ምዕራፍ 8 · 9 ደቂቃ ንባብ · 11 ደቂቃ ማዳመጥ
የሚናገረው ድምፅ
በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።—ዮሐንስ 1:1
የክርስትናን እውነቶች ያልተማረ አስተዋይ ተራ ሰው ይህን ጥቅስ ቢያገኝ፣ ዮሐንስ ሊያስተምር የፈለገው መናገርና አሳቡን ለሌሎች ማካፈል የእግዚአብሔር ባሕርይ እንደ ሆነ ነው ብሎ ሳይደመድም አይቀርም። ትክክልም ይሆናል። ቃል አሳብ የሚገለጥበት መንገድ ነው፤ ይህም ስያሜ ለዘላለማዊው ወልድ መሰጠቱ ራስን መግለጥ በመለኮት ውስጥ ያለ ባሕርይ እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔርም ራሱን ለፍጥረቱ ለመናገር ዘወትር እንደሚሻ እንድናምን ይመራናል። መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ ይህን አሳብ ይደግፋል። እግዚአብሔር እየተናገረ ነው። እግዚአብሔር ተናገረ አይደለም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር እየተናገረ ነው። በባሕርዩ ያለማቋረጥ የሚናገር አምላክ ነው። ዓለምን በሚናገረው ድምፁ ይሞላል።
ልንጋፈጣቸው ከሚገቡን ታላላቅ እውነታዎች አንዱ እግዚአብሔር በዓለሙ ውስጥ የሚያሰማው ድምፅ ነው። እጅግ አጭሩና ብቸኛው አጥጋቢ የዓለም አፈጣጠር ትምህርት ይህ ነው፦ «እርሱ ተናገረ፥ ሆኑም።» የተፈጥሮ ሕግ ለምን እንዳለ መልሱ በፍጥረቱ ውስጥ የሚኖረው ሕያው የእግዚአብሔር ድምፅ ነው። ዓለማትን ሁሉ ወደ መኖር ያመጣው ይህ የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ነው ተብሎ ሊታሰብ አይችልም፤ የተጻፈ ወይም የታተመ ቃል ከቶ አይደለምና፤ ይልቁንም በነገሮች ሁሉ መዋቅር ውስጥ የተነገረ የእግዚአብሔር ፈቃድ መግለጫ ነው። ይህ የእግዚአብሔር ቃል ዓለምን በሕያው አቅም የሚሞላ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ነው። የእግዚአብሔር ድምፅ በተፈጥሮ ውስጥ ካሉ ኃይሎች ሁሉ እጅግ የበረታ ነው፤ እንዲያውም በተፈጥሮ ውስጥ ያለ ብቸኛው ኃይል ነው፤ ጉልበት ሁሉ በዚህ ያለው በኃይል የተሞላው ቃል እየተነገረ ስለ ሆነ ብቻ ነውና።
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ የተጻፈ ስለ ሆነም በቀለም፣ በወረቀትና በቆዳ ግዴታዎች የታጠረና የተወሰነ ነው። የእግዚአብሔር ድምፅ ግን ሉዓላዊው አምላክ ነጻ እንደ ሆነ ሕያውና ነጻ ነው። «እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።» ሕይወቱ በሚነገሩት ቃላት ውስጥ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው የእግዚአብሔር ቃል ኃይል ሊኖረው የሚችለው በዓለማት ውስጥ ካለው የእግዚአብሔር ቃል ጋር ስለሚስማማ ብቻ ነው። የተጻፈውን ቃል ሁሉን የሚችል የሚያደርገው አሁን የሚናገረው ድምፅ ነው። አለዚያ በመጽሐፍ ሽፋኖች መካከል ተቈልፎ በእንቅልፍ ተኝቶ በቀረ ነበር።
እግዚአብሔር በፍጥረት ጊዜ ከነገሮች ጋር በአካል ተገናኝቶ፣ እንደ አናጢ እየቀረጸ፣ እያገጣጠመና እየገነባ እንደ ሠራ አድርገን ስናስብ ዝቅተኛና ኋላቀር አመለካከት እንይዛለን። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሌላ ያስተምራል፦ «በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ።… እርሱ ተናገረ፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም።» «ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ… በእምነት እናስተውላለን።» ደግሞም እግዚአብሔር እዚህ የሚያመለክተው የተጻፈውን ቃሉን ሳይሆን የሚናገረውን ድምፁን እንደ ሆነ ማስታወስ አለብን። የታሰበው ዓለምን የሚሞላው ድምፁ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስን በማይቈጠሩ ምዕተ ዓመታት የሚቀድመው ያ ድምፅ፣ ከፍጥረት ንጋት ጀምሮ ዝም ያላለው፣ ነገር ግን አሁንም እስከ ዓለማት ሩቅ ዳርቻ ድረስ የሚያስተጋባው ያ ድምፅ።
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው። በመጀመሪያ ምንም ላልነበረው ተናገረ፤ እርሱም አንዳች ነገር ሆነ። ትርምስ ሰማው፤ ሥርዓትም ሆነ፤ ጨለማ ሰማው፤ ብርሃንም ሆነ። «እግዚአብሔርም አለ — እንዲሁም ሆነ።» እነዚህ መንታ ሐረጎች እንደ ምክንያትና ውጤት በዘፍጥረት የፍጥረት ታሪክ ውስጥ ሁሉ ይደጋገማሉ። አለ የሚለው ሆነ ለሚለው ምክንያት ነው። ሆነ የሚለው ወደ ቀጣይ የአሁን ጊዜ የተሸጋገረው አለ ነው።
እግዚአብሔር በዚህ እንዳለና እየተናገረ እንደ ሆነ — እነዚህ እውነቶች ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ሁሉ በስተጀርባ ናቸው፤ ያለ እነርሱ መገለጥ ከቶ ሊኖር አይችልም ነበር። እግዚአብሔር መጽሐፍ ጽፎ፣ ያለ ረዳት የተተዉ አእምሮዎች ከሩቅ እንዲያነቡት በመልእክተኛ አልላከውም። መጽሐፍን ተናገረ፤ በተናገራቸውም ቃላት ውስጥ ይኖራል፤ ቃላቱን ዘወትር እየተናገረ ኃይላቸው በዘመናት ሁሉ ጸንቶ እንዲኖር ያደርጋል። እግዚአብሔር በጭቃ ላይ እፍ አለ፤ ሰውም ሆነ፤ በሰዎች ላይ እፍ ይላል፤ ጭቃም ይሆናሉ። «የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ» የሚለው በውድቀት ጊዜ የተነገረ፣ እግዚአብሔር የሰውን ሁሉ ሞት የወሰነበት ቃል ነበር፤ ሌላም ተጨማሪ ቃል መናገር አላስፈለገውም። ከልደት እስከ መቃብር በምድር ፊት ላይ የሚያልፈው ያ አሳዛኝ የሰው ልጆች ሰልፍ የመጀመሪያው ቃሉ በቂ እንደ ነበረ ማስረጃ ነው።
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ላለው ለዚያ ጥልቅ ንግግር በቂ ትኩረት አልሰጠንም፦ «ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።» ሥርዓተ ነጥቡን እንደ ፈለግን ብናዘዋውረውም እውነቱ አሁንም በዚያው አለ፤ የእግዚአብሔር ቃል በነፍስ ውስጥ እንዳለ ብርሃን የሰዎችን ሁሉ ልብ ይነካል። በሰዎች ሁሉ ልብ ውስጥ ብርሃኑ ያበራል፣ ቃሉ ያስተጋባል፤ ከእነርሱም ማምለጫ የለም። እግዚአብሔር ሕያው ከሆነና በዓለሙ ውስጥ ካለ፣ እንዲህ ያለ ነገር የግድ መሆን አለበት። ዮሐንስም እንዲሁ እንደ ሆነ ይናገራል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከቶ ሰምተው የማያውቁ ሰዎች እንኳ ከልባቸው የሚያመካኙትን ሁሉ ለዘላለም ለማስወገድ በሚበቃ ግልጽነት ተሰብኮላቸዋል። «እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።» «ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የማይታየው ባሕርዩ፥ እርሱም የዘላለም ኃይሉና አምላክነቱ፥ ከተፈጠረው ነገር ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም የሚያመካኙት አጡ።»
ይህ ሁለንተናዊ የእግዚአብሔር ድምፅ በጥንቶቹ ዕብራውያን ዘንድ ብዙ ጊዜ ጥበብ ተብሎ ይጠራ ነበር፤ ከሰው ልጆችም ምላሽ ፈልጎ በምድር ሁሉ ላይ በየስፍራው እያስተጋባና እየመረመረ እንዳለ ይነገርለት ነበር። የምሳሌ መጽሐፍ ስምንተኛው ምዕራፍ እንዲህ ብሎ ይጀምራል፦ «ጥበብ አትጮኽምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን አትሰጥምን?» ጸሐፊው ቀጥሎ ጥበብን «በከፍታዎች ራስ ላይ፥ በመንገድ አጠገብ፥ በጎዳናዎች መካከል» እንደ ቆመች ውብ ሴት አድርጎ ይስላታል። ማንም መስማት እንዳያመልጠው ከየአቅጣጫው ድምፅዋን ታሰማለች። «ሰዎች ሆይ፥ እናንተን እጠራለሁ፤ ድምፄም ወደ ሰው ልጆች ነው።» ከዚያም አላዋቂዎችና ሰነፎች ቃልዋን ያደምጡ ዘንድ ትማጸናለች። ይህች የእግዚአብሔር ጥበብ የምትማጸነው ለመንፈሳዊ ምላሽ ነው፤ ሁልጊዜ የፈለገችው፣ ነገር ግን እምብዛም ልታገኘው የማትችለው ምላሽ። አሳዛኙ ነገር ዘላለማዊ ደኅንነታችን በመስማታችን ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው፤ እኛ ግን ጆሮዎቻችን እንዳይሰሙ አሠልጥነናቸዋል።
ይህ ሁለንተናዊ ድምፅ ዘወትር ሲያስተጋባ ኖሯል፤ ሰዎችም የፍርሃታቸውን ምንጭ ባላስተዋሉ ጊዜ እንኳ ብዙ ጊዜ አውኳቸዋል። በሰዎች ልብ ላይ እንደ ሕያው ጉም የሚንጠባጠበው ይህ ድምፅ፣ የታሪክ መዝገብ ከተጀመረበት ንጋት ጀምሮ ሚሊዮኖች የመሰከሩለት የሕሊና መታወክና ዘላለማዊነትን የመናፈቅ ያልታወቀ ምክንያት ሆኖ ይሆንን? ይህን ለመጋፈጥ መፍራት አያስፈልገንም። የሚናገረው ድምፅ እውነታ ነው። ሰዎች ለእርሱ እንዴት ምላሽ እንደ ሰጡ ማንኛውም ተመልካች ሊያስተውለው ይችላል።
እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ለጌታችን በተናገረ ጊዜ፣ የሰሙት ራሳቸውን ማእከል ያደረጉ ሰዎች ነገሩን በተፈጥሮ ምክንያቶች አስረዱት፤ «ነጐድጓድ ነው» አሉ። ድምፁን በተፈጥሮ ሕግ የማስረዳት ይህ ልማድ የዘመናዊ ሳይንስ ሥር መሠረት ነው። ሕያውና እስትንፋስ ባለው ዓለም ውስጥ ለማንም አእምሮ ሊገባ የማይችል፣ እጅግ ድንቅና እጅግ የሚያስፈራ ምሥጢራዊ አንዳች ነገር አለ። የሚያምን ሰው አስተውላለሁ ብሎ አይመካም። በጉልበቱ ተንበርክኮ «እግዚአብሔር» ብሎ ያንሾካሹካል። የምድር ሰውም ይንበረከካል፤ ነገር ግን ለማምለክ አይደለም። የሚንበረከከው ለመመርመር፣ ለመፈለግ፣ የነገሮችን ምክንያትና አሠራር ለማግኘት ነው። በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው በዓለማዊ ዘመን ውስጥ ነው። የአስተሳሰብ ልማዳችን የሳይንቲስቱ እንጂ የሚያመልከው ሰው አይደለም። ከመስገድ ይልቅ ለማስረዳት እናዘነብላለን። «ነጐድጓድ ነው» ብለን እንናገራለን፤ ምድራዊ መንገዳችንንም እንሄዳለን። ድምፁ ግን አሁንም ያስተጋባል፤ ይመረምራልም። የዓለም ሥርዓትና ሕይወት በዚያ ድምፅ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ ሰዎች ግን ትኩረት ለመስጠት አብዛኛውን ጊዜ እጅግ የተጠመዱ ወይም እጅግ ግትሮች ናቸው።
እያንዳንዳችን ልናስረዳቸው ያልቻልናቸው ገጠመኞች አጋጥመውናል፤ ድንገተኛ የብቸኝነት ስሜት፣ ወይም በሁለንተናው ስፋት ፊት የመደነቅና የመፍራት ስሜት። ወይም ከሌላ ፀሐይ እንደ ወጣ ብርሃን ያለ አላፊ የብርሃን ጉብኝት ደርሶብን፣ ከሌላ ዓለም እንደ ሆንን፣ መገኛችንም መለኮታዊ እንደ ሆነ በቅጽበት ብልጭታ አረጋግጦልናል። በዚያ ያየነው፣ የተሰማን ወይም የሰማነው በትምህርት ቤቶች ከተማርነው ሁሉ ጋር የሚቃረን፣ ከቀድሞ እምነቶቻችንና አስተያየቶቻችን ሁሉ ጋርም እጅግ የሚለያይ ሊሆን ይችላል። ለአንድ አፍታ ደመናዎቹ ተጠቅልለው ሲነሡና እኛ ራሳችን ስናይና ስንሰማ፣ ያካበትናቸውን ጥርጣሬዎች ለጊዜው ለማቆም ተገደድን። እንዲህ ያሉትን ነገሮች እንደ ፈለግን እናስረዳቸው፤ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ገጠመኞች በዓለም ውስጥ ካለው ከእግዚአብሔር ሀልዎትና ከሰው ልጆች ጋር ለመነጋገር ከሚያደርገው የማያቋርጥ ጥረት ሊመነጩ እንደሚችሉ ቢያንስ ዕድሉን እስክንቀበል ድረስ ለእውነታዎቹ ፍትሕ አልሰጠንም ብዬ አስባለሁ። እንዲህ ያለውን መላምት በቀላል ልብ አናጣጥለው።
የራሴ እምነት ይህ ነው (በዚህም ማንም ባይከተለኝ አይከፋኝም)፦ ሰው በዓለም ያስገኘው መልካምና ውብ ነገር ሁሉ በምድር ላይ ለሚያስተጋባው ለፈጣሪው ድምፅ በኃጢአት የታገደና ጉድለት ያለበት ምላሹ ውጤት ነው። ከፍ ያለውን የበጎነት ሕልማቸውን ያለሙት የሥነ ምግባር ፈላስፎች፣ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ዘላለማዊነት ያሰላሰሉት የሃይማኖት አሳቢዎች፣ ከተራ ነገሮች ንጹሕና ዘላቂ ውበትን የፈጠሩት ባለ ቅኔዎችና ሠዓሊዎች — እነዚህን እንዴት እናስረዳቸዋለን? «ልዩ ተሰጥኦ ነበር» ብሎ በቀላሉ መናገር አይበቃም። ታዲያ ልዩ ተሰጥኦ ምንድር ነው? ልዩ ተሰጥኦ ያለው ሰው በሚናገረው ድምፅ የተወረሰ፣ በደብዛዛ ብቻ የሚያስተውላቸውን ግቦች ለማሳካት እንደ ተያዘ ሰው የሚደክምና የሚታገል ሰው ሆኖ ይሆንን? ታላቁ ሰው በድካሙ ውስጥ እግዚአብሔርን ሊስት መቻሉ፣ እንዲያውም በእግዚአብሔር ላይ ተናግሮ ወይም ጽፎ ሊሆን መቻሉ የማቀርበውን አሳብ አያፈርሰውም። በቅዱሳት መጻሕፍት ያለው የእግዚአብሔር የቤዛነት መገለጥ ለሚያድን እምነትና ከእግዚአብሔር ጋር ለሚገኝ ሰላም አስፈላጊ ነው። ወደ ዘላለማዊነት የሚገፋፉት ደብዛዛ መነሣሣቶች ከእግዚአብሔር ጋር ወደሚያሳርፍና ወደሚያረካ ኅብረት እንዲያደርሱን ከሞት በተነሣው አዳኝ ማመን አስፈላጊ ነው። ለእኔ ይህ ከክርስቶስ ውጭ ለሚገኘው ለበጎው ነገር ሁሉ ተቀባይነት ያለው ማብራሪያ ነው። ነገር ግን የእኔን አሳብ ሳትቀበል መልካም ክርስቲያን መሆን ትችላለህ።
የእግዚአብሔር ድምፅ ወዳጃዊ ድምፅ ነው። ቀድሞውኑ ሊቃወመው ቈርጦ ካልተነሣ በቀር ማንም ሊሰማው መፍራት አያስፈልገውም። የኢየሱስ ደም የሰውን ዘር ብቻ ሳይሆን ፍጥረትን ሁሉ ደግሞ ሸፍኖአል። «በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ፥ በምድር ያሉትን ቢሆን በሰማያትም ያሉትን ቢሆን፥ ሁሉን በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር ሊያስታርቅ ፈቅዶአልና።» ወዳጃዊ ሰማይን ያለ ስጋት መስበክ እንችላለን። ምድር ብቻ ሳትሆን ሰማያትም በቍጥቋጦው ውስጥ በተገለጠው በእርሱ በጎ ፈቃድ ተሞልተዋል። ፍጹሙ የማስተስረያ ደም ይህን ለዘላለም ያጸናል።
የሚያደምጥ ሁሉ የሚናገረውን ሰማይ ይሰማል። ይህ ሰዎች አድምጡ የሚለውን ምክር በደስታ የሚቀበሉበት ሰዓት በእርግጥ አይደለም፤ ማድመጥ ዛሬ የሕዝቡ ተወዳጅ ሃይማኖት ክፍል አይደለምና። ከዚያ እጅግ ተቃራኒ በሆነው ዋልታ ላይ ነን። ሃይማኖት ጫጫታ፣ ብዛት፣ እንቅስቃሴና ጕራ ሰውን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ያደርጉታል የሚለውን አስከፊ ኑፋቄ ተቀብሎአል። ነገር ግን ልንጽናና እንችላለን። በመጨረሻው ታላቅ ግጭት ማዕበል ለተያዘ ሕዝብ እግዚአብሔር፦ «ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ» ይላል፤ ብርታታችንና ደኅንነታችን በጫጫታ ሳይሆን በጸጥታ እንደ ሆነ ሊነግረን የፈለገ ይመስል አሁንም ይህን ይላል።
እግዚአብሔርን ለመጠበቅ ጸጥ ማለታችን አስፈላጊ ነው። ብቻችንን መሆናችንም፣ ቢቻልም መጽሐፍ ቅዱሳችንን በፊታችን ዘርግተን መሆናችን የተሻለ ነው። ከዚያም ከፈቀድን ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብና በልባችን ሲናገረን መስማት ልንጀምር እንችላለን። ለአብዛኛው ሰው ሂደቱ እንዲህ ያለ ይመስለኛል፦ በመጀመሪያ በገነት ውስጥ የሚመላለስ ሀልዎት የሚመስል ድምፅ። ከዚያም የሚናገር ድምፅ፣ ይበልጥ የሚገባ ነገር ግን ገና ግልጽ ያልሆነ። ከዚያም መንፈስ ቅዱስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማብራት የሚጀምርበት ያ አስደሳች ጊዜ ይመጣል፤ ቀድሞ ድምፅ ብቻ፣ ወይም ቢበዛ የሚናገር ድምፅ የነበረው አሁን የሚገባ ቃል ይሆናል፤ እንደ ውድ ወዳጅ ቃል የሞቀ፣ የቀረበና ግልጽ ቃል። ከዚያም ሕይወትና ብርሃን ይመጣሉ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝና ጌታ፣ ሁሉም ነገር አድርጎ የማየት፣ በእርሱም የማረፍና እርሱን የማቀፍ ችሎታ ይመጣል።
እግዚአብሔር በዓለሙ ውስጥ የሚናገር አምላክ መሆኑን እስክናምን ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ለእኛ ሕያው መጽሐፍ ከቶ አይሆንም። ከሞተና ግላዊ ካልሆነ ዓለም ወደ ቀኖናዊ መጽሐፍ ቅዱስ መዝለል ለአብዛኞቹ ሰዎች ከአቅም በላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የእግዚአብሔር ቃል አድርገው መቀበል እንደሚገባቸው ሊያምኑ፣ እንደዚያም አድርገው ሊያስቡት ሊሞክሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን በገጹ ላይ ያሉት ቃላት በእርግጥ ለእነርሱ እንደ ሆኑ ማመን አይቻላቸውም። ሰው «እነዚህ ቃላት ለእኔ የተነገሩ ናቸው» ብሎ ሊናገር ይችላል፤ በልቡ ግን እንደዚያ እንደ ሆኑ አይሰማውም፣ አያውቅምም። የተከፋፈለ ሥነ ልቡና ሰለባ ነው። እግዚአብሔርን በሌላ ስፍራ ሁሉ ዲዳ፣ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ተናጋሪ አድርጎ ሊያስበው ይሞክራል።
ብዙው ሃይማኖታዊ አለማመናችን ስለ እውነት መጻሕፍት በያዝነው የተሳሳተ አመለካከትና የተሳሳተ ስሜት ምክንያት እንደ ሆነ አምናለሁ። ዝም ያለ አምላክ በድንገት በመጽሐፍ ውስጥ መናገር ጀመረ፤ መጽሐፉም ሲፈጸም ዳግመኛ ለዘላለም ወደ ዝምታ ተመለሰ። አሁን መጽሐፉን የምናነበው እግዚአብሔር ለአጭር ጊዜ የመናገር ስሜት በያዘው ጊዜ የተናገረውን እንደሚመዘግብ ሰነድ አድርገን ነው። እንዲህ ያለ አሳብ በአእምሯችን ይዘን እንዴት ልናምን እንችላለን? እውነታው ግን እግዚአብሔር ዝም ያለ አለመሆኑ፣ ከቶም ዝም ብሎ አለማወቁ ነው። መናገር የእግዚአብሔር ባሕርይ ነው። የቅድስት ሥላሴ ሁለተኛው አካል ቃል ተብሎ ይጠራል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር የማያቋርጥ ንግግር የማይቀር ፍሬ ነው። በምናውቃቸው በሰው ቃላት የተቀመጠ፣ ለእኛ ያለው የአሳቡ የማይሳሳት መግለጫ ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳችንን አንድ ጊዜ የተነገረ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን አሁን የሚናገር መጽሐፍ እንደ ሆነ በማሰብ ስንቀርበው፣ ከሃይማኖታዊው ጭጋግ ውስጥ አዲስ ዓለም እንደሚወጣ አስባለሁ። ነቢያት ዘወትር «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» ይሉ ነበር። ሰሚዎቻቸው የእግዚአብሔር ንግግር በቀጣይ የአሁን ጊዜ ውስጥ እንዳለ እንዲያስተውሉ ፈልገው ነበር። በአንድ ወቅት አንድ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ተነገረ ለማመልከት ኃላፊ ጊዜን በትክክል ልንጠቀም እንችላለን፤ ነገር ግን አንድ ጊዜ የተወለደ ልጅ በሕይወት መኖሩን እንደሚቀጥል፣ ወይም አንድ ጊዜ የተፈጠረ ዓለም መኖሩን እንደሚቀጥል፣ አንድ ጊዜ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል መነገሩን ይቀጥላል። እነዚህም ፍጹም ያልሆኑ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው፤ ልጆች ይሞታሉና፣ ዓለማትም ነድደው ያልቃሉና፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
እግዚአብሔርን ለማወቅ ልትከተል ብትወድድ፣ ይናገርሃል ብለህ እየጠበቅህ ወዲያውኑ ወደ ተከፈተው መጽሐፍ ቅዱስ ና። እንደ ፈለግህ ልታንቀሳቅሰው የምትችል ዕቃ ነው በሚል አሳብ አትምጣ። ከዕቃ በላይ ነው፤ ድምፅ ነው፣ ቃል ነው፣ የሕያው እግዚአብሔር ራሱ ቃል ነው።
ጌታ ሆይ፥ ማድመጥን አስተምረኝ። ዘመኑ ጫጫታ የበዛበት ነው፤ ጆሮዎቼም ያለማቋረጥ በሚያጠቁአቸው በሺህ በሚቈጠሩ ሻካራ ድምፆች ደክመዋል። ብላቴናው ሳሙኤል፦ «ተናገር፥ ባሪያህ ይሰማልና» ባለህ ጊዜ የነበረውን መንፈስ ስጠኝ። በልቤ ውስጥ ስትናገር ልስማህ። የምድር ድምፆች ጠፍተው ብቸኛው ድምፅ የሚናገረው ድምፅህ ዜማ በሚሆንበት ጊዜ ቃናው የተለመደ ይሆንልኝ ዘንድ፣ የድምፅህን ቃና ልላመድ። አሜን።