ምዕራፍ 9 · 12 ደቂቃ ንባብ · 15 ደቂቃ ማዳመጥ
የነፍስ እይታ
የእምነታችንን ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን…—ዕብራውያን 12:2
በምዕራፍ ስድስት የጠቀስነውን ያንን አስተዋይ ተራ ሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀርብ እናስበው። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚይዝ ቀድሞ ምንም ሳያውቅ ወደ እርሱ ይቀርባል። ፈጽሞ ከአድልዎ ነጻ ነው፤ የሚያረጋግጠውም ሆነ የሚከላከለው ነገር የለውም።
እንዲህ ያለው ሰው ብዙም ሳያነብ አእምሮው ከገጹ ላይ ጎልተው የሚታዩ አንዳንድ እውነቶችን ማስተዋል ይጀምራል። እነዚህም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ስላደረገው ግንኙነት ከተጻፈው ታሪክ በስተጀርባ ያሉ፣ ቅዱሳን ሰዎችም «በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው» በጻፉት ጽሑፍ ውስጥ የተሸመኑ መንፈሳውያን መርሆች ናቸው። ማንበቡን ሲቀጥል እነዚህ እውነቶች ግልጽ እየሆኑለት በሄዱ ቁጥር ቍጥር ሊሰጣቸውና በእያንዳንዱ ቍጥር ሥር አጭር ማጠቃለያ ሊጽፍ ይፈልግ ይሆናል። እነዚህ ማጠቃለያዎች የመጽሐፍ ቅዱሳዊ የሃይማኖት መግለጫው አንቀጾች ይሆናሉ። ተጨማሪ ንባብ እነዚህን ነጥቦች ከማስፋትና ከማጠንከር በቀር አይለውጣቸውም። ሰዋችን መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የሚያስተምረውን እያገኘ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው ነገሮች ዝርዝር ውስጥ በላይኛው ስፍራ የእምነት ትምህርት ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት የሚሰጠው ታላቅ ክብደት ያለው ስፍራ እንዳያስተውለው ሊያመልጠው የማይችል እጅግ ግልጽ ነው። ምናልባትም እንዲህ ብሎ ይደመድማል፦ በነፍስ ሕይወት ውስጥ እምነት ከሁሉ የላቀ አስፈላጊ ነገር ነው። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም። እምነት ማናቸውንም ነገር ያስገኝልኛል፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ወደ የትኛውም ስፍራ ያደርሰኛል፤ ያለ እምነት ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ፣ ይቅርታ፣ ነጻ መውጣት፣ መዳን፣ ኅብረት፣ ማናቸውም መንፈሳዊ ሕይወት ከቶ ሊኖር አይችልም።
ወዳጃችን ወደ ዕብራውያን ምዕራፍ አሥራ አንድ በደረሰ ጊዜ በዚያ ለእምነት የተነገረው አንደበተ ርቱዕ ውዳሴ እንግዳ ሆኖ አይታየውም። ጳውሎስ ለሮሜና ለገላትያ በጻፋቸው መልእክቶቹ ለእምነት ያቀረበውን ብርቱ ሙግት አስቀድሞ አንብቦአልና። በኋላም የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ለማጥናት ቢቀጥል፣ የተሐድሶ አባቶች እምነት በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ያለውን ማዕከላዊ ስፍራ ባሳዩ ጊዜ በትምህርታቸው ውስጥ የነበረውን አስደናቂ ኃይል ይረዳል።
እንግዲህ እምነት ይህን ያህል እጅግ አስፈላጊ ከሆነ፣ እግዚአብሔርን በመፈለጋችንም ውስጥ ያለ እርሱ የማይሆን ግዴታ ከሆነ፣ ይህን እጅግ የከበረ ስጦታ ይዘነው እንደ ሆነ ወይም እንዳልያዝነው በጥልቅ መጨነቃችን ፍጹም ተፈጥሮአዊ ነው። አእምሮአችንም ያለው ባሕርይ እንዲህ ስለ ሆነ ይዋል ይደር እንጂ ስለ እምነት ምንነት መጠየቃችን አይቀርም። እምነት ምን ነው? የሚለው ጥያቄ፣ እምነት አለኝን? ከሚለው ጥያቄ አጠገብ ይቀመጣል፤ መልስም በየትም ስፍራ የሚገኝ ቢሆን መልስ ይጠይቃል።
ስለ እምነት የሚሰብኩ ወይም የሚጽፉ ሁሉ ማለት ይቻላል ስለ እርሱ የሚናገሩት ብዙውን ጊዜ ያንኑ ነገር ነው። እምነት የተስፋ ቃልን ማመን እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔርን በቃሉ መቀበል እንደ ሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስን እውነት ነው ብሎ መቍጠርና በእርሱ ላይ መራመድ እንደ ሆነ ይነግሩናል። የቀረው የመጽሐፉ ወይም የስብከቱ ክፍል ብዙውን ጊዜ በእምነታቸው ምክንያት ጸሎታቸው የተመለሰላቸውን ሰዎች ታሪክ በመተረክ ይያዛል። እነዚህ መልሶች በአብዛኛው እንደ ጤና፣ ገንዘብ፣ የአካል ጥበቃ ወይም በንግድ መሳካት ያሉ ተግባራዊና ጊዜያዊ ባሕርይ ያላቸው ቀጥተኛ ስጦታዎች ናቸው። ወይም መምህሩ የፍልስፍና ዝንባሌ ያለው ከሆነ ሌላ መንገድ ይዞ በሜታፊዚክስ ማዕበል ውስጥ ያሰጥመናል፣ ወይም ደጋግሞ እየበየነና እንደገና እየበየነ፣ ቀጭኑን የእምነት ጠጕር እየላጨ እየቀጠነ በመጨረሻ እንደ ሸረሪት ድር በሚመስሉ ስስ ፍቅፋቂዎች ውስጥ እስኪጠፋ ድረስ በሥነ ልቡና ቃላት ክምር ይቀብረናል። እርሱ ሲጨርስ እኛ ተስፋ ቈርጠን እንነሣለን፤ «በገባንበት በዚያው በር» ተመልሰን እንወጣለን። በእርግጥ ከዚህ የተሻለ ነገር ሊኖር ይገባል።
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እምነትን ለመበየን የተደረገ ጥረት ከሞላ ጎደል የለም። በዕብራውያን 11:1 ካለው አሥራ አራት ቃላት ካሉት አጭር ብያኔ በቀር ሌላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብያኔ አላውቅም፤ በዚያም እንኳ እምነት የተበየነው በሥራው እንጂ በፍልስፍና አይደለም፤ ይኸውም እምነት በሥራ ላይ ሲውል ምን እንደ ሆነ የሚገልጽ እንጂ በባሕርይው ምን እንደ ሆነ አይደለም። የእምነትን መኖር አስቀድሞ ይቀበልና እምነት ራሱ ምን እንደ ሆነ ሳይሆን ምን እንደሚያስገኝ ያሳያል። እኛም እስከዚያው ድረስ ብቻ ሄደን ከዚያ ወዲያ ለማለፍ ባንሞክር ጥበበኞች እንሆናለን። ከወዴት እንደሚመጣና በምን መንገድ እንደሚመጣ ተነግሮናል፦ «እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው»፤ ደግሞም «እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።» ይህን ያህል ግልጽ ነው፤ ቶማስ አ ኬምፒስን ቃሉን ቀይሬ ልጥቀሰው፦ «የእምነትን ብያኔ ከማወቅ ይልቅ እምነትን ብለማመድ እመርጣለሁ።»
ከዚህ ወዲያ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ «እምነት … ነው» የሚሉት ቃላት ወይም ተመሳሳያቸው በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ፣ በሚያምን ሰው ሲለማመድ እምነት በሥራ ላይ ምን እንደ ሆነ የሚያመለክቱ እንደ ሆኑ እንዲረዱአቸው እለምናለሁ። እዚህ ላይ የብያኔን አሳብ ትተን እምነትን በተግባር ሊለማመድ እንደሚችል ነገር እናስበዋለን። የአሳባችን መልክ ተግባራዊ እንጂ ንድፈ አሳባዊ አይሆንም።
በዘኍልቍ መጽሐፍ ውስጥ ባለ አንድ አስደናቂ ታሪክ እምነት በሥራ ላይ ሲውል ይታያል። እስራኤል ተስፋ ቈርጦ በእግዚአብሔር ላይ ተናገረ፤ እግዚአብሔርም እሳታማዎች እባቦችን በመካከላቸው ሰደደ። «ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሕዝብ ሞተ።» ከዚያም ሙሴ ስለ እነርሱ እግዚአብሔርን ለመነ፤ እርሱም ሰማው፥ ለእባቦቹም ንድፊያ መድኃኒት ሰጣቸው። ሙሴ የናስ እባብ ሠርቶ ሕዝቡ ሁሉ በሚያዩት ስፍራ በዓላማ ላይ እንዲሰቅለው አዘዘው፤ «የተነደፈውም ሁሉ ሲያየው በሕይወት ይኖራል።» ሙሴም ታዘዘ፤ «እባብም ሰውን በነደፈ ጊዜ ሰውዬው የናሱን እባብ ሲመለከት በሕይወት ኖረ» (ዘኍልቍ 21:4-9)።
በአዲስ ኪዳን ይህ አስፈላጊ ታሪክ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከራሱ ያላነሰ ባለ ሥልጣን ተተርጕሞልናል። ለሚሰሙት እንዴት ሊድኑ እንደሚችሉ እያስረዳቸው ነው። በማመን እንደ ሆነ ይነግራቸዋል። ከዚያም ይህን ግልጽ ለማድረግ በዘኍልቍ መጽሐፍ ያለውን ይህን ድርጊት ይጠቅሳል፦ «ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፥ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው የሰው ልጅ ደግሞ ሊሰቀል ይገባዋል» (ዮሐንስ 3:14-15)።
ተራው ሰዋችን ይህን ሲያነብ አንድ አስፈላጊ ግኝት ያገኛል። «መመልከት» እና «ማመን» አንድ ትርጕም ያላቸው ቃላት እንደ ሆኑ ያስተውላል። በብሉይ ኪዳኑ እባብ ላይ «መመልከት» በአዲስ ኪዳኑ ክርስቶስ «ከማመን» ጋር አንድ ነው። ይኸውም መመልከቱና ማመኑ አንድ ነገር ናቸው። እስራኤል በውጫዊ ዓይኖቻቸው ሲመለከቱ፣ ማመን ግን በልብ እንደሚደረግ ይረዳል። እንዲህ ብሎ የሚደመድም ይመስለኛል፦ እምነት የነፍስ እይታ ወደ አዳኝ አምላክ ነው።
ይህን ባየ ጊዜ ቀደም ብሎ ያነበባቸውን ክፍሎች ያስታውሳል፤ ትርጕማቸውም እንደ ጎርፍ ይመጣበታል። «ወደ እርሱ ተመለከቱ፥ ብርሃንም አገኙ፤ ፊታቸውም አላፈረም» (መዝሙር 34:5)። «በሰማያት የምትኖር ሆይ፥ ወደ አንተ ዓይኖቼን አነሣሁ። እነሆ፥ የባሪያዎች ዓይኖች ወደ ጌቶቻቸው እጅ፥ የባሪያይቱም ዓይኖች ወደ እመቤቷ እጅ እንደሚመለከቱ፥ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዓይኖቻችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለከታሉ» (መዝሙር 123:1-2)። እዚህ ምሕረትን የሚሻ ሰው በቀጥታ ወደ ምሕረት አምላክ ይመለከታል፤ ምሕረትም እስኪሰጠው ድረስ ዓይኖቹን ከእርሱ ከቶ አያነሣም። ጌታችንም ራሱ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይመለከት ነበር። «ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ» (ማቴዎስ 14:19)። በእርግጥም ኢየሱስ ሥራዎቹን የሚሠራው ውስጣዊ ዓይኖቹን ሁልጊዜ በአባቱ ላይ በማኖር እንደ ሆነ አስተምሮአል። ኃይሉ ወደ እግዚአብሔር ባለማቋረጥ በመመልከቱ ውስጥ ነበር (ዮሐንስ 5:19-21)።
እኛ ከጠቀስናቸው ከእነዚህ ጥቂት ጥቅሶች ጋር በመንፈስ የተገለጠው ቃል አጠቃላይ አካሄድ ፍጹም ይስማማል። ይህም በዕብራውያን መልእክት ውስጥ፣ የሕይወትን ሩጫ «የእምነታችንን ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን» እንድንሮጥ በተመከርንበት ስፍራ ተጠቃልሎልናል። ከዚህ ሁሉ እንደምንማረው እምነት አንድ ጊዜ ተደርጎ የሚያበቃ ድርጊት ሳይሆን፣ ልብ ወደ ሥላሴ አምላክ የሚያደርገው የማያቋርጥ እይታ ነው።
እንግዲህ ማመን የልብን ትኵረት ወደ ኢየሱስ ማቅናት ነው። አእምሮን አንሥቶ «እነሆ የእግዚአብሔር በግ» ብሎ መመልከትና በቀረው ዕድሜአችን ሁሉ ያንን መመልከት ከቶ አለማቋረጥ ነው። በመጀመሪያ ይህ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ወደ ድንቅ አካሉ በጸጥታና ያለ ውጥረት አጽንተን ስንመለከት እየቀለለ ይሄዳል። ልብን የሚሰርቁ ነገሮች ሊያደናቅፉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ልብ አንድ ጊዜ ለእርሱ ከተሰጠ፣ ከእርሱ ርቆ ከሚሄድበት ከእያንዳንዱ አጭር ጕዞ በኋላ ትኵረቱ እንደገና ይመለሳል፤ እንደ ተቅበዝባዥ ወፍ ወደ መስኮቷ እንደምትመለስ በእርሱ ላይ ያርፋል።
ይህን አንድ ራስን መስጠት፣ ለዘላለም ወደ ኢየሱስ ለመመልከት የልብን ዓላማ የሚያጸና ይህን አንድ ታላቅ የፈቃድ ውሳኔ አጽንዖት ልሰጠው እወዳለሁ። እግዚአብሔር ይህን ዓላማ እንደ ምርጫችን ይቀበለዋል፤ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ለሚከብቡን ለሺህ ልብ የሚሰርቁ ነገሮችም የሚገባውን ያህል ይታገሣል። የልባችንን አቅጣጫ ወደ ኢየሱስ እንዳቀናን ያውቃል፤ እኛም ልናውቀው እንችላለን፤ ከጊዜ በኋላ ከእኛ በኩል ምንም የንቃት ጥረት የማይጠይቅ እንደ መንፈሳዊ ልማዳዊ ምላሽ የሚሆን የነፍስ ልማድ እየተሠራ እንዳለ በማወቅም ራሳችንን ልናጽናና እንችላለን።
ከበጎ ምግባሮች ሁሉ ራሱን ከሁሉ ያነሰ የሚመለከተው እምነት ነው። በባሕርይው የራሱን መኖር እንኳ በጭንቅ ያውቃል። በፊቱ ያለውን ሁሉ እንደሚያይ ራሱን ግን ከቶ እንደማያይ ዓይን፣ እምነትም ባረፈበት አካል ተይዞ ለራሱ ምንም ትኵረት አይሰጥም። ወደ እግዚአብሔር ስንመለከት ራሳችንን አናይም—እንዴት ያለ የተባረከ መገላገል ነው! ራሱን ለማንጻት የታገለና ከተደጋጋሚ ውድቀት በቀር ምንም ያላገኘ ሰው፣ ነፍሱን መነካካት ትቶ ወደ ፍጹሙ ሲመለከት እውነተኛ እፎይታ ያገኛል። ወደ ክርስቶስ ሲመለከት ለረጅም ጊዜ ሊያደርጋቸው ሲሞክር የኖረው ነገሮች በውስጡ ይፈጸማሉ። በእርሱ ውስጥ መፈለግንም ማድረግንም የሚሠራ እግዚአብሔር ይሆናል።
እምነት በራሱ የሚያስመሰግን ሥራ አይደለም፤ ምስጋናው ወደ እርሱ በሚቀናው በእርሱ ዘንድ ነው። እምነት የእይታችንን አቅጣጫ መለወጥ ነው፤ ከራሳችን እይታ ትኵረት መውጣትና እግዚአብሔርን ወደ ትኵረት ማምጣት ነው። ኃጢአት እይታችንን ወደ ውስጥ አጣምሞ ራሱን የሚመለከት አደረገው። አለማመን እግዚአብሔር ሊኖርበት በሚገባው ስፍራ ራስን አስቀምጧል፤ «ዙፋኔን ከእግዚአብሔር ዙፋን በላይ ከፍ አደርጋለሁ» ካለው ከሉሲፈር ኃጢአት ጋር በአደገኛ ሁኔታ ይቀራረባል። እምነት ወደ ውስጥ ሳይሆን ወደ ውጭ ይመለከታል፤ ሕይወትም ሁሉ በሥርዓቱ ይቀናል።
ይህ ሁሉ እጅግ ቀላል ይመስል ይሆናል። እኛ ግን የምናቀርበው ይቅርታ የለንም። እርዳታን ፍለጋ ወደ ሰማይ ለመውጣት ወይም ወደ ጥልቁ ለመውረድ ለሚሹ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ «ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም … የእምነት ቃል ነው።» ቃሉ ዓይኖቻችንን ወደ ጌታ እንድናነሣ ያነሣሣናል፤ የተባረከው የእምነት ሥራም ይጀምራል።
ወደ እግዚአብሔር ለመመልከት ውስጣዊ ዓይኖቻችንን ስናነሣ፣ ወደ እኛ መልሰው የሚመለከቱ ወዳጃዊ ዓይኖችን ማግኘታችን አይቀርም፤ የእግዚአብሔር ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ወዲያና ወዲህ ይመለከታሉ ተብሎ ተጽፎአልና። የልምምድ ጣፋጭ ቋንቋ፦ «አንተ የምታየኝ አምላክ ነህ» የሚል ነው። ወደ ውጭ የሚመለከቱት የነፍስ ዓይኖች ወደ ውስጥ የሚመለከቱትን የእግዚአብሔር ዓይኖች ሲገናኙ፣ ሰማይ እዚሁ በዚህች ምድር ላይ ጀምሯል።
«ጥረቴ ሁሉ ወደ አንተ የዞረው ጥረትህ ሁሉ ወደ እኔ ስለ ዞረ ነው፤ በትኵረቴ ሁሉ ወደ አንተ ብቻ የምመለከተውና የአእምሮዬን ዓይኖች ከቶ ወደ ሌላ የማላዞረው አንተ በማያቋርጥ እይታህ ስለምታቅፈኝ ነው፤ ፍቅሬን ወደ አንተ ብቻ የማቀናው አንተ ራስህ ፍቅር የሆንህ ወደ እኔ ብቻ ራስህን ስላዞርህ ነው። ጌታ ሆይ፥ ደስ የሚያሰኘው ጣፋጭነትህ እጅግ በፍቅር የሚያቅፈኝ ያ እቅፍ ካልሆነ ሕይወቴ ምንድር ነው?» ይህን የጻፈው ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የነበረው የኩሳው ኒኮላስ ነው።
ስለዚህ የእግዚአብሔር ሽማግሌ ሰው ተጨማሪ ነገር ልናገር እወዳለሁ። ዛሬ በክርስቲያን አማኞች መካከል በየትም ስፍራ ብዙ አይታወቅም፤ በዘመናችን ፋንዳሜንታሊስቶች ዘንድ ደግሞ ፈጽሞ አይታወቅም። እንደ እርሱ ያለ መንፈሳዊ ጣዕም ካላቸው ሰዎችና ከሚወክሉት የክርስትና አስተሳሰብ ትምህርት ቤት ጋር ጥቂት ብንተዋወቅ ብዙ እናተርፋለን ብዬ አስባለሁ። የክርስትና ሥነ ጽሑፍ በዘመናችን የወንጌላውያን መሪዎች ዘንድ ተቀባይነትና ይሁንታ እንዲያገኝ፣ ያንኑ የአስተሳሰብ መስመር፣ ከእርሱ መውጣት ደኅንነት የሌለበትን አንድ ዓይነት «የፓርቲ መስመር» በቅርብ መከተል አለበት። በአሜሪካ ግማሽ ምዕተ ዓመት የቈየው ይህ ነገር በራሳችን የረካንና የተደላደልን አድርጎናል። እርስ በርሳችን በባርነት በሚመስል ታማኝነት እንኮራረጃለን፤ ከሁሉ የበረታ ጥረታችንም በዙሪያችን ያለ ሰው ሁሉ የሚናገረውን ያንኑ ነገር ለመናገር ለመሞከር ይውላል—ይሁን እንጂ ያንኑ ለመናገር ምክንያት ለማግኘት፣ በተፈቀደው ጭብጥ ላይ አንዲት ትንሽ ደኅንነቷ የተጠበቀ ልዩነት፣ ወይም ከዚህ ያልበለጠ ቢሆን ቢያንስ አዲስ ምሳሌ ለማግኘት ነው።
ኒኮላስ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ፣ የጌታ ወዳጅ፣ ለኢየሱስ አካል ባለው ፍቅር የሚያበራና የሚያንጸባርቅ ሰው ነበር። ሥነ መለኮቱ ትክክለኛ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ያለ ነገር ሁሉ ሊሆን እንደሚጠበቅበት መዓዛ ያለውና ጣፋጭ ነበር። ለምሳሌ ስለ ዘላለም ሕይወት ያለው አስተሳሰብ በራሱ ውብ ነው፤ ካልተሳሳትሁም ዛሬ በእኛ መካከል ካለው አስተሳሰብ ይልቅ በመንፈሱ ለዮሐንስ 17:3 የቀረበ ነው። ኒኮላስ እንዲህ ይላል፤ የዘላለም ሕይወት «አንተ እኔን፥ አዎን፥ የነፍሴን ስውር ስፍራዎች እንኳ ከቶ ሳታቋርጥ የምትመለከትበት ያ የተባረከ እይታ እንጂ ሌላ አይደለም። በአንተ ዘንድ መመልከት ሕይወትን መስጠት ነው፤ ያለማቋረጥ ከሁሉ የጣፈጠውን የአንተን ፍቅር ማካፈል ነው፤ ፍቅርን በማካፈል ለአንተ ፍቅር ልቤን ማንደድ ነው፤ በማንደድም መመገብ፥ በመመገብም ናፍቆቴን ማቀጣጠል፥ በማቀጣጠልም የደስታን ጠል ማጠጣት፥ በማጠጣትም የሕይወትን ምንጭ በውስጤ ማፍሰስ፥ በማፍሰስም እንዲበዛና እንዲጸና ማድረግ ነው።»
እንግዲህ እምነት ልብ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርገው እይታ ከሆነ፣ ይህ እይታም ሁሉን የሚያዩትን የእግዚአብሔርን ዓይኖች ለመገናኘት ውስጣዊ ዓይኖችን ማንሣት ብቻ ከሆነ፣ ሊደረጉ ከሚችሉ ነገሮች ሁሉ እጅግ ቀላል ከሆኑት አንዱ እንደ ሆነ ይከተላል። ከሁሉ የሚበልጠውን አስፈላጊ ነገር ቀላል ማድረጉና ከእኛ መካከል ለደካማውና ለድሀው በሚቻል ክልል ውስጥ ማኖሩ ለእግዚአብሔር የሚመስለው ነው።
ከዚህ ሁሉ አያሌ መደምደሚያዎችን በትክክል ማውጣት ይቻላል። ለምሳሌ ቀላልነቱ። ማመን መመልከት ስለ ሆነ ያለ ልዩ መሣሪያ ወይም ያለ ሃይማኖታዊ ቍሳቍስ ሊደረግ ይችላል። ያ አንድ የሕይወትና የሞት ጕዳይ የሆነው አስፈላጊ ነገር ለአጋጣሚ ተለዋዋጭነት ከቶ እንዳይገዛ እግዚአብሔር አረጋግጧል። መሣሪያ ሊበላሽ ወይም ሊጠፋ ይችላል፤ ውኃ ሊያፈስስ ይችላል፤ መዛግብት በእሳት ሊጠፉ ይችላሉ፤ አገልጋዩ ሊዘገይ ወይም ቤተ ክርስቲያኑ ሊቃጠል ይችላል። እነዚህ ሁሉ ከነፍስ ውጭ ያሉና ለአጋጣሚ ወይም ለመሣሪያ ብልሽት የተጋለጡ ናቸው፤ መመልከት ግን የልብ ነገር ነው፤ ማንም ሰው ቆሞም ሆነ ተንበርክኮ ወይም ከማናቸውም ቤተ ክርስቲያን አንድ ሺህ ማይል ርቆ በመጨረሻው ጣር ተኝቶ በስኬት ሊያደርገው ይችላል።
ማመን መመልከት ስለ ሆነ በማናቸውም ጊዜ ሊደረግ ይችላል። ለዚህ ከድርጊቶች ሁሉ ለሚጣፍጠው ድርጊት አንዱ ወቅት ከሌላው ወቅት አይበልጥም። እግዚአብሔር መዳንን በወር መባቻ ወይም በበዓል ወይም በሰንበት ላይ ከቶ አላስደገፈውም። ሰው በትንሣኤ እሑድ ለምሳሌ ከቅዳሜ ነሐሴ 3 ወይም ከሰኞ ጥቅምት 4 ይልቅ ወደ ክርስቶስ አይቀርብም። ክርስቶስ በአማላጅነቱ ዙፋን ላይ እስከ ተቀመጠ ድረስ እያንዳንዱ ቀን መልካም ቀን ነው፤ ቀኖችም ሁሉ የመዳን ቀኖች ናቸው።
በዚህ እግዚአብሔርን የማመን የተባረከ ሥራ ስፍራም ቢሆን ግድ አይሰጥም። ልብህን አንሣና በኢየሱስ ላይ እንዲያርፍ አድርግ፤ የባቡር መኝታ ክፍል ወይም ፋብሪካ ወይም ማድቤት ቢሆን እንኳ ወዲያውኑ በመቅደስ ውስጥ ነህ። አእምሮህ እርሱን ለመውደድና ለመታዘዝ የተዘጋጀ ከሆነ ከየትኛውም ስፍራ እግዚአብሔርን ልታይ ትችላለህ።
አሁን አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል፦ «ይህ የምትናገረው ነገር በጥሪያቸው ባሕርይ ለጸጥታ ማሰላሰል የሚያውሉት ብዙ ጊዜ ላላቸው እንደ መነኮሳት ወይም እንደ አገልጋዮች ላሉ ልዩ ሰዎች አይደለምን? እኔ ሥራ የበዛብኝ ሠራተኛ ነኝ፤ ብቻዬን የማሳልፈውም ጊዜ ጥቂት ነው።» የምገልጸው ሕይወት ጥሪያቸው ምንም ይሁን ምን ለእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ እንደ ሆነ ስናገር ደስ ይለኛል። በእርግጥም በየዕለቱ ብዙ ታታሪ ሠራተኞች በደስታ ይለማመዱታል፤ ከማንም አቅም በላይም አይደለም።
ብዙዎች የምናገርለትን ምሥጢር አግኝተዋል፤ በውስጣቸው ስለሚሆነው ነገር ብዙም ሳያስቡ ይህን በውስጥ ወደ እግዚአብሔር የመመልከት ልማድ ዘወትር ይለማመዳሉ። በልባቸው ውስጥ እግዚአብሔርን የሚያይ አንድ ነገር እንዳለ ያውቃሉ። በምድራዊ ጕዳዮች ለመሰማራት የንቃት ትኵረታቸውን ለማንሣት በሚገደዱበት ጊዜ እንኳ በውስጣቸው ሁልጊዜ የሚቀጥል ስውር ኅብረት አለ። ትኵረታቸው ከአስፈላጊ ሥራ ለአንድ አፍታ ብቻ ይለቀቅ እንጂ ወዲያውኑ እንደገና ወደ እግዚአብሔር ይበራል። ይህ የብዙ ክርስቲያኖች ምስክርነት ሆኖአል፤ እጅግ ብዙዎች ከመሆናቸው የተነሣ ይህን በዚህ መንገድ ስገልጸው እንኳ የሆነን ሰው የምጠቅስ ይመስለኛል፤ ከማን ወይም ከስንቶች እንደ ሆነ ግን ላውቅ ከቶ አልችልም።
የተለመዱት የጸጋ መንገዶች ዋጋ የላቸውም የሚል ስሜት ልተው አልፈልግም። በእርግጥ ዋጋ አላቸው። የግል ጸሎት በክርስቲያን ሁሉ ሊለማመድ ይገባዋል። ረጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ማሰላሰል ጊዜያት እይታችንን ያነጻሉ፥ ያቀኑታልም፤ በቤተ ክርስቲያን መገኘት አመለካከታችንን ያሰፋል፥ ለሌሎችም ያለንን ፍቅር ይጨምራል። አገልግሎትና ሥራ እንቅስቃሴም፤ ሁሉም መልካም ናቸው፤ ክርስቲያን ሁሉም ሊሰማራባቸው ይገባዋል። ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ሥር ትርጕም የሚሰጣቸው ውስጣዊው እግዚአብሔርን የመመልከት ልማድ ይሆናል። ውጫዊ ዓይኖቻችን የዚህን አላፊ ዓለም ትዕይንቶች እያዩ ሳሉ ወደ እግዚአብሔር እንድንመለከት የሚያስችሉን አዲስ ዓይኖች (እንዲህ ማለት ከተቻለ) በውስጣችን ይዳብራሉ።
አንድ ሰው የግል ሃይማኖትን ከልክ በላይ እያገዘፍን ነው፣ የአዲስ ኪዳን «እኛ» በራስ ወዳድ «እኔ» እየተተካ ነው ብሎ ይሰጋ ይሆናል። ሁሉም በአንድ መቃኛ የተቃኙ መቶ ፒያኖዎች በራሳቸው እርስ በርሳቸውም እንደሚቃኙ አስበህ ታውቃለህን? የሚስማሙት እርስ በርሳቸው በመቃኘት ሳይሆን እያንዳንዳቸው በግል ሊገዙለት ወደሚገባቸው ወደ ሌላ መሥፈርት በመቃኘት ነው። እንዲሁም በአንድነት የተሰበሰቡ መቶ አምላኪዎች እያንዳንዳቸው ወደ ክርስቶስ ቢመለከቱ፣ «የአንድነት» ንቃት አድሮባቸው የቀረበ ኅብረት ለማግኘት ለመጣጣር ዓይኖቻቸውን ከእግዚአብሔር ቢያዞሩ ሊሆኑ ከሚችሉት በላይ በልብ እርስ በርሳቸው ይቀራረባሉ። የግል ሃይማኖት ሲነጻ የማኅበር ሃይማኖት ፍጹም ይሆናል። ብልቶቹ ጤናማ በሆኑ መጠን አካሉ ይበረታል። እርሷን ያቀፉት ብልቶች የተሻለና ከፍ ያለ ሕይወት መፈለግ ሲጀምሩ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ሁሉ ትጠቀማለች።
ከላይ የተነገረው ሁሉ እውነተኛ ንስሐንና ሕይወትን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር መስጠትን አስቀድሞ ይጠይቃል። ይህን መጥቀስ እምብዛም አያስፈልግም፤ እንዲህ ያለውን ራስን መስጠት ያደረጉ ሰዎች ብቻ እስከዚህ ድረስ ያነባሉና።
በውስጥ ወደ እግዚአብሔር የመመልከት ልማድ በውስጣችን ሲጸና፣ ከእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎችና ከአዲስ ኪዳን መንፈስ ጋር ይበልጥ ወደሚስማማ አዲስ የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃ እንገባለን። እግራችን እዚህ በሰዎች መካከል በቀላሉ የግዴታ ዝቅተኛ መንገድ ላይ ሲራመድ እንኳ ሥላሴ አምላክ ማደሪያችን ይሆናል። በእርግጥም የሕይወትን ሱሙም ቦኑም—ከሁሉ የላቀውን መልካም ነገር—አግኝተናል። «ሊመኙት የሚቻል የደስታ ሁሉ ምንጭ በዚያ አለ፤ ከእርሱ የሚሻል በሰዎችና በመላእክት ሊታሰብ አይችልም ብቻ ሳይሆን፣ ከእርሱ የሚሻል በህልውና ሊኖር ከቶ አይችልም! እርሱ የአስተዋይ ምኞት ሁሉ ፍጹም ጣሪያ ነውና፤ ከእርሱም የሚበልጥ ሊኖር አይችልም።»
ጌታ ሆይ፥ ወደ አንተ እንድመለከትና እንድረካ የሚጋብዘኝን መልካም ቃል ሰምቻለሁ። ልቤ ምላሽ ለመስጠት ይናፍቃል፤ ነገር ግን አንተን በድንግዝግዝ ብቻ እስካይህ ድረስ ኃጢአት እይታዬን አጨልሞታል። በገዛ ክቡር ደምህ ታነጻኝና በውስጤ ንጹሕ ታደርገኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤ በምድራዊ ጕዞዬ ዘመን ሁሉ በተገለጡ ዓይኖች ወደ አንተ እመለከት ዘንድ። ከዚያም በቅዱሳንህ ልትከበር በሚያምኑትም ሁሉ ልትደነቅ በምትገለጥበት ቀን አንተን በፍጹም ክብርህ ለማየት የተዘጋጀሁ እሆናለሁ። አሜን።