ምዕራፍ 106 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
ራሳችንንና ያለንን ሁሉ ለእግዚአብሔር ማቅረብና ስለ ሁሉ መጸለይ
ደቀ መዝሙሩ፦
አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነው። ለዘላለም የአንተ ሆኜ እኖር ዘንድ ራሴን የፈቃድ መባ አድርጌ ልሰጥህ እናፍቃለሁ። አቤቱ፥ ለዘላለማዊ አገልግሎትህ፣ ለአምልኮህና የዘላለም ምስጋና መሥዋዕት እንዲሆን ዛሬ ራሴን በቅን ልብ አቀርብልሃለሁ። በማይታይ ሁኔታ በሚገኙ መላእክት ፊት ለእኔና ለሕዝብህ ሁሉ መዳን ዛሬ ደግሞ ለአንተ ከማቀርበው ከዚህ ከክቡር ሥጋህ ቅዱስ መባ ጋር ተቀበለኝ።
አቤቱ፥ በፊትህና በቅዱሳን መላእክትህ ፊት፣ መጀመሪያ ኃጢአት መሥራት ከቻልሁበት ቀን ጀምሮ እስከዚች ሰዓት ድረስ የሠራኋቸውን ኃጢአቶችና በደሎች ሁሉ በማስተስረያ መሠዊያህ ላይ አቀርብልሃለሁ፤ ይኸውም ሁሉንም በፍቅርህ እሳት እንድታቃጥላቸውና እንድትበላቸው፣ ነውራቸውን ሁሉ እንድታጠፋ፣ ሕሊናዬንም ከበደል ሁሉ እንድታነጻ፣ ሁሉንም ፈጽመህ ይቅር በማለትና በሰላም መሳም በምሕረት በመቀበል በኃጢአት ያጣሁትን ጸጋህን እንድትመልስልኝ ነው።
ስለ ኃጢአቶቼ ሁሉ በትሕትና ከመናዘዝና ከማልቀስ፣ ምሕረትህንም ያለ ማቋረጥ ከመለመን በቀር ምን ማድረግ እችላለሁ? አምላኬ ሆይ፥ በፊትህ በቆምሁ ጊዜ በምሕረትህ ስማኝ ብዬ እለምንሃለሁ። ኃጢአቶቼ ሁሉ እጅግ ያሳዝኑኛል። ዳግመኛ ልሠራቸው ከቶ አልወድም። በእነርሱ አዝናለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ድረስ አዝናለሁ። ንስሐ ለመግባትና በአቅሜ መጠን ሁሉ ካሳ ለመክፈል ዝግጁ ነኝ።
አምላክ ሆይ፥ ስለ ቅዱስ ስምህ ይቅር በለኝ፤ ኃጢአቶቼን ይቅር በለኝ። በእጅግ ክቡር ደምህ የተቤዠሃትን ነፍሴን አድናት። እነሆ፥ ራሴን ለምሕረትህ አቀርባለሁ። ራሴን በእጆችህ አደራ እሰጣለሁ። እንደ ክፉና እንደ ተንኰለኛ መንገዴ ሳይሆን እንደ ቸርነትህ አድርግልኝ።
ደግሞም ያለኝን መልካም ነገር ሁሉ፣ ጥቂትና ያልተሟላ ቢሆንም እንኳ፣ አቀርብልሃለሁ፤ ይኸውም ይበልጥ ንጹሕና ይበልጥ ቅዱስ እንድታደርገው፣ በእርሱ ደስ እንዲልህ፣ በፊትህ ተቀባይነት እንዲያገኝ እንድታደርገውና ከዕለት ወደ ዕለት ይበልጥ እንድትፈጽመው፣ በመጨረሻም እኔን ሰነፍና የማልረባ ፍጥረት ወደ መልካምና ደስተኛ ፍጻሜ እንድትመራኝ ነው።
ደግሞም የታማኝ አገልጋዮችህን ቅዱስ ምኞቶች ሁሉ፣ የወላጆቼን፣ የወዳጆቼን፣ የወንድሞቼንና የእኅቶቼን፣ የምወዳቸውንም ሁሉ ችግሮች አቀርብልሃለሁ፤ ስለ አንተ ብለው ለእኔ ወይም ለሌሎች ቸርነት ያደረጉትን ሁሉ፣ ለእነርሱና ለወገኖቻቸው ጸሎቴንና ቅዳሴዬን የፈለጉትንና የለመኑትን ሁሉ፣ ገና በሥጋ ሕያዋን ቢሆኑ ወይም ከዚህ ዓለም ያለፉ ቢሆኑ፣ ሁሉም የጸጋህን ርዳታ፣ የመጽናናትህን ብርታት፣ ከአደጋ መጠበቅን፣ ከሚመጣውም ቅጣት መዳንን እንዲያገኙ፣ ከክፉ ነገርም ሁሉ ነጻ ወጥተው ደስ ብሏቸው የተትረፈረፈ ምስጋና ለአንተ እንዲያቀርቡ አቀርብልሃለሁ።
ደግሞም እነዚህን ጸሎቶችና የማስተስረያውን መሥዋዕት በተለይ በማንኛውም መንገድ ለበደሉኝ፣ ላሳዘኑኝ ወይም ስሜን ላጠፉ፣ ጕዳት ወይም ሥቃይ ላደረሱብኝ፣ ደግሞም በማንኛውም ጊዜ ዐውቄም ሆነ ሳላውቅ በቃል ወይም በሥራ ላሳዘንኋቸው፣ ላወክኋቸው፣ ላስቀየምኋቸውና ለበደልኋቸው ሁሉ አቀርብልሃለሁ። እርስ በርሳችን የሠራነውን ኃጢአትና በደል ሁላችንንም በአንድነት ይቅር ትል ዘንድ ፈቃድህ ይሁን።
አቤቱ፥ ጥርጣሬን፣ ቍጣን፣ መቈጣትን፣ ክርክርን፣ ፍቅርንም የሚጐዳና የወንድማማችነትን መዋደድ የሚያጐድል ማንኛውንም ነገር ሁሉ ከልባችን አስወግድ። አቤቱ፥ ምሕረትህን የሚለምኑትን ማራቸው፤ ማረን፤ ለሚያስፈልጋቸው ጸጋን ስጥ፤ በሞገስህ ደስ ለመሰኘትና የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት የተገባን አድርገን።
ምዕራፍ 106 ተጠናቋል
ራሳችንንና ያለንን ሁሉ ለእግዚአብሔር ማቅረብና ስለ ሁሉ መጸለይ