እግዚአብሔርን ፍለጋ
መግቢያ

ምዕራፍ 1 · 1 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

መግቢያ

ይህ እግዚአብሔርን በተጠማ ልብ የተዘጋጀ፣ ስለ ውስጣዊው ሕይወት የቀረበ ድንቅ ጥናት ነው፤ ይህ ልብ ቢያንስ የመንገዶቹን ዳርቻ፣ ለኃጢአተኞች ያለውን የፍቅሩን ጥልቅ ባሕር፣ የማይቀረብ ግርማውንም ከፍታ ለመጨበጥ የሚጓጓ ነው—ደግሞም የጻፈው በቺካጎ የሚኖር አንድ ሥራ የበዛበት መጋቢ ነው!

ዳዊት ሃያ ሦስተኛውን መዝሙር በሳውዝ ሆልስተድ ጎዳና ላይ ሲጽፍ፣ ወይም የመካከለኛው ዘመን አንድ ምሥጢራዊ ሰው በአንድ የእንጨት ቤት ሁለተኛ ፎቅ ላይ ባለች ትንሽ የጥናት ክፍል ውስጥ መነሣሣትን ሲያገኝ ማን ሊያስብ ይችላል? ያውም ማለቂያ የሌላቸው ጎዳናዎች እንደ ዳማ ሰሌዳ በተሳሰሩበት በዚያ ሰፊና ጠፍጣፋ ከተማ፣

የሕይወት የተጨናነቁ መንገዶች በሚገናኙበት፣
የዘርና የጐሣ ጩኸት በሚሰማበት፣
በጐስቋላነትና በችጋር መናኸሪያዎች፣
በፍርሃት በጨለመ፣ ጥላ ባጠላበት ደጃፍ፣
የስግብግብነት ወጥመዶች በተሸሸጉባቸው መንገዶች …

ነገር ግን የኒው ዮርኩ ዶክተር ፍራንክ ሜሰን ኖርዝ በማይሞተው ግጥማቸው እንደሚሉት፣ አቶ ቶዘርም በዚህ መጽሐፍ እንዲህ ይላሉ፦

ከራስ ወዳድነት ጠብ ጩኸት በላይ፣
የሰው ልጅ ሆይ፣ ድምፅህን እንሰማለን።

ከጸሐፊው ጋር ያለኝ ትውውቅ በቤተ ክርስቲያናቸው ባደረግኋቸው አጫጭር ጉብኝቶችና በፍቅር በተሞላ ኅብረት ብቻ የተወሰነ ነው። በዚያም ራሳቸውን በራሳቸው ያስተማሩ ምሁር፣ የማይጠግቡ አንባቢ፣ እጅግ አስደናቂ የሥነ መለኮትና የመንፈሳዊ ሕይወት መጻሕፍት ስብስብ ያላቸው፣ እግዚአብሔርንም በመፈለግ እስከ እኩለ ሌሊት መብራት የሚያቃጥሉ የሚመስሉ ሰው አገኘሁ። መጽሐፋቸው የረጅም ማሰላሰልና የብዙ ጸሎት ፍሬ ነው። የስብከቶች ስብስብ አይደለም። ስለ መድረኩና ስለ ምእመናን መቀመጫ ሳይሆን እግዚአብሔርን ስለ ተጠማች ነፍስ ይናገራል። ምዕራፎቹ በሙሴ ጸሎት፣ «ክብርህን አሳየኝ»፣ ወይም በጳውሎስ አድናቆት፣ «የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው!» ሊጠቃለሉ ይችላሉ። ይህ የአእምሮ ሳይሆን የልብ ሥነ መለኮት ነው።

ጥልቅ ማስተዋል፣ የአጻጻፍ ስክነትና የሚያድስ ሁሉን አቀፍ አመለካከት አለበት። ጸሐፊው ብዙ ጥቅሶችን አያቀርቡም፤ ነገር ግን የዘመናትን ቅዱሳንና ምሥጢራውያን ያውቋቸዋል—አውግስጢኖስን፣ የኩዛውን ኒኮላስን፣ ቶማስ አ ኬምፒስን፣ ፎን ሂውግልን፣ ፊኒን፣ ዌስሊንና ሌሎች ብዙዎችን። አሥሩ ምዕራፎች ልብን የሚመረምሩ ናቸው፤ በእያንዳንዳቸው መጨረሻ ያሉት ጸሎቶችም ለጓዳ እንጂ ለመድረክ አይደሉም። ሳነባቸው የእግዚአብሔር ቅርበት ተሰማኝ።

ይህ ለእያንዳንዱ መጋቢ፣ ሚስዮናዊና ለእግዚአብሔር ያደረ ክርስቲያን የሚሆን መጽሐፍ ነው። ስለ እግዚአብሔር ጥልቅ ነገርና ስለ ጸጋው ባለ ጠግነት ይናገራል። ከሁሉም በላይ ቅንነትና ትሕትና ዋና ቃናው ነው።

ሳሙኤል ኤም. ዝዌመር

ኒው ዮርክ ከተማ


ቀጣይ