የተቀጠቀጠ ሸምበቆ
የክርስቶስ አገዛዝ ድል አድራጊ ነው

ምዕራፍ 22 · 10 ደቂቃ ንባብ · 12 ደቂቃ ማዳመጥ

የክርስቶስ አገዛዝ ድል አድራጊ ነው

ሦስተኛው ድምዳሜ ይህ አገዛዝ ድል አድራጊ መሆኑ ነው። ምክንያቶቹም እነዚህ ናቸው፦

1. ክርስቶስ በመጀመሪያ ሁሉን በገዛ ራሱ አካል ድል ስላደረገ፣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ስለ ሆነ ነው (ሮሜ 9:5)፤ ስለዚህም ከኃጢአት፣ ከሞት፣ ከሲኦል፣ ከሰይጣን፣ ከዓለምና ከሌሎችም ሁሉ በላይ ነው። በራሱ ድል እንደ ነሣቸው እንዲሁ በልባችንና በሕሊናችን ውስጥ ድል ይነሣቸዋል። ሕሊና ሰውን ንጉሥ ወይም ጐስቋላ ያደርገዋል ማለት ልማዳችን ነበር፤ ምክንያቱም ሕሊና ከእኛ ጋር ወይም በእኛ ላይ ለእግዚአብሔር ይፈርድ ዘንድ በውስጣችን ተተክሎአል። እንግዲህ የተፈጥሮ ሕሊና ይህን ያህል ብርቱ ከሆነ፣ ከራሱ ብርሃን በተጨማሪ የመለኮታዊ እውነት ብርሃን በውስጡ በገባ ጊዜ ምን ያህል ይሆን? ወይ ራሳችንን በድፍረት ቀና አድርገን እንድንሄድ፣ ወይም ከራሳችን በታች እንድንዋረድ በማድረግ ያለ ጥርጥር ያሸንፋል። በጸጋ ለክርስቶስ እውነት ራሱን ቢያስገዛ፣ በዚያን ጊዜ ሞትን፣ ሲኦልን፣ ፍርድንና መንፈሳውያን ጠላቶችን ሁሉ ከቁብ ሳይቈጥር በድፍረት ያልፋቸዋል፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ክርስቶስ በሕሊና ውስጥ መንግሥቱን ያቆማል፤ ሕሊናንም እንደ ገነት ያለ ስፍራ ያደርገዋል።

ነፍስ ከምታደርጋቸው ግጭቶች ሁሉ እጅግ የበረታው በሕሊናና በእግዚአብሔር ፍትሕ መካከል ያለው ነው። እንግዲህ በክርስቶስ ደም የተረጨው ሕሊና አሁን በክርስቶስ ከረካው ከእግዚአብሔር ፍትሕ የሚመጡበትን ጥቃቶች ካሸነፈ፣ ማናቸውንም ሌላ ተቃውሞ ሁሉ ያሸንፋል።

2. የምንጋፈጠው ከተረገሙና ከተኰነኑ ጠላቶች ጋር ነው፤ ስለዚህ በውስጣችን ባለው መንፈስ ፊት መውደቅ ከጀመሩ በእርግጥ ይወድቃሉ፤ ዳግመኛ ቢነሡም የሚነሡት የባሰ ውድቀት ለመውደቅ ነው።

3. ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን ለጥበቃውና ለትምህርቱ በአደራ የሰጠው የእውነት መንፈስ፣ የክርስቶስም በትረ መንግሥት የሆነው የመንፈስ እውነት ለዘላለም ይኖራሉ፤ ስለዚህ በማይጠፋው በመንፈስ ዘር የተወለደችው ነፍስ (1ኛ ጴጥሮስ 1:23)፣ ይህም እውነት ለዘላለም መኖር ብቻ ሳይሆን የሚቃወሟቸውን ሁሉ ደግሞ ማሸነፍ አለባቸው፤ ቃሉም መንፈሱም በሥራቸው ኃያላን ናቸውና (ዕብራውያን 4:12)። እግዚአብሔር አሳልፎ በሰጠው ሰዎች ውስጥ ክፉው መንፈስ ከቶ ሥራ ፈትቶ የማይቀመጥ ከሆነ፣ መሪነታቸውና አገዛዛቸው በአደራ በተሰጠው ሰዎች ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ፈትቶ ይቀመጣል ብለን ልናስብ አንችልም። አይደለም፤ በእነርሱ ውስጥ እንደሚኖር፣ እንዲሁ ሁሉ በሁሉ እስኪሆን ድረስ በእርሱ ላይ የሚነሣውን ሁሉ ያስወጣል።

መንፈሳዊ የሆነው ዘላለማዊ ነው፤ እውነት በራሱም ሆነ በነፍስ ውስጥ በተከተበ ጊዜ የክርስቶስ መንፈስ ጨረር ነው፤ ስለዚህ እውነቱም፣ በእርሱም የተሠራው ጸጋ ጥቂት ቢሆንም፣ ያሸንፋሉ፤ በግዙፍ ሰው እጅ ያለ ትንሽ ነገር ታላቅ ሥራ ይሠራል። በክርስቶስ የበረታ ጥቂት እምነት ድንቅ ነገሮችን ያደርጋል። 4. ላለው ሁሉ ይሰጠዋል (ማቴዎስ 25:29)፤ በማናቸውም ርኵሰት ወይም ፈተና ላይ የሚገኝ ድል የመጨረሻው ድል መያዣ ነው። ኢያሱ ድል ባደረጋቸው በአምስቱ ነገሥታት ላይ እግሩን ባኖረ ጊዜ፦ እግዚአብሔር በጠላቶቻችን ሁሉ እንዲሁ ያደርጋል እንዳለ (ኢያሱ 10:25)፣ ሰማይ አሁንም የእኛ ነው፤ የምንጋደለው ሙሉ በሙሉ እስክንወርሰው ድረስ ብቻ ነው።

5. ክርስቶስ እንደ ንጉሥ የሚያዝዝ ብርሃን ወደ ነፍስ ያስገባል፤ አንገትንም ያጎብጣል፤ የውስጡንም ሰው የብረት ጅማት ያለሰልሳል፤ መግዛት በጀመረበትም ስፍራ ለዘላለም ይገዛል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም (ሉቃስ 1:33)።

6. የክርስቶስ የመምጣቱ ዓላማ ስለ እኛም በእኛም ውስጥ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ ነበር፤ የትንሣኤውም ዓላማ የድሉን ማረጋገጫ ለእኛ ማተም እንደ ሆነ፣ እንዲሁ ደግሞ፦ 1. ነፍሳችንን በኃጢአት ከመሞት ሕያው ለማድረግ፤ 2. ከኃጢአት በደል ጋር አብረው ከሚመጡት ከመንፈሳዊ ሞት ወጥመዶችና ጣሮች ነፍሳችንን ነጻ ለማውጣት፤ 3. ፀሐይ ከወፍራም ደመና ውስጥ ይበልጥ በክብር ብልጭ ብላ እንደምትወጣ፣ ነፍሳችንን ይበልጥ ተጽናንታ እንድትነሣ ለማድረግ፤ 4. ከልዩ ልዩ መንሸራተቶችና ውድቀቶች ይበልጥ በርትተን እንድንነሣ ለማድረግ፤ 5. ከዚህ ሕይወት አስጨናቂና ጨለማ ሁኔታዎች ሁሉ ሊያወጣን፤ 6. በመጨረሻም ሥጋችንን ከአፈር ሊያስነሣ ነው። መንፈስ ራስ የሆነልንን ክርስቶስን ከሞት ጣር፣ ከውርደቱም ዝቅተኛ ደረጃ ባስነሣው ጊዜ ያሳየውን ያንኑ ኃይል፣ አሁን በዚያ መሥዋዕት ቍጣው ከበረደለት ከእግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት የተገኘውን ያንኑ ኃይል፣ መንፈስ አካሉ በሆነችው በቤተ ክርስቲያንና በእያንዳንዱ ብልቷ ውስጥ ያሳያል። ይህም ኃይል በእምነት ይተላለፋል፤ በእምነት በሁለቱም የውርደቱና የክብሩ ሁኔታዎች ከክርስቶስ ጋር ከተባበርን በኋላ ራሳችንን ከክርስቶስ ጋር እንደ ሞትን ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ተነሣንና በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አብረን እንደ ተቀመጥን እናያለን (ኤፌሶን 2:6)። አሁንም ራሳችንን እንደ ሞትንና እንደ ተነሣን፣ በዚህም ምክንያት ራስ በሆነልን በክርስቶስ ጠላቶቻችንን ሁሉ ድል እንደ ነሣን ስንረዳ፣ በዚህ ሁሉ ዓላማው እኛን ራሱን እንድንመስል ማድረግ መሆኑን ስንረዳ፣ በዚህ እምነት ወደ መልኩ እንለወጣለን (2ኛ ቆሮንቶስ 3:18)፤ እንዲሁም ለወገኖቹ ሁሉ የመንፈሳዊ ብርታት ሁሉ ግምጃ ቤት ከሆነው ከእርሱ በምንቀዳው ኃይል፣ እርሱ እንደ ሆነ፣ በመንፈሳውያን ጠላቶቻችን ሁሉ ላይ አሸናፊዎች እንሆናለን። ክርስቶስ በመጨረሻ በእኛ ዓላማውን ይፈጽማል፤ እምነትም በዚህ ተረጋግታ ታርፋለች፤ ይህም መተማመን እጅግ የሚሠራ ነው፤ በዓላማዎቹ ከክርስቶስ ጋር እንድንተባበር ያነሣሣናል።

ለቤተ ክርስቲያንም በአጠቃላይ እንዲሁ ነው፤ በክርስቶስ ድልዋን ታገኛለች። ክርስቶስ ያንን ያማረ ምስል፣ ማለትም ተቃዋሚ የሆነውን አገዛዝ ሁሉ፣ የሚያደቅቀው ያለ እጅ ከተራራ የተፈነቀለው ያ ትንሽ ድንጋይ ነው (ዳንኤል 2:35)፤ ታላቅ ተራራ ሆኖ ምድርን ሁሉ እስኪሞላ ድረስ ያደቅቃል። ስለዚህ ከተራራው የተፈነቀለው ድንጋይ በመጨረሻ ራሱ ተራራ ይሆናል። እንግዲህ አንተ ተራራ ሆይ፣ በዚህ ተራራ ላይ ለመነሣት የምታስብ ማን ነህ? ሁሉ በፊቱ ተዘርሮ ይደለደላል፤ ተራራ የሚያህለውን ከፍ ከፍ ያለውን አሳብ ሁሉ ያወርዳል፤ የሥጋ ለባሽንም ሁሉ ትዕቢት ያዋርዳል። ገለባ ከነፋስ፣ ጭድ ከእሳት ጋር ሲታገል፣ ተረከዝ የመውጊያውን ብረት ሲቃወም፣ ገል ከሸክላ ሠሪው ጋር ሲከራከር፣ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሲታገል፣ ድሉ ወደ የትኛው ወገን እንደሚሄድ ማወቅ ቀላል ነው። ነፋሳት ክርስቶስ ያለባትን መርከብ ሊያናውጧት ይችላሉ እንጂ ሊገለብጧት አይችሉም። ማዕበሎች ዓለቱን ሊመቱት ይችላሉ፤ ነገር ግን የሚሰባበሩት ራሳቸው ናቸው።

ይህ እንዲህ ከሆነ፣ በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንና በብዙ ጸጋ ያላቸው ክርስቲያኖች ላይ ስለ ምን እንዲህ ይሆናል? ድሉ ከጠላት ጋር የሄደ ይመስላልና።

ለመልሱም ይህን አስታውስ፦ 1. የእግዚአብሔር ልጆች በመከራቸው አብዛኛውን ጊዜ የሚያሸንፉት በመታገሥ ነው፤ በዚህ ጠቦቶች አንበሶችን፣ ርግቦችም ንስሮችን በመከራ ያሸንፋሉ፤ ይኸውም አብልጦ በተሠቃየ ጊዜ አብልጦ ድል የነሣውን ክርስቶስን ይመስሉ ዘንድ ነው፤ ከክርስቶስ የትዕግሥት መንግሥት ጋር የኃይል መንግሥት ነበረ።

2. ይህ ድል ቀስ በቀስ የሚገኝ ነው፤ ስለዚህ የመጀመሪያውን ምት እንደ መቱ ወዲያውኑ ድል ማድረግ፣ ገና ሲነሡም በሩጫቸው መጨረሻ መድረስ የሚፈልጉ እጅግ ችኩሎች ናቸው። እስራኤላውያን ወደ ከነዓን በሚያደርጉት ጉዞ ድል እንደሚያገኙ እርግጠኞች ነበሩ፤ ቢሆንም እስከ መጨረሻ ተዋግተው መዝለቅ ነበረባቸው። እግዚአብሔር ክርስቶስ ስለ እኛ ድል ያደረጋቸው ጠላቶች ምን ያህል ጨካኞች እንደ ሆኑ ቶሎ እንድንረሳ አይፈልግም፤ መዝሙረኛው፦ ሕዝቤ እንዳይረሳ አትግደላቸው ይላል (መዝሙር 59:11)። ይኸውም ከእነርሱ በሚደርስብን መከራ ልምድ በሥልጣናቸው ሥር እንዳንወድቅ በፍርሃት እንጠበቅ ዘንድ ነው።

3. እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ በተቃራኒ ነገሮች ይሠራል፤ ድልን ሊሰጥ ሲያስብ፣ በመጀመሪያ እንድንሸነፍ ይፈቅዳል፤ ሊያጽናና ሲያስብ፣ አስቀድሞ ያስፈራል፤ ሊያጸድቀን ሲያስብ፣ አስቀድሞ ይኰንነናል፤ ሊያከብረው ያሰበውን አስቀድሞ ያዋርደዋል። ክርስቲያን ሲሸነፍ እንኳ ያሸንፋል፤ በአንዳንድ ኃጢአቶች ሲሸነፍ፣ እንደ መንፈሳዊ ትዕቢት፣ መዘናጋትና እንደ መሳሰሉት ባሉ ይበልጥ አደገኛ በሆኑ ሌሎች ኃጢአቶች ላይ ድል ያገኛል።

4. የክርስቶስ ሥራ በቤተ ክርስቲያንም በክርስቲያኖችም ልብ ውስጥ ይበልጥ ወደ ፊት ይሄድ ዘንድ ብዙ ጊዜ ወደ ኋላ ይሄዳል፤ ዘር በክረምት ወራት በመሬት ውስጥ እንደሚበሰብስ፣ በኋላ ግን ይበልጥ አምሮ እንደሚበቅል፣ ክረምቱም በከበደ መጠን ጸደዩ ይበልጥ እንደሚያብብ፣ እንዲሁ በመውደቅ መቆምን እንማራለን፤ ድካማችን በመገለጡም ብርታትን እናገኛለን፤ በመናወጥ ጠልቀን ሥር እንሰዳለን፤ ችቦዎችም ሲንቀሳቀሱ ይበልጥ ደምቀው እንደሚነዱ፣ እንዲሁ ክርስቶስ ከነጻነቱ የተነሣ አገዛዙን በውስጣችን በዚህ መንገድ ሊጠብቅ ደስ ይለዋል። በዚህ ነገር ክርስቶስ ለእኛ ከሚያሳየው አያያዝ ጋር እንዲስማማ እምነታችንን ለመለማመድ እንትጋ፤ ስንሸነፍ እንደምናሸንፍ እናምን፤ ስንወድቅም ዳግመኛ እንደምንነሣ እናምን። ያዕቆብ የሚያነክስበትን ምት ከተመታ በኋላ እንኳ በረከቱን እስኪያገኝ ድረስ መታገሉን አልተወም (ዘፍጥረት 32:24)፤ እንዲሁ እኛም ከቶ ትግሉን አንተው፤ ነገር ግን በአሳባችን ጅማሬውን፣ እድገቱንና ፍጻሜውን አንድ ላይ እናስተሳስር፤ ያን ጊዜም ከጠላቶች ሁሉ ተደራሽነት ርቀን ራሳችንን በሰማይ እናያለን። የእግዚአብሔር ጸጋ በዚህ ፍጹም ባልሆነ ሁኔታ እንኳ በመጀመሪያው የፍጹምነት ሁኔታ ከነበረው ከሰው ነጻ ፈቃድ ይበልጥ ብርቱ መሆኑን ራሳችንን እናረጋግጥ፤ አሁን የተመሠረተው በክርስቶስ ላይ ነውና፤ እርሱም የእምነታችን ራስ እንደ ሆነ እንዲሁ ፈጻሚዋ ይሆናል (ዕብራውያን 12:2)፤ እኛ ይበልጥ ጸጋ ባለበት ኪዳን ሥር ነንና።

አንዳንዶች ሥር የሰደደ እምነት ይጸናል፤ ደካማ እምነት ግን ከንቱ ሆኖ ሊቀር ይችላል የሚሉት ነገር በዚህ የመጽሐፍ ቃል የተቃወመ ይመስላል፤ እጅግ ብርቱው እምነት ሊናወጥ እንደሚችል፣ እንዲሁ እውነት ባለበት ስፍራ እጅግ ደካማው እምነት እንኳ የሚያሸንፍ ያህል ሥር ሰድዶአልና። ከንቃት ጋር ያለ ድካም ጸንቶ ይቆማል፤ ከልክ ካለፈ መተማመን ጋር ያለ ብርታት ግን ይወድቃል። ድካሙን አምኖ የሚቀበል ድካም እግዚአብሔር ብርታቱን የሚፈጽምበት እጅግ የተገባ ስፍራና መሣሪያ ነው፤ ድካሞቻችንን ማወቃችን ከራሳችን አውጥቶ ብርታታችን ወዳለበት ወደ እርሱ ይነዳናልና።

ከዚህም የተነሣ ድካም ከመዳን ማረጋገጫ ጋር አብሮ ሊኖር እንደሚችል ይከተላል፤ ደቀ መዛሙርት ድካማቸው ሁሉ ቢኖርም ስማቸው በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ እንዲላቸው ታዘዋል (ሉቃስ 10:20)። በመቀደስ ውስጥ ከትግል ጋር ያሉ ውድቀቶች የመጽደቃችንን ሰላምና የመዳናችንን ማረጋገጫ ሊያደክሙ አይገባም። ዋናው ነገር በውስጣችን ምን ክፉ ነገር እንዳለ ሳይሆን ምን መልካም ነገር እንዳለ ነው፤ ምን ርኵሰቶች እንዳሉ ሳይሆን ለእነርሱ ያለን ዝንባሌ ምን እንደ ሆነ ነው፤ ልዩ ልዩ ውድቀቶቻችን ምን እንደ ሆኑ ሳይሆን የሕይወታችን ፈትልና አቅጣጫ ምን እንደ ሆነ ነው፤ ክርስቶስ በእኛ ዘንድ ያለውን ጉድለት አለመውደዱ እኛን ወደ መጥላት አያመራምና፤ ድካሞቻችንን ሁሉ በድል ወደ ማስገዛት ያመራል እንጂ። አንዳንዶች ከትግል በኋላ፣ ሰይጣን ሊይዛቸው በተቃረበ ጊዜ፣ እንዲህ ያለች ጥቂትና የምትናወጥ እምነት በእንዲህ ያሉ ታላላቅ ውጊያዎች ደግፋ ስለ ያዘቻቸው በእግዚአብሔር ቸርነት ተደነቁ። በእውነትም ልብ ቅን ከሆነ፣ ጥቂት ጸጋ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት፣ በጠላቶቻችንም ላይ ድልን ለማግኘት ምን ያህል እንደምታሸንፍ የሚያስደንቅ ነው። የጣፋጩ አዳኛችን ቸርነት እንዲህ ነው፤ ሁልጊዜ ብርታቱን በድካማችን ማሳየት ደስ ይለዋል።

ስለዚህ በመጀመሪያ፣ ለድሆችና ለደካሞች ክርስቲያኖች ታላቅ መጽናናት ይሆን ዘንድ ይህን ይወቁ፦ ከሰማይ የወረደ ፍንጣሪ እያንጣጣና እያጤሰ በሚነድ እርጥብ እንጨት ሥር ቢለኰስም፣ በመጨረሻ ሁሉን ይበላል። አንድ ጊዜ የተቀጣጠለ ፍቅር እንደ ሞት የበረታ ነው፤ ብዙ ውኃ ሊያጠፋው አይችልም፤ ስለዚህም ብርቱ ነበልባል ወይም የእግዚአብሔር ነበልባል ተብሎ ተጠርቶአል (መኃልየ መኃልይ 8:6)፤ በልብ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ የተለኰሰ ነው። በእኛ ውስጥ ያለው ያ ጥቂት ነገር ከዘላለማዊ ምንጭ ይመገባል። በኤልያስ ዘመን ከሰማይ የወረደው እሳት ከእግዚአብሔር መምጣቱን ለማሳየት ውኃውን ሁሉ እንደ ላሰ (1ኛ ነገሥት 18:38)፣ እንዲሁ ይህ እሳት ርኵሰታችንን ሁሉ ይበላል፤ በውጭ ያለ መከራም ሆነ በውስጥ ያለ ርኵሰት አያጠፋውም። በጠዋት ደመናዎች ፀሐይን ሊሰውሯት እንደሚፈልጉ በዙሪያዋ ሲሰበሰቡ ብዙ ጊዜ እናያለን፤ ፀሐይ ግን ሙሉ ብርታቷ እስክትደርስ ድረስ ቀስ በቀስ ታበናቸዋለች። በመጀመሪያ ፍርሃትና ጥርጣሬ የዚህን እሳት መቀጣጠል ያግዳሉ፤ በመጨረሻ ግን ከሁሉም በላይ ይወጣል፤ ክርስቶስም ያሸንፋል፤ ከዚያም በውስጣችን ያሉትን የገዛ ጸጋዎቹን ይደግፋል። ጸጋ አስቀድሞ እኛን ያሸንፈናል፤ እኛም በእርሱ ሌላውን ሁሉ እናሸንፋለን፤ በውስጣችን ያሉ ርኵሰቶችም ሆኑ በውጭ ያሉ ፈተናዎች።

በእውነት ቃል የተወለደችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ትምህርት አክሊሏ አድርጋለች፤ ጨረቃንም፣ ማለትም ዓለምንና ዓለማዊ ነገሮችን ሁሉ፣ ከእግሮችዋ በታች ትረግጣለች (ራእይ 12:1)። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል (1ኛ ዮሐንስ 5:4)። ክርስቶስ በተለይ የሚገዛበት እምነት ነፍስን እጅግ ከፍ ያደርጋታል፤ በክርስቶስ መንፈስ ከፍ ያለ ባሕርይ ያላቸው ባለጠግነት፣ ክብር፣ ውበትና ተድላ ስለ ተገለጡላት ሌላውን ነገር ሁሉ እጅግ በታች እንዳለ አድርጋ ትመለከታለች።

እንግዲህ የታሰበልንን መጽናናት እንዳናጣ፣ በተለይ ልናስተውላቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች አሉ፦ 1. ይህ የድል ተስፋ የተሰጠለት እንዲህ ያለ ፍርድ ወይም አገዛዝ በውስጣችን የተቋቋመ መሆኑን፤ 2. በውስጣችን ያለው የክርስቶስ ፍርድ በእውነት ድል አድራጊ ይሆን ዘንድ ራሳችንን እንዴት መምራት እንዳለብን የሚያሳዩ አንዳንድ መመሪያዎችን።

በውስጣችን ያለው የክርስቶስ ፍርድ ድል አድራጊ እንደሚሆን የምናውቅባቸው ማስረጃዎች እነዚህ ናቸው፦ 1. ሥጋና ደም በተቃራኒው የቻለውን ቢናገርም፣ የክርስቶስን መንገዶች ሁሉ ትክክለኛነት ከተሞክሮ ማስረዳት ብንችል፣ እግዚአብሔርም ወደ ሰማይ ሊያመጣን በክርስቶስ የወሰደውን መንገድ በፈቃደኝነት ብንቀበል፣ ዘወትርም ከደረስንበት በላይ የሆነውን የጸጋ መጠን ብንወድድ፣ እርሱንም ለማግኘት ብናቅድና አስቀድመን ብናስብ። ሌሎች ሰዎች ሕሊናቸው በነቃ ጊዜ የአካሄዳቸውን ትክክለኛነት ማስረዳት አይችሉም። 2. የሃይማኖት ምክንያቶች በእኛ ዘንድ እጅግ ብርቱ ምክንያቶች ሲሆኑ፣ ከዓለማዊ ብልጠት ከሚመጡ ምክንያቶችም ይበልጥ ሲያሸንፉ። 3. ለዓላማዎቻችን እጅግ ታማኞች፣ ከሕጋችንም ጋር እጅግ ጽኑዎች ሆነን ምንም ተስፋ ወይም ፍርሃት ወደ ሌላ መንገድ ሊያዘነብለን ሳይችል፣ ዘወትር ከሕጋችን ጋር የሚስማማውንና የሚለየውን ስንመለከት። 4. እውነት ከሕይወታችን ይበልጥ የተወደደች ስለ ሆነች ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ የማንችል ስንሆን (2ኛ ቆሮንቶስ 13:8)፤ እውነት በማንኛውም ሥጋዊ ሰው ልብ ውስጥ ይህ ሉዓላዊነት የላትም። 5. በማን አገዛዝ ሥር እንደምንኖር የመምረጥ ነጻነት ቢኖረን እንኳ፣ በውስጥ ሰውነታችን በክርስቶስ አገዛዝ ደስ ስለሚለን፣ ከማንም በፊት እርሱን ብቻ እንዲገዛን ብንመርጥ፤ ይህ ከክርስቶስ ጋር አንድ አሳብ እንዳለን፣ ከፍቅር ጣፋጭ ግዳጅ በቀር በሌላ ሳንገደድ ወደ ክርስቶስ አገልግሎት የምንመጣ ነጻና በፈቃዳችን የምንገዛ ሕዝብ መሆናችንን ያሳያልና። በሁሉም ነገር ራሳችንን ለእርሱ አሳልፈን ለመስጠት ፈቃደኞች እስክንሆን ድረስ በክርስቶስ መንፈስ አገዛዝ ደስ ሲለን፤ ፈቃዳችን ወደ ፈቃዱ ሲመጣ ያን ጊዜ መንግሥቱ ወደ እኛ መጥቶአልና፤ መልካም ወይም ክፉ የሚያደርገን የፈቃዳችን ዝንባሌ ነውና።

6. በግፊትና በድንገተኛ ስሜት ሳይሆን በሥርዓት የተመራና ወጥ የሆነ ሕይወት በሥርዓት የተመራ ልብን ያሳያል፤ በሰዓት ውስጥ መዶሻው በትክክል ሲመታ፣ የሰዓቱም ቆጣሪ መርፌ በትክክል ሲያመለክት፣ መንኰራኵሮቹ በትክክል መገጣጠማቸው ምልክት እንደ ሆነ። 7. የክርስቶስ ፈቃድ ከማናቸውም ምድራዊ ኪሳራ ወይም ጥቅም ጋር በሚፎካከርበት ጊዜ፣ በዚያን ጊዜ በዚያ ልዩ ጉዳይ ልብ ለክርስቶስ ቢያጎነብስ፣ ይህ እውነተኛ ምልክት ነው፤ የጸጋ ኃይል እጅግ እውነተኛ ፈተና እኛን እጅግ በሚነኩን በእንደዚህ ያሉ ልዩ ጉዳዮች ውስጥ ነውና፤ በዚያ ርኵሰታችን ከሁሉ ይበልጥ ይበረታልና። ክርስቶስ በወንጌል ያንን ጐበዝ እጅግ ቀርቦ በነካው ጊዜ (ማቴዎስ 10:22)፣ በእርሱ ደቀ መዝሙር አጣ። 8. ለሥጋና ለዓለም አካሄድ ተቃራኒ ቢሆኑም ክርስቶስን ደስ የሚያሰኙ መንፈሳዊ ተግባራትን መፈጸም ስንችል። ደግሞም ተፈጥሮአችን ወደሚያዘነብልበትና እጅግ ወደሚያደላበት፣ ከዘመኑም ዝንባሌ ጋር ወደሚስማማውና ሌሎች ተገዝተው ወደሚኖሩበት ክፉ ነገር፣ እንደ በቀል መሻት፣ ጠላትን መጥላት፣ የግል ዓላማና እንደ መሳሰሉት፣ ራሳችንን ማሸነፍ ስንችል፣ ያን ጊዜ ጸጋ በውስጣችን ከተፈጥሮ በላይ፣ ሰማይም ከምድር በላይ እንደ ሆነ፣ ድልንም እንደሚያገኝ ይገለጣል።

ይህን ይበልጥ ለማብራራትና ራሳችንን በመፈተን እንዲረዳን፣ ሦስት የድል ደረጃዎች እንዳሉ ማወቅ አለብን፦ 1. ብንሸነፍም ስንቃወም፤ 2. ጸጋ በትግል ቢሆንም የበላይነት ሲያገኝ፤ 3. ርኵሰት ሁሉ ፈጽሞ ሲገዛ። እንግዲህ የመቃወም ብርታት ብቻ ቢኖረንም እንኳ፣ በውስጣችን ያለው የክርስቶስ አገዛዝ ድል አድራጊ እንደሚሆን ልናውቅ እንችላለን፤ ስለ ዲያብሎስ የተነገረው ስለ መንፈሳውያን ጠላቶቻችን ሁሉ ተነግሮአልና፤ ብንቃወማቸው በጊዜው ከእኛ ይሸሻሉ (ያዕቆብ 4:7)፤ ደግሞም ከገዛ ጸጋው ጋር የሚወግነው በእኛ ያለው በዓለም ካለው ይልቅ ታላቅ ነውና (1ኛ ዮሐንስ 4:4)። እንግዲህ በመቃወም ብቻ ድልን ተስፋ ማድረግ ከቻልን፣ መንፈስ የበላይነትን ባገኘ ጊዜ ምንን ተስፋ ልናደርግ አንችልም?

ገጽ 1 / 1 · 10 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ