የመንፈስ ቅዱስ ማንነትና ሥራ
የመንፈስ ቅዱስ አካልነት

ምዕራፍ 1 · 16 ደቂቃ ንባብ · 21 ደቂቃ ማዳመጥ

የመንፈስ ቅዱስ አካልነት

ሰው የመንፈስ ቅዱስን ሥራ በትክክል ከመረዳቱ በፊት፣ በመጀመሪያ መንፈስን ራሱን ማወቅ አለበት። ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ለሚነሣው ስሕተትና ጽንፈኝነት ተደጋጋሚ ምንጭ የሆነው፣ እርሱን በመጀመሪያ እንደ አካል ሳያውቁ ሥራውን ለማጥናትና ለመረዳት መሞከር ነው። መንፈስ ቅዱስ አምልኮአችንን፣ እምነታችንን፣ ፍቅራችንንና ፈጽመን ለእርሱ ራሳችንን መስጠታችንን ሊቀበል የሚገባው መለኮታዊ አካል ነውን፣ ወይስ ከእግዚአብሔር የሚወጣ ተጽዕኖ ብቻ፣ ወይም እግዚአብሔር የሚሰጠን ኃይል ወይም ብርሃን ብቻ ነው፣ የሚለውን መወሰናችን ከአምልኮ አንጻር እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። መንፈስ ቅዱስ አካል፣ ያውም መለኮታዊ አካል ሆኖ ሳለ እኛ እንደዚያ ሳናውቀው ብንቀር፣ ለአንድ መለኮታዊ ህላዌ የሚገባውን አምልኮ፣ እምነትና ፍቅር፣ ለእርሱ መሰጠትንም እየቀማነው ነው።

ደግሞም መንፈስ ቅዱስ እኛ በድካማችንና በአላዋቂነታችን እንደ ምንም ብለን ልንይዘውና ልንጠቀምበት የሚገባ ምሥጢራዊና አስደናቂ ኃይል ብቻ ነውን፣ ወይስ እኛን ሊይዘንና ሊጠቀምብን የሚገባ፣ ወሰን በሌለው ሁኔታ ቅዱስ፣ ወሰን በሌለው ሁኔታ ጥበበኛ፣ ወሰን በሌለው ሁኔታ ኃያልና ወሰን በሌለው ሁኔታ ርኅሩኅ የሆነ እውነተኛ አካል ነው፣ የሚለውን መወሰናችን ከተግባር አንጻርም እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የመጀመሪያው አስተሳሰብ ፈጽሞ አረማዊ ነው፤ የሚገለገልበት የራሱ አምላክ ካለው ከአፍሪካዊው የጣዖት አምላኪ አስተሳሰብ በመሠረቱ አይለይም። ሁለተኛው አስተሳሰብ ግን ልዕልና ያለውና ክርስቲያናዊ ነው። ብዙዎች እንደሚያደርጉት መንፈስ ቅዱስን ኃይል ወይም ተጽዕኖ ብቻ አድርገን ብናስበው፣ ዘወትር የሚያሳስበን «ከመንፈስ ቅዱስ የበለጠ እንዴት ላገኝ እችላለሁ?» የሚለው ይሆናል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው መለኮታዊ አካል አድርገን ብናስበው፣ አሳባችን ይልቁንም «መንፈስ ቅዱስ ከእኔ የበለጠ እንዴት ሊያገኝ ይችላል?» የሚል ይሆናል። መንፈስ ቅዱስን እንደ ምንም ብለን ልንይዘውና ልንጠቀምበት የሚገባ መለኮታዊ ተጽዕኖ ወይም ኃይል አድርጎ ማሰብ ወደ ራስን ከፍ ማድረግና በራስ ወደ መመካት ይመራል።

ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ የሚያስብ፣ ነገር ግን እርሱን እንደ ተቀበለ በስሕተት የሚያምን ሰው ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ትዕቢተኛ ይሆናል፤ ከሌሎች ክርስቲያኖች የሚበልጥ መስሎ ይመላለሳል። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች «እኔ የመንፈስ ቅዱስ ሰው ነኝ» ወይም «እኔ የመንፈስ ቅዱስ ሴት ነኝ» ሲሉ ብዙ ጊዜ ይሰማል። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ወሰን የሌለው ግርማ፣ ክብር፣ ቅድስናና ኃይል ያለው መለኮታዊ አካል መሆኑን፣ በሚያስደንቅ ራስን ዝቅ ማድረግም በዚያ ማደሪያውን ሊያደርግ፣ ሕይወታችንን ሊይዝና ሊጠቀምበት ወደ ልባችን እንደ መጣ አንድ ጊዜ ብንረዳ፣ ይህ አሳብ ይበልጥ በአክብሮትና በፍርሃት እንድንመላለስ ያደርገናል። መለኮታዊ ግርማና ክብር ያለው አካል በልቤ እንደሚኖርና ሊጠቀምብኝ ዝግጁ እንደ ሆነ ከሚለው አሳብ የበለጠ ዝቅ የሚያደርግ ወይም ልብን የሚያጥለቀልቅ ሌላ አሳብ አላውቅም።

መንፈስ ቅዱስን እንደ አካል ማወቃችን ከሕይወት ተሞክሮ አንጻርም እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በሺዎችና በአሥር ሺዎች የሚቈጠሩ ወንዶችና ሴቶች መንፈስ ቅዱስን ቸር ተጽዕኖ ብቻ (እውነት ነው፣ ከእግዚአብሔር የሚወጣ) አድርገው ሳይሆን፣ ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እውነተኛ የሆነ እውነተኛ አካል፣ ዘወትር የሚገኝ አፍቃሪ ወዳጅና ኃያል ረዳት አድርገው ባወቁት ጊዜ ወደ ሕይወታቸው ስለ መጣው በረከት ሊመሰክሩ ይችላሉ፤ እርሱ ሁልጊዜ ከጎናቸው የሚሆን ብቻ ሳይሆን በየቀኑና በየሰዓቱ በልባቸው የሚኖር፣ በማንኛውም የሕይወት ችግር ጊዜ ጉዳያቸውን ሊይዝላቸው ዝግጁ የሆነ ነው። በሺዎች የሚቈጠሩ አገልጋዮች፣ የክርስቲያን ሠራተኞችና እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የኑሮ ደረጃ ያሉ ክርስቲያኖች፣ መንፈስ ቅዱስ አካል መሆኑን (በሥነ መለኮት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ተሞክሮ) በተረዱና በዚህም እርሱን ባወቁ ጊዜ የክርስትና ሕይወታቸው ፈጽሞ ስለ መለወጡ በአካል ነግረውኛል ወይም ጽፈውልኛል። መንፈስ ቅዱስ አካል መሆኑን የሚያረጋግጡ ቢያንስ አራት የተለያዩ የማስረጃ መስመሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ።

1. የአካልነት መለያ ባሕርያት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥተዋል። የአካልነት መለያ ባሕርያት ወይም ምልክቶች ምንድን ናቸው? እውቀት፣ ስሜት ወይም የልብ መነካት፣ እና ፈቃድ ናቸው። የሚያስብ፣ የሚሰማውና የሚፈቅድ ማንኛውም ህላዌ አካል ነው። መንፈስ ቅዱስ አካል ነው ስንል፣ አንዳንዶች እንደ ሰው ሥጋዊ ገላ — እጅና እግር፣ ዓይንና ጆሮ፣ አፍና የመሳሰሉት — አሉት ማለታችን ይመስላቸዋል፤ እነዚህ ግን የአካልነት ሳይሆኑ የግዙፍ ሥጋ ባሕርያት ናቸው። እነዚህ የአካልነት ባሕርያት ወይም ምልክቶች ሁሉ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ለመንፈስ ቅዱስ ደጋግመው ተሰጥተዋል።

በ1ኛ ቆሮንቶስ 2:10-11 እንዲህ እናነባለን፦ «መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም።» እዚህ ላይ እውቀት ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶአል። መንፈስ ቅዱስ እውነትን እንድንረዳ አእምሮአችንን የሚያበራ ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ እውነትን የሚያውቅ ህላዌ መሆኑን እንማራለን።

በ1ኛ ቆሮንቶስ 12:11 ደግሞ «ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል» እናነባለን። እዚህ ላይ ፈቃድ ለመንፈስ ተሰጥቶአል፤ መንፈስ ቅዱስ እኛ ይዘን እንደ ፈቃዳችን የምንጠቀምበት ኃይል ሳይሆን፣ እንደ ፈቃዱ የሚጠቀምብን ሉዓላዊ ግርማ ያለው አካል መሆኑን እንማራለን። ይህ ልዩነት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ወደ ትክክለኛ ግንኙነት ለመግባታችን መሠረታዊ ጠቀሜታ አለው። በአገልግሎት ኃይልንና ብቃትን የሚሹ ብዙ ቅን ፈላጊዎች የሚስቱት በዚሁ ነጥብ ላይ ነው።

እነርሱ በሥራቸው እንደ ራሳቸው ፈቃድ ሊጠቀሙበት የሚችሉትን አንድ ምሥጢራዊና ብርቱ ኃይል ለመያዝ እጃቸውን እየዘረጉና እየታገሉ ነው። በዕውርነታቸውና በአላዋቂነታቸው ይዘው የሚጠቀሙበት መለኮታዊ ኃይል እንደሌለ፣ ነገር ግን ወሰን በሌለው ሁኔታ ኃያል ብቻ ሳይሆን ወሰን በሌለው ሁኔታ ጥበበኛም የሆነ፣ እነርሱን ሊይዛቸውና እንደ ራሱ ፍጹም ፈቃድ ሊጠቀምባቸው የሚፈቅድ አካል እንዳለ እስኪገነዘቡ ድረስ የሚፈልጉትን ኃይል ፈጽሞ አያገኙም። ቆም ብለን ስናስበው፣ እንደ እኛ ያሉ አላዋቂዎችና ለስሕተት እጅግ የተጋለጡ ፍጥረታት ይዘው የሚጠቀሙበት መለኮታዊ ኃይል ባለመኖሩ ደስ ሊለን ይገባል። እንዲህ ያለ ኃይል ቢኖር ኖሮ ውጤቱ ምንኛ አስፈሪ በሆነ ነበር! ነገር ግን ፈጽሞ የማይሳሳት መለኮታዊ አካል፣ እኛን ሊይዘንና እርሱ የሚሻለውን ስጦታ ሊሰጠን፣ እንደ ጥበበኛና አፍቃሪ ፈቃዱም ሊጠቀምብን የሚፈቅድ አንድ እንዳለ ስንረዳ፣ ምንኛ ቅዱስ ደስታ ወደ ልባችን ሊመጣ ይገባዋል!

በሮሜ 8:27 «ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና» እናነባለን። በዚህ ክፍል አሳብ ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶአል። «አሳብ» ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል የማሰብን፣ የስሜትንና የዓላማን ትርጉም የሚያጠቃልል ሰፊ ቃል ነው። ይኸው ቃል በሮሜ 8:7 ላይም ተጠቅሶአል፤ በዚያም «ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል» እናነባለን። ስለዚህ በዚህ ክፍል የአካልነት መለያ ምልክቶች ሁሉ ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥተዋል።

የመንፈስ ቅዱስ አካልነት እጅግ ልብ በሚነካና ብዙ ትርጉም በሚሰጥ መንገድ የተገለጠው በሮሜ 15:30 ነው፦ «ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር እየጸለያችሁ ከእኔ ጋር ትጋደሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ»፤ እዚህ ላይ «ፍቅር» ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶአል። አንባቢ ቆም ብሎ «የመንፈስ ፍቅር» በሚሉት በእነዚህ ቃላት ላይ ቢያሰላስል መልካም ያደርጋል። ስለ እግዚአብሔር አብ ፍቅር ብዙ ጊዜ እናሰላስላለን፤ የዕለት ተዕለትና የዘወትር አሳባችን ጉዳይ ነው። ስለ ወልድ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርም ብዙ ጊዜ እናሰላስላለን። ስለ አዳኙ ፍቅር ሳያሰላስል አንድ ቀን የሚያሳልፍ ሰው ራሱን ክርስቲያን ብሎ ለመጥራት ማን ያስባል? ነገር ግን ስለ «መንፈስ ፍቅር» ምን ያህል ጊዜ አሰላስለናል?

ክርስቲያኖች ሊኖሩ በሚገባቸው መንገድ የምንኖር ከሆነ፣ በሕይወታችን በየቀኑ በእግዚአብሔር አብ ፊት ተንበርክከን ወደ ፊቱ ቀና ብለን፦ «አባት ሆይ፣ ታላቅ ፍቅርህ አንድያ ልጅህን በቀራንዮ መስቀል ላይ ስለ እኔ እንዲሞት እንድትሰጥ ስላደረገህ አመሰግንሃለሁ» እንላለን።

በሕይወታችን በየቀኑ ደግሞ ወደ ጌታችንና አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ቀና ብለን፦ «የከበርህ ጌታና አዳኝ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለህን መተካከል አጥብቀህ እንዳትይዝ እስኪያደርግህ ድረስ ስለ ወደድኸኝ አመሰግንሃለሁ። ይልቁንም ያንን ትተህ፣ የሰማይን ክብር ሁሉ ወደ ኋላ ትተህ ወደዚህ ወደ ተሰበረ ዓለም መጣህ፤ ኃጢአቴን በራስህ ላይ ተሸከምህ፤ በቀራንዮ መስቀል ላይም በእኔ ፋንታ ሞትህ» እንላለን። ነገር ግን ምን ያህል ጊዜ ተንበርክከን መንፈስ ቅዱስን፦ «ዘላለማዊና ወሰን የሌለህ የእግዚአብሔር መንፈስ ሆይ፣ እኔን ለመፈለግ ወደዚህ ጨለማና ኃጢአተኛ ዓለም እስክትመጣ ድረስ ስለ ወደድኸኝ አመሰግንሃለሁ። ምን ያህል እንደ ጠፋሁና አዳኝ ምን ያህል እንደሚያስፈልገኝ በመጨረሻ እስካየሁ ድረስ በትዕግሥት ተከታተልኸኝ። ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ የሚያስፈልገኝ አዳኝ መሆኑን እንዳይ ዓይኖቼን ከፈትህ» እንላለን? ቢሆንም መዳናችንን ለአብ ፍቅርና ለወልድ ፍቅር ባለ ዕዳ እንደ ሆንን ሁሉ፣ ለመንፈስ ፍቅርም በእውነት ባለ ዕዳዎች ነን። እግዚአብሔር አብ ፍጹም ጠፍቼ ሳለሁ በፍቅሩ ወደ እኔ ተመልክቶ፣ በገዛ ልጁ በቀራንዮ መስቀል ላይ በሞተው ሞት ፍጹም ማስተስረያ ባያዘጋጅልኝ ኖሮ፣ ዛሬ በሲኦል በሆንሁ ነበር።

የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ፍጹም ጠፍቼ ሳለሁ በፍቅሩ ወደ እኔ ተመልክቶ፣ ለአብ በመታዘዝ ስለ ምድር ኀፍረት ሁሉ የሰማይን ክብር ሁሉ ትቶ፣ በቀራንዮ መስቀል ላይ የእኔን ስፍራ — የእርግማንን ስፍራ — ወስዶ ሕይወቱን ፈጽሞ ስለ እኔ ባያፈስስ ኖሮ፣ ዛሬ በሲኦል በሆንሁ ነበር። ነገር ግን ለወልድ ጸሎት መልስ ሆኖ በአብ የተላከው (ዮሐንስ 14:16) የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር ባይኖር ኖሮ — ያ ፍቅር ፍጹም ዕውርና ጠፍቼ ሳለሁ እንዲፈልገኝ፣ እኔ የልመናውን ድምፅ ያለማቋረጥ ጆሮ ዳባ ልበስ ብዬ ሳለሁ ቀን ከቀን፣ ሳምንት ከሳምንት፣ ዓመት ከዓመት እንዲከተለኝ፣ ለዚያ ቅዱስ መሄድ ስቃይ ሊሆንበት በሚገባቸው የኃጢአት መንገዶች ውስጥ እንዲከተለኝ ባያደርገው ኖሮ፣ በመጨረሻም እስክሰማው ድረስ፣ ዓይኖቼንም ከፍቶ ፍጹም መጥፋቴን እንዳይ አድርጎ ኢየሱስን ፍላጎቴን ሁሉ የሚያሟላ አዳኝ አድርጎ ባይገልጥልኝና ይህን ኢየሱስን የግሌ አዳኝ አድርጌ እንድቀበለው ባያስችለኝ ኖሮ — ይህ ትዕግሥተኛ፣ ታጋሽ፣ የማይታክት፣ ወሰን በሌለው ሁኔታ ርኅሩኅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር ባይኖር ኖሮ፣ ዛሬ በሲኦል በሆንሁ ነበር። ኦ፣ መንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ ወይም ኃይል ወይም ብርሃን ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ልክ እንደ እግዚአብሔር አብ ወይም እንደ ልጁ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ የሆነ አካል ነው።

የመንፈስ ቅዱስ አካልነት በአዲስ ኪዳን እንደ ተገለጠ ሁሉ በብሉይ ኪዳንም በእውነት ተገልጦአል፤ በነህምያ 9:20 «ታስተምራቸው ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፥ ለጥማቸውም ውኃ ሰጠሃቸው» እናነባለንና። እዚህ ላይ ማስተዋልም በጎነትም ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥተዋል። አንዳንዶች የመንፈስ ቅዱስ አካልነት በአዲስ ኪዳን መገኘቱ እውነት ቢሆንም በብሉይ ኪዳን አይገኝም ይሉናል። በዚህ ክፍል ግን በእርግጥ ይገኛል። እርግጥ ነው፣ የመንፈስ ቅዱስ አካልነት ትምህርት በብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን የተገለጠውን ያህል ሙሉ በሙሉ አልዳበረም። ትምህርቱ ግን በዚያ አለ።

የመንፈስ ቅዱስ አካልነት ከኤፌሶን 4:30 ይበልጥ በርኅራኄና ልብ በሚነካ ሁኔታ የተገለጠበት ክፍል በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምናልባት አይገኝም፦ «ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ።» እዚህ ላይ ኀዘን ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶአል። መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ለማብራት፣ ለመቀደስና ኃይል ለመስጠት ወደ ሕይወታችን የሚመጣ ዕውርና ግዑዝ ተጽዕኖ ወይም ኃይል አይደለም። አይደለም፤ እርሱ ከዚያ እጅግ በማይለካ መጠን ይበልጣል፤ በልባችን ሊኖር የሚመጣ ቅዱስ አካል ነው፤ የምናደርገውን እያንዳንዱን ድርጊት፣ የምንናገረውን እያንዳንዱን ቃል፣ የምናስተናግደውን እያንዳንዱን አሳብ፣ በአእምሮአችን ውስጥ እንዲያልፍ የሚፈቀድለትን እጅግ ፈጣን ምኞት እንኳ የሚያይ ነው፤ በድርጊት ወይም በቃል ወይም በሥራ ርኩስ፣ ቅድስና የጎደለው፣ ደግነት የሌለው፣ ራስ ወዳድ፣ ወራዳ፣ ጠባብ ወይም ሐሰት የሆነ ነገር ቢኖር፣ ይህ ወሰን በሌለው ሁኔታ ቅዱስ የሆነው በእርሱ እጅግ ያዝናል። ቅዱስ ሕይወት ለመኖርና በቅዱሱ ፊት በጥንቃቄ ለመመላለስ ከዚህ አሳብ የበለጠ ሰውን የሚረዳ አሳብ አላውቅም። አንድ ወጣት አሁን ለሚያጠቃው ፈተና ቢሸነፍ ቅድስት እናቱ ልትሰማና ከቃል በላይ ልታዝን እንደምትችል በማሰቡ ብቻ በወጣትነት ዘመን ለሚከቡት ፈተናዎች ከመሸነፍ የተጠበቀበት ጊዜ ምን ያህል ነው!

አንድ ወጣት ሊገባበት ባሰበው በአንድ የኃጢአት ስፍራ በር ላይ እጁን አድርጎ ሳለ፦ «እዚያ ብገባ እናቴ ልትሰማ ትችላለች፤ ይህም ሊገድላት ይቀርባል» የሚል አሳብ መጥቶበት፣ እናቱን እንዳያሳዝን ለዚያ በር ጀርባውን ሰጥቶ ንጹሕ ሕይወት ለመኖር የሄደበት ጊዜ ምን ያህል ነው!

ነገር ግን ከማንኛዋም እናት ይልቅ ቅዱስ የሆነ፣ በዚህች ምድር ላይ ከተመላለሰች እጅግ ንጽሕት ሴት ይልቅ ለኃጢአት ስሱ የሆነ፣ የትኛዋም እናት ወድዳ በማታውቀው ፍቅር የሚወድደን አንድ አለ፤ እኛ ክርስቲያኖች ከሆንን ይህ አንዱ በልባችን ይኖራል፤ በቀንም ሆነ በሌሊት ጨለማ ተሸፍነን የምናደርገውን እያንዳንዱን ድርጊት ያያል፤ በአደባባይም ሆነ በስውር የምንናገረውን እያንዳንዱን ቃል ይሰማል፤ የምናስተናግደውን እያንዳንዱን አሳብ ያያል፤ ለቅጽበት እንኳ በአእምሮአችን እንዲያርፍ የሚፈቀድለትን እያንዳንዱን ምኞትና ምናብ ይመለከታል፤ በድርጊት ወይም በቃል ወይም በአሳብ ወይም በምኞት ቅድስና የጎደለው፣ ርኩስ፣ ራስ ወዳድ፣ ወራዳ፣ ጠባብ፣ ደግነት የሌለው፣ ጨካኝ፣ ፍትሕ የጎደለው ወይም በማንኛውም መንገድ ክፉ የሆነ ነገር ቢኖር፣ በእርሱ ያዝናል። «ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ» የሚሉት ቃላት ወደ ልባችን ጠልቀው እንዲገቡና የሕይወታችን መመሪያ እንዲሆኑ ብንፈቅድ፣ ከብዙ ኃጢአት ይጠብቁናል።

አንድ አሳብ ወይም ምኞት ወደ አእምሮዬ ለመግባት በሩን አንኳኩቶ መስተንግዶ ሊያገኝ ሲቃረብ፣ «መንፈስ ቅዱስ ያንን አሳብ ያያል፤ በእርሱም ያዝናል» የሚለው አሳብ መጥቶልኝ ያ አሳብ የሄደበት ጊዜ ምን ያህል ነው!

2. አካል ብቻ ሊፈጽማቸው የሚችሉ ብዙ ሥራዎች ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥተዋል። የመንፈስ ቅዱስን አካልነት ብንክድ፣ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ትርጉም የለሽና ሞኝነት ይሆናሉ። ለምሳሌ፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 2:10 «መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው» እናነባለን። ይህ ክፍል መንፈስ ቅዱስን የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንድንረዳ የሚያስችለን ብርሃን ብቻ አድርጎ ሳይሆን፣ ራሱ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር የሚመረምርና ከዚያም ያገኛቸውን ውድ ግኝቶች ለእኛ የሚገልጥ አካል አድርጎ ያቀርበዋል።

በራእይ 2:7 «መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ» እናነባለን።

እዚህ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወደ አእምሮአችን የሚመጣ ግዑዝ የማስተዋል ብርሃን ብቻ ሳይሆን፣ የሚናገርና ከጥበቡ ጥልቀት የእግዚአብሔርን ውድ እውነት በሚያደምጠው አገልጋዩ ጆሮ ሹክ የሚል አካል ሆኖ ቀርቦልናል።

በገላትያ 4:6 «ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ» እናነባለን። እዚህ ላይ መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ አማኝ ልብ ውስጥ እንደሚጮኽ ተገልጦአል። በልባችን የልጅነታችንን ዋስትና የሚያስገኝ መለኮታዊ ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን፣ በልባችን የሚጮኽ፣ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ከመንፈሳችን ጋር የሚመሰክር ነው። (ሮሜ 8:16ንም ተመልከት።) መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጸልይ ሆኖም ተገልጦአል። በሮሜ 8:26 «እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል» እናነባለን። መንፈስ ቅዱስ እንድንጸልይ የሚገፋፋን ተጽዕኖ ብቻ ወይም እንዴት እንደምንጸልይ የሚያስተምረን ብርሃን ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ በእኛ ውስጥና በእኛ በኩል የሚጸልይ አካል መሆኑ ከዚህ ክፍል ግልጽ ነው።

እያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ ስለ እርሱ የሚጸልዩ ሁለት መለኮታዊ አካላት እንዳሉት በማሰብ ውስጥ አስደናቂ መጽናናት አለ፤ አንዱ በአንድ ወቅት በዚህች ምድር ላይ የነበረው፣ ፈተናዎቻችንን ሁሉ የሚያውቀው፣ በድካማችን ሊራራልን የሚችለው፣ አሁንም ወደ አብ ቀኝ ያረገውና በዚያ የሥልጣንና የኃይል ስፍራ ሆኖ ሊያማልድልን ዘወትር በሕይወት የሚኖረው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ዕብራውያን 7:25፤ 1ኛ ዮሐንስ 2)፤ ሌላውም ልክ እንደ እርሱ መለኮታዊ የሆነ፣ በየቀኑ ከጎናችን የሚመላለስ — አዎን፣ በማንነታችን ውስጠኛ ጥልቀት የሚኖርና እኛ ራሳችን ፍላጎታችንን ሳናውቀው እንኳ የሚያውቀው፣ ከዚያም ጥልቀት ስለ እኛ ወደ አብ የሚማልድ — አካል ነው። በእነዚህ ሁለት መለኮታዊ አካላት የሚጸለይለት አማኝ ያለበት ሁኔታ በእውነት ፍጹም ዋስትና ያለው ነው።

ደግሞም በዮሐንስ 15:26 «ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል» እናነባለን። እዚህ መንፈስ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነቱን የሚሰጥ አካል ሆኖ ቀርቦልናል፤ አማኙ ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክር የሚያስችል ብርሃን ብቻ ሳይሆን ራሱ የሚመሰክር አካል ነው፤ በዚህና በሚቀጥለው ቍጥርም በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነትና እርሱ በመሰከረለት አማኝ ምስክርነት መካከል ግልጽ ልዩነት ተደርጎአል፤ በሚቀጥለው ቍጥር «እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ» እናነባለንና። ስለዚህ ሁለት ምስክሮች አሉ፤ መንፈስ ቅዱስ ለአማኙ ይመሰክራል፤ አማኙም ለዓለም ይመሰክራል።

መንፈስ ቅዱስ መምህር ተብሎም ተጠርቶአል። በዮሐንስ 14:26 «አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል» እናነባለን። እንዲሁም በዮሐንስ 16:12-14 «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና» እናነባለን። በብሉይ ኪዳንም በነህምያ 9:20 «ታስተምራቸው ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፥ ለጥማቸውም ውኃ ሰጠሃቸው» ተብሎአል።

በእነዚህ ክፍሎች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እውነትን እንድንረዳ የሚያስችለን ብርሃን ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን እውነት ቀን በቀን ሊያስተምረን ወደ እኛ የሚመጣ አካል መሆኑ ግልጽ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን እጅግ ዝቅተኛ የሆነው አማኝ እንኳ የእግዚአብሔርን እውነት እንዲረዳ አእምሮው መብራቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሊያውቀው የሚያስፈልገውን እውነት በየዕለቱ የሚያስተምረው መለኮታዊ መምህር ማግኘቱ መብቱ ነው (1ኛ ዮሐንስ 2:20-27)።

መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች መሪና መንገድ አሳያቸው ሆኖም ተገልጦአል። በሮሜ 8:14 «በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና» እናነባለን። እርሱ እግዚአብሔር እንድንሄድበት የሚፈልገውን መንገድ እንድናይ የሚያስችለን ተጽዕኖ ብቻ ወይም በዚያ መንገድ እንድንሄድ ብርታት የሚሰጠን ኃይል ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን እጃችንን ይዞ እግዚአብሔር እንድንመላለስባቸው በሚፈልጋቸው መንገዶች በርኅራኄ የሚመራን አካል ነው።

መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎታቸው የማዘዝ ሥልጣን ያለው አካል ሆኖም ተገልጦአል። ስለ ሐዋርያው ጳውሎስና ስለ ባልንጀሮቹ በሐዋርያት ሥራ 16:6-7 እንዲህ እናነባለን፦ «በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤ በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘንድ ሞከሩ፥ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም።» እዚህ የጳውሎስንና የባልንጀሮቹን አካሄድ የሚመራ አካል፣ እነርሱም ሥልጣኑን የተቀበሉትና ወዲያውኑ የተገዙለት አካል አለ።

ከዚህም በላይ፣ መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛው ባለ ሥልጣን፣ ሰዎችን ወደ ሥራ የሚጠራና ለኃላፊነት የሚሾም ሆኖ ተገልጦአል። በሐዋርያት ሥራ 13:2 «እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ» እናነባለን። በሐዋርያት ሥራ 20:28 ደግሞ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ» እናነባለን። እውነትን በቅንነት ለሚፈልግ ሰው፣ እዚህ የቀረበልን አካል — ያውም መለኮታዊ ግርማና ሉዓላዊነት ያለው አካል — መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

እዚህ ከተጠቀሱት ክፍሎች ሁሉ አካል ብቻ ሊፈጽማቸው የሚችሉ ብዙ ሥራዎች ለመንፈስ ቅዱስ መሰጠታቸው ግልጽ ነው።

3. ለአካል ብቻ ሊነገር የሚችል ሹመት ለመንፈስ ቅዱስ ተነግሮለታል።

አዳኛችን በዮሐንስ 14:16-17 እንዲህ ይላል፦ «እኔም አብን እለምናለሁ፥ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።» ጌታችን ሊተዋቸው እንደ ሆነ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሮአቸው ነበር። አስፈሪ የብቸኝነት ስሜት ያዛቸው። ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ ብቻቸውን ትቶአቸው ሲሄድ ስለሚደርስባቸው ብቸኝነትና ፍጹም ረዳት ማጣት ሲያስቡ ኀዘን ልባቸውን ሞላ (ዮሐንስ 16:6)።

ሊያጽናናቸውም ጌታ ብቻቸውን እንደማይቀሩ፣ እርሱ ትቶአቸው የሚሄደው ወደ አብ እንደ ሆነ፣ አብንም እንደሚለምን፣ አብም እርሱ በሌለበት ጊዜ በእርሱ ፋንታ ሌላ አጽናኝ እንደሚሰጣቸው ነገራቸው። በእርሱ ፋንታ ሊመጣ ያለው ሌላው አጽናኝ ግዑዝ ተጽዕኖ ብቻ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ያለውን ቃል ሊጠቀም ይችል ነበርን? ይልከው የነበረው ይህ አጽናኝ ግዑዝ ተጽዕኖ ወይም ኃይል ብቻ ቢሆን ኖሮ፦ «እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ» ሊል ይችል ነበርን?

አይደለም፤ አንድ መለኮታዊ አካል እየሄደ ነበር፤ ልክ እንደ እርሱ መለኮታዊ የሆነ ሌላ አካል በእርሱ ፋንታ ሊመጣ ነበር፤ አንዱ በአብ ፊት እነርሱን ሊወክል መሄዱ ለደቀ መዛሙርቱ ይጠቅማቸው ነበር፤ ልክ እንደ እርሱ መለኮታዊና በቂ የሆነ ሌላው በእርሱ ፋንታ ሊመጣ ነበርና። ጌታችንና አዳኛችን ስለ ሌላው አጽናኝ መምጣትና ከእኛ ጋር ስለ መኖሩ የሰጠው ይህ ተስፋ ለዚህ ለአሁኑ ዘመን ከተስፋዎች ሁሉ የሚበልጠውና እጅግ መልካሙ ነው። ይህ የአብ የተስፋ ቃል (የሐዋርያት ሥራ 4)፣ የተስፋዎች ሁሉ ተስፋ ነው። የመንፈስ ቅዱስን ስሞች ወደ ማጥናት ስንደርስ እንደ ገና እንመለከተዋለን።

4. ለአካል ብቻ ሊነገር የሚችል አያያዝ በመንፈስ ቅዱስ ላይ እንደ ተፈጸመ ተነግሮአል። በኢሳይያስ 63 «እነርሱ ግን ዐመፁ፥ ቅዱስ መንፈሱንም አሳዘኑ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆነባቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው» እናነባለን። እዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተዐመፀበትና እንዳዘነ ተነግሮናል (ኤፌሶን 4:30)። ሊዐመፅበት የሚችለው አካል ብቻ ነው፤ ያውም ሥልጣን ያለው አካል ብቻ። ሊያዝን የሚችለው አካል ብቻ ነው።

ተጽዕኖን ወይም ኃይልን ብቻ ማሳዘን አይቻልም። በዕብራውያን 10:29 «የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?» እናነባለን። እዚህ መንፈስ ቅዱስ «እንደ ተክፋፋ» ተነግሮናል (ማለትም «በንቀት እንደ ተዋረደ» — የታየር የአዲስ ኪዳን የግሪክኛ-እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት)።

በዓለማት ሁሉ ውስጥ በንቀት ሊዋረድ (ወይም ሊሰደብ) የሚችል አንድ ዓይነት ህላዌ ብቻ ነው፤ እርሱም አካል ነው። ተጽዕኖን ወይም ኃይልን ወይም ከአካል በቀር ማንኛውንም ዓይነት ህላዌ በንቀት ማዋረድ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ደግሞም በሐዋርያት ሥራ 5:3 «ጴጥሮስም። ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ?» እናነባለን። እዚህ መንፈስ ቅዱስ ሊዋሹትና ሊያታልሉት የሚቻል ሆኖ ቀርቦአል። ከአካል በቀር ማንንም ሊዋሹት አይቻልም።

በማቴዎስ 12:31-32 «ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም» እናነባለን።

እዚህ መንፈስ ቅዱስ ሊሰደብ እንደሚችል ተነግሮናል። ከአካል በቀር ማንኛውንም ነገር መሳደብ አይቻልም። መንፈስ ቅዱስ አካል ካልሆነ፣ እርሱን መሳደብ የሰውን ልጅ፣ ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ራሱን ከመሳደብ የበለጠ ከባድና ወሳኝ ኃጢአት ሊሆን በፍጹም አይችልም።

እንግዲህ መንፈስ ቅዱስ አካል መሆኑን የሚያረጋግጡ አራት የተለያዩና ወሳኝ የማስረጃ መስመሮች አሉን።

አብዛኞቻችን ይህን በንድፈ አሳብ ደረጃ እናምናለን፤ ነገር ግን ስለ እርሱ በእውነት በምናስበውና ለእርሱ ባለን ተግባራዊ አቋም፣ በእውነት አካል እንደ ሆነ አድርገን እንይዘዋለንን? ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጉባኤ ላይ ስለ መንፈስ ቅዱስ አካልነት ያደረግሁትን ንግግር ስጨርስ፣ ለብዙ ዓመታት የቤተ ክርስቲያን አባል የነበረች፣ በዘመናችን ካሉት ቤተ እምነቶች መካከል ትክክለኛ አስተምህሮን አጥብቆ በመያዝ ከሚታወቁት የአንዱ አባል የሆነች አንዲት ሴት «ከዚህ በፊት እንደ አካል አስቤው አላውቅም ነበር» አለችኝ። ይህች ክርስቲያን ሴት ብዙ ጊዜ እንዲህ ብላ እንደ ዘመረች አያጠራጥርም፦ «በረከት ሁሉ ከእርሱ የሚፈስስ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ በምድር ያላችሁ ፍጥረታት ሁሉ አመስግኑት፤ እናንተ በላይ ያላችሁ የሰማይ ሠራዊት አመስግኑት፤ አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን አመስግኑ።» ደግሞም «ክብር ለአብ፣ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን፤ በመጀመሪያ እንደ ነበረ፣ አሁንም ዘወትርም ለዘላለም ዓለም፤ አሜን» ብላ ብዙ ጊዜ እንደ ዘመረች አያጠራጥርም።

ነገር ግን ቃላትን መዘመር አንድ ነገር ነው፤ የምንዘምረውን ትርጉም መገንዘብ ግን ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው። ይህች ክርስቲያን ሴት ስለ እምነት ትምህርቷ ብትጠየቅ ኖሮ፣ በመለኮት ውስጥ ሦስት አካላት — አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ — እንዳሉ እንደምታምን መናገሯ አይቀርም ነበር፤ ነገር ግን የሥነ መለኮት ምስክርነት አንድ ነገር ነው፤ የምንመሰክረውን እውነት በተግባር መገንዘብ ደግሞ ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው።

ስለዚህ በእምነት መግለጫዎችህ ምንም ያህል ትክክለኛ አስተምህሮ ቢኖርህ ይህ ጥያቄ ፈጽሞ አስፈላጊ ነው፦ መንፈስ ቅዱስን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት እውነተኛ አካል፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ብርቱ፣ እንደ እርሱም መተማመንህ፣ ፍቅርህና ራስህን መስጠትህ የሚገባው አድርገህ ትመለከተዋለህን? መንፈስ ቅዱስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ጌታችን ከሄደ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሊሆንና ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር አብሮ በኖረባቸው ቀናት ለእነርሱ የነበረውን ለእኛ ሊሆን ነው (ዮሐንስ 14:16-17)።

እርሱ ለአንተ እንደዚያ ነውን? ታውቀዋለህን? በሕይወትህ በየሳምንቱ «የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን» (2ኛ ቆሮንቶስ 13:14) የሚለውን ሐዋርያዊ ቡራኬ ትሰማለህ፤ ነገር ግን ስትሰማው ትርጉሙን ትረዳዋለህን? የመንፈስ ቅዱስን ኅብረት ታውቃለህን? የመንፈስ ቅዱስን አብሮነት? የመንፈስ ቅዱስን አጋርነት?

የመንፈስ ቅዱስን ጓደኝነት? የመንፈስ ቅዱስን የቅርብ የግል ወዳጅነት?

እውነተኛው የክርስትና ሕይወት — የነጻነት፣ የደስታ፣ የኃይልና የሙላት ሕይወት — ምሥጢሩ ሁሉ በዚህ ውስጥ ነው። መንፈስ ቅዱስን ዘወትር አብሮ የሚገኝ ወዳጅ አድርጎ መያዝ፣ እንደዚህ ያለ ወዳጅ እንዳለውም ማወቅ፣ በሁሉም ዘርፎቹ ሕይወትን ፈጽሞ ለእርሱ አገዛዝ መስጠት — እውነተኛ የክርስትና ኑሮ ይህ ነው።

የመንፈስ ቅዱስ አካልነት ትምህርት የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮትነትና ማስተስረያው ትምህርቶች ኢየሱስ ያስተማረውን ሃይማኖት እንደሚለዩት ሁሉ፣ ያንኑ ሃይማኖት የሚለይ ነው። ነገር ግን ትምህርቱን ማመን ብቻ በቂ አይደለም፤ ሰው መንፈስ ቅዱስን ራሱን ማወቅ አለበት። የዚህ ምዕራፍ ዓላማ ሁሉ (እግዚአብሔር በአክብሮት እንድናገረው ይርዳኝ) ወዳጄን መንፈስ ቅዱስን ከአንተ ጋር ማስተዋወቅ ነው።

ምዕራፍ 1 ተጠናቋል

የመንፈስ ቅዱስ አካልነት

ገጽ 1 / 1 · 16 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀጣይ