ምዕራፍ 7 · 3 ደቂቃ ንባብ
የእግዚአብሔር ቃል ኃይል
«ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን» 1ኛ ተሰሎንቄ 2:13።
የሰው ቃል ዋጋ የሚወሰነው ተናጋሪውን በማወቄ ላይ ነው። አንድ ሰው፦ «ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን እሰጥሃለሁ» ብሎ ቃል ሲገባልኝ፣ ተናጋሪው አንድ ሽልንግ ብቻ ያለው ድሀ ቢሆን ወይም ሀብቱን ከእኔ ጋር ሊካፈል የሚያቀርብ ሚሊየነር ቢሆን እንዴት ያለ ልዩነት አለ! ፍሬያማ ለሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሚያስፈልጉት የመጀመሪያዎቹ ነገሮች አንዱ እግዚአብሔርን ሁሉን የሚችል አምላክ አድርጎ ማወቅና የቃሉን ኃይል ማወቅ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ኃይል ወሰን የለውም። «በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ተሠሩ። እርሱ ተናገረ፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም» መዝሙር 33:9። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ሁሉን ቻይነቱ ይሠራል፤ ቃሉ የመፍጠር ኃይል አለው፤ የሚናገርለትንም ያንኑ ነገር ወደ መኖር ይጠራዋል።
የሕያው እግዚአብሔር ቃል ሕይወትን የሚሰጥ ሕያው ቃል ነው። ያልነበረውን ወደ መኖር መጥራት ብቻ ሳይሆን የሞተውን እንኳ እንደ ገና ሕያው ማድረግ ይችላል።
ሕያው የማድረግ ኃይሉ የሞቱትን ሥጋዎች ሊያስነሣ፣ ለሞቱ ነፍሳትም የዘላለምን ሕይወት ሊሰጥ ይችላል። መንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ የሚመጣው በእርሱ በኩል ነው፤ እኛ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ተወልደናልና። ከብዙዎች የተሰወረው የእግዚአብሔር ቃል በረከት ከሚገኝባቸው ጥልቅ ምሥጢሮች አንዱ እዚህ አለ፤ እርሱም ቃሉ ባለው የመፍጠርና ሕያው የማድረግ ብርታት ማመን ነው። ቃሉ የሚያዝዘውን ወይም ተስፋ የሚሰጠውን ያንኑ ዝንባሌ ወይም ጸጋ በእኔ ውስጥ ይሠራል። «በሚያምኑት ዘንድ በብርቱ ይሠራል።» በመንፈስ ቅዱስ በኩል ወደ ልብ በተቀበለ ጊዜ ኃይሉን ሊቋቋም የሚችል ምንም ነገር የለም «በሚያምኑት ዘንድ በብርቱ ይሠራል።» «የእግዚአብሔር ድምፅ በኃይል ነው።»
ሁሉም ነገር የተመካው ያንን ቃል ወደ ልብ የመቀበልን ጥበብ በመማር ላይ ነው። ይህንንም ጥበብ በመማር ረገድ የመጀመሪያው እርምጃ፦ በቃሉ ሕያውነት፣ በሁሉን ቻይነቱና በመፍጠር ኃይሉ ማመን ነው። በቃሉ፦ «‹ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁ› ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሙታንን ሕያዋን በሚያደርግና የሌለውን እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በእግዚአብሔር ፊት» ሮሜ 4:17 ይህ ከፍጥረት ጀምሮ እስከ ሙታን ትንሣኤ ድረስ ስለ እግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ እውነት እንደ ሆነ ሁሉ፣ በቅዱስ መጽሐፉ ውስጥ ለእኛ ስለ ተነገረው ቃል ሁሉ ደግሞ እውነት ነው። ይህንን እንደሚገባን እንዳናምን የሚከለክሉን ሁለት ነገሮች አሉ።
አንደኛው፣ በዙሪያችን ሁሉ፣ ምናልባትም በራሳችንም ውስጥ፣ ቃሉ በሰው ጥበብ ወይም ባለማመን ወይም በዓለማዊነት ከንቱ ሆኖ ሲቀር የምናየው አስከፊ ተሞክሮ ነው። ሌላው ደግሞ ቃሉ ዘር ነው የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቸል ማለታችን ነው።
ዘሮች ትናንሽ ናቸው፤ ዘሮች ለረጅም ጊዜ ተኝተው ሊቆዩ ይችላሉ፤ ዘሮች መሰወር አለባቸው፤ በበቀሉም ጊዜ እድገታቸው ዝግ ያለ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሥራ የተሰወረና የማይታይ፣ ዝግ ያለና ደካማ የሚመስል በመሆኑ በሁሉን ቻይነቱ አናምንም። ይህንን ከመጀመሪያ ትምህርቶቻችን አንዱ እናድርገው። የማጠናው ቃል የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው፤ የሚያስፈልገኝን ሁሉ፣ አብ የሚፈልገውንም ሁሉ በእኔ ውስጥ ይሠራል።
ይህ እምነት ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እንዴት ያለ ተስፋ በከፈተልን ነበር! የእግዚአብሔር ጸጋ መዝገቦችና በረከቶች ሁሉ በእጃችን ሊደርሱ የሚችሉ መሆናቸውን ባየን ነበር። ቃሉ ጨለማችንን የማብራት ኃይል አለው፤ በልባችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ብርሃን፣ የፍቅሩን ስሜትና የፈቃዱን እውቀት ያመጣል። ቃሉ ጠላትን ሁሉ ድል እንድናደርግና እግዚአብሔር እንድናደርግ የሚጠይቀንን ማናቸውንም ነገር እንድናደርግ በብርታትና በድፍረት ሊሞላን ይችላል።
ቃሉ ያነጻል፤ ይቀድሳልም፤ በእኛ ውስጥ እምነትንና መታዘዝን ይሠራል፤ በእኛም ውስጥ ጌታችንን የመምሰል የእያንዳንዱ ባሕርይ ዘር ይሆናል። በቃሉ በኩል መንፈስ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል፤ ይህም ማለት በቃሉ ያለውን ሁሉ በእኛ ውስጥ እውነት ያደርገዋል፤ በዚህም ልባችንን የአብና የወልድ ማደሪያ እንዲሆን ያዘጋጀዋል።
ይህን ቀላል እውነት በእውነት ብናምን ኖሮ ከእግዚአብሔር ቃልና ከማለዳው ሰዓት ጋር ባለን ግንኙነት ላይ እንዴት ያለ ለውጥ በመጣ ነበር። እያንዳንዱ አማኝ ሊፈጽመው ለሚገባው ለዚያ የቃሉ አገልግሎት የምንሠለጥንበትን ጉዞ የቃሉን ኃይል በገዛ ተሞክሮአችን በመፈተን እንጀምር። የእግዚአብሔርን ቃል ታላቅ ኃይል፣ ያንን ታላቅ የእምነት ትምህርት ለመማር በጸጥታ ራሳችንን እያዘጋጀን ይህንን መሻት እንጀምር።
የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው ስንል ከዚህ ያላነሰ ነገር ማለታችን ነው! ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ በእኛ ውስጥ እውነት ያደርገዋልና። ያንን ኃይል ስለሚያደናቅፈው ነገር ብዙ የምንማረው፣ ከእነዚህ እንቅፋቶች ነጻ ለመውጣት ብዙ የምናሸንፈው፣ ያንንም ሥራ ለመቀበል ብዙ አሳልፈን የምንሰጠው ይኖረናል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የሚናገርለትን በረከት ሁሉ በልብ ውስጥ ለመሥራት ሁሉን የሚችል ኃይል እንዳለው ለማመን በቈረጠ ውሳኔ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ብቻ ብንጀምር ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል ይህን ቀላል እውነት በእውነት ብናምን ኖሮ ከእግዚአብሔር ቃልና ከማለዳው ሰዓት ጋር ባለን ግንኙነት ላይ እንዴት ያለ ለውጥ በመጣ ነበር። እያንዳንዱ አማኝ ሊፈጽመው ለሚገባው ለዚያ የቃሉ አገልግሎት የምንሠለጥንበትን ጉዞ የቃሉን ኃይል በገዛ ተሞክሮአችን በመፈተን እንጀምር። የእግዚአብሔርን ቃል ታላቅ ኃይል፣ ያንን ታላቅ የእምነት ትምህርት ለመማር በጸጥታ ራሳችንን እያዘጋጀን ይህንን መሻት እንጀምር። የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው ስንል ከዚህ ያላነሰ ነገር ማለታችን ነው! ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ በእኛ ውስጥ እውነት ያደርገዋልና። ያንን ኃይል ስለሚያደናቅፈው ነገር ብዙ የምንማረው፣ ከእነዚህ እንቅፋቶች ነጻ ለመውጣት ብዙ የምናሸንፈው፣ ያንንም ሥራ ለመቀበል ብዙ አሳልፈን የምንሰጠው ይኖረናል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የሚናገርለትን በረከት ሁሉ በልብ ውስጥ ለመሥራት ሁሉን የሚችል ኃይል እንዳለው ለማመን በቈረጠ ውሳኔ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ብቻ ብንጀምር ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል።
ምዕራፍ 7 ተጠናቋል
የእግዚአብሔር ቃል ኃይል