም ልባቸውን እናቀልጥና እንለውጥ ዘንድ በተቻለን መጠን አሳማኞችና ቍም ነገረኞች እንድንሆን ያዝዘናል። ትዕቢት ግን አጠገባችን ቆሞ ሁሉን ይቃወማል፤ መጫወቻዎቹንና ከንቱ ነገሮቹን ያቀርባል። ከማሳመር ይልቅ ያረክሳል፤ በሚመሰገን ጌጥ ስም ስብከታችንን በልጅነት ጌጣጌጦች ያዋርዳል፤ ልክ አንድ ልዑል የቲያትር ተዋናይ ወይም ፊቱን የተቀባ ቀልደኛ ልብስ እንዲለብስ እንደሚደረግ ያህል። ብርሃኑን ያደበዝዝ ዘንድ መስኮቱን ቀለም እንድንቀባ ያግባባናል፤ ያለ ጥቅም መናገር እንደምንችል እንዲያውቁ፣ ሕዝባችን ሊያስተውሉት የማይችሉትን እንድንናገራቸው ያደርገናል። ግልጽና የሚወጋ ንግግር ቢኖረን፣ ሸካራነቱን፣ አለመስተካከሉንና ትርፍነቱን እሞርዳለሁ በሚል ሰበብ ስለቱን ያስወግዳል፤ የስብከታችንንም ሕይወት ያደነዝዛል። እግዚአብሔር ሰዎችን ለሕይወታቸው እንደምንታገል አድርገን እንድንይዛቸውና በተቻለን ትጋት ሁሉ እንድንለምናቸው ሲያዝዘን፣ ይህ የተረገመ ኃጢአት ሁሉን ይቈጣጠራል፤ እጅግ ቅዱሳን የሆኑትን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ይኰንናል፤ እንዲህም ይለናል፦ «ምን! ሕዝቡ እብዶች እንደ ሆናችሁ እንዲያስቡ ታደርጋላችሁን? እንደምትቈጡ ወይም እንደምትቃዡ እንዲናገሩ ታደርጋላችሁን? በእርጋታና በልክ መናገር አትችሉምን?» በዚህ መንገድ ትዕቢት የብዙ ሰዎችን ስብከት ያዘጋጃል፤ ትዕቢት የሚያዘጋጀውን ደግሞ ዲያብሎስ ያዘጋጀዋል፤ ዲያብሎስ ምን ዓይነት ስብከት እንደሚያዘጋጅና ለምን ዓላማ እንደ ሆነ በቀላሉ መገመት እንችላለን። ጉዳዩ ከእግዚአብሔር ቢሆንም፣ አለባበሱ፣ አቀራረቡና ዓላማው ግን ከሰይጣን ከሆነ፣ ስኬትን ለመጠበቅ ብዙ ምክንያት የለንም።

ትዕቢት ስብከቱን ካዘጋጀ በኋላ ከእኛ ጋር ወደ መድረክ ይወጣል፤ የድምፃችንን ቃና ይቀርጻል፤ ስናቀርብ ያነቃቃናል፤ ምንም ያህል አስፈላጊ ቢሆን ደስ የማያሰኘውን ነገር እንድንተው ያደርገናል፤ ከንቱ ሙገሳንም እንድናሳድድ ያደርገናል። ባጭሩ የሁሉ ድምር ይህ ነው፦ ሰዎች የእግዚአብሔርን ክብር መሻትና ራሳቸውን መካድ ሲገባቸው፣ በጥናትም በስብከትም ራሳቸውን እንዲሹና እግዚአብሔርን እንዲክዱ ያደርጋቸዋል። «እግዚአብሔርን እጅግ ደስ ለማሰኘትና እጅግ የሚበዛ መልካም ነገር ለማድረግ ምን ልናገር? እንዴትስ ልናገረው?» ብለው መጠየቅ ሲገባቸው፣ «የተማርሁና ብቁ ሰባኪ ሆኜ እንድቈጠር፣ የሚሰሙኝም ሁሉ እንዲያሞግሱኝ ምን ልናገር? እንዴትስ ላቅርበው?» ብለው እንዲጠይቁ ያደርጋቸዋል። ስብከቱ ሲያልቅ ትዕቢት ከእነርሱ ጋር ወደ ቤት ይሄዳል፤ ለነፍሳት መዳን ተሳክቶላቸው እንደ ሆነ ከማወቅ ይልቅ ተመስግነው እንደ ሆነ ለማወቅ እንዲጓጉ ያደርጋቸዋል። ኀፍረት ባይኖር ኖሮ፣ ሰዎችን እንዴት እንደ ወደዷቸው ለመጠየቅና ሙገሳቸውን ለማውጣት ልባቸው በፈቀደ ነበር። እጅግ ከፍ ተደርገው እንደ ታሰቡ ቢገነዘቡ፣ ግባቸውን እንዳገኙ ሰዎች ደስ ይላቸዋል፤ ደካሞች ወይም ተራ ሰዎች ብቻ ተደርገው እንደ ተቈጠሩ ቢያዩ ግን፣ ያሰቡትን ሽልማት እንዳጡ ሰዎች ይከፋቸዋል።

ነገር ግን ይህም ቢሆን ሁሉ ወይም የከፋው አይደለም፤ ከዚህ የከፋ ሊኖር የሚችል ከሆነ። ኦ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ አገልጋዮች በሕዝብ ዘንድ ለመወደድና በሰዎች ግምት ከሁሉ በላይ ለመቀመጥ እጅግ ስለሚጓጉ ከእነርሱ ይልቅ የተመረጡትን የወንድሞቻቸውን ችሎታና ስም ይቀናሉ ተብሎ ስለ እነርሱ መነገሩ ምንኛ ያሳዝናል! ለሌላው የሚሰጠው ሁሉ ከእነርሱ ምስጋና የተወሰደ ይመስል፣ እግዚአብሔርም ስጦታዎቹን የሰጣቸው በዓለም ላይ እንደ ዝነኛ ሰዎች እንዲመላለሱ የራሳቸው ጌጥና ማስጌጫ ብቻ እንዲሆኑ ይመስል፣ ለሌሎች የሰጣቸውም ስጦታዎች ሁሉ በክብራቸው መንገድ ላይ የቆሙ ቢመስሉ ሊረገጡና ሊናቁ የሚገባቸው ይመስል! እንዴት ያለ ነገር ነው! ቅዱስ ሰው፣ የክርስቶስ ሰባኪ ሆኖ ሳለ የክርስቶስ መልክ ያለበትን ይቀናል፤ ክርስቶስ ክብሩን ሊያገኝባቸው የሚገቡትን ስጦታዎቹንም ይጠላል፤ ይህም ሁሉ ክብራችንን የሚያደናቅፉ ስለሚመስሉ ነው። እውነተኛ ክርስቲያን ሁሉ የክርስቶስ አካል ብልት አይደለምን? ስለዚህም ከአካሉ ሁሉና ከእያንዳንዱ ብልቱ በረከት ተካፋይ አይደለምን? ሰውስ ሁሉ ስለ ወንድሞቹ ስጦታዎች እግዚአብሔርን ማመስገን አይገባውምን? ይህም እግር ከዓይን አመራር እንደሚጠቀም እርሱም በእነርሱ ድርሻ ስላለው ብቻ ሳይሆን፣ የራሱ ዓላማ በራሱ ስጦታዎች እንደሚፈጸም ሁሉ በወንድሞቹ ስጦታዎችም ሊፈጸም ስለሚችል ጭምር ነው። የእግዚአብሔር ክብርና የቤተ ክርስቲያን ደስታ ዓላማው ካልሆነ ክርስቲያን አይደለምና። የጌታውን ሥራ እንዲሠራ ስለ ረዳው ብቻ ሠራተኛ ሌላውን ሠራተኛ ይጠላልን? ሆኖም ወዮ! ይህ ከባድ ወንጀል በክርስቶስ አገልጋዮች መካከል ምንኛ የተለመደ ነው! በገዛ ዝናቸው መንገድ ላይ የቆሙትን ሰዎች ስም በስውር ሊያጠፉ ይችላሉ፤ ውሸታሞችና ስም አጥፊዎች ሆነው እንዳይገኙ በኀፍረት ምክንያት በግልጽና በይፋ ቃል ሊያደርጉት የማይችሉትን፣ በጥቅሉና በክፋት ፍንጭ ያደርጉታል፤ ክስ ማጣበቅ በማይችሉበትም ጥርጣሬ ያስነሣሉ። አንዳንዶችም እስከዚህ ድረስ ይሄዳሉ፦ ከእነርሱ የበለጠ ብቃት ያለው ማንም ሰው ከእነርሱ ይልቅ እንዳይመሰገን ብለው ወደ መድረካቸው እንዲወጣ አይፈቅዱም። እግዚአብሔርን መፍራት በጥቂቱ እንኳ ያለው ሰው የእግዚአብሔርን ስጦታዎች እንዲህ መቅናቱ፣ ከእርሱ ይልቅ ሊመረጥ በሚችል በሌላ ሰው ሥራው ከሚፈጸም ይልቅ ሥጋውያን አድማጮቹ ሳይለወጡ፣ እንቅልፋሞቹም ሳይነቁ ቢቀሩ መምረጡ አስፈሪ ነገር ነው። አዎን፣ ይህ የተረገመ ክፉ ልማድ እስከዚህ ድረስ ይሠለጥናል፤ የብዙ ሰባኪዎች እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ታላላቅ ጉባኤዎች ውስጥ፣ በብዙ ስፍራዎች በፍቅርና በጸጥታ አብረው የሚኖሩና የእግዚአብሔርን ሥራ በአንድ ልብ የሚያካሂዱ ሁለት እኩል ሰዎችን ማግኘት እንኳ አንችልም ማለት ይቻላል። ነገር ግን ከሁለቱ አንዱ በችሎታ ከሌላው እጅግ ያነሰ ሆኖ እንዲህ መቈጠሩን ካልተቀበለ፣ ወይም የሌላው ረዳት ካህን ሆኖ በእርሱ ካልተገዛ፣ ስለ ቅድሚያ ይጣላሉ፤ አንዱ በሌላው ተቀባይነት ይቀናል፤ እርስ በርሳቸውም በመራራቅና በቅናት ይመላለሳሉ፤ ይህም ለሙያቸው ኀፍረት፣ ለሕዝባቸውም ታላቅ በደል ነው። በሕዝብ ጉዳይ ላይ ተጽዕኖና ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች በትልልቅ ጉባኤዎች ውስጥ ከአንድ በላይ መጋቢ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማሳመን ስደክም፣ «ፈጽሞ አይስማሙም» ብለው እንደሚነግሩኝ ሳስበው አፍራለሁ። ተቃውሞው ለአብዛኞቹ መሠረት የሌለው እንደ ሆነ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን ለአንዳንዶቹ እንኳ እውነት መሆኑ የሚያሳዝን ነገር ነው። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች በትዕቢት እጅግ ከመራቃቸው የተነሣ፣ የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያግዝ እኩል ረዳት ማግኘት በሚችሉበት ጊዜ፣ ማንም በክብሩ እንዲካፈላቸው ወይም በሕዝቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እንዲቀንስ ከመፍቀድ ይልቅ፣ ከአቅማቸው በላይ ቢሆንም ሸክሙን ሁሉ በራሳቸው ላይ መውሰድን ይመርጣሉ።

ሰዎች የራሳቸውን አሳብ እጅግ ከፍ የሚያደርጉት፣ ከእነርሱ መለየትና ከእግዚአብሔር መለየት አንድ እንደ ሆነ ያህል በጥቃቅን ነገሮች ከእነርሱ የሚለዩትን ሁሉ የሚነቅፉትም ከዚሁ የተነሣ ነው። የቤተ ክርስቲያን እምነት ገዦች እንደ ሆኑ ያህል ሁሉ በፍርዳቸው እንዲስማማ ይጠብቃሉ፤ እኛም የጳጳሱን አለመሳሳት እየተቃወምን ሳለ፣ ከእኛ ብዙዎቻችን ራሳችን ጳጳሳት ለመሆን፣ የማንሳሳት እንደ ሆንን ሁሉ በውሳኔያችን እንዲጸና እንፈልጋለን። እርግጥ ነው፣ ይህን በግልጽ ከመናገር የሚከለክለን ጨዋነት አለን፤ ሰዎች እንዲቀበሉት የምንጠብቀው በምክንያታችን የሚታየውን የእውነት ማስረጃ ብቻ እንደ ሆነ፣ ቅንዓታችንም ለእውነት እንጂ ለራሳችን እንዳልሆነ እናስመስላለን፤ ነገር ግን የእኛ የሆነው ሁሉ እውነት ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ሁሉ፣ ምክንያታችንም ትክክል ተደርጎ መወሰድ አለበት፤ በነጻነት ቢመረመርና አሳሳች ሆኖ ቢገኝ፣ የእኛ ስለ ሆነ እኛ ራሳችን ይህን ለማየት እጅግ የምንዘገይ እንደ ሆንን ሁሉ፣ ለሌሎች መገለጡም ያስቈጣናል። ስሕተቶቻችንን እንዲህ ተሟጋች ሆነን እንይዛለን፤ በእነርሱ ላይ የተነገረው ሁሉ በእኛ ማንነት ላይ የተነገረ ይመስል፣ እውነትንና የሰዎችን ነፍሳት የበደልንባቸው ክርክሮቻችን ፈጽመው በመረታታቸውም ከባድ በደል የደረሰብን ይመስለናል። በትዕቢታችን ምክንያት ነገሩ እዚህ ደርሷል፦ አንድ ስሕተት ወይም አሳሳች ክርክር በአንድ የተከበረ ስም ጥላ ሥር ቢወድቅ (ይህም ብርቅ አይደለም)፣ ወይ ድሉን ልንለቅለትና እውነትን አሳልፈን ልንሰጥ፣ አለዚያም ያንን ስሕተት የሚደግፈውን ስም የምንበድል ልንሆን ግድ ይሆንብናል፤ በማንነታቸው ላይ ምንም ባትነኩ እንኳ፣ በክርክሮቻቸው ላይ በምትመቱት ምት ሁሉ ሥር ራሳቸውን ያኖራሉና፤ ስለ እነርሱ ራሳቸው የተናገራችሁ ያህል አጥብቆ ይሰማቸዋል፤ ደካማ ክርክር የደካማ ሰው ምልክት ነው ተብሎ በሌሎች ዓይን የሚቈጠር ይመስላቸዋልና። ስለዚህ እርቃናቸውን በመግለጥ ስሕተቶቻቸውንና የሐሰት አመክንዮአቸውን ማሳፈር ግዴታችሁ እንደ ሆነ ብታስቡ፣ ማንነታቸውን እንዳሳፈራችሁ አድርገው ይወስዱታል፤ እንዲህም ስማቸው ለስሕተቶቻቸው ምሽግና መከላከያ ግንብ ይሆናል፤ የሚከበሩበት ክብርም ንግግራቸውን ሁሉ ከጥቃት ሊጠብቅ ይገባዋል።

በእርግጥም መንፈሳችን እጅግ ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሣ፣ ማንም ሊገሥጸን ወይም ሊቃወመን ግዴታው በሚሆንበት ጊዜ፣ በነገሩም በአቀራረቡም ብዙውን ጊዜ ትዕግሥት እናጣለን። እኛ የምንለውን የሚል፣ አሳባችንን የሚጋራ፣ ዝናችንንም የሚያስፋፋ ሰው፣ በሌላ ረገድ ለአክብሮታችን ብዙም የማይገባ ቢሆን እንኳ እንወደዋለን። የሚቃወመንና ከእኛ የሚለየው፣ ስለ ስሕተቶቻችንም በግልጽ የሚነግረንና ጥፋቶቻችንን የሚያሳውቀን ግን በእኛ ዘንድ ተወዳጅ አይደለም። በተለይም የዓለም ዓይን በላያችን ባለበት በሕዝብ ፊት በምናደርገው ክርክር ማንኛውንም ተቃውሞ ወይም ግልጽ ንግግር ልንታገሥ አንችልም ማለት ይቻላል። የስድብ ንግግር መጠላት እንዳለበት፣ ለእውነት ያለን ታማኝነት እስከሚፈቅደው ድረስ ለአንዳችን የሌላው ስም መጠንቀቅ እንዳለብን አውቃለሁ። ነገር ግን ትዕቢታችን ብዙዎቻችንን የማያደንቁን ሰዎች ሁሉ እንደሚንቁን፣ አዎን፣ የምንናገረውን ሁሉ የማያደንቁና ፍርዳቸውን በእጅግ ግልጽ ስሕተቶቻችን ሥር የማያስገዙ ሁሉ እንደሚንቁን እንድናስብ ያደርገናል። እጅግ ስሱዎች ከመሆናችን የተነሣ ሰው ሲነካን እንጎዳለን ማለት ይቻላል፤ እጅግ ልበ ትዕቢተኞች ከመሆናችንም የተነሣ በምስጋና ቃላት ያልሠለጠነና ከተራው ሰው በላይ በሽንገላ ያልተካነ ሰው፣ ከፍ ያለው መንፈሳችን የሚይዘውና ለክብራችን እንደ በደል የሚቈጥረው አንድ ቃል ወይም አንድ ቸልታ ሳይገኝበት፣ በጥንቃቄ ሊይዘንና በየአጋጣሚው የምንጠብቀውን ሊያሟላ እንዴት እንደሚችል አያውቅም ማለት ይቻላል።

ይህ እጅግ ከባድ ኃጢአት እንዲህ መቃለሉና ከቅዱስ የልብና የሕይወት ሁኔታ ጋር እንደሚስማማ መታሰቡ ብዙ ጊዜ እንደ አስደነቀኝ እመሰክራለሁ፤ ከዚህ እጅግ ያነሱ ኃጢአቶች ግን በሕዝባችን ዘንድ ሲገኙ እኛ ራሳችን የሚያስኰንኑ እንደ ሆኑ እናውጃለንና። በዚህ ረገድ እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰባኪዎችና እግዚአብሔርን በማይፈሩ ኃጢአተኞች መካከል ያለውን ልዩነት ሳይ ደግሞ ይበልጥ ተደነቅሁ። ለሰካራሞች፣ ለዓለማውያን ወይም ላልተለወጡ አላዋቂዎች ስንናገር፣ እስከ መጨረሻው እናዋርዳቸዋለን፤ በተቻለን መጠን በግልጽ እንናገራቸዋለን፤ ኃጢአታቸውን፣ ኀፍረታቸውንና ጕስቍልናቸውን እንነግራቸዋለን፤ ሁሉንም በትዕግሥት እንዲታገሡ ብቻ ሳይሆን በምስጋና እንዲቀበሉም እንጠብቃለን። እኔ የምገናኛቸውም አብዛኞቹ በትዕግሥት ይቀበሉታል፤ ብዙ ከባድ ኃጢአተኞችም አጥብቀው የሚገሥጹትን ሰባኪዎች ከሁሉ ይበልጥ ያመሰግናሉ፤ ኃጢአታቸውን በግልጽ የማይነግራቸውን ሰው መስማት ግድ እንደማይላቸውም ይናገራሉ። ነገር ግን እግዚአብሔርን ለሚፈሩ አገልጋዮች ስለ ስሕተታቸው ወይም ስለ ኃጢአታቸው ብንናገር፣ ካላከበርናቸውና ካልተቀበልናቸው፣ በተቻለንም መጠን በለስላሳ ቃል ካልተናገርን፣ አዎን፣ ከተግሣጻችን ጋር ምስጋናን ካልቀላቀልን፣ የተግሣጹን ወይም የማስተባበያውን ኃይል ሁሉ እስኪያሰጥም ድረስ ሙገሳው ካልበለጠ፣ የማይታገሡት በደል እንደ ደረሰባቸው አድርገው ይቈጥሩታል ማለት ይቻላል። ወንድሞች ሆይ፣ ይህ የሚያሳዝን ኑዛዜ እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ስለዚህ ከመነገራችን ይልቅ ይህ ሁሉ በመካከላችን መኖሩ ይበልጥ ሊያሳዝነን ይገባል። ክፋቱ ሊሰወር ቢችል ኖሮ ባልገለጥሁት ነበር፤ ቢያንስ በሁሉ ፊት እንዲህ በግልጽ ባልገለጥሁት ነበር። ነገር ግን ወዮ! ለዓለም ዓይን ከተገለጠ ብዙ ዘመን ሆኖታል። ክብራችንን ጣዖት በማድረጋችን ራሳችንን አዋርደናል፤ ኀፍረታችንን እናሳትማለን፣ ኀፍረታችንን እንሰብካለን፤ በዚህም ለዓለም ሁሉ እናውጀዋለን። እንዲህ ያለ ታላቅ ኃጢአት እጅግ የሠለጠነባቸውን ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ብላቸው ከመጠን በላይ በቸርነት እንደምናገር አንዳንዶች ያስባሉ። ትዕቢት የሠለጠነበት፣ ያልተጠላበት፣ ያልተለቀሰበትና በአብዛኛው ያልተገደለበት ስፍራ እውነተኛ እግዚአብሔርን መምሰል ሊኖር እንደማይችል በእርግጥ አውቃለሁ፤ እያንዳንዱም ሰው የገዛ ልቡን በጥብቅ እንዲጠራጠርና እንዲመረምር እለምናለሁ። ነገር ግን ከላይ በተጠቀሱት የትዕቢት መገለጫዎች በአንዱ ወይም በአብዛኞቹ ጥፋተኛ የሆኑ ሁሉ ጸጋ የሌላቸው ከሆኑ፣ ጌታ ለዚህች አገር አገልጋዮች ይራራላቸው፣ ፈጥኖም ሌላ መንፈስ ይስጠን፤ እንዲያ ከሆነ ጸጋ ብዙዎቻችን ካሰብነው እጅግ የበለጠ ብርቅ ነገር ነውና። ሆኖም የክርስቶስን አገልጋዮች ሁሉ በዚህ ክስ ውስጥ ለማስገባት እንዳላሰብሁ መናገር ግድ ይለኛል። ለመለኮታዊው ጸጋ ምስጋና ይሁንና፣ በትሕትናና በየዋህነት የታወቁ፣ በዚህም ረገድ ለመንጎቻቸውና ለወንድሞቻቸው ምሳሌ የሆኑ አንዳንዶች በመካከላችን አሉ። ይህ ክብራቸው ነው፤ ክብራቸውም ይሆናል፤ በእግዚአብሔርና በመልካም ሰዎች ሁሉ ዓይን፣ እግዚአብሔርን በማይፈሩትም ዓይን እንኳ፣ በእውነት የተከበሩና የተወደዱ ያደርጋቸዋል። ኦ፣ የቀረነውም እንደ እነርሱ ብቻ ብንሆን! ነገር ግን ወዮ! የሁላችንም ሁኔታ እንዲህ አይደለም።

ጌታ ስለዚህ ኃጢአት ከልብ በሆነ የኀዘን እንባ በእግሩ ሥር ቢጥለን ምንኛ መልካም ነበር! ወንድሞች ሆይ፣ የኃጢአታችንን ክፋት አይተን እንታደስ ዘንድ ይህን ጉዳይ ከራሴ ልብና ከእናንተ ልብ ጋር ጥቂት ልከራከርበት። ትዕቢት የአጋንንት ኃጢአት — የሲኦል በኵር — አይደለምን? የሰይጣን መልክ በብዙው የሚገኝበት እርሱ አይደለምን? እንደ እኛ እርሱንና መንግሥቱን ለመቃወም በተሰለፉ ሰዎች ዘንድስ ሊታገሡት ይገባልን? የወንጌል ዓላማ ራሱ እኛን ማዋረድ ነው፤ የጸጋም ሥራ በትሕትና ይጀመራል፣ በትሕትናም ይቀጥላል። ትሕትና ለክርስቲያን ጌጥ ብቻ አይደለም፤ የአዲሱ ፍጥረት አስፈላጊ ክፍል ነው እንጂ። ክርስቲያን መሆንና ትሑት አለመሆን እርስ በርሱ የሚጣረስ ነገር ነው። ክርስቲያን መሆን የሚሹ ሁሉ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ፣ «ወደ እኔ ኑ»፣ «ከእኔም ተማሩ» ባለው ቃል መሠረት ወደ እርሱ መጥተው ሊማሩ ይገባቸዋል፤ የሚያስተምራቸውም ትምህርት እርሱ «የዋህ በልቤም ትሑት» እንደ ሆነ እነርሱም የዋሆችና ትሑታን እንዲሆኑ ነው። ጌታችንና መምህራችን ለዚህ ዓላማ ስንት ትእዛዛትንና ስንት ድንቅ ምሳሌዎችን ሰጥቶናል! የአገልጋዮቹን እግር ሲያጥብና ሲያብስ እያየነው እኛ አሁንም ትዕቢተኞችና ገዢዎች መስለን እንኖራለንን? እርሱ ከሕዝቡ እጅግ ዝቅተኛ ከሆኑት ጋር ሲውል፣ እኛ ግን ልናስተውላቸው እንደማይገባን ቈጥረን እንሸሻቸዋለንን? ከባለጠጎችና ከከበሩ ሰዎች በቀር ሌላው ለእኛ ባልንጀርነት የማይመጥን ይመስለናልን? ከእኛ መካከል ስንቶቻችን ርዳታችንን አብዝተው በሚሹት በድሆች ጎጆ ከምንገኝ ይልቅ በመኳንንት ቤት አዘውትረን እንገኛለን? ከእኛ ብዙዎቻችን እጅግ ከተቸገሩትና ከለማኞቹ ሰዎች ጋር በየዕለቱ እየተገኘን የሕይወትንና የመዳንን መንገድ ማስተማርን እንደ ውርደት እንቈጥረዋለን፤ የባለጠጎችን ነፍስ ብቻ ለመጠበቅ ኃላፊነት የተቀበልን ይመስል! ወዮ! የምንታበይበት ምን አለን? በሥጋችን ነውን? ከእንስሶች ጋር በሚመሳሰል ነገር የተሠራ አይደለምን? በቅርቡስ እንደ ሬሳ የሚያስጠላና የሚያጸይፍ አይሆንምን? በጸጋዎቻችን ነውን? በእነርሱ ይበልጥ በታበይን ቍጥር የምንታበይበት ነገር ያንሳል። የጸጋ ባሕርይ በብዙው በትሕትና የሚገለጥ ከሆነ በእርሱ መታበይ ታላቅ ሞኝነት ነው። በዕውቀታችንና በትምህርታችን ነውን? ምንም ዕውቀት ቢኖረን ትሑታን የምንሆንበት ምን ያህል ምክንያት እንዳለን ማወቃችን አይቀርም፤ ከሌሎች የበለጠ የምናውቅ ከሆንንም፣ ትሑታን የምንሆንበትን ምክንያት ከሌሎች አብልጠን ማወቅ ይገባናል። እጅግ የተማሩት እንኳ ከማያውቁት ጋር ሲነጻጸር የሚያውቁት ምንኛ ጥቂት ነው! ነገሮች ከአቅማችሁ በላይ እንደ ሆኑ ማወቅ፣ ምን ያህልም አላዋቂዎች እንደ ሆናችሁ ማወቅ ለትዕቢት ታላቅ ምክንያት አይሆንም ብሎ ሰው ያስባል። ደግሞስ አጋንንት ከእናንተ የበለጠ አያውቁምን? አጋንንት በሚበልጡአችሁ ነገርስ ትታበያላችሁን? ሥራችን ራሱ ለሕዝባችን ታላቁን የትሕትና ትምህርት ማስተማር ነው፤ እንግዲያስ እኛ ራሳችን ትዕቢተኞች መሆናችን ምንኛ የማይገባ ነው? ትሕትናን ልናጠና፣ ትሕትናንም ልንሰብክ ይገባናል፤ ታዲያ ትሕትናን ልንይዝና ልንለማመድ አይገባንምን? ትሕትናን የሚሰብክ ትዕቢተኛ ሰባኪ ቢያንስ ራሱን የሚኰንን ሰው ነው። ይህን የሚያህል ርኩስ ኃጢአት በቀላሉ የማንለየው መሆናችን፣ ይልቁንም እጅግ ትዕቢተኞች የሆኑ ብዙዎች በሌሎች ላይ ሲነቅፉት በራሳቸው ግን ልብ የማይሉት መሆኑ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! ዓለም ከእኛ መካከል አንዳንዶቹ ከፍ ከፍ ለማለት የሚመኝ ልብ እንዳላቸው፣ የላይኛውን ስፍራ እንደሚፈልጉ፣ በሄዱበት ሁሉ ገዦችና ሥልጣን ያዦች መሆን እንዳለባቸው፣ አለዚያ ከእነርሱ ጋር መኖርም ሆነ መሥራት እንደማይቻል ያስተውላል። በማናቸውም ምክክር እውነትን ለመፈለግ ሳይሆን፣ ምናልባት እነርሱን ለማስተማር የሚበቁትን ሌሎችን ለማዘዝ ይመጣሉ። በአጭሩ ዓለም እስኪያስተጋባው ድረስ እንዲህ ያለ የእብሪትና የገዥነት መንፈስ አላቸው፤ ይሁን እንጂ በራሳቸው ላይ አያዩትም!

ወንድሞች ሆይ፣ ከራሴ ልብና ከእናንተ ልብ ጋር በቅርብ ልነጋገር እወዳለሁ። የትሕትናን ጸጋ ሳንይዘው ስለ እርሱ መልካም መናገራችን፣ ወይም በትዕቢት ኃጢአት እየተዘፈቅን በእርሱ ላይ መናገራችን ያድነናል እንደ ሆነ እንድታስቡ እለምናችኋለሁ። ከእኛ ብዙዎቻችን በውስጣችን የሚሰማን የትዕቢት መጠን ከቅንነት ጋር አብሮ ሊኖር ይችል እንደ ሆነ አጥብቀን የምንመረምርበት ምክንያት የለንምን? ሰካራሙን ካልታቀበ ሊድን እንደማይችል፣ ሴሰኛውንም ንጹሕ ካልሆነ ሊድን እንደማይችል ስንነግረው፣ እኛ ትዕቢተኞች ከሆንን ትሑታን ካልሆንን ልንድን እንደማንችል ለራሳችን የምንናገርበት እኩል ታላቅ ምክንያት የለንምን? በእርግጥም ትዕቢት ከስካርም ሆነ ከዝሙት የሚበልጥ ኃጢአት ነው፤ ትሕትናም እንደ መጠን ማወቅና እንደ ንጽሕና አስፈላጊ ነው። ወንድሞች ሆይ፣ በእውነት ሰው በስካርና በርኩሰት መንገድ እንደሚቻኰል ሁሉ፣ ወንጌልን በትጋት በመስበክና ለቅዱስ ሕይወት የሚቀና በመምሰል መንገድም እንዲሁ በእርግጥ፣ ደግሞም ይበልጥ በስውር፣ ወደ ሲኦል ሊቻኰል ይችላል። ቅድስና ለእግዚአብሔር ራስን መስጠትና ለእርሱ መኖር ካልሆነ ምንድር ነው? የጥፋት ሁኔታስ ለሥጋዊው ራስ ራስን መስጠትና ለራስ መኖር ካልሆነ ምንድር ነው? ከትዕቢተኛ ሰው ይበልጥ ለራሱ የሚኖር፣ ወይም ለእግዚአብሔር ያነሰ የሚኖር ማን አለ? ትዕቢትስ አንድን ሰባኪ በሥራው ከሌሎች የሚበልጥ በሚመስልበት ጊዜ እንኳ ለራሱ እንዲያጠና፣ ለራሱ እንዲጸልይና እንዲሰብክ፣ ለራሱም እንዲኖር ሊያደርገው አይችልምን? ቅኖች መሆናችንን የሚያረጋግጠው ትክክለኛ መነሻና ዓላማ የሌለው ሥራ አይደለም። ሥራው የእግዚአብሔር ሊሆን ይችላል፤ እኛ ግን ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለራሳችን ልንሠራው እንችላለን። በዚህ ነጥብ ላይ የማያቋርጥ አደጋ እንደሚሰማኝ እመሰክራለሁ፤ ከክርስቶስ ይልቅ ለራሴ እንዳላጠና፣ ለራሴ እንዳልሰብክ፣ ለራሴም እንዳልጽፍ ካልተጠነቀቅሁ ቶሎ እሰናከላለሁ፤ ከዚህም ሁሉ በኋላ ኃጢአቱን መኰነን ሲገባኝ ራሴን አላጸድቅም። ወንድሞች ሆይ፣ በአገልግሎት ሥራ ውስጥ ሰውን እጅግ ከፍ ባሉ የአምልኮ ሥራዎች ውስጥ እንኳ ወደ ራስ ወዳድነት የሚያስቱ ምን ያህል ማጥመጃዎች እንዳሉ እንድታስቡ እለምናችኋለሁ። የአምላካዊ ሰው ዝና እንደ ተማረ ሰው ዝና ታላቅ ወጥመድ ነው። ነገር ግን በእግዚአብሔር መምሰል ፈንታ የእግዚአብሔርን መምሰል ዝና ለሚይዝ ወዮለት! «እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።» ዘመኑ ሁሉ ለትምህርትና ለባዶ ሥርዓቶች በሆነበት ጊዜ የትዕቢተኞች ፈተና በዚያ በኩል ነበር። አሁን ግን በእግዚአብሔር በማይነገር ምሕረት እጅግ ሕያው የሆነ ተግባራዊ ስብከት ተከብሮ፣ እግዚአብሔርን መምሰልም ራሱ ተከብሮ ሳለ፣ የትዕቢተኞች ፈተና ቀናተኛ ሰባኪዎችና አምላካውያን ሰዎች መስሎ መታየት ነው። ሕዝቡ እኛን ለመስማት ሲጋፋ፣ በምንናገረውም ልቡ ሲነካ፣ አሳቡንና ፍቅሩንም ለእኛ ሲያስገዛ ማየት ምንኛ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው! በአገሩ ሁሉ እጅግ ብቁና እጅግ አምላካዊ ሰው ተብሎ መወደስ፣ በምድሪቱም ሁሉ በከፍተኛ መንፈሳዊ ብቃት መታወቅ ምንኛ የሚማርክ ነገር ነው! ወዮ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ጥቂት ጸጋ ከእንደዚህ ያሉ ማባበያዎች ጋር ሲጣመር በዓለም ላይ የክርስቶስን ጉዳይ በማስፋፋት ረገድ ከቀዳሚዎቹ ጋር እንድትሰለፉ ለማድረግ ይበቃል። እንዲያውም ትዕቢት ያለ ልዩ ጸጋ ይህን ሊያደርግ ይችላል።

ስለዚህ ራሳችሁን ተጠራጠሩ፤ በጥናታችሁም ሁሉ መካከል ትሕትናን ማጥናታችሁን አትዘንጉ። «ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።» መልካሞችም ሆኑ ክፉዎች ሰዎች ሁሉ ማለት ይቻላል ትዕቢተኛውን እንደሚጸየፉ፣ ትሑቱንም እንደሚወዱ ዘወትር አስተውላለሁ። በእርግጥም ትዕቢት ራሱን እስከዚህ ድረስ ይቃረናል፤ የራሱን አስቀያሚነት ስለሚያውቅ ብዙ ጊዜ የትሕትናን ተራ ልብስ ይዋሳል። በባሕርያችን ውስጥ እጅግ ሥር የሰደደ፣ ከነፍስም እንደ ማናቸውም ኃጢአት በጭንቅ የሚነቀል ኃጢአት ስለ ሆነ ልንጠረጥረው ይበልጥ ምክንያት አለን።

2. ሙያችንና ቃል ኪዳናችን ለሚጠይቀው ሰዎች እንደሚገባ ራሳችንን በቁም ነገር፣ ያለ ገደብና በትጋት ለጌታ ሥራ አናውልም። ይህን ሥራ በሙሉ ኃይላቸው የሚሠሩ ብዙዎች ስላሉ ጌታን እባርካለሁ። ነገር ግን ወዮ! አምላካውያን መጋቢዎች ብለን የምንቈጥራቸው እንኳ አብዛኞቹ ሥራቸውን ምንኛ ጐደሎና በቸልተኝነት ይፈጽማሉ! በሙሉ ለሥራው እንደ ተሰጡና ያላቸውን ሁሉ ለዚያው ዓላማ እንደ ቀደሱ ሰዎች ሆነው በአገልግሎታቸው የሚመላለሱ ከእኛ መካከል ምንኛ ጥቂቶች ናቸው! ለዚህ ኑዛዜ ያለኝን መሠረት ታዩ ዘንድ፣ የኃጢአተኛ ቸልተኝነታችንን አንዳንድ ምሳሌዎች እጠቅሳለሁ።

(1) ለሥራችን እንደሚገባ ራሳችንን የሰጠን ብንሆን ኖሮ በጥናታችን እንዲህ ቸልተኞች ባልሆንን ነበር። ማስተዋላቸውን በትክክል ለማነጽና ለቀጣዩ ሥራቸው ራሳቸውን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን ድካም የሚደክሙ ሰዎች ጥቂቶች ናቸው። አንዳንዶች በጥናታቸው ደስ አይሰኙም፤ ሊሸከሙት እንደ ተገደዱ እንደማይወደድ ግዴታ ቈጥረው አልፎ አልፎ አንድ ሰዓት ብቻ ይወስዳሉ፤ ከቀንበሩም ሥር በወጡ ጊዜ ደስ ይላቸዋል። ተፈጥሮአዊው የዕውቀት ምኞት፣ ወይም እግዚአብሔርንና መለኮታዊ ነገሮችን የማወቅ መንፈሳዊ ምኞት፣ ወይም የታላቁ አላዋቂነታችንና የድካማችን ግንዛቤ፣ ወይም የአገልግሎት ሥራችን ክብደት ስሜት — ከእነዚህ ሁሉ አንዱስ እንኳ ከጥናታችን ጋር አጥብቆ አያቈራኘንምን? እውነትንም በመፈለግ ይበልጥ እንድንደክም አያደርገንምን? አንድ መጋቢ ሊያስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች ምንኛ ብዙ ናቸው! እነርሱን አለማወቅስ ምንኛ ታላቅ ጕድለት ነው! በሥራችንስ እንዲህ ያለውን ዕውቀት ምንኛ እንናፍቀዋለን! የሚነበቡ እጅግ ብዙ መጻሕፍት፣ ልናውቃቸውም የሚገቡ እጅግ ብዙ ጉዳዮች እያሉ ብዙ መጋቢዎች የሚያጠኑት ስብከታቸውን ለማዘጋጀት ብቻ ነው፤ ከዚያ በላይ እጅግ ጥቂት ነው። እንዲያውም ስብከታችንን በማጥናት ረገድ እንኳ እጅግ ቸልተኞች ነን፤ ጥቂት ራቁት እውነቶችን ብቻ እንሰበስባለን፤ እነርሱንም ወደ ሰዎች ኅሊናና ልብ የምናደርስባቸውን እጅግ ኃይለኛ አገላለጾች አናስብም። ሰዎችን እንዴት እንደምናሳምንና ወደ ውስጣቸው እንደምንገባ፣ እያንዳንዱንም እውነት እንዴት ወደ ልባቸው ጥልቅ እንደምናደርስ ልናጠና ይገባናል እንጂ፣ የግድ ካልሆነ በቀር ይህን ሁሉ በድንገት ለሚመጣልን ችሎታ መተው የለብንም። ወንድሞች ሆይ፣ ሰዎች ብርቱ ጥናት፣ የማይታክት ድካምና ልምድ ሳይኖራቸው የተማሩ ወይም ጥበበኞች እንደማይሆኑ በእርግጥ ልምድ ያስተምራችኋል።

(2) ለሥራችን ከልብ ራሳችንን የሰጠን ብንሆን ኖሮ፣ ከእኛ አብዛኞቻችን ከምንሠራው ይልቅ ሥራው በብርቱ ኃይልና በቁም ነገር ይሠራ ነበር። በሙሉ ኃይላቸው የሚሰብኩ፣ ወይም ስለ ዘላለም ደስታና ስለ ዘላለም ሥቃይ ከልባቸው እንደሚናገሩ ሰዎችን በሚያሳምን ሁኔታ የሚናገሩ መጋቢዎች ምንኛ ጥቂቶች ናቸው! የሞቱና ያንቀላፉ ኃጢአተኞች ጉባኤ በአንድ መጋቢ ፊት ተቀምጦ ሊያነቃቸው ወይም ሊቀሰቅሳቸው የሚችል አንድ ቃል እንኳ ሳይሰሙ ማየት የሰውን ልብ ያሳምማል። ወዮ! እጅግ በመፍዘዝና እጅግ በልዝብታ ስለምንናገር ያንቀላፉ ኃጢአተኞች መስማት አይችሉም። ምቱ እጅግ ቀሎ ስለሚያርፍ ልበ ደንዳና ኃጢአተኞች ሊሰማቸው አይችልም። አብዛኞቹ መጋቢዎች ድምፃቸውን እንኳ አያነሡም፤ በብርቱ ለመናገርም ራሳቸውን አያነቃቁም። ጮክ ብለውና በብርቱ ቢናገሩም፣ ይህን በጉዳዩ ክብደትና ጽኑነት የሚያጅቡት ምንኛ ጥቂቶች ናቸው! ያለዚህ ግን ድምፁ የሚያደርገው መልካም ነገር ጥቂት ነው፤ ጉዳዩ ካልተስማማ ሕዝቡ ተራ ጩኸት አድርጎ ይቈጥረዋል። አንዳንድ መጋቢዎች ምን ያህል ግሩም ትምህርት በእጃቸው እንዳለ፣ ነገር ግን በቅርብና በሕያው አተገባበር ጕድለት በእጃቸው ላይ እንዲሞት እንደሚተዉት፣ ኃጢአተኞችን ለማሳመን ምን ያህል ተስማሚ ጉዳይ እንዳላቸውና ምን ያህል ጥቂት እንደሚጠቀሙበት፣ ወደ ልብ ቢያደርሱት ምን ያህል መልካም ሊያደርጉ እንደሚችሉና ይህን ግን ሊያደርጉት እንደማይችሉ ወይም እንደማይፈልጉ መስማት ሰውን እስከ ልቡ ድረስ ያሳዝነዋል።

ወገኖቼ ሆይ፣ የባልንጀሮቻችን የዘላለም ሕይወት ወይም የዘላለም ሞት የተያዘበትን እንደ እኛ ያለ ታላቅ መልእክት ምንኛ በግልጥ፣ ምንኛ በቅርብ፣ ምንኛ በብርቱ ልናደርሰው ይገባናል! ከምንም ነገር ይልቅ የሚጐድለን ይህ ቁም ነገር ይመስለኛል፤ ሆኖም ለእንዲህ ያለ ጉዳይ ቀላልና ፍዝ ከመሆን የበለጠ የማይስማማ ነገር የለም። ምን! ስለ እግዚአብሔርና ስለ ሰዎች መዳን በቀዝቃዛ መናገር? ሕዝባችን መለወጥ ወይም መኰነን እንዳለበት እያመንን በእንቅልፍ ድምፅ እንናገራለንን? ወንድሞች ሆይ፣ በእግዚአብሔር ስም፣ የኃጢአተኞችን ልብ ለማንቃት ብቁ ትሆኑ ዘንድ ወደ መስበኪያው ከመውጣታችሁ በፊት የራሳችሁን ልብ ለማንቃት ተጣጣሩ። መንቃት ወይም መኰነን እንዳለባቸው፣ ያንቀላፋ ሰባኪም ያንቀላፉ ኃጢአተኞችን በጭንቅ እንደሚያነቃ አስታውሱ። የእግዚአብሔርን ቅዱሳት ነገሮች በቃል ከፍተኛ ምስጋና ብትሰጡአቸውም፣ በቀዝቃዛ ብታደርጉት ግን በጉዳዩ ያላችሁትን በአቀራረባችሁ የምትሽሩ ትመስላላችሁ። ታላላቅ ነገሮችን፣ ይልቁንም እንዲህ ያሉ እጅግ ታላላቅ ነገሮችን ያለ ብዙ ስሜትና ግለት መናገር አንድ ዓይነት ንቀት ነው። ቃላቱ ብቻ ሳይሆኑ አቀራረቡም ሊገልጣቸው ይገባል። «እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ በኃይልህ አድርገው» ተብለን ከታዘዝን፣ ለሰዎች መዳን እንደሚደረግ ስብከት ያለ ሥራ በእርግጥ በሙሉ ኃይላችን ሊደረግ ይገባዋል። ነገር ግን ወዮ፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች በቍጥር ምንኛ ጥቂቶች ናቸው! በመልካም መጋቢዎች መካከል እንኳ ሕዝቡ ሲሰሙት ሲሰብክ ሊሰማቸው የሚችል፣ ብርቱ፣ የሚያሳምንና ኃይለኛ የአነጋገር ስልት ያለውን ሰው የምናገኘው እዚህም እዚያም አንድ አንድ ብቻ ነው።

በአቀራረባችሁ ዘወትር እንድትጮኹ ባልመክራችሁም (ይህ ግለታችሁን የተናቀ ያደርገዋልና)፣ ዘወትር ግን ቁም ነገረኞች መሆናችሁን አረጋግጡ፤ ጉዳዩ በሚጠይቅበት ጊዜም (ቢያንስ በአተገባበሩ ክፍል እንደሚገባው)፣ ድምፃችሁን አንሡ፤ መንፈሳችሁንም አትቈጥቡ። እዚህ ወይም በሲኦል መንቃት እንዳለባቸው ሰዎች አድርጋችሁ ሕዝባችሁን ተናገሩአቸው። በእምነት ዓይንና በርኅራኄ ዙሪያቸውን ተመልከቱአቸው፤ ሁሉም ለዘላለም በምን ዓይነት የደስታ ወይም የሥቃይ ሁኔታ ውስጥ መሆን እንዳለባቸው አስቡ፤ ያን ጊዜ ብርቱዎች እንደሚያደርጋችሁ፣ ልባችሁንም ስለ ሁኔታቸው እንደሚያቀልጠው ይመስለኛል። እንደ መንግሥተ ሰማያት ወይም እንደ ሲኦል ስለ ሆነ ታላቅ ጉዳይ አንዲት ቀዝቃዛ ወይም ግድ የለሽ ቃል እንኳ አትናገሩ። ምንም ብታደርጉ ሕዝቡ ከልባችሁ እንደ ሆናችሁ ይዩ። ወንድሞች ሆይ፣ በእውነት የሚሠሩት ሥራዎች ታላላቅ ናቸው፤ በቀልድም ይፈጸማሉ ብላችሁ ማሰብ የለባችሁም። ከሰዎች ጋር በመቀለድ፣ ወይም የለሰለሰ ተረት በመንገር፣ ወይም ያጌጠ ንግግር በማሰማት ልባቸውን ልትሰብሩ አትችሉም። እንደሚናገረው የማያስብ የሚመስለውን፣ ወይም ልመናው ቢፈጸምም ባይፈጸምም ብዙም ግድ የማይሰጠውን ሰው የእንቅልፍ ልመና ሰምተው ሰዎች እጅግ የሚወዱትን ተድላቸውን አይጥሉም። ሥራው የእግዚአብሔር ነው፤ እርሱም በደካማው መሣሪያ ሊያደርገው ይችላል ብትሉ፣ እኔ እመልሳለሁ፦ እውነት ነው፤ እንዲህ ሊያደርግ ይችላል፤ ሆኖም የተለመደው መንገዱ በመሣሪያዎች መሥራት ነው፤ የሚሰበከውን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የስብከቱንም አቀራረብ ለሥራው መሣሪያ ያደርጋል።

ከአድማጮቻችን አብዛኞቹ ዘንድ የአነባበቡና የድምፁ ቃና ራሱ ትልቅ ነገር ነው። እጅግ መልካሙ ጉዳይ እንኳ ልብን በሚነካ ሁኔታ ካልቀረበ በጭንቅ ያንቀሳቅሳቸዋል። በተለይ ምንም ዓይነት ማስመሰል እንዳይኖር፣ ይልቁንም ከእነርሱ ከአንዱ ጋር በግል እንደምትነጋገሩ ሆናችሁ በቅርበት እንድትናገሩአቸው ተጠንቀቁ። የቅርበት ቃናና አገላለጽ መጓደል በአብዛኛው አቀራረባችን ውስጥ ያለ ትልቅ ስሕተት ነው፤ ልናርመውም በእጅጉ ልንጠነቀቅበት የሚገባ ነው። አንድ ሰው ትምህርቱን እንደሚያነበንብ ወይም ንግግር እንደሚደግም ትምህርት ቤት ልጅ የማንበብ ወይም የንግግር ቃና ሲኖረው፣ በሚናገረው ማናቸውም ነገር የሚነኩ ጥቂቶች ናቸው። እንግዲህ ለጌታ ሥራ ራሳችንን እናንቃ፤ ለሕዝባችንም ስለ ሕይወታቸው እንደምንናገር ሆነን እንናገራቸው፤ «ከእሳት ነጥቃችሁ» እንደ ተባለውም በኃይል እንደምናድን ሆነን እናድናቸው። ሰይጣን በድግምት ከይዞታው አይወጣም፤ የእርሱ ምሽግ የሆኑትን የኃጢአተኞችን ነፍሳት መክበብ፣ ዋና ኃይሉ ያለበትንም ስፍራ ፈልገን ማግኘት፣ የእግዚአብሔርንም መድፍ በእርሱ ላይ ደግነን ክፍተት እስኪከፈት ድረስ አጥብቀን መደብደብ ይገባናል፤ ከዚያም በኋላ በዘዴያቸው መልሰው እንዲጠግኑት አንፍቀድላቸው። ከአእምሮ ካላቸው ፍጥረታት ጋር የምንሠራ ስለ ሆንን፣ እነርሱም አእምሮአቸውን በእውነት ላይ አላግባብ ስለሚጠቀሙበት፣ ስብከቶቻችን ሁሉ የሚያሳምኑ እንዲሆኑ፣ የመጽሐፍ ቅዱስንና የአእምሮን ብርሃን እግዚአብሔርን በማይፈሩት ሰዎች ፊት እጅግ ደምቆ እንዲበራ፣ ሆን ብለው ዓይናቸውን ካልጨፈኑ በቀር እንዲያዩ እስኪያስገድዳቸው ድረስ ማድረግ አለብን። በቃላት ብቻ የተሞላ ስብከት፣ የቱንም ያህል በሥርዓት ቢዘጋጅ፣ የማስረጃ ብርሃንና የቅንዓት ሕይወት ከጐደለው ምስል ወይም በሚገባ የለበሰ ሬሳ ብቻ ነው።

በስብከት ውስጥ የነፍሳት ኅብረት አለ፤ ከእኛ ነፍስም ወደ እነርሱ ነፍስ የሆነ ነገር ይተላለፋል። እኛም እነርሱም ማስተዋልና ፈቃድ ስሜትም እንዳለን፣ የጥረታችን አቅጣጫ ከማስተዋላችን ወደ ማስተዋላቸው የተሟላውን የማስረጃ ብርሃን ማስተላለፍ፣ ከራሳችንም እንደሚተላለፍ ሆኖ ቅዱስ ስሜትን በውስጣቸው በማቀጣጠል ልባቸውን ማሞቅ ሊሆን ይገባዋል። ለአድማጮቻችን የምናቀርባቸው ታላላቅ ነገሮች በቂ ምክንያት ከጐናቸው አላቸው፤ በእግዚአብሔርም ቃል ውስጥ በፊታቸው በግልጥ ተቀምጠዋል። ስለዚህ እንደ ጎርፍ በማስተዋላቸው ላይ እንድንመጣ፣ በምክንያታችንና በክርክራችንም ከንቱ ተቃውሞአቸውን ሁሉ እንድናሳፍር፣ ሁሉንም በፊታችን እንድንጥል፣ እነርሱም ለእውነት ኃይል እንዲገዙ እንዲገደዱ በሁሉ ዓይነት ማስረጃ የታጠቅን ልንሆን ይገባናል።

(3) ለእግዚአብሔር ሥራ ከልብ ራሳችንን የሰጠን ከሆንን፣ በዙሪያችን ላሉት መጋቢ ለሌላቸው ምስኪን ጉባኤዎች ለምን አንራራም? ብቁ መጋቢዎችን እንዲያገኙ ለመርዳትስ ለምን አንተጋም? እስከዚያው ድረስም የራሳችን መንጋ ሥራ ጊዜ በሰጠን ቍጥር አልፎ አልፎ ለርዳታቸው ለምን አንወጣም? አላዋቂነት በበዛባቸው ስፍራዎች፣ በተለይ ሰዎችን ለመለወጥ ዓላማ እጅግ ሕያዋንና ኃይለኞች በሆኑ ሰባኪዎች የሚቀርብ ስብከት፣ የዘወትር አገልግሎት በሌለበት ስፍራ ታላቅ ርዳታ ሊሆን ይችላል።

3. ራሳችንንና ያለንን ሁሉ እንደሚገባን ለእግዚአብሔር አገልግሎት አለመስጠታችንን የሚያሳይ ሌላው የሚያሳዝን ማስረጃ፣ ከክርስቶስ ጥቅምና ሥራ በተቃራኒ ለዓለማዊ ጥቅማችን የምንሰጠው የበላይ ትኩረት ነው። ይህን በሦስት ምሳሌዎች አሳያለሁ፦

(1) የመጋቢዎች እንደ ወቅቱ መገለባበጥ። ማንም ከሚያስተዳድሩት ጋር እንዲጣላ፣ ወይም ከሕጋዊ ትእዛዞቻቸው ማናቸውንም እንዳይታዘዝ አልፈልግም። ነገር ግን አብዛኞቹ መጋቢዎች ለዓለማዊ ጥቅም ሲሉ ዓላማቸውን ሊያሳካላቸው ከሚችለው ወገን ጋር ዘወትር ራሳቸውን ማስማማታቸው ለመጋቢዎች ትንሽ ነቀፋ አይደለም። ዓለማዊ ጥቅምን ከፈለጉ ከዓለማዊው ሥልጣን ጋር ራሳቸውን ያስማማሉ፤ የሕዝብን ውዳሴ ከፈለጉ ይበልጥ ተከብሮ ካለው የቤተ ክርስቲያን ወገን ጋር ራሳቸውን ያስማማሉ። ወዮ! ይህ እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋ በሽታ ነው። በቈስጠንጢኖስ ዘመን ቀናውን እምነት የያዙት ምንኛ በዝተው ነበር! በቈስጠንጢዮስ ዘመን ግን ሁሉም ማለት ይቻላል አርዮሳውያን ሆኑ፤ በኒቅያ ጉባኤ ከተገኙት ሰዎች መካከል እንኳ ያልካዱ ወይም እውነትን አሳልፈው ያልሰጡ ጳጳሳት እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። በእርግጥም ሊቤሪዮስ ብቻ ሳይሆን በብዙ የቀና እምነት ጉባኤዎች ሊቀ መንበር የነበረው ታላቁ ኦስዮስ ራሱ በወደቀ ጊዜ፣ ከደካሞች ሰዎች ምን የተሻለ ይጠበቃል? ዓለማዊ ጥቅም ባይኖር ኖሮ፣ በዓለም ባሉ አገሮች ሁሉ መጋቢዎች ሁሉም ወይም ሁሉም ማለት ይቻላል እጅግ ተከብሮ ያለውና ከዓለማዊ ጥቅማቸው ጋር እጅግ የሚስማማው ሃይማኖት ተከታዮች የሚሆኑት እንዴት ነው? በግሪኮች መካከል ሁሉም የግሪክ እምነት ተከታዮች ናቸው፤ በጳጳሱ ተከታዮች መካከል ሁሉም ማለት ይቻላል የጳጳሱ ተከታዮች ናቸው፤ በኖርዌይ፣ በስዊድንና በዴንማርክ ሁሉም ማለት ይቻላል ሉተራውያን ናቸው፤ በሌሎችም አገሮች እንዲሁ ነው። ሰዎች እውነትን ለመመርመር በሚነሡበት ጊዜ ሥጋዊ ጥቅም ብዙ ባያዘነብላቸው ኖሮ፣ በአንድ አገር ሁሉም ትክክል፣ በሌላ አገር ደግሞ ሁሉም ስሕተት መሆናቸው እንግዳ ነገር ነው። የአእምሮ ልዩነትና ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሌሎች ሁኔታዎች በተለያዩ ነጥቦች ላይ ብዙ የአሳብ ልዩነትን ማስከተላቸው አይቀርም ነበር። ነገር ግን ንጉሡና የባለ ሥልጣናቱ ጅረት በአንድ መንገድ ይሂዱ፣ አብዛኞቹ መጋቢዎችም ምንም ልዩ ምርመራ ሳያደርጉ እስከ ፀጕር ጫፍ ድረስ ሲስማሙአቸው ታያላችሁ። በዚህች ምድር በተለያዩ ጊዜያት ተራዎቹ መጋቢዎች ሃይማኖታቸውን ከንጉሡ ጋር ምንኛ በብዛት ለወጡ! የሰማዕታት ታሪክ መጽሐፋችን እንደሚመሰክረው ሁሉም አይደሉም፤ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ። ያው በቀላሉ የሚመራ ደዌም አሁንም ይከተለናል፤ ስለዚህም ጠላቶቻችን ዝናና ሹመት ሃይማኖታችንና ዋጋችን እንደ ሆኑ እንዲናገሩ ምክንያት ይሆናቸዋል።

(2) ዓለማዊ ነገሮችን እጅግ እናስባለን፤ ጊዜያዊ ጥቅማችንን ከሚጎዱ ወይም ከሚያደናቅፉ ተግባሮችም እንሸሻለን። መጋቢዎች ራሳቸውን በዓለማዊ ሥራ ውስጥ ማስጠማቸው ምንኛ የተለመደ ነው! ወደ ማረሻ ሄደን ለኑሮአችን እንድንደክም፣ ያለ ብዙ ጥናትም እንድንሰብክ የሚነግሩን ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ ወገኖች እንድንሆን የሚፈልጉትን ዓይነት የሆኑ ብዙዎች ናቸው። ይህ በቀላሉ የሚማሩት ትምህርት ነው። ሰዎች የራሳቸው ነፍስና ቤተ ክርስቲያን ጥንቃቄያቸውን ሁሉ እንዲያገኙ ሌላውን ጭንቀት ለማስወገድ አይጨነቁም።

በተለይም ቢፈጸሙ ሀብታችንን ሊቀንሱ የሚችሉ ተግባሮች ምንኛ በተለምዶ ቸል ይባላሉ! ለምሳሌ ሕዝቡ የሚገባንን ክፍያ እንዳይከፍሉን ሊያደናቅፍ ይችላል በማለት በአብያተ ክርስቲያናቸው ውስጥ የቤተ ክርስቲያንን ተግሣጽ ለማቋቋም የማይደፍሩ፣ የማይፈልጉም ብዙዎች የሉምን? በንብረታቸው እንዳያስቀይሙአቸው ብለው ኃጢአተኞችን በተግሣጽ አያስቀይሙም። «ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው» ብለው ማወጅ የሚችሉ፣ ስለ መጐምጀት አደጋም ረጅም ንግግር ማድረግ የሚችሉ አንዳንድ ሰዎች ሊመልሱት የማይችሉት ብርቱ ክርክር ገንዘብ ሆኖ አገኘዋለሁ። ለእነርሱ አሁን ከዚህ በቀር ሌላ አልናገርም፦ ጠንቋዩ ስምዖን የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ሊገዛ መሻቱ እንዲህ ያለ ገዳይ ኃጢአት ከሆነ፣ ስጦታውን፣ ጉዳዩንና የሰዎችን ነፍሳት በገንዘብ መሸጥ ምን ይሆን? ገንዘባችን ከእኛ ጋር እንዳይጠፋስ የምንፈራበት ምን ያህል ምክንያት አለን!

(3) በምጽዋት ሥራዎችና ያለንን ሁሉ ለጌታችን አገልግሎት በማዋል ረገድ ፍሬ ቢስ መሆናችን። ዓለማዊ ጥቅም በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን ጥቅም ላይ እጅግ ባያይል ኖሮ፣ አብዛኞቹ መጋቢዎች በመልካም ሥራ ይበልጥ ፍሬያማ በሆኑ፣ ያላቸውንም ለክብሩ ይበልጥ ባዋሉ ነበር።

የምጽዋት ሥራዎች ጭፍን ጥላቻን በብርቱ እንደሚያስወግዱ፣ ልብንም ለአምላካዊ ቃል እንደሚከፍቱ ልምድ ሙሉ በሙሉ አረጋግጧል። ሰዎች መልካም ለማድረግ የተሰጣችሁ መሆናችሁን ካዩ፣ እናንተ መልካሞች እንደ ሆናችሁ፣ የምታሳምኑአቸውም ነገር መልካም እንደ ሆነ በቀላሉ ያምናሉ። እንደምትወዱአቸውና መልካማቸውን እንደምትሹ ሲያዩ በቀላሉ ይታመኑባችኋል። የዓለምን ነገር እንደማትፈልጉ ሲያዩም አሳባችሁን እምብዛም አይጠረጥሩም፤ የምትፈልጉትንም እንዲፈልጉ በቀላሉ ይሳባሉ። መጋቢዎች መልካም ለማድረግ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ቢያዘጋጁ፣ ችሎታቸውንና ሀብታቸውንም ሁሉ ለዚያ ዓላማ ቢሰጡ ምንኛ ብዙ መልካም ሊያደርጉ ይችሉ ነበር! ለሰዎች ሥጋ መልካም ማድረግ ትንሽ ነገር ነው፣ ይህም ወደ እኛ ብቻ እንጂ ወደ እግዚአብሔር አይስባቸውም አትበሉ፤ የሰዎችን መለወጥ እጅግ የሚያደናቅፈው ጭፍን ጥላቻ ነውና፣ ይህም ያንን ለማስወገድ ይረዳል። ሰዎች ከእኛ ለመማር ፈቃደኞች ቢሆኑ ብቻ ይበልጥ መልካም ልናደርግላቸው እንችል ነበር፤ ይህም ፈቃደኞች ያደርጋቸዋል፤ ከዚያም ቀጣዩ ትጋታችን ሊጠቅማቸው ይችላል። ወንድሞች ሆይ፣ ከእናንተ የሚጠበቀው ተራ እግዚአብሔርን መምሰል እንዳልሆነ ሁሉ ተራ ምጽዋትም እንደ ሆነ አታስቡ፤ እለምናችኋለሁ። እንደ መክሊታችሁ መጠን ከሌሎች እጅግ ልትበልጡ ይገባችኋል። ለድሀ ጥቂት መስጠት ብቻ አይበቃም፤ ይህን ሌሎችም እንደ እናንተ ያደርጉታል። ነገር ግን ለጌታችሁ አገልግሎት በሀብታችሁ የምታደርጉት ልዩ ነገር ምንድር ነው? የሌላችሁን መስጠት እንደማትችሉ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር ሊሰጥ የሚገባው ይመስለኛል። ታላቁ ተቃውሞ፦ «የምናስተዳድራቸው ሚስትና ልጆች አሉን፤ ጥቂት ነገር አሁን አይበቃቸውም፤ ለማኞች አድርገን ልንተዋቸውም አይገባንም» የሚል እንደ ሆነ አውቃለሁ። ለዚህም እንዲህ እመልሳለሁ፦

[ሀ] ከሐዋርያው ከዚህ ቃል ይበልጥ አላግባብ የሚጣመሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጥቂቶች ናቸው፦ «ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።» ይህ ቃል የውርስ ድርሻ ለማከማቸትና ለዘር ልጆች የተትረፈረፈ ሀብት ለማዘጋጀት ሰበብ ይደረጋል፤ ሐዋርያው ግን የሚናገረው ራሳቸው መርዳት እየቻሉ ድሆች ዘመዶቻቸውንና ቤተ ሰቦቻቸውን ከጋራው ገንዘብ እንዲጦሩ በቤተ ክርስቲያን ላይ በሚጥሉት ላይ ብቻ ነው፤ ይኸውም አንድ ሰው እናቱ ወይም ልጁ የሆነች ባልቴት በቤቱ ኖራ፣ ራሱ በቂ ሀብት እያለው የአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን እንዲጦራት እንደሚፈልግ ያለ ነው። ተከታዮቹ ቃላትም ሐዋርያው የሚናገረው ስለ ወደፊት ድርሻ ሳይሆን ስለ አሁኑ ርዳታ መሆኑን ያሳያሉ፤ «ባልቴቶች ያሉት» ሰዎች «ይርዱአቸው፥ ቤተ ክርስቲያንም እውነተኞችን ባልቴቶች እንድትረዳ አይክበዱባት» ብሎ ያዝዛልና።

[ለ] ልጆቻችሁን ሌሎች ሰዎች እንደሚያደርጉት አድርጋችሁ፣ ሌላ ታላቅ ዝግጅት ሳያስፈልጋቸው በሆነ ሐቀኛ ሙያ ወይም ሥራ የራሳቸውን መተዳደሪያ ማግኘት እንዲችሉ ማሳደግ ትችላላችሁ። ልግስናችሁና ጥንቃቄያችሁ ከቤት መጀመር እንዳለበት አውቃለሁ፤ ነገር ግን በዚያ ማብቃት የለበትም። ልጆቻችሁ ለእግዚአብሔር እጅግ የሚጠቅሙ ሆነው እንዲገኙ በተቻላችሁ መጠን ልታስተምሯቸው ግዴታ አለባችሁ፤ ነገር ግን ባለ ጠጎች አድርጋችሁ ልትተዉአቸው፣ ወይም ለእነርሱ የሚበልጥ ስንቅ ለማዘጋጀት ብቻ ብላችሁ ሌሎችን አስፈላጊ የልግስና ሥራዎች ልትተዉ አልታዘዛችሁም። ለቤተ ሰቦቻችን በምናደርገው ዝግጅትና ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በምናደርገው መካከል አንዳች መመጣጠን ሊኖር ይገባል። ራሱንና ያለውን ሁሉ ለእግዚአብሔር የሰጠ፣ በእውነት ለጋስና ራሱን የሚክድ ልብ ተገቢውን መጠን ከሁሉ የተሻለ ይፈርዳል፤ ከወጪ መንገዶችም የትኛው እግዚአብሔርን አብልጦ እንደሚያገለግል አይቶ ያንኑ መንገድ ይይዛል።

[ሐ] ሰዎች በመውደቃቸው ራሳቸውንና የሚናገሩትን እምነት እንዳያቈስሉ፣ ራስን ባለመግዛት ፈተና ሥር ረጅም ጊዜ እንዲቆዩ እንደማልወድ እመሰክራለሁ። ቢሆንም ሰዎች ሳያገቡ እንዲኖሩ፣ በልግስና ሥራ የአገልግሎታቸውን ዓላማ እንዳያራምዱ ከሚያግዱአቸው ከሚስትና ከልጆች ከሚመጡ ፈተናዎችም ነጻ እንዲሆኑ፣ የሥጋን ምኞት ለመግደል ከዚህ የበለጠ ምንም ማድረግ አለመቻላቸው ከባድ ነገር ይመስለኛል። የማያገባ ከሚያገባ የተሻለ የሚያደርግ ከሆነ፣ በእርግጥ አገልጋዮች ከሁሉ የተሻለውን ለማድረግ ሊተጉ ይገባቸዋል። «ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው» ከተባለ ደግሞ፣ ወደዚያ ለመድረስ ልንጣጣር ይገባናል። ይህ ከሮማ ቤተ ክርስቲያን ብልሃቶች ሁሉ እጅግ ከፍ ካሉት አንዱ ነው፤ ጳጳሳት፣ ካህናትና ሌሎች የምንኵስና ማኅበራት እንዳያገቡ ግዴታቸው እንደ ሆነ ያስተምራሉ፤ በዚህም የቤተ ክርስቲያንን ገቢ የሚያሟጥጥ ወይም ጥንቃቄያቸውን የሚወስድ ዘር የላቸውም፤ ይልቁንም የሕዝቡን ጉዳይ የራሳቸው ጥቅም አድርገው በሕይወት ሳሉ ራሳቸውን ለእርሱ ያውላሉ፤ ሲሞቱም ያላቸውን ሁሉ ለእርሱ ይተዋሉ። ስለ ተሻለ ጉዳይ የቆምን እኛ ሊደረግ በሚቻልበት ስፍራ ራስን በመካድ ልንመስላቸው አለመቻላችን የሚያሳዝን ነው።

[መ] ማግባት የግድ የሆነባቸው ግን ራሳቸውንና ልጆቻቸውን ማስተዳደር የሚችሉትን ሊያገቡ፣ ወይም ምድራዊ ገቢያቸው በሚፈቅደው መጠን ሊያስተዳድሩአቸው፣ ከቤተ ክርስቲያንም ገንዘብ የቻሉትን ያህል ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሊያውሉ ይገባቸዋል።

ማንንም ወደ ጽንፍ ልገፋ አልወድም። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ሥጋና ደም መልካም ሰዎችን እንኳ እጅግ ስለሚያዳላቸው ግዴታዎቻቸውን፣ እጅግ ታላቅ ዋጋና ክብደት ያላቸውን ግዴታዎች እንኳ፣ እንደ ጽንፍ ይቈጥሯቸዋል። የዓለም ከንቱ ነገሮች ባያሳውሩን ኖሮ፣ የሕዝብ ጥቅም ወይም ሌላ የሚበልጥ በጎ ነገር ራሳችንንና ቤተ ሰቦቻችንን እንድንክድ በጠራን ጊዜ ባስተዋልነው ነበር። ከተትረፈረፈው ዝግጅታችን ይልቅ እጅግ የሚጠቅሙትን ሥራዎች ሳንሠራ ከምንተው፣ በዓለም ላይ በቍጠባና በድህነት ብንኖር ለምን አይሻልም? እኛ ግን በግዴታ ጉዳዮች ከሥጋና ከደም ጋር እንመካከራለን፤ ምን ምክር እንደሚሰጠንም በቀላሉ ልናውቅ እንችላለን። በቂ ኑሮ ሊኖረን ይገባል ይለናል፤ የብዙ ቀናተኛ ሰዎች በቂ ኑሮ ግን በምሳሌው ውስጥ ካለው ባለ ጠጋ ሰው ደረጃ ብዙም የሚያንስ አይደለም (ሉቃስ 16:19)። ከሁሉ የተሻለውን ካልለበሱና ስለዚያ ባለ ጠጋ «ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር» እንደ ተባለው ካልኖሩ በቂ ኑሮ ያላቸው አይመስላቸውም። የማይጠፋን አክሊል የሚሰብክ ሰው የሚያልፈውን ከንቱ ነገር አብዝቶ ሊፈልግ አይገባውም። ባለ ጠግነትን መናቅ የሚሰብክም ራሱ ሊንቀው፣ በሕይወቱም ሊያሳየው ይገባዋል። ራስን መካድንና ሥጋን መግደልን የሚሰብክም ትምህርቱ እንዲታመን ከፈለገ፣ በሚሰብክላቸው ሰዎች ዓይን ፊት እነዚህን በጎነቶች ሊለማመድ ይገባዋል። ክርስቲያኖች ሁሉ የተቀደሱ ናቸው፤ ስለዚህም ራሳቸውና ያላቸው ሁሉ «ለጌታውም የሚጠቅም» እንዲሆን የተለየ ነው። አገልጋዮች ግን ሁለት ጊዜ የተቀደሱ ናቸው፤ እንደ ክርስቲያኖችም እንደ አገልጋዮችም ለእግዚአብሔር የተሰጡ ናቸው፤ ስለዚህም ባላቸው ሁሉ እርሱን ሊያከብሩ እጥፍ ግዴታ አለባቸው። ወንድሞች ሆይ፣ ስንት ብዙ መልካም ሥራዎች በፊታችን አሉ፤ ከእነርሱም እጃችንን የምናሳርፍባቸው ምንኛ ጥቂቶች ናቸው! ዓለም ካለን በላይ ከእኛ እንደሚጠብቅ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ልበ ቢሶች የሚጠብቁትን ማሟላት ባንችል፣ እግዚአብሔር፣ ሕሊናና ጻድቃን ሰዎች ሁሉ የሚጠብቁትን ለማሟላት የምንችለውን እናድርግ። «በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና።» በተለይ የሚበልጥ ገቢ ያላቸው አገልጋዮች መልካም በማድረግ የሚበልጡ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ለአሁኑ አንድ ምሳሌ ብቻ እሰጣለሁ። በዓመት መቶ ሃምሳ፣ ሁለት መቶ ወይም ሦስት መቶ ፓውንድ ደመወዝ የሚያገኙ፣ አጥቢያዎቻቸውም እጅግ ሰፊ ከመሆናቸው የተነሣ የአገልግሎቱን ሥራ ሩቡን እንኳ ለመሥራት፣ ወይም በዓመት አንድ ጊዜ እንኳ ከሕዝባቸው ግማሹን ለማስተማር በግል ለማነጋገር የማይችሉ አንዳንድ አገልጋዮች አሉ፤ ሆኖም አስፈላጊው ይህ ብቻ እንደ ሆነ በሕዝብ ፊት በመስበክ ይረካሉ፤ የሚረዱአቸውን አንድ ወይም ሁለት ትጉ ሰዎች ከመደጐም ይልቅ ቀሪውን ሁሉ ከሞላ ጎደል ሳይሠሩ ይተዉታል፤ ይህም ብዙዎችን ለዘላለም አደጋ ወይም ኵነኔ ያጋልጣል። ረዳት ቢኖራቸውም እንኳ፣ ለሥራው ብቃቱ ደካማ የሆነ አንድ ወጣት ብቻ ነው እንጂ መንጋውን በታማኝነትና በትጋት የሚጠብቅ፣ እጅግ አስፈላጊ የሆነውንም የግል ትምህርት የሚሰጣቸው አይደለም። ይህ እግዚአብሔርን ለራሳችን መጠቀሚያ ማድረግና በዓለም የተሟላ ኑሮ እንዲኖረን የሰዎችን ነፍሳት መሸጥ ካልሆነ፣ ታዲያ ምንድር ነው? እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በሰዎች ዘንድ ምርጥ ሰባኪዎችና ቅዱሳን አገልጋዮች ተብለው ሲቈጠሩ፣ በክርስቶስ ዘንድ ግን ጨካኝ ነፍስ ገዳዮች ተብለው እንዳይቈጠሩ፣ አሳልፈው ለኵነኔ የሰጧቸው የእነዚያ ነፍሳት ጩኸትም ለዘላለም ዓለም በጆሮአቸው እንዳያስተጋባ ሊፈሩ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ። ከዚያ በኋላ ዞር ብላችሁ ሳትመለከቷቸው፣ የሚያስፈልጋቸውንም የቅርብ ርዳታ እየከለከላችኋቸው፣ ለብዙ ነፍሳት ርዳታ ሊሰጥ የሚገባውን ገቢ ወደ ገዛ ሥጋችሁ እያዞራችሁ፣ አንድ መልካም ስብከት መስበክ ብቻ ይበቃልን? እናንተ ራሳችሁ የሰዎችን ሥጋ ብቻ ሳይሆን ነፍሳቸውንም የምትጨቍኑ ታላላቅ ጨቋኞች ሆናችሁ ሳለ፣ በጨቋኞች ላይ እንዴት አፋችሁን ልትከፍቱ ትችላላችሁ? እናንተ ራሳችሁ እንዲህ ምሕረት የለሾች ሆናችሁ ሳለ ምሕረት በሌለበት ላይ እንዴት ልትሰብኩ ትችላላችሁ? እናንተ ራሳችሁ እንዲህ ታማኝነት የጐደላችሁ ሆናችሁ ሳለ ታማኝ ባልሆኑ አገልጋዮች ላይ እንዴት ልትናገሩ ትችላላችሁ? ኃጢአቱ ስላልተስተዋለ፣ በሰዎችም ዓይን አስጸያፊ ስላልሆነ፣ ወይም የምትከለክሉት ልግስና ሕዝቡ በመከልከላችሁ የማይወቅሳችሁ ዓይነት ስለ ሆነ ትንሽ አይሆንም። ታላቁ ጠላታቸው ሰይጣን ራሱ በጥፋታቸው ሥራ ሁሉ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ፈቃዳቸውን አግኝቶአል። ስለዚህ ፈቃዳቸውን ማግኘታችሁ ኃጢአታችሁን አያቀልለውም፤ ይህን ፈቃድ ለዘላለም ጥቅማቸው ከምታገኙት ይልቅ ለዘላለም ጉዳታቸው ቶሎ ልታገኙት ትችላላችሁና።

አሁንም፣ ክቡራን ሆይ፣ የተነገረውን እንድታስቡበት እለምናችኋለሁ፤ እስቲ ተመልከቱ፤ የወንጌል አገልጋዮች ታላቁና የሚያሳዝነው ኃጢአት ለእግዚአብሔር ፈጽመው አለመሰጠታቸው፣ ራሳቸውንና ያላቸውን ሁሉ የያዙትን የተባረከ ሥራ ለማካሄድ አሳልፈው አለመስጠታቸው አይደለምን? ሥጋን ደስ ማሰኘትና ራስን መፈለግ፣ ከክርስቶስም ጥቅም የተለየ ጥቅም፣ ብዙውን ግዴታችንን እንድንዘነጋ፣ ከሥራውም እጅግ ርካሽ በሆነውና በብዙዎች በሚመሰገነው ክፍል ብቻ እግዚአብሔርን እንድናገለግል፣ ለወጪና ለመከራ ከሚያጋልጠን ደግሞ ወደ ኋላ እንድንል አያደርጉንምን? ይህስ ከእኛ ብዙዎቹ ሰማያውያን መስለው ምድራውያን እንደ ሆኑ፣ የላይኛውን እየሰበኩ የታችኛውን እንደሚያስቡ፣ ሰዎችን ዓለምን እንዲንቁ እየጠሩ ዓለምን ጣዖት እንደሚያደርጉ አያሳይምን? ሳልቪያንም እንደሚለው፦ «ከእግዚአብሔር በላይ ሌላን ነገር ከሚያስቀድም ሰው ይበልጥ መዳንን ቸል የሚል የለም»፤ እግዚአብሔርን የሚንቁ የገዛ መዳናቸውን የሚንቁ ሆነው ይገኛሉ።

4. የመላዋን ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም አሳንሰን በመመልከት እጅግ በደለኞች ነን። ስለ አንድነትና ስለ ሰላም የማይናገርን፣ ወይም ቢያንስ በግልጥ የሚቃወመውን ሰው እምብዛም ባላገኝም፣ እርሱን ለማስፋፋት የሚተጉ ሰዎችን ማግኘት የተለመደ አይደለም፤ ይልቁንም ራሳቸው የመለያየት መሣሪያዎች ባይሆኑ እንኳ፣ ሰዎች እርሱን የሚጠሉና በጥርጣሬ የሚመለከቱት ሆነው እናገኛቸዋለን። ጳጳሳውያን የኩላዊት ቤተ ክርስቲያንን ስም ለረጅም ጊዜ አላግባብ ስለ ተጠቀሙበት፣ እነርሱን በመቃወም ብዙዎች ከሃይማኖት መግለጫዎቻቸው አውጥተውታል፤ ወይም የነገሩን ምንነት ሳያስተውሉ ወይም ሳያስቡበት ስሙን ብቻ ይዘዋል፤ ወይም እንደ አካሉ ብልቶች ባይመላለሱም እንዲህ ያለ አካል መኖሩን ማመን ብቻ በቂ እንደ ሆነ ያስባሉ። ጳጳሳውያን ቤተ ክርስቲያንን ጣዖት ቢያደርጉአት፣ እኛ ስለዚህ ልንክዳት፣ ቸል ልንላት ወይም ልንከፋፍላት ይገባናልን? ሃይማኖትን በወገንተኝነት መንገድ መያዝ፣ ለዓለም አቀፋዊቱ ቤተ ክርስቲያንም ፍቅርና ርኅሩኅ ጥንቃቄ ከማድረግ ይልቅ ያንን ፍቅርና አክብሮት በአንድ ወገን ብቻ መወሰን፣ በመላው የክርስቲያን ዓለም የሚገኝ ታላቅና የተለመደ ኃጢአት ነው። ይህ ማለት በግምታችንና በኅብረታችን ንጹሓን የሆኑትን ክፍሎች ከርኩሳኑ አናስቀድም፣ ወይም በኃጢአታቸው ከማንም ጋር ለመካፈል እንቢ አንበል ማለት አይደለም፤ ነገር ግን እጅግ የደከመውና የታመመው ክፍል እንኳ ልንራራለትና በአቅማችን ሁሉ ልንረዳው ይገባል፤ ኅብረትም በተፈቀደው መጠን ሁሉ ሊጠበቅ፣ ከግድ የሆነ አስፈላጊነት በቀር በየትም ስፍራ ሊሸሽ አይገባውም፤ ልክ በሰፈራችን ቸነፈር ወይም ለምጽ የያዛቸውን ልንወዳቸው፣ የምንችለውን ርዳታ ሁሉ ልናደርግላቸው፣ ከእነርሱ ጋር ያለንን ትክክለኛ ዝምድና ሁሉ ልናውቅና ልናካፍላቸው እንደሚገባን፣ ምንም እንኳ በአንድ ስፍራ ከእነርሱ ጋር ልንቀላቀል ባይገባንም፤ እንዲሁም እንደዚያ በማይተላለፉ በሌሎች በሽታዎች ደግሞ ርዳታ በሚያስፈልጋቸው መጠን ለመርዳት ከእነርሱ ጋር አብልጠን ልንሆን እንችላለን።

የኩላዊት ቤተ ክርስቲያን አባላት ነን ከሚሉት ብዙ ሕዝብ መካከል ኩላዊ መንፈስ ያላቸውን ሰዎች ማግኘት ብርቅ ነው። ሰዎች መላዋን ቤተ ክርስቲያን በሁለንተናዊ አስተሳሰብ አያስቡአትም፣ አያከብሩአትምም፤ ይልቁንም የራሳቸውን ወገን እርሱ ብቻ ሙሉዋ እንደ ሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ሉተራውያን የሚባሉ፣ ካልቪኒስቶች የሚባሉ፣ በእነዚህም መካከል ንዑሳን ክፍፍሎች፣ በእኛም መካከል እንዲሁ ሌሎች ወገኖች ቢኖሩ፣ አብዛኞቻቸው ለወገናቸው መበልጸግ አጥብቀው ይጸልያሉ፤ ነገሩ በተሳካላቸው ጊዜም ደስ ይላቸዋል፣ ያመሰግናሉም፤ ሌላ ወገን መከራ ቢደርስበት ግን ለቤተ ክርስቲያን አንዳችም ጕዳት እንዳልሆነ አድርገው ብዙም ግድ አይሰጣቸውም። ብዙ አሕዛብን ይቅርና በምድር ላይ ብዙ ከተሞችን እንኳ የማይዝ እጅግ ትንሽ ቁራጭ ቢሆንም፣ መላዋ ቤተ ክርስቲያን እነርሱ እንደ ሆኑ፣ ለእነርሱ መልካም በሆነ ጊዜም ለቤተ ክርስቲያን መልካም እንደ ሆነ አድርገው ለመመላለስ ዝግጁዎች ናቸው። ቤተ ክርስቲያንን በሮማ አጥር ውስጥ ስለ ወሰነ ጳጳሱን የክርስቶስ ተቃዋሚ ብለን እንኰንነዋለን፤ ያ ደግሞ ያለ ጥርጥር አስጸያፊ መለያየት ነው፤ ነገር ግን ወዮ! ስንቶች ናቸው እየገሠጹአቸው ከልክ በላይ የሚመስሏቸው! ጳጳሳውያን ሮማዊ የሚለውን ቃል ወደ ሃይማኖት መግለጫቸው አሹልከው በማስገባት፣ ሌሎች ኩላውያን እንደሌሉና ቤተ ክርስቲያንም ከዚያ የሰፋ ወሰን እንደሌላት ኩላዊት ቤተ ክርስቲያንን የሮማ ኩላዊት ቤተ ክርስቲያን እንዳደረጉአት፣ ብዙ ሌሎችም በየወገኖቻቸው እንዲሁ ያደርጋሉ። አንዳንዶች የሉተራውያን ኩላዊት ቤተ ክርስቲያን፣ አንዳንዶች የተሐድሶ ኩላዊት ቤተ ክርስቲያን፣ አንዳንዶች የአናባፕቲስቶች ኩላዊት ቤተ ክርስቲያን ያደርጓታል፤ ሌሎችም እንዲሁ። በመካከላቸው ካልተለያዩ ደግሞ ከሞላ ጎደል ከመላው የክርስቲያን ዓለም ቢሆን እንኳ ከሌሎች በመለየታቸው ብዙም አይጨነቁም። የወገናቸውን ሰላም የቤተ ክርስቲያን ሰላም አድርገው ይቈጥሩታል። ስለዚህ ከዚያ ወዲያ ባያራምዱት አያስደንቅም።

በቤተ ክርስቲያን ቍስል የሚያዝን ወይም የሚደማ፣ ወይም ቍስሏን እንደ ራሱ ቍስል አድርጎ ልቡ የሚነካ፣ ወይም ፈውሷን አጥብቆ አስቦ የሚያውቅ ሰው ማግኘት ምንኛ ብርቅ ነው! የለም፤ ይልቁንም ከሞላ ጎደል እያንዳንዱ ወገን የሌሎቹ ደስታ ወደ እርሱ በመመለሳቸው ላይ እንደ ተመሠረተ ያስባል፤ በሐሳቡ ስላልተስማሙም ይውደቁ! ብለው ይጮኻሉ፤ ያ የቤተ ክርስቲያን መነሣት ማለትም የራሳቸው መነሣት መንገድ እንደ ሆነ አስበው ውድቀታቸውን ሲሰሙ ደስ ይላቸዋል። በተለያዩ ወገኖች መካከል ያለውን የክርክሮቹን እውነተኛ ሁኔታ የሚያስተውሉ፣ ወይም ከእነርሱ ስንቶቹ የቃል ብቻ፣ ስንቶቹም እውነተኛ እንደ ሆኑ በሚገባ ለይተው የሚያውቁ ምንኛ ጥቂቶች ናቸው! ይህን የሚያስተውሉትም ትክክለኛ ግንዛቤና መግባባት እንዲገኝ ብለው ለሌሎች ቢገልጡት፣ ስሕተታቸውን እንደ ማቃለልና በኃጢአታቸው ሥጋዊ በሆነ መንገድ እንደ መተባበር ይቈጠራል። ብዙዎች እስኪያረጁ፣ ወይም የሰዎችን መንፈስና መርሕ በብዙ እስኪለማመዱ፣ የቤተ ክርስቲያንንም እውነተኛ ሁኔታና የልዩ ልዩ ልዩነቶችን ከቀድሞው ይልቅ አብልጠው እስኪያዩ ድረስ ለሰላም አይቀኑም። ከዚያም የሰላም ድርሳኖቻቸውን መጻፍ ይጀምራሉ፤ እንደነዚህ ያሉም ብዙዎች እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛሉ። በምኞቱና በስሜቱ ግለት ውስጥ ያለ ወጣት የሥነ ምግባር ፍልስፍናን ለመስማት የሚገባ አድማጭ እንዳልሆነ እንደ ተፈረደ፣ እንዲሁ ሲበስሉ ለሰላምና ለአንድነት የሚቀኑ ያው ወጣቶች፣ በወጣትነታቸው ግለት ግን ለወገኖቻቸው ሲሉ በእነዚህ ላይ የሚቀኑ ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለዚህም ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት ሰላም ፈጣሪዎች ይህን ያህል ታላቅ ግዴታ በመፈጸም የራሳቸውን ሕሊና ከማሳረፍ፣ ጥቂቶችንም ከማለዘብና ከተጨማሪ በደል ከማዳን፣ ሲሞቱም በእልከኛ፣ በትዕቢተኛና ሰላም በሌለው ዓለም ላይ ምስክርን ትተው ከማለፍ የበለጠ ታላቅ መልካም ነገር እምብዛም አያደርጉም። እንዲያውም አንድ ሰው የማስታረቅ ሥራን ቢሞክር ብቻ፣ ወይ አንዳች ኑፋቄን እንደሚደግፍ ወይ ቅንዓቱ እንደ ቀዘቀዘ ብዙውን ጊዜ በጥርጣሬ ይታያል። ለወገኖችና ለአንዳንድ ልዩ እውነቶች ብቻ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ለሆኑት ታላላቅ መሠረታዊ እውነቶች ቅንዓት የማያስፈልግ ይመስል። ዲያብሎስም በዚህ መንገድ ታላቅ ብልጫ አግኝቷል፤ የራሱን ወኪሎች፣ ምስኪኖቹን ሶሲኒያውያን፣ ለኩላዊና ከሁሉ ለላቀ ኩላዊ አንድነትና ሰላም እጅግ ብዙ ድርሳናት እንዲጽፉ አሠርቷቸዋልና፤ ይህንንም ያደረጉት ለራሳቸው ዓላማ ነበር። በዚህም የሰላም ጠላት፣ ስለ ሰላም ሐሳብ የሚያቀርብ ማንም ቢሆን ለራሱ ስሕተቶች ቸልታ እንዲደረግለት ሰላም የሚያስፈልገው ሰው እንደ ሆነ ወዲያውኑ እንዲጠረጠር አድርጓል። ከእነርሱ የበለጠ የአንድነትና የሰላም ወዳጆች የሌሉ ይመስል ኑፋቄ መታመኑ፣ የቤተ ክርስቲያን ደኅንነት በእጅጉ የተመካበት ያን ያህል ታላቅና አስፈላጊ ግዴታም በእንዲህ ያለ ጥርጣሬ ወይም ውርደት ውስጥ መውደቁ የሚያስፈራ ነገር ነው። ወንድሞች ሆይ፣ ይህን ሁሉ የምናገረው ያለ ግልጽ ምክንያት አይደለም። የሰዎቹን ቅድስናና የክርክራችንን ጉዳይ ትንሽነት ስናስብ፣ ከሰማይ በታች ያሉ አብዛኞቹ አሕዛብ ያወቁትን ያህል የሚያሳዝን መለያየት እኛም በእንግሊዝ በመካከላችን አለ። እንድንጣላ የሚያደርገን አብዛኛው ነገር የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ትክክለኛ ቅርጽና ሥርዓት ብቻ ነው። ፕሬስቢቴሪያን፣ ኤጲስ ቆጶሳዊና ነጻ ጉባኤያዊ በሚገባ እንዳይስማሙ ርቀቱ ያን ያህል ታላቅ ነውን? ከልባቸው ፈቃደኞችና ለሰላም ቀናተኞች ቢሆኑ ኖሮ ይስማሙ ነበር። እንደሚስማሙ አውቃለሁ። ከሁሉም ወገኖች ካሉ አንዳንድ ልከኛ ሰዎች ጋር ተነጋግሬአለሁ፤ ከሚቀበሉት ነገርም ሥራው ቀላል እንደ ሆነ እረዳለሁ። የሰዎች ልብ የቤተ ክርስቲያንን ሁኔታ ቢገነዘብ፣ በእውነትም እርስ በርስ በፍቅር ቢነካ፣ ከልባቸውም ሰላምን ለመፈለግ ራሳቸውን ቢሰጡ፣ አስተማማኝና ደስ የሚያሰኝ ሰላምን መመሥረት ቀላል ሥራ በሆነ ነበር። በእያንዳንዱ ነጥብ መስማማት ባንችል እንኳ፣ ልዩነቶቻችንን በቀላሉ ማጥበብ፣ በዋናው ነገር በመስማማታችንም ኅብረት መያዝ እንችል ነበር፤ ጥቂቶቹንና ትንንሾቹን አለመግባባቶቻችንንም በቤተ ክርስቲያን ላይ አደጋ ወይም ችግር ሳያመጡ የምንይዝበትን ከሁሉ የተጠበቀ መንገድ እንወስን ነበር። ነገር ግን ይህ በብዙ ተደርጓልን? አልተደረገም። ፊታችን ሁሉ እንዲያፍር ይነገር፤ አልተደረገም። እያንዳንዱ ወገን አሁን እንደ ወደደ ራሱን ያሞካሽ፤ ወንጌል በዓለም እስካለ ድረስ ይህ ለእንግሊዝ አገልጋዮች ኀፍረት ሆኖ ይመዘገባል።

ወይኔ፣ ይህን ኃጢአት ምን ያህል የከፉ የሚያባብሱ ነገሮች ያጅቡታል! ከሐዋርያት ዘመን ወዲህ ከእነዚህ የበለጠ እግዚአብሔርን መምሰልን የተናገሩ ሰዎች የነበሩ አይመስለኝም። አብዛኞቹ ለአንድነትና ለተሐድሶ በተቀደሱ መሐላዎችና ቃል ኪዳኖች ታስረዋል፤ ሁሉም የሰላምን ዋጋ ይመሰክራሉ፤ አብዛኞቹም ስለ እርሱ ይሰብካሉ፣ ይናገራሉም፤ ቢሆንም እርሱን መፈለግ የማይገባው ይመስል ዝም ብለው ተቀምጠው ቸል ይሉታል። «ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ»፣ «ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ» የሚሉትን ጥቅሶች ያነባሉ፤ ይሰብኩባቸውማል፤ ነገር ግን እርሱን ከመከተልና የሚቻላቸውን ሁሉ ከማድረግ እጅግ ርቀው፣ ብዙዎች በእርሱ ላይ ያጕረመርማሉ፤ ሊያስፋፉት የሚጥሩትንም ሁሉ ይጠላሉ፣ ይነቅፋሉም፤ ለሰላም ያለ ቅንዓት ሁሉ ለቅድስና ካለን ቅንዓት መቀነስ የመነጨ ይመስል፣ ቅድስናና ሰላምም ዳግመኛ ሊታረቁ በማይችሉበት ሁኔታ የተጣሉ ይመስል። ነገር ግን ስምምነት ለአምልኮት የታመነ ወዳጅ እንደ ሆነ፣ አምልኮትም ዘወትር ወደ ስምምነት እንደሚገፋ በረጅም ልምድ ታውቋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስሕተቶችና ኑፋቄዎች በክርክር ይወለዳሉ፤ ክርክርም በእነርሱ ይወለዳል፣ ይመገባልም። የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንደ አንድ ሆነው — አንድ ልብ፣ አንዲት ነፍስና አንድ አንደበት ኖሯቸው — አብረው መኖር፣ እርስ በርሳቸው በእምነትና በቅድስና መተናነጽ፣ በኃጢአት ላይ እርስ በርሳቸው መገሠጽና መረዳዳት፣ በሚመጣውም ክብር ተስፋ አብረው ደስ መሰኘት በሚገባቸው ስፍራ፣ እኛ በተቃራኒው እርስ በርስ በመጠራጠር ኖረናል፣ ቅዱሱን ፍቅር በመራራ ጥል አስጥመናል፣ እርስ በርሳችን ለማዋረድና ለመናድ፣ በትክክልም ሆነ በስሕተት የራሳችንን ወገን ለማብዛት ተግተናል ብለን በኀዘን አይተናል። ለወንድሞች ባለን ፍቅር የእምነታችን ቅንነት ምልክት አድርገን እንመካ የነበርን እኛ፣ አሁን ያንን ወደ ወገን ፍቅር ብቻ ለውጠነዋል፤ ያንን ወገን የሚቃወሙትም ከፍቅራችን ይልቅ ቍጣችንን፣ ቅናታችንንና ክፋታችንን አብዝተው ይቀበላሉ። ይህ በሁሉ ዘንድ እንዳልሆነ፣ በማንም እውነተኛ አማኝ ዘንድም ገዥ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ቢሆንም በራሳቸውም በሌሎችም ዘንድ ከሁሉ ይበልጥ ቅኖች ተብለው የሚታሰቡትን የብዙዎችን ቅንነት እንድንጠራጠር የሚያደርግ ያህል የተለመደ ነው። በዚህ ነበልባል የተለበለብነው እኛ ብቻ አይደለንም፤ ሕዝባችንንም ወደ እርሱ ጐትተን በውስጡ አሳድገናቸዋል፤ ስለዚህም በአገሪቱ ያሉ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች አብዛኞቹ ወደ ወገኖች ተከፋፍለዋል፤ የቀድሞውን አምልኮታቸውን ብዙውን ወደ ከንቱ አስተያየቶችና ክርክሮች፣ ወደ ቅናትና ጠላትነት ለውጠዋል። አዎን፣ ቀድሞ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ማላገጥ ጸጋ የሌለው ምስኪን የመሆኑ እርግጠኛ ምልክት ይደረግ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የእነርሱን አስተያየት የማይጋሩትን በስውር ከማላገጥና ከማማት የሚቈጠቡ ምንኛ ጥቂቶች ናቸው! ቀናተኛ የሆነ የሊቃነ ጳጳሳት ደጋፊ ፕሬስቢቴሪያኑን በአክብሮት ሊንቅና ሊያማ ይችላል፤ ፕሬስቢቴሪያኑም ነጻ ጉባኤያዊውን፤ ነጻ ጉባኤያዊውም ሁለቱንም። ከሁሉም የከፋው ደግሞ፣ ተራው ያልተማረ ሕዝብ ይህን ሁሉ ማስተዋሉ ነው፤ በእኛ ላይ ማላገጥ ብቻ ሳይሆን በእኛ ምክንያት በሃይማኖት ላይ ልባቸው ይደነድናል፤ ሃይማኖተኞች እንዲሆኑ ልናግባባቸው በሞከርን ጊዜ ብዙ ወገኖችን ያያሉና ከየትኛው ጋር እንደሚተባበሩ አያውቁም፤ ትክክለኛው የትኛው እንደ ሆነ እርግጠኞች ስላልሆኑም ከማናቸውም ከመሆን ከአንዳቸውም አለመሆን እኩል እንደ ሆነ ያስባሉ፤ በዚህም በመለያየታችን ምክንያት ሺዎች ሃይማኖትን ሁሉ ወደ መናቅ ደርሰዋል፤ ብዙ ምስኪን ሥጋውያንም እኛ ምንም ሳንይዝ እነርሱ የቀድሞ ሥርዓታቸውን ስለ ያዙ ከሁለቱ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ማሰብ ጀምረዋል። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ የተማሩና የተከበሩ እንደ ሆኑ፣ እንዲህ ያለ ጐጂ ዓላማም እንደሌላቸው አውቃለሁ። ሰዎችን በድንቍርና ማደንደን ዓላማቸው አይደለም። ነገር ግን የሚፈጸመው ነገር ይህ ነው። ክፉ እያደረጉ መልካም ማሰብ ብርቅ አይደለም። ሕዝቡ እንዲህ ወደ ገዛ ጥፋታቸው ሲሮጡ፣ የሰዎችም ነፍሳት በየወገናቸውና በየጥቅማቸው በሚከራከሩ የሃይማኖት መምህራን ጥል ሲጠፉ እያየ፣ በምድር ላለ ለማንም ሰው በማክበር ዝም ብሎ ተቀምጦ አንደበቱን የሚገታ ማን ነው? ልቤን የሚያውቅ ጌታ ያውቃል (እኔ ራሴ ልቤን የማውቀው ከሆነ)፤ ከእነዚህ ወገኖች የአንዱም እንዳልሆንሁ፣ እንዲሁ ከዚህ አንዲትንም ቃል ለአንዱ ወገን በወገንተኝነት በማድላት ወይም ሌላውን እንደ ወገን በመቃወም አልናገርም፤ ይልቁንም በማንም ሰው ላይ በቍጣ አልናገርም፤ በሕሊናዬ ብደፍርስ ኖሮ፣ ላከብራቸው የሚገባኝን እንዳላሰናክል በመፍራት ይህን ሁሉ ዝም ባልሁት ነበር። ነገር ግን እኔ ከክርስቶስ አገልጋይ በቀር ምንድር ነኝ? ሕይወቴስ እርሱን ከማገልገል በቀር ምን ዋጋ አለው? ለቤተ ክርስቲያን ጥፋትስ የማን ሞገስ ሊክሰኝ ይችላል? ነፍሳት ሲጠፉስ ዝም ሊል የሚችል ማን ነው? እግዚአብሔር ጌታዬ፣ ቃሉም መመሪያዬ፣ ሥራው ጉዳዬ፣ ለነፍሳትም መዳን የሥራው ፍሬ ግቤ እስከ ሆነ ድረስ፣ እኔስ በበኩሌ አልችልም። የጌታውን ጥቅምና በሕይወቱ ያለውን ዋና ግብ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ከሚቃረን ነገር ጋር ሊታረቅ የሚችል ማን ነው? ይህም ቢሆን ስለ ራሴ ኃላፊነት ብቻ ቢሆን ኖሮ ከዚህ አንዳችም ባልተናገርሁ ነበር፤ በዚያ፣ እግዚአብሔር ይመስገን፣ ቍስሉ በብዙ ሌሎች ስፍራዎች ካለው ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ነው። ነገር ግን በአቅራቢያ ስላሉና በሩቅ ስላሉ ሌሎች ጉባኤዎች ያለኝ እውቀት እነዚህን ምልከታዎች ከእኔ አውጥቷቸዋል። በእርግጥ በሕይወት እስካለን ድረስ ስለ ሰላም ልንናገር እንችላለን፤ ነገር ግን ወደ ሐዋርያዊው ቀላልነት በመመለስ ካልሆነ በቀር ፈጽሞ አናገኘውም። የጳጳሳውያን እምነት ሰዎች ሁሉ፣ እንዲያውም የራሳቸው ሰዎች ሁሉ እንኳ፣ ሊስማሙበት የማይችሉት እጅግ ትልቅ ነው፤ ከእሳት፣ ከስቅላት ገመድና ከማሰቃያ መሣሪያ በተወሰዱ ማስረጃዎች ባያስገድዱት ኖሮ። ብዙ የጳጳሳውያን ተቃዋሚዎችም፣ በሚጭኑአቸው ነገሮች ዓይነት ከእነርሱ እጅግ ርቀው ሳሉ፣ በሚፈርሙአቸው የእምነት መግለጫዎች አሰልቺ ርዝመትና በሚጭኑአቸው ነገሮች አዲስነት እነርሱን እጅግ ይመስሏቸዋል። አንድ ጊዜ ወደ ጥንቱ የእምነት ቀላልነት በተመለስን ጊዜ፣ ያን ጊዜ እንጂ ከዚያ በፊት አይደለም፣ ወደ ጥንቱ ፍቅርና ሰላም እንመለሳለን። ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም ከሁሉ እጅግ አስፈላጊ ነገር አድርጌ ለወንድሞቼ ሁሉ የምመክረው ይህ ነው፤ በአስፈላጊ እውነቶች ይተባበሩ፤ ሊታገሡ በሚችሉ ነገሮችም እርስ በርሳቸው ይታገሡ፤ እግዚአብሔር ካደረገው የሚሰፋ የሃይማኖት መግለጫና የሚበዙ የግድ አስፈላጊ ነገሮችን አያድርጉ። ለዚህም ዓላማ የሚከተሉትን ነገሮች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፦

(1) እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች፣ በተለይም መላ አብያተ ክርስቲያናት በሁለቱም ወገን ባሉባቸው አከራካሪ አስተያየቶች ላይ ከመጠን ያለፈ ክብደት አትጣሉ።

(2) በመጨረሻ ወደ ፍልስፍናዊ እርግጠኛ አለመሆን በሚመለሱ ክርክሮች ላይ ከመጠን ያለፈ ክብደት አትጣሉ፤ ስለ ነጻ ፈቃድ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ አሠራር ሁኔታና ስለ መለኮታዊ ውሳኔዎች ያሉ አንዳንድ የማይጠቅሙ ክርክሮች እንደዚህ ያሉ ናቸው።

(3) የቃል ብቻ በሆኑና ቢተነተኑ ከዚያ ያለፈ ሆነው በማይገኙ ክርክሮች ላይ ከመጠን ያለፈ ክብደት አትጣሉ። በዓለም ታላቅ ጩኸት ከሚያሰሙትና ቤተ ክርስቲያንን ከሚቀድዱት ክርክሮች መካከል እንደዚህ ያሉት፣ ካነጋገርኋቸው ብርቱ ተከራካሪዎች ከሞላ ጎደል ማንም የሚያስተውል ከሚመስለው ወይም ሊያምን ከሚችለው እጅግ የሚበዙ ናቸው (ይህን በእርግጠኛ እውቀት ላይ ተመሥርቼ በድፍረት እናገራለሁ)።

(4) መጻሕፍት ለእኛ ከተሰጡ ወዲህ በየትኛውም ዘመን መላዋ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በካደችው ወይም ባላወቀችው በማናቸውም የእምነት ነጥብ ላይ ከመጠን ያለፈ ክብደት አትጣሉ።

(5) ይልቁንም ይበልጥ ንጹሓንና አስተዋዮች ከነበሩት ዘመናት ማናቸውም ፈጽሞ ባላወቋቸው ነጥቦች ላይ ታላቅ ክብደት ልትጥሉ አይገባችሁም።

(6) ከሁሉም ይልቅ ደግሞ ከሐዋርያት ወዲህ አንድም ዘመን ተቀብሎት በማያውቀው፣ ሁሉም በአብዛኛው ተቃራኒውን በያዙበት በማናቸውም ነጥብ ላይ ብዙ ክብደት ልትጥሉ አይገባችሁም።

አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስንና የጥንቶቹን የሃይማኖት መግለጫዎች ፈርሞ ሶሲኒያዊነትን ወይም ሌሎች ኑፋቄዎችን ሊይዝ እንደሚችል ይነገራል። ለዚህም እመልሳለሁ፤ የራሳችሁ አእምሮ የሚፈጥረውን ሌላ መፈተኛም እንዲሁ ሊፈርም ይችላል፤ ለቤተ ክርስቲያን ኅብረት መፈተኛ ከማድረግ ይልቅ መናፍቃንን ለመያዝ ወጥመድ ስታዘጋጁ ግባችሁን ትስታላችሁ፤ መናፍቁ በሕሊናው አዳላጭነት ሰብሮ ያልፋል፤ ልበ ርኅሩኁ ክርስቲያን ግን ምናልባት በወጥመዱ ይያዛል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ጋር አጥብቃችሁ ባትጣበቁ፣ በአዲሱ የሃይማኖት መግለጫችሁ ቤተ ክርስቲያን አዲስ መለያየት ሊደርስባት ይችላል።

እግዚአብሔር የተሰበሩትን አብያተ ክርስቲያናቱን የሚፈውስበት ያ የተባረከ ዘመን እስኪደርስ በሕይወት የሚኖር ሰው፣ እኔ የምማጠንለት ይህ ሁሉ በተግባር ላይ ሲውል ያያል፤ ይህም ልከኝነት አዲስ መከፋፈልን በሚያመጣው ቅንዓት ቦታ ሲተካ፣ የመጽሐፍ ቅዱስም በቂነት ትምህርት ሲጸና፣ የሰዎችም ሁሉ የእምነት መግለጫዎችና ማብራሪያዎች እንደ ረዳት መሣሪያዎች ብቻ ሲከበሩ እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከሚስማሙበት በላይ የቤተ ክርስቲያን ኅብረት መፈተኛ ሆነው ሳይቀርቡ ያያል። ይሁን እንጂ የፈውስ ዘመን እስኪመጣ ድረስ፣ የሚፈውሱ እውነቶች ተቀባይነት ያገኛሉ ብለን ልንጠብቅ አንችልም፤ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዘንድ የፈውስ መንፈስ የለምና። ሥራው የሚሠራበት ጊዜ ሲደርስ ግን ሠራተኞቹ ለእርሱ ይዘጋጃሉ፤ የዚህ ያህል የከበረ ሥራ ፈጻሚዎችም ብፁዓን ይሆናሉ።

5. በመጨረሻም፣ የታወቁትን ተግባራት፣ ለምሳሌ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓተ ተግሣጽ፣ በመፈጸም ረገድ እጅግ ቸልተኞች ነን። የተሐድሶ ሥራ እንዲጀመር ቢታሰብ፣ ተጎትተው ከሚወሰዱበት በላይ ፈቀቅ የማይሉ ስንቶች ናቸው! ሁሉም ያንኑ ያህል እንኳ ቢያደርጉ መልካም በሆነ ነበር። ሥራው አስቸጋሪና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል የሚሆን በመሰለ ጊዜ ደግሞ ለእርሱ እንዴት እንዘገያለን! ላለመሥራቱም ስንት ምክንያቶች እናቀርባለን! ባለፉት ብዙ ዓመታት በእንግሊዝ ውስጥ ከሥርዓተ ተግሣጽ ይበልጥ የተወራለት፣ የተጸለየለትና የተከራከሩበት ምን ነገር አለ? በእርግጥም ለአንዱ ወገን ወይም ለሌላው በመከራከር ቀናተኞች የማይመስሉ ሰዎች ጥቂቶች ናቸው፤ አንዳንዶች ለጳጳሳት አስተዳደር፣ አንዳንዶች ለፕሬስቢቴሪያን አስተዳደር፣ አንዳንዶችም ለጉባኤ አስተዳደር ይከራከራሉ። ነገር ግን ወደ አፈጻጸሙ ስንመጣ፣ እኔ እስከማየው ድረስ፣ ፈጽመን ተስማምተናል፤ አብዛኞቻችን ለየትኛውም መንገድ አይደለንም። አንዳንድ ጊዜ የእንግሊዝን ገጽታ ስመለከት፣ በአገሪቱ ውስጥ ሥርዓተ ተግሣጽን በሚገባ የሚፈጽሙ ጉባኤዎች ምን ያህል ጥቂቶች እንደ ሆኑ ሳይ፣ በዚያውም ልክ ስለ እርሱ ምን ያህል ብዙ መጻሕፍት እንደ ተጻፉ፣ የአገሪቱም አገልጋዮች ከሞላ ጎደል ሁሉ ለእርሱ እንዴት እንደ ቆሙ ሳስብ እደነቃለሁ። ስለ እርሱ እንዴት በቅንዓት ተከራከሩ! በተቃዋሚዎቹም ላይ ብዙ ተገቢ ጩኸት አሰሙ! ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን በአፈጻጸሙ ረገድ ጥቂት ወይም ምንም አያደርጉም። ተግባራቸው ልባቸው እንደሚቃወመው ለሚያሳየው ነገር እንዲህ ቀናተኛ ደጋፊዎች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምን እንደ ሆነ ተደንቄአለሁ። ነገር ግን የክርክር ቅንዓት ከቅዱስ፣ ከታዛዥና በተግባር ከሚገለጥ ቅንዓት ይልቅ ለተፈጥሮአችን እንደሚቀርብ አያለሁ። በእንግሊዝ ውስጥ በአደራ የተሰጣቸውን መንጋ የማያውቁ፣ አባላቱ እነማን እንደ ሆኑ ሊናገሩ የማይችሉ፣ አንድንም እልከኛ ኃጢአተኛ ከቶ ያላወጡ፣ አንድንም በሕዝብ ፊት ወደ መናዘዝና የመታረም ቃል ወደ መግባት ያላመጡ፣ እንዲህ ወዳለው ንስሐ ይጠሩት ዘንድ አንድንም በሕዝብ ፊት እንኳ ያልመከሩ ስንት መጋቢዎች አሉ! እነርሱ ግን የጌታን እራት ቍርባን ካልሰጧቸው ተግባራቸውን የፈጸሙ ይመስላቸዋል (ምናልባትም ሰዎቹ ራሳቸው በፈቃዳቸው የሚርቁት ሊሆን ይችላል)፤ በዚያው ጊዜ ግን የአብያተ ክርስቲያናታችን ቋሚ አባላት አድርገን እንተዋቸዋለን (የቤተ ክርስቲያን አባልነት ከጌታ እራት በመካፈል ብቻ አይገኝምና፤ አለዚያማ በሕፃንነታቸው የተጠመቁ ልጆች ምንድር ናቸው?)፤ ከቤተ ክርስቲያንም ጋር ያለውን ሌላውን ኅብረት ሁሉ እንፈቅድላቸዋለን፤ ስለ ኃጢአታቸውም ወደ ግል ንስሐ አንጠራቸውም። በግል እንዲገሠጹና እንዲመከሩ፣ በሕዝብ ፊትም ወደ ንስሐ እንዲጠሩ፣ ንስሐ ሳይገቡ ቢቀሩም እንዲወገዱ የእግዚአብሔር ሥርዓት አይደለምን? እነዚህ ተግባራት ካልሆኑ ስለ እነርሱ በዓለም ውስጥ ይህን ያህል ጩኸትና ሁከት ያነሣነው ለምንድር ነው? ተግባራት ከሆኑ ደግሞ የማንፈጽማቸው ለምንድር ነው? ብዙዎቹ ቃሉን መስማት እንኳ ይሸሻሉ። የቤተ ክርስቲያን የጥንቱ ሥርዓተ ተግሣጽ ከዚህ የጠበቀ ነበር፤ በትሩሎ የተደረገው ስድስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ «ያለ አስገዳጅ ችግር ሦስት ቀን ተከታትሎ ከቤተ ክርስቲያን የቀረ ሁሉ ይወገዝ» ብሎ ደንግጎ ነበርና።

ወንድሞች ሆይ፣ ማንኛውንም ወገን ማስቀየም አልሻም፤ ነገር ግን እነዚህ ኃጢአቶች በምክንያቶች፣ በማቃለያዎች ወይም በመካድ ሊሸፈኑ እንደማይገባ መናገር ግድ ይለኛል። ለረጅም ጊዜ ሥርዓተ ተግሣጽን ከፍ ከፍ አድርገን አውጀናል፤ እያንዳንዱም ወገን የራሱን መንገድ አውጇል። ሕዝቡ የእናንተን የአስተዳደር ሥርዓት እንዲያከብሩ ትወዳላችሁን ወይስ አትወዱም? እንደምትወዱ ጥርጥር የለውም። እንዲያከብሩት ከፈለጋችሁ ደግሞ በአንዳች ብልጫው ምክንያት መሆን አለበት። እንግዲያስ ያን ብልጫ አሳዩአቸው። ምንድር ነው? በምንስ ይገኛል? እንዲያምኑአችሁም ከፈለጋችሁ በወረቀት ላይ ብቻ ሳይሆን በተግባር፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በሥራ አሳዩአቸው። ሕዝቡ ነገሩ ራሱ ሳይኖር የሥርዓተ ተግሣጽን ዋጋ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ይህን ሁሉ ጩኸት ያሰማችሁለት ስምና ጥላ ብቻ ነውን? ምንም መልካም የማያደርገውን ነገር መልካም ነው ብለው እንዴት ሊያስቡ ይችላሉ? በእውነት ጉዳያችንን ለመደገፍ ትክክለኛውን መንገድ እንዳልያዝን እፈራለሁ፤ ስለ እርሱ የጋለ ክርክር እያደረግን ሳለ አሳልፈን እንሰጠዋለን። እውነቱን ተናገሩ፤ ለረጅም ጊዜ ሲከራከሩለት የኖሩትን ሥርዓተ ተግሣጽ በሰዎች ዘንድ መልካም ስሙን ያቆዩለት እነዚህ ሁለት ነገሮች አይደሉምን? ይኸውም፣ እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዘንድ ለእርሱ የቆሙት መጋቢዎቻቸው መልካም ስም ብቻ፣ ከኃጢአተኞችም ብዙዎቹ ዘንድ ደግሞ አለመፈጸሙ ነው፤ ጥርስ እንደሌለው፣ እንደ ጠበቁትም እንደማያስቸግራቸው አግኝተውታልና። አስተዳደራችን በእርሱ ሊታረሙ ወይም ሊወገዱ በሚገባቸው ሰዎች ድምፅ የሚደገፍበት ደረጃ ላይ ቢደርስ፣ ከሁሉ የከፉትም ሰዎች በኃጢአታቸው ስለሚወዳጃቸው ወዳጆቹ ቢሆኑ፣ ያን ጊዜ ጌታን በእርሱ ላይ እናስነሣዋለን፤ እርሱም በእኛ ላይ እንደ ተነሣ ሆኖ ይገለጣል። ይህን ያህል ከተከራከሩለት ጊዜ ጀምሮ በአንድ አውራጃ ሁሉ የተፈጸመውን የሥርዓተ ተግሣጽ አፈጻጸም ሁሉ በአንድነት ሰብስቡ፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎችን በፍሬው ምክንያት እንዲወድዱት ለመሳብ የሚያስችል ያህል የሚታይ ይሆናል ብዬ እጠራጠራለሁ። በእናንተ ጉባኤዎች ውስጥ ከሥርዓተ ተግሣጽ ባዶ ስም በቀር ምንም ካላሳያችኋቸው፣ ቃልን ሳይሆን ሥራን፣ የተሐድሶን ስም ብቻ ሳይሆን ተሐድሶን የሚሹ ብዙዎች ወደ ተለዩት ጉባኤዎች ቢሻገሩ እንዴት ትደነቃላችሁ? ክርስቲያኖች ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥርዓቶች ያከብራሉ፤ ከንቱ ነገሮችም አድርገው አይቈጥሩአቸውም፤ ስለዚህም ያለ እነርሱ ለመኖር አይፈቅዱም። ሥርዓተ ተግሣጽ ለቤተ ክርስቲያን የማያስፈልግ ነገር አይደለም፤ በከበረውና በተዋረደው መካከል በሥርዓተ ተግሣጽ ልዩነት ባታደርጉ ሕዝቡ በመለየት ያደርገዋል። በአብያተ ክርስቲያናቶቻችሁ ውስጥ በግልጽ የሚታወቁ አላዋቂዎችና ሃይማኖት ፈጽሞ የሌላቸው ብዙ ሃያዎችን ወይም መቶዎችን ብታቆዩ፣ በሕዝብ ፊት (ምናልባትም በግል እንኳ) ባትገሥጹአቸው፣ ወደ ንስሐም ባትጠሩአቸው፣ ባታወጡአቸውም፣ አንዳንድ ፈሪ ነፍሳት በራሳቸው ላይ ሊወድቅ የተቃረበ እንደሚመስላቸው ከፈራረሰ ሕንጻ እንደሚሸሹ ከአብያተ ክርስቲያናቶቻችሁ ቢሸሹ ልትደነቁ አይገባችሁም። እባካችሁ አስቡ፤ በሥርዓተ ተግሣጽ እንደምታደርጉት በቍርባንም ረገድ እንዲሁ ብታደርጉባቸው፣ ኅብስቱንና ወይኑን ብቻ አሳይታችሁ የቤዛቸውን ፍቅር ከሚያስታውሱት ከእነዚህ መታሰቢያዎች ከቶ እንዲቀምሱ ባትፈቅዱላቸው፣ የቍርባን ስም ብቻ ያረካቸዋል ወይም ኅብረታችሁን ይወድዳሉ ብላችሁ ልትጠብቁ ትችላላችሁን? እንግዲያስ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በሚለው ቃል ባዶ ድምፅ ይረካሉ ብላችሁ ለምን ታስባላችሁ?

ደግሞም ከእናንተ የተለየ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር በምታደርጉት ክርክር ሁሉ በጉዳያችሁ ላይ እንዴት ያለ ጉዳት እንደምታመጡ አስቡ። የእናንተ መርሆች ከእነርሱ ቢሻሉ፣ የእነርሱ ተግባር ግን ከእናንተ ቢሻል፣ ሕዝቡ ጥያቄው ስሙ ወይስ ነገሩ ራሱ፣ ጥላው ወይስ አካሉ፣ የቱ ይበልጥ ተፈላጊ ነው የሚል እንደ ሆነ ያስባሉ፤ በአጠቃቀሙ ለይስሙላ ብቻ መሆናችሁን፣ እንዲያውም ፈጽሞ እንደማትጠቀሙበት ስለሚያዩ መንገዳችሁን የሚያታልል ባዶ ሥርዓት ብቻ አድርገው ይቈጥሩታል። አሁን በምናገረው ነገር የአስተዳደር ሥርዓታችሁን እየተቃወምሁ አይደለሁም፤ ይልቁንም እደግፈዋለሁ፤ ለእርሱ እንዲህ ቀናተኞች የምትመስሉት እናንተ ራሳችሁ የምትቃወሙት መሆናችሁን እነግራችኋለሁ፤ በክርክራችሁ ሁሉ ከምታስከብሩት ይልቅ ባለመፈጸማችሁ ይበልጥ ታዋርዱታላችሁና። ሥራችሁንም ሳትጨርሱ በታማኝነት መፈጸሙ ከሁሉ የበረታ ማስረጃችሁ እንደሚሆን ታገኛላችሁ። እስከዚያ ድረስ ግን ሕዝቡ እንዲህ ብላችሁ በግልጽ እንዳወጃችሁ አድርገው ይረዱአችኋል፦ በሕዝብ ፊት የሚደረግ ምክርን፣ መናዘዝን ወይም ውግዘትን አንፈልግም፤ የእኛ መንገድ ምንም መልካም ሳናደርግ የአንድን አስተዳደር ባዶ ስም ብቻ ከፍ ማድረግ ነው። ማንንም ይህን ታላቅ ተግባር ጊዜውን ባልጠበቀ ሁኔታ እንዲፈጽም ልገፋፋ አልሻም። ነገር ግን የሚገባው ጊዜ ከቶ አይመጣምን? ወቅቱ አይደለም በሚል ሰበብ ስብከትንና ቍርባንን ይህን ያህል ዓመታት ትተዉ ነበርን? ስትሞቱ ለእርሱ የተሻለ ጊዜ ታገኛላችሁን? ምንም እንኳ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጁለት ቢቆዩም በዚህ አስፈላጊ ሥራ አንዳች ሳያደርጉ አስቀድመው የሞቱ ስንት ናቸው! አንዳንዶች ከሌሎች ይልቅ ብዙ ተስፋ አስቈራጭ ነገሮችና እንቅፋቶች እንዳሉባቸው አውቃለሁ፤ ነገር ግን ከእንዲህ ያለ ተግባር ነጻ የሚያደርገን ተስፋ አስቈራጭ ነገርና እንቅፋት ምንድር ነው? አስቀድመን ካቀረብናቸው ምክንያቶች በተጨማሪ እነዚህ ጥቂቶች በጥንቃቄ ይታሰቡ፦

(1) ለሕዝባችን ስንሰብክ፣ የታወቀውን ማንኛውንም ተግባር ሆን ብሎና ያለማቋረጥ ቸል ብሎ መኖርን እንዴት ያለ አሳዛኝ ምልክት እናደርገዋለን! እኛስ ከዓመት ወደ ዓመት፣ እንዲያውም በዘመናችን ሁሉ እንዲሁ እናደርጋለንን? ምክንያት ማቅረብ የዚህን ምልክት አደጋ የሚያስወግድ ከሆነ፣ እንደ እናንተ ምክንያት የማያገኝ ሰው ማን ነው?

(2) በክርስቶስ ሥራ ታማኝነት ማጣትን ባናሳይ እንኳ ስንፍናንና ታካችነትን በግልጽ እናሳያለን። የምናገረው ከልምድ ነው። ከዚህ ተግባር ለረጅም ጊዜ የከለከለኝና በእርሱ ላይ አጥብቆ የተሟገተው ስንፍና ነበር። በእርግጥ አስቸጋሪና አድካሚ ሥራ ነው፤ የክፉዎችንም ቍጣ በላያችን ስለሚያመጣ በተወሰነ መጠን ራስን መካድ የሚጠይቅ ነው። ነገር ግን ሥጋዊ ምቾታችንንና ጸጥታችንን፣ ወይም የክፉ ሰዎችን ፍቅርና ሰላም ከጌታችን ከክርስቶስ አገልግሎት ልናስበልጥ እንደፍራለንን? ሰነፍ ባሪያዎች መልካም ዋጋ ሊጠብቁ ይችላሉን? ወንድሞች ሆይ፣ እኛ የዚህ አውራጃ መጋቢዎች በስምምነታችን ሁለተኛ አንቀጽ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለን ቃል እንደ ገባን አስቡ፦ «እግዚአብሔር ተግባራችንን እስካሳወቀን ድረስ በታማኝነት ልንፈጽመው እንደምንተጋ፣ በንብረታችን ላይ በሚደርስ በማናቸውም ፍርሀት ወይም ኪሳራ፣ በሰዎች ፊት መጨፍገግና ቍጣ፣ ወይም በማናቸውም እንዲህ ባለ ሥጋዊ ምክንያት እንደማንተው በእግዚአብሔር እርዳታ ተስማምተናል፤ ወስነናልም።» እባካችሁ ይህን ቃል ኪዳን አጥኑ፤ አፈጻጸማችሁንም ከእርሱ ጋር አስተያዩ። እንዲህ ቃል በመግባታችሁ በወጥመድ የተያዛችሁ አይምሰላችሁ፤ ቃል ኪዳናችሁ ይህን ከማድረጉ በፊት የእግዚአብሔር ሕግ ለዚያው ተግባር ግዴታ ጥሎባችኋልና። እዚህ ያለው ሌሎችም እንደ እናንተ የታሰሩበት ነገር ብቻ ነው።

(3) ሥርዓተ ተግሣጽን ቸል ማለት የማይሞቱ ነፍሳትን ለማሳሳት ብርቱ ዝንባሌ አለው፤ ክርስቲያኖች ያልሆኑ ሰዎች እንደ ክርስቲያን ተቈጥረው እንዲኖሩ ሲፈቀድላቸውና በእግዚአብሔር ሥርዓት ከሌሎቹ ሳይለዩ ሲቀሩ ክርስቲያኖች እንደ ሆኑ ያስባሉና፤ ደግሞም የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች እንዲህ የሚታገሡት ስለ ሆነ፣ ሌሎችን የሚያሰናክሉ ሰዎች ኃጢአታቸውን ሊታገሡት የሚቻል ነገር አድርገው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።

(4) ክርስትናን ራሱን በዓለም ዓይን እናረክሰዋለን፤ ክርስቶስ ከሰይጣን የበለጠ ለቅድስና የቆመ እንዳልሆነ፣ ወይም የክርስትና ሃይማኖት ከዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች የበለጠ ቅድስናን እንደማይጠይቅ እንዲያምኑ የበኩላችንን እናደርጋለን። ቅዱሳንና ያልተቀደሱ ሁሉ እነርሱን ለመለየት አንዳች መንገድ ሳይወሰድ የአንድ በረት በጎች እንዲሆኑ ከተፈቀደላቸው፣ ቤዛችንን እርሱ በዚህ ጥፋተኛ እንደ ሆነ፣ የትእዛዛቱም ጠባይ ይህ እንደ ሆነ አስመስለን ስሙን እናጠፋለን።

(5) ከሁሉ የከፉት በአብያተ ክርስቲያናቶቻችን ውስጥ ሳይገሠጹ እንዲኖሩ በመፍቀዳችን መለያየትን እናጸናለን፤ በዚህም ብዙ ቅን ክርስቲያኖች ከእኛ መለየት ግዴታቸው እንደ ሆነ ያስባሉ። ከተለዩት አብያተ ክርስቲያናት አባላት መካከል ልከኞች ከነበሩ ከአንዳንዶቹ ጋር ተነጋግሬአለሁ፤ መለያየትንም በመቃወም ተከራክሬአቸዋለሁ፤ እነርሱም የፕሬስቢቴሪያን አመለካከት እንዳላቸው ወይም በእርሱ ላይ የሚሉት ነገር እንደሌላቸው አረጋገጡልኝ፤ ነገር ግን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተቀላቀሉት ከፍጹም ችግር የተነሣ ነው፤ ሥርዓተ ተግሣጽ የክርስቶስ ሥርዓት እንደ መሆኑ የሚችሉት ሁሉ ሊጠቀሙበት ይገባል ብለው አስበዋልና፤ ስለዚህም ሊያገኙት እየቻሉ ከዚያ በኋላ ያለ እርሱ ለመኖር አልደፈሩም፤ ስለ እርሱ እንደ ጻፉት ሥርዓተ ተግሣጽን የሚፈጽሙ የፕሬስቢቴሪያን አብያተ ክርስቲያናትንም ሊያገኙ አልቻሉም፤ የተለዩትም ለጊዜው ብቻ እንደ ሆነ፣ ፕሬስቢቴሪያኖች ሥርዓተ ተግሣጽን እስኪጠቀሙ ድረስ እንደ ሆነ፣ ያን ጊዜም በፈቃዳቸው ወደ እነርሱ እንደሚመለሱ ነገሩኝ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ከእኛ ለመለየት እንዲህ ያለ ምክንያት ስላገኙ ማዘኔን እመሰክራለሁ። የአብያተ ክርስቲያናቶቻችን አባላት ሆነው ሳሉ በደለኞችን ከቍርባን መከልከል ብቻ ሥርዓተ ተግሣጽን ከዚያ በላይ ከመፈጸም ነጻ አያደርገንም።

(6) በራሳችንና በጉባኤዎቻችን ላይ የእግዚአብሔርን ቍጣ ለማምጣት፣ በዚህም የድካማችንን ፍሬ ለማጥፋት ብዙ እናደርጋለን። የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን መልአክ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሳቾችን በመታገሡ ከተገሠጸ፣ እኛም በዚያው ምክንያት በግልጽ የሚታወቁ፣ ሌሎችን የሚያሰናክሉና ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን በመታገሣችን ልንገሠጽ እንችላለን።

ይህን ያህል ለተከራከሩለት ሥርዓተ ተግሣጽ አፈጻጸም የእንግሊዝን መጋቢዎች አሁን የሚከለክሏቸው እንቅፋቶች ምንድር ናቸው? እኔ ማወቅ እስከ ቻልሁ ድረስ ዋናው ምክንያት ይህ ነው፦ «የሥራው አስቸጋሪነትና በእርሱ ምክንያት ሊደርስብን የሚችለው ችግርና መከራ ነው። አንድን ኃጢአተኛ በሕዝብ ፊት ብንገሥጽ ይቈጣል፤ የሞት ጥላቻም ይይዝብናል። በእውነተኛ ንስሐ በሕዝብ ፊት እንዲመሰክሩ ልናሳምን የምንችለው እጅግ ጥቂቶችን ነው። ልናወግዛቸው ብንነሣ በእኛ ላይ በቍጣ ያብዳሉ። እግዚአብሔር እንደሚፈልግብን በደብሩ ውስጥ ካሉት እልከኛ ኃጢአተኞች ሁሉ ጋር ብንሠራ በመካከላቸው መኖር አይቻልም ነበር፤ በሁሉ ዘንድ እንዲህ የተጠላን እንሆን ነበር፤ ስለዚህም ሕይወታችን የማይመች እንደሚሆን ሁሉ ድካማችንም ፍሬ ቢስ ይሆን ነበር፤ ሰዎች በእኛ ላይ በጥላቻ በተያዙ ጊዜ አይሰሙንምና፤ ስለዚህ የሚከተለው ጉዳት ከመልካሙ የሚበልጥ ስለ ሆነ ተግባሩ ለእኛ ተግባር መሆኑ ይቀራል።» ሥርዓተ ተግሣጽ ላለመፈጸሙ ዋናዎቹ ምክንያቶች እነዚህ ናቸው፤ ከዚህም ጋር እያንዳንዱን በደለኛ በግል መምከር የሚያስከፍለን ታላቅ ድካም አለ። ለዚህ ሁሉ እንዲህ ብዬ እመልሳለሁ፦

[ሀ] እነዚህ ምክንያቶች፣ በተለይም በአንዳንድ ዘመናትና ስፍራዎች፣ በሥርዓተ ተግሣጽ ላይ እንደሚሠሩ ሁሉ በክርስትና ራሱ ላይም እንዲሁ አይሠሩምን? ክርስቶስ «በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት» አልመጣም፤ የእርሱን ሰላም እናገኛለን እንጂ የዓለምን አይደለም፤ ዓለም እንደሚጠላን ነግሮናልና። ብራድፎርድ ወይም ሁፐር፣ ወይም በንግሥት ሜሪ ዘመን በእሳት የተቃጠሉት ማንኛቸውም፣ ተሐድሶን በግልጽ በመቀበል ተግባር ላይ ከዚህ ሁሉ የበለጠ ምክንያት ሊያቀርቡ አይችሉም ነበርን? «የተጠላን ያደርገናል፤ ሕይወታችንንም ለእሳት ነበልባል ያጋልጣል» ሊሉ አይችሉም ነበርን? ስለ እርሱ ብሎ ያለውን ሁሉ የራሱንም ሕይወት የማይጠላ ክርስቲያን እንዳልሆነ ክርስቶስ ደምድሞአል፤ እኛ ግን የዓለማዊ ኪሳራን ስጋት በሥራው ላይ እንደ ምክንያት እናቀርባለን! ከመከራ መሸሽ፣ አደጋ የሌላቸውንና ቀላሎቹን ሥራዎች ብቻ መያዝ፣ የቀሩትንም ተግባራት እንዳልሆኑ ራሳችንን ማሳመን ግብዝነት ካልሆነ ምንድር ነው? በእርግጥም ከመከራ የማምለጫው የተለመደው መንገድ ይህ ነው፤ ለመከራ የሚያጋልጠንን ተግባር ቸል ማለት። ተግባራችንን በታማኝነት ብንፈጽም፣ ከእኛ በፊት የነበሩት በአሕዛብና በሌሎች ከሓዲዎች መካከል እንዳገኙት ያለውን ዕጣ መጋቢዎች ክርስቲያን ነን በሚሉት መካከል ያገኙ ነበር። ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል ካልቻላችሁ ግን እጃችሁን በዕርፉ ላይ ለምን ጫናችሁ? አስቀድማችሁስ ተቀምጣችሁ ዋጋውን ለምን አልቈጠራችሁም? የአገልግሎት ሥራ እንዲህ ያለ ታማኝነት በጎደለው ሁኔታ የሚፈጸመው በሥጋዊ መንገድ ስለሚጀመር ነው፤ ሰዎች የምቾት፣ የክብርና የመከበር ሕይወት አድርገው ይገቡበታል፤ ግባቸውንም ለመድረስ፣ የጠበቁትንም በትክክልም ሆነ በስሕተት ለማግኘት ይወስናሉ። ጥላቻንና መከራን አልጠበቁም፤ ሥራቸውን በመተው ቢሆን እንኳ ይሸሹታል።

[ለ] መልካም ልታደርጉላቸው የማትችሉ ትሆናላችሁ የሚለውን በተመለከተ እንዲህ እመልሳለሁ፤ ያ ምክንያት በግልጽ ስብከት፣ በመገሠጽ ወይም ክፉ ሰዎች በእርሱ ምክንያት በሚጠሉን በማናቸውም ሌላ ተግባር ላይም እንዲሁ ይሠራል። እግዚአብሔር መልካም እንዲያደርጉ የራሱን ሥርዓቶች ይባርካል፤ አለዚያማ ባልሠራቸውም ነበር። ሌሎችን የሚያሰናክሉትን በሕዝብ ፊት ብትመክሩና ብትገሥጹ፣ ወደ ንስሐም ብትጠሩአቸው፣ እልከኞቹንም ብታወጡ፣ ከምትገሥጹአቸው ለብዙዎቹ፣ ምናልባትም ለተወገዙት ለራሳቸው መልካም ልታደርጉ ትችላላችሁ። ቢያንስ የእግዚአብሔር መንገድ መሆኑን እርግጠኛ ነኝ፤ መገሠጽም ምንም መልካም በማያደርግበት ጊዜ የመጨረሻው መንገዱ ነው። ስለዚህ የመጨረሻው መንገድ ሊሠራበት የሚገባው የቀደሙት ሁሉ አስቀድመው ከንቱ እንደ ሆኑ ሲታሰብ ብቻ ሆኖ ሳለ፣ የቀደሙትን መንገዶች እንዳናከሽፍ ብለን የመጨረሻውን መንገድ ቸል ማለት ጠማማነት ነው። ይሁን እንጂ በደለኛው ምንም ጥቅም ባያገኝ፣ በውስጥ ያሉትና በውጭ ያሉት ከእርሱ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ፤ ቤተ ክርስቲያኑም ከዓለም በግልጽ ስትለይ፣ የሰማይና የገሃነም ወራሾችም ፈጽመው ሳይደባለቁ፣ ዓለምም ክርስቶስና ሰይጣን የሚታገሉት ለበላይነት ብቻ እንደ ሆነ፣ ለቅድስና ወይም ለኃጢአት ያላቸውም ዝንባሌ አንድ ዓይነት እንደ ሆነ እንዲያስብ ሳይደረግ ሲቀር፣ እግዚአብሔር ክብሩን ያገኛል።

[ሐ] ነገር ግን በመንገዱ ላይ እንደምታስቡት ያሉ ችግሮች እንደሌሉ፣ ሥርዓተ ተግሣጽም እንደምታስቡት የማይጠቅም ነገር እንዳልሆነ ልንገራችሁ። እኔ ራሴ በጥቂቱና ዘግይቼ ስለ ሞከርሁት እግዚአብሔርን እባርካለሁ። ከንቱ እንዳልሆነ፣ የሚያስከትላቸውም አደጋዎች ቸልተኝነታችንን ይቅር የሚያሰኙ እንዳልሆኑ በልምድ መናገር እችላለሁ።

እመሰክራለሁ፤ ፈቃዴ ቢፈጸም ኖሮ፣ የማይሰብክ ሰው ቸልተኛ ሰባኪ ሆኖ እንደሚወገድ ሁሉ፣ ሕዝቡን በሥርዓተ ተግሣጽ የማይመራ ሰውም ቸልተኛ መጋቢ ሆኖ ይወገድ ነበር፤ መምራት እንደ መስበክ ሁሉ የመጋቢ ሹመት ዋና ክፍል እንደ ሆነ እርግጠኛ ነኝና።

በእነዚህ መናዘዞች ከዚህ በላይ አልቀጥልም። አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችንም ከላይ በተጠቀሱት በእነዚህ ኃጢአቶች በደለኞች ነን ብለን ከመጮኽና ስለ ስሕተቶቻችን ነፍሳችንን በጌታ ፊት ከማዋረድ በቀር ምን ቀረ? ይህ «ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ» የሚለውን መፈጸም ነውን? ይህ በጥቅሱ ውስጥ ከተሰጠን አርአያ ጋር ይመሳሰላልን? አሁን ልበ ደንዳኖችና ያልተዋረድን ሆነን ብንገኝ፣ ለራሳችንና ለቤተ ክርስቲያን ምንኛ አሳዛኝ ምልክት በሆነ ነበር! አገልግሎቱ ብዙ ጊዜ በብዙ ዓይነት ጠላቶች ዛቻና ስም ማጥፋት ደርሶበታል፤ ይህም የእነርሱን ርኩስ ክፋት የሚያሳይ ቢሆንም የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሆነ ቍጣ ደግሞ ሊጠቍመን ይችላል። ወንድሞች ሆይ፣ እመኑኝ፤ የእንግሊዝ አገልጋዮች በአገሪቱ ኃጢአቶች ውስጥ ትንሾቹም የመጨረሻዎቹም አይደሉም። ስለዚህ ሕዝባችንን ለረጅም ጊዜ ወደ ጠራንበት መዋረድ እኛም የበኩላችንን የምንወስድበት ጊዜ ነው። አእምሮአችን በእኛ ዘንድ ካለ፣ እግዚአብሔር በእኛ ላይ እንደ ተቈጣ፣ ይህንም ሕዝብ ወደ ንስሐ የጠራው ድምፅ ለሌሎች እንደ ተናገረ ሁሉ ለእኛም እንደ ተናገረ ልናስተውል እንችላለን። በብዙ አስደናቂ ማዳኖችና ጥበቃዎች የታወጁትን የንስሐ ትእዛዛት በተመለከተ «የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ»፤ የሚያይ ዓይን ያለውም በብዙ የደም መስመሮች ተጽፈው ይያቸው። እግዚአብሔር በእሳትና በሰይፍ ወደ መዋረድ ሲጠራን ቆይቶአል፤ ፍርድ «ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ» እንደ ጀመረ ሁሉ፣ መዋረድም በዚያው ባይጀምር ለእኛም ለአገሪቱም አሳዛኝ ትንቢት ይሆናል።

ምን! ሕዝባችንን ወደ ነጻና ሙሉ መናዘዝ እየጠራን ኃጢአታችንን እንክዳለን ወይም እናቃልላለንን? ለራሳችን በማዘን ራቁትነታችንን የምንሸፍንበት የበለስ ቅጠል ከመፈለግ፣ እኛ ከእርሱ ያስበለጥነውን የራሳችንን ክብር ፍርስራሽ ላይ የነፈግነውን ክብሩን እንዲገነባ እግዚአብሔርን ከማስገደድ፣ በፈቃዳችንም ልንሰጠው እምቢ ያልነውን በከፋ ፍርድ እንዲወስደው ከማድረግ ይልቅ በትሑት መናዘዝ ለእግዚአብሔር ክብርን መስጠት አይሻልምን? ወዮ! እግዚአብሔር ክብሩን እንደሚችለው እንዲያገኝ ብታስገድዱት፣ ለዘላለም ኀዘናችሁና ውርደታችሁ ሊያገኘው ይችላል። በግልጽ የተሠሩ ኃጢአቶች ከምንናዘዛቸው ይልቅ ስንሰውራቸው ይበልጥ ያዋርዱናል። ውርደታችን ኃጢአቱ እንጂ መናዘዙ አይደለም። በፀሓይ ፊት ሠርተናቸዋል፤ ስለዚህም ሊሰወሩ አይችሉም፤ እነርሱን ለመሸፈን የሚደረገው ሙከራም በደላችንንና ኀፍረታችንን ከመጨመር በቀር ሌላ አያደርግም። ኃጢአታችን በክብራችን ላይ ያደረሰውን ስብራት ለመጠገን ከነጻ መናዘዝና ከመዋረድ በቀር ሌላ መንገድ የለም። የራሴን ኃጢአቶች ከመናዘዝ ልቈጠብ አልደፈርሁም፤ የእነርሱን በመናዘዜ የሚሰናከል ቢኖር፣ በራሴ ላይ ያደረግሁትን ብቻ እንዳደረግሁ ይወቅ። የኃጢአታቸውን መናዘዝ ለመካድ ቢደፍሩም በራሳቸው ኃላፊነት ያድርጉት። ነገር ግን በእውነት ትሑታን የሆኑት የክርስቶስ አገልጋዮች ሁሉ በየጉባኤዎቻቸው ፊት ኃጢአቶቻቸውን ይበልጥ በጽኑ ለማልቀስና መታረምን ቃል ለመግባት እንደሚነሣሡ አልጠራጠርም።

ቀዳሚ ቀጣይ