ምዕራፍ 19 · 5 ደቂቃ ንባብ
ከሰው ዕጣ ፈንታ ጋር የሚስማማ ጸሎት
«እርሱም። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው።»—ማቴዎስ 22:20።
«እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር።»—ዘፍጥረት 1:26።
«ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?» ኢየሱስ ጠላቶቹ ሊያጠምዱት ባሰቡ ጊዜ ያከሸፋቸውና የግብርን ጉዳይ በተመለከተ ያለውን ግዴታ እልባት የሰጠው በዚህ ጥያቄ ነበር። ጥያቄውና በውስጡ ያለው መርሕ በሁሉም ስፍራ የሚሠሩ ናቸው፤ ከሰው ራሱ ይበልጥ ግን እውነትነታቸው የሚገለጥበት ስፍራ የለም። ሰው የተሸከመው መልክ ዕጣ ፈንታውን ይወስናል። የእግዚአብሔርን መልክ የተሸከመ በመሆኑ እርሱ የእግዚአብሔር ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ የተፈጠረበት ዓላማ ነው። ጸሎት ከመለኮታዊው መገኛው ጋር ያለው የድንቅ መመሳሰሉ አንድ ክፍል ነው፤ አንድም ሦስትም የሆነው አምላክ ብፅዕናውን በሚያገኝበት የፍቅር ኅብረት ጥልቅ ምሥጢር፣ ጸሎት ምድራዊ መልኩና ምሳሌው ነው።
ጸሎት ምን እንደ ሆነና በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ድንቅ ኃይል ይበልጥ ባሰላሰልን መጠን፣ በእግዚአብሔር ምክር ውስጥ እንዲህ ያለ ስፍራ የተሰጠው ሰው ማን ነው? ምንስ ነው? ብለን ለመጠየቅ ይበልጥ እንገደዳለን። ኃጢአት ሰውን እጅግ ከማዋረዱ የተነሣ፣ አሁን ካለበት ሁኔታ ተነሥተን ምን እንዲሆን ታስቦ እንደ ነበር ፈጽሞ መገመት አንችልም። የእግዚአብሔር ዓላማ ምን እንደ ነበረና ያን ዓላማ እንዲፈጽም ለሰው የተሰጡት ችሎታዎች ምን እንደ ነበሩ ለማወቅ፣ እግዚአብሔር ራሱ ስለ ሰው አፈጣጠር ወደ ሰጠው ምስክርነት መመለስ አለብን።
የሰው ዕጣ ፈንታ እግዚአብሔር በፍጥረት ጊዜ ከተናገረው ቃል በግልጽ ይታያል። ይኸውም ምድርን እንዲሞላ፣ እንዲገዛት፣ በእርሷና በውስጧ ባለው ሁሉ ላይ እንዲሠለጥን ነበር። እነዚህ ሦስቱም አባባሎች ሰው የእግዚአብሔር እንደ ራሴ ሆኖ እዚህ በምድር ላይ እንዲገዛ ታስቦ እንደ ነበረ ያሳዩናል። የእግዚአብሔር ምክትል ገዥ እንደ መሆኑ የእግዚአብሔርን ስፍራ ሊይዝ ነበረው፤ ራሱ ለእግዚአብሔር እየተገዛ፣ ሌላውን ሁሉ ለእርሱ እንዲገዛ ማድረግ ነበረበት። በምድር ላይ የሚደረገው ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲደረግ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ የምድር ታሪክ ሙሉ በሙሉ በእጁ ሊሆን ነበረው።
ሊይዘው የነበረው ስፍራና በእጁ የነበረው ኃይል ከእንዲህ ያለው ዕጣ ፈንታ ጋር የሚስማማ ነበር። አንድ ምድራዊ ንጉሥ ወደ ሩቅ አውራጃ እንደ ራሴ ሲልክ፣ እንደ ራሴው ስለሚከተለው መርሕ ምክር እንደሚሰጥና ምክሩም ተግባራዊ እንደሚሆን፣ እንዲሁም መርሑን ለማስፈጸም ወይም የመንግሥቱን ክብር ለመጠበቅ የሚያስፈልጉትን ወታደሮችና ሌሎች መሣሪያዎች ለመጠየቅ ነጻነት እንዳለው ይታወቃል። መርሑ ተቀባይነት ካላገኘ፣ የንጉሡን ፍላጎት ይበልጥ ለሚረዳ ለሌላ ሰው ስፍራውን እንዲለቅ ይጠራል፤ እስከ ታመነ ድረስ ግን ምክሩ ይፈጸማል። ሰውም እንዲሁ የእግዚአብሔር እንደ ራሴ ሆኖ ሊገዛ ነበረው፤ ሁሉ በፈቃዱና በአገዛዙ ሥር ሊደረግ፣ በምክሩና በልመናውም ሰማይ በምድር ላይ በረከቱን ሊያፈስ ነበረው። በሰማይ ባለው ንጉሥና የዚህ ዓለም ጌታ በሆነው በታማኝ አገልጋዩ በሰው መካከል ያለው ግንኙነት የሚጠበቅበት ድንቅ፣ ሆኖም ቀላልና እጅግ ተፈጥሯዊ መስመር ጸሎቱ ሊሆን ነበረው። የዓለም ዕጣ ፈንታ በሰው ምኞት፣ ፈቃድና ጸሎት ሥልጣን ሥር ተሰጥቶ ነበር።
በኃጢአት ምክንያት ይህ ሁሉ አስከፊ ለውጥ ደረሰበት፤ የሰው ውድቀት ፍጥረትን ሁሉ ከእርግማን በታች አደረገው። በቤዛነት ደግሞ የክቡር መታደስ ጅማሬ ታየ። እግዚአብሔር ነገሥታት፣ አዎን፣ ታላቁ ንጉሥ የሚወጡበትን ሕዝብ ለራሱ በአብርሃም ማዘጋጀት እንደ ጀመረ ወዲያውኑ፣ የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ጸሎት ከእርሱ ጋር የሚገናኙትን ሰዎች ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ምን ያህል ኃይል እንዳለው እናያለን። ጸሎት ለራሳችን በረከትን የምናገኝበት መንገድ ብቻ፣ ወይም በዋናነት፣ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን የሰዎችን ዕጣ ፈንታና እነርሱን የሚገዛውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመንካት የሚሠራበት የንጉሣዊ መብቱ መግለጫ እንደ ሆነ በአብርሃም እናያለን። አብርሃም ለራሱ ሲጸልይ አንድ ጊዜ እንኳ አናገኘውም። ለሰዶምና ለሎጥ፣ ለአቢሜሌክ፣ ለእስማኤል ያቀረበው ጸሎት፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ሰው በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ታሪክ ለመቅረጽ ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያረጋግጣል።
ይህ ከመጀመሪያው የሰው ዕጣ ፈንታ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ከፍ ያለ ጥሪ ለሰው እንዴት ሊያደራ እንደ ቻለም ያስተምረናል። ይህም በራሱ መልክና ምሳሌ ስለ ፈጠረው ነበር። የውጭው አገዛዝ ያለ ውስጣዊ ብቃት አልተሰጠውም ነበር፤ በመሠልጠንና የሁሉ ጌታ በመሆን የእግዚአብሔርን መልክ መሸከሙ ሥሩ በውስጣዊው መመሳሰል፣ በባሕርዩ ውስጥ ነበር። በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ውስጣዊ ስምምነትና መግባባት፣ የጅማሬ እግዚአብሔርን መምሰልም ነበር፤ ይህም ሰውን በእግዚአብሔርና በዓለሙ መካከል መካከለኛ እንዲሆን እውነተኛ ብቃት ሰጠው፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመተርጎም፣ የፍጥረትን ፍላጎት ለማቅረብ፣ የእግዚአብሔርን ልግስና ለመቀበልና ለማደል ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ ሊሆን ነበረውና። የእግዚአብሔርን አገዛዝ ሊሸከም የቻለው የእግዚአብሔርን መልክ በመሸከሙ ነበር፤ በእርግጥም እግዚአብሔርን እጅግ ይመስል ነበር፤ ወደ እግዚአብሔር ዓላማ ለመግባትና ዕቅዱን ለመፈጸም እጅግ ችሎታ ነበረው፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ዓለም የሚያስፈልገውን የመለመንና የማግኘት ድንቅ መብት ሊያደራው ቻለ። ኃጢአት የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለጊዜው ቢያደናቅፍም፣ ጸሎት ሰው ባይወድቅ ኖሮ ሊሆን የሚችለውን ሆኖ ይቀራል፤ ይኸውም ሰው እግዚአብሔርን የመምሰሉ ማረጋገጫ፣ ከማይታየው ዘላለማዊ አምላክ ጋር የሚገናኝበት መንገድ፣ የዓለማትን ዕጣ ፈንታ የያዘውን እጅ ለመያዝ የተፈቀደለት ኃይል ነው። ጸሎት ምሕረትን የሚለምን ሰው ጩኸት ብቻ አይደለም፤ ሰው ከመለኮት መገኘቱን አውቆ፣ በንጉሣዊ ነጻነት የዘላለማዊውን አምላክ ምክር አስፈጻሚ እንዲሆን የተፈጠረና ለዚያም ችሎታ ያለው መሆኑን ተረድቶ፣ ፈቃዱን የሚገልጥበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ነው።
ኃጢአት ያጠፋውን ጸጋ መልሶታል። የፊተኛው አዳም ያጣውን ሁለተኛው መልሶ አግኝቶታል። ሰው በክርስቶስ የቀድሞ ስፍራውን መልሶ ያገኛል፤ በክርስቶስ የምትኖረው ቤተ ክርስቲያንም «የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል» የሚለውን ተስፋ ትወርሳለች። እንዲህ ያለው ተስፋ በመጀመሪያ ደረጃ ለራሳችን የሚያስፈልገንን ጸጋ ወይም በረከት በፍጹም አያመለክትም። ይልቁንም እንደ እርሱ ለአብ ሥራና ክብር ብቻ የሚኖሩ፣ የሰማያዊው የወይን ግንድ ፍሬ የሚያፈሩ ቅርንጫፎች ከመሆናችን ስፍራ ጋር ይያያዛል። ይህ ተስፋ በእርሱ ለሚኖሩ፣ ከመታዘዝና ራስን ከመሠዋት ሕይወቱ ጋር በእርሱ ሊኖሩ ራሳቸውን ለተዉ፣ ሕይወታቸውን አጥተው በእርሱ ላገኙ፣ አሁንም ሙሉ በሙሉ ለአብና ለመንግሥቱ ጉዳይ ራሳቸውን ለሰጡ ነው። አዲሱ ፍጥረታቸው ወደ ቀድሞው ዕጣ ፈንታቸው እንደ መለሳቸው፣ የእግዚአብሔርን መልክና ምሳሌ፣ ከእርሱም ጋር የመሠልጠንን ኃይል እንደ መለሰላቸው የሚረዱት እነዚህ ናቸው። እንደ እነዚህ ያሉት እያንዳንዳቸው በየክበባቸው የሰማይን ኃይላት በዚህ በምድር ላይ ለማግኘትና ለማደል በእርግጥ ኃይል አላቸው። በቅዱስ ድፍረት የሚፈልጉትን ማስታወቅ ይችላሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ካህናት ይኖራሉ፤ እንደ ነገሥታትም ሊመጣ ያለው የዓለም ኃይል በእጃቸው መሆን ይጀምራል። «የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል» ወደሚለው ተስፋ ፍጻሜ ይገባሉ።
የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ሆይ! ጥሪሽ ከምታውቂው ይልቅ ከፍ ያለና የተቀደሰ ነው። እግዚአብሔር ለእርሱ ነገሥታትና ካህናት በሆኑት ብልቶችሽ በኩል ዓለምን ሊገዛ ይወዳል፤ ጸሎታቸው የሰማይን በረከት ያሰጣል፣ ይከለክላልም። ራሳቸው በመዳናቸው ብቻ በማይረኩ፣ ነገር ግን በወልድ በኩል እንደሚያደርገው አብ በእነርሱም በኩል ክቡር ምክሩን ሁሉ ይፈጽም ዘንድ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ በሚሰጡ ምርጦቹ፣ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ በሚጮኹ በእነዚህ ምርጦቹ፣ እግዚአብሔር የሰው የመጀመሪያ ዕጣ ፈንታ ምን ያህል ድንቅ እንደ ነበረ ሊያረጋግጥ ይወዳል። ሰው በምድር ላይ የእግዚአብሔርን መልክ የተሸከመ እንደ መሆኑ፣ ምድር በእርግጥ በእጁ ተሰጥታ ነበር። እርሱ በወደቀ ጊዜ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደቀ፤ ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ ይኖራል። አሁን ግን ተቤዥቷል፤ የቀድሞው ክብሩ መታደስ ጀምሯል። የዘላለም ዓላማው መፈጸምና የመንግሥቱ መምጣት፣ በክርስቶስ እየኖሩ ራስ በሆናቸው በእርሱ፣ በታላቁ ካህንና ንጉሥ፣ ስፍራቸውን ለመያዝ በተዘጋጁና በጸሎታቸውም አምላካቸው ምን እንዲያደርግ እንደሚፈልጉ ለመናገር በሚደፍሩ ሕዝቡ ላይ እንዲመሠረት በእርግጥ የእግዚአብሔር ዓላማ ነው። በምድር ላይ የእግዚአብሔርን መልክ የተሸከመና እንደ ራሴው እንደ መሆኑ፣ የተቤዠው ሰው በጸሎቱ የዚህችን ምድር ታሪክ መወሰን አለበት። ሰው የተፈጠረው፣ አሁንም እንደ ገና የተቤዠው፣ እንዲጸልይና በጸሎቱም እንዲሠለጥን ነው።
«ጌታ ሆይ፥ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን።»
ጌታ ሆይ! ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጎበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? ከመላእክት ጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት። በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛህለት። አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ እንዴት ድንቅ ነው!
ጌታ አምላክ ሆይ! ኃጢአት ሰውን እንዴት ያለ ዝቅታ ላይ አወረደው! አገልጋይህና እንደ ራሴህ የመሆኑን መለኮታዊ ዕጣ ፈንታውን እንኳ እስከማያውቅ ድረስ አእምሮውን እንዴት እጅግ አጨለመው! ወዮ! ሕዝብህ እንኳ ዓይናቸው በተከፈተ ጊዜ ጥሪያቸውን ለመቀበልና ሰዎችን ይባርኩ ዘንድ በሰዎችም ዘንድ ኃይል እንዲኖራቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ኃይልን ለመሻት ምንኛ ዝግጁ አይደሉም!
ጌታ ኢየሱስ ሆይ! አብ ሰውን እንደ ገና የክብርና የምስጋና ዘውድ የጫነለትና እርሱ እንድንሆን የሚወደውን እንድንሆን መንገድ የከፈተልን በአንተ ነው። ጌታ ሆይ፣ ሕዝብህን ማር፣ ርስትህንም ጎብኝ! በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ በኃይል ሥራ፤ የሚያምኑትን ደቀ መዛሙርትህንም በንጉሣዊ ክህነታቸውና አንተ እንዲህ ያለ ድንቅ ተስፋ በሰጠኸው በጸሎት ኃይል መንግሥትህን ለማገልገል፣ በአሕዛብ ላይ ለመሠልጠንና የእግዚአብሔርን ስም በምድር ሁሉ ላይ ለማክበር እንዲወጡ አስተምራቸው። አሜን።
ምዕራፍ 19 ተጠናቋል
ከሰው ዕጣ ፈንታ ጋር የሚስማማ ጸሎት