ክርስቶስን መምሰል
የመከራ ጥቅም

ምዕራፍ 13 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ

የመከራ ጥቅም

አንዳንድ ጊዜ ፈተናና መከራ ቢደርስብን ለእኛ መልካም ነው፤ በዚህ ዓለም በመፈተን ላይ ያለን መሆናችንን፣ በምንም ዓለማዊ ነገርም ተስፋ ማድረግ እንደማይገባን ብዙ ጊዜ ያሳስቡናልና። መልካም እያደረግንና መልካምን እያሰብን ሳለን እንኳ አንዳንድ ጊዜ ተቃውሞ ቢገጥመንና ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ቢፈርዱብን ለእኛ መልካም ነው። እነዚህ ነገሮች ትሑታን እንድንሆን ይረዱናል፤ ከከንቱ ውዳሴም ይጠብቁናል። በውጫዊ ሁኔታ ሁሉ ሰዎች ምንም ዋጋ ሳይሰጡን፣ በበጎም ሳያስቡን ሲቀሩ፣ ያን ጊዜ ልባችንን የሚያየውን እግዚአብሔርን ለመፈለግ ይበልጥ እንዘነብላለን። ስለዚህ ሰው የሰዎችን መጽናናት እንዳያስፈልገው በእግዚአብሔር ላይ ራሱን አጥብቆ ሊተክል ይገባዋል።

በጎ ፈቃድ ያለው ሰው ሲጨነቅ፣ ሲፈተንና በክፉ አሳቦች ሲሠቃይ፣ ያለ እርሱ አንዳች መልካም ነገር ሊያደርግ የማይችለው እግዚአብሔር ታላቁ ፍላጎቱ እንደ ሆነ በግልጽ ይገነዘባል። በጐስቋላነቱና በመከራው አዝኖ ያለቅሳል፤ ይጸልያልም። ከዚህ በላይ መኖር ይታክተዋል፤ ተለይቶ ከክርስቶስ ጋር ይኖር ዘንድ ሞትን ይመኛል። ያን ጊዜ ፍጹም ዋስትናና ሙሉ ሰላም በምድር ላይ ሊገኙ እንደማይችሉ በሙላት ያስተውላል።

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ