ምዕራፍ 2 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
መቅድም
ጨለማ ሁሉን ሊውጥ ጥቂት በቀረበት በዚህ ሰዓት አንድ የሚያበረታታ ጭላንጭል ይታያል፤ በወግ አጥባቂው ክርስትና በረት ውስጥ ሃይማኖታዊ ሕይወታቸው ለእግዚአብሔር ለራሱ እያደገ በሚሄድ ረሀብ የሚታወቅ ሰዎች ቍጥራቸው እየበዛ ይገኛል። መንፈሳዊ እውነታዎችን ይናፍቃሉ፤ በቃላት አይሸነገሉም፤ ትክክለኛ በሆኑ የእውነት «ትርጓሜዎች»ም አይረኩም። እግዚአብሔርን ተጠምተዋል፤ ከሕያው ውኃ ምንጭ ጠልቀው እስኪጠጡም ድረስ አይጠግቡም።
በሃይማኖታዊው አድማስ ላይ በየትም ስፍራ ላስተውለው የቻልሁት ብቸኛው እውነተኛ የመነቃቃት ምልክት ይህ ነው። ምናልባት በዚህም በዚያም ያሉ ጥቂት ቅዱሳን ሲጠባበቋት የነበረችው የሰው እጅ የምታህል ደመና ይህች ትሆናለች። ለብዙ ነፍሳት የሕይወት ትንሣኤ ሊያስገኝ፣ በክርስቶስ ከማመን ጋር አብሮ ሊሄድ የሚገባውን ያን ብሩህ መደነቅ—በዘመናችን ከእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ከሞላ ጎደል የሸሸውን ያን መደነቅ—መልሶ ሊያስገኝ ይችላል።
ነገር ግን ይህ ረሀብ በሃይማኖት መሪዎቻችን ዘንድ ሊታወቅ ይገባዋል። የዘመኑ ወንጌላዊነት (ምሳሌውን ልቀይርና) መሠዊያውን አዘጋጅቶ መሥዋዕቱን በየብልቱ ከፋፍሎታል፤ አሁን ግን በከፍተኛው ቀርሜሎስ አናት ላይ የእሳት ምልክት እንኳ አለመኖሩ ቅንጣት ሳያሳስበው ድንጋዮቹን በመቍጠርና ብልቶቹን እንደ ገና በማስተካከል የረካ ይመስላል። ነገር ግን የሚያሳስባቸው ጥቂቶች ስላሉ እግዚአብሔር ይመስገን። እነርሱም መሠዊያውን እየወደዱና በመሥዋዕቱም ደስ እያላቸው፣ የእሳቱ ቀጣይ አለመኖር ግን ሊዋጥላቸው የማይችል ሰዎች ናቸው። ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን ይሻሉ። ቅዱሳን ነቢያት ሁሉ ስለ እርሱ የጻፉትንና መዝሙረኞችም የዘመሩለትን የክርስቶስን ፍቅር «ሰርስሮ የሚገባ ጣፋጭነት» ለራሳቸው ሊቀምሱ ተጠምተዋል።
ዛሬ የክርስቶስን ትምህርት መሠረታውያን ሐሳቦች በትክክል የሚያቀርቡ የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን እጥረት የለም፤ ነገር ግን ከእነዚህ ብዙዎቹ በአገልግሎታቸው ውስጥ የተገለጠ ሀልዎት፣ በግል ሕይወታቸውም ውስጥ የተለየ ምንም ነገር አለመኖሩን በሚገርም ሁኔታ ሳያውቁ፣ የእምነትን መሠረታውያን ትምህርቶች ዓመት ከዓመት በማስተማር የረኩ ይመስላሉ። ትምህርታቸው ፈጽሞ ሊያረካው የማይችለው ናፍቆት በደረታቸው ውስጥ ለሚሰማቸው አማኞች ዘወትር ያገለግላሉ።
በፍቅር እንደምናገር ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በመድረኮቻችን ያለው ጕድለት እውነተኛ ነው። የሚልተን አስፈሪ ዓረፍተ ነገር ለእርሱ ዘመን እንደ ተስማማ ሁሉ ለዘመናችንም ልክ ይስማማል፦ «የተራቡት በጎች ቀና ብለው ይመለከታሉ፤ ግን አይመገቡም።» የእግዚአብሔር ልጆች በአብ ማዕድ ላይ ተቀምጠው ሳሉ በረሀብ ሲሠቃዩ ማየት ከባድ ነገር ነው፤ በመንግሥቱም ውስጥ ትንሽ ቅሌት አይደለም። የዌስሊ ቃላት እውነትነት በዓይናችን ፊት ተረጋግጧል፦ «ኦርቶዶክሳዊነት፣ ማለትም ትክክለኛ አስተያየት፣ ቢበዛ የሃይማኖት እጅግ ቀጭን ክፍል ነው። ትክክለኛ ዝንባሌዎች ያለ ትክክለኛ አስተያየቶች ሊኖሩ ባይችሉም፣ ትክክለኛ አስተያየቶች ግን ያለ ትክክለኛ ዝንባሌዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ፍቅርም ሆነ ወደ እርሱ ያዘነበለ አንድም ትክክለኛ ዝንባሌ ሳይኖር ስለ እግዚአብሔር ትክክለኛ አስተያየት ሊኖር ይችላል። ለዚህ ሰይጣን ማስረጃ ነው።»
ቃሉን ለማሰራጨት ለሚሠሩት ግሩማን የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራትና ለሌሎች ውጤታማ ድርጅቶች ምስጋና ይግባቸውና፣ ዛሬ «ትክክለኛ አስተያየቶች» ያላቸው ብዙ ሚሊዮን ሰዎች አሉ፤ ምናልባትም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ። ያም ሆኖ እውነተኛ መንፈሳዊ አምልኮ ከዚህ ይበልጥ ያሽቆለቆለበት ጊዜ ኖሮ ያውቅ ይሆን ብዬ እጠይቃለሁ። በብዙ የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች የአምልኮ ጥበብ ፈጽሞ ጠፍቷል፤ በስፍራውም «ፕሮግራም» የተባለው ያ እንግዳና ባዕድ ነገር ገብቷል። ይህ ቃል ከቴአትር መድረክ ተውሶ በመካከላችን አሁን አምልኮ ተብሎ ለሚታለፈው የሕዝብ አገልግሎት ዓይነት በሚያሳዝን ብልሃት ተሰጥቷል።
ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ በሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊቀር የማይችል ግዴታ ነው። ያለ እርሱ ማንኛውም ቤተ ክርስቲያን በቃሉ ጥብቅ ትርጕም የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ማብራሪያ ሰሚዎቹን አንዳችም እውነተኛ መንፈሳዊ ምግብ እንዳያገኙ በሚያደርግ መንገድ ሊካሄድ ይችላል። ነፍስን የሚመግበው እግዚአብሔር ራሱ እንጂ ተራ ቃላት አይደሉምና፤ ሰሚዎቹ እግዚአብሔርን በግል ተሞክሮ ካላገኙትና እስኪያገኙትም ድረስ እውነትን በመስማታቸው የተሻሉ አይሆኑም። መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ግብ አይደለም፤ ይልቁንም ሰዎችን ወደ ቅርብና አርኪ የእግዚአብሔር እውቀት የሚያደርስ መንገድ ነው፤ ይኸውም ወደ እርሱ እንዲገቡ፣ በሀልዎቱ ደስ እንዲላቸው፣ የእግዚአብሔርን የራሱን ውስጣዊ ጣፋጭነት በልባቸው እምብርትና ማዕከል እንዲቀምሱና እንዲያውቁ ነው።
ይህ መጽሐፍ የተራቡት የእግዚአብሔር ልጆች በዚህ መንገድ እንዲያገኙት ለመርዳት የቀረበ ትሑት ሙከራ ነው። ልቤ ራሱ እጅግ ደስ የሚያሰኙና ለእኔም ድንቅ የሆኑ መንፈሳዊ እውነታዎችን ያገኘበት ግኝት ከመሆኑ በቀር እዚህ አዲስ ነገር የለም። ከእኔ በፊት የነበሩ ሌሎች ወደ እነዚህ ቅዱሳት ምሥጢራት ከእኔ እጅግ አርቀው ገብተዋል፤ ነገር ግን እሳቴ ትልቅ ባይሆንም እውነተኛ ነው፤ ሻማቸውን በነበልባሉ የሚያበሩ ሰዎችም ይኖሩ ይሆናል።
ኤ. ደብሊው. ቶዘር
ቺካጎ፣ ኢሊኖይ
ጁን 16፣ 1948