ከክርስቶስ ጋር በጸሎት ትምህርት ቤት
ጸሎት ሠራተኞችን ያስገኛል

ምዕራፍ 10 · 6 ደቂቃ ንባብ

ጸሎት ሠራተኞችን ያስገኛል

«በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።»—ማቴዎስ 9:37-38።

ጌታ ደቀ መዛሙርቱን እንዲጸልዩ፣ እንዲሁም እንዴት እንደሚጸልዩ ብዙ ጊዜ አስተምሯቸዋል፤ ስለ ምን እንደሚጸልዩ ግን እምብዛም አልነገራቸውም። ይህን ለራሳቸው የችግር ስሜትና ለመንፈስ ምሪት ተወው። እዚህ ግን እንዲያስታውሱት በግልጽ ያዘዛቸው አንድ ነገር አለ፦ መከሩ ብዙ፣ አጫጆችም የሚያስፈልጉ ከመሆናቸው አንጻር ሠራተኞችን እንዲልክ ወደ መከሩ ጌታ መጮኽ አለባቸው። በእኩለ ሌሊት ወደ ወዳጁ ስለ ሄደው ሰው በተናገረው ምሳሌ ጸሎት ለራስ ብቻ የሚደረግ እንዳልሆነ እንዲያስተውሉ እንደ ፈለገ፣ እዚህም ጸሎት ለሌሎች በረከት የሚመጣበት ኃይል መሆኑን ያሳያቸዋል። አብ የመከሩ ጌታ ነው፤ ስለ መንፈስ ቅዱስ በምንጸልይበት ጊዜ፣ ለሥራው ሠራተኞችን እንዲያዘጋጅና እንዲልክ ልንጸልይ ይገባናል።

ደቀ መዛሙርቱን ስለዚህ ነገር እንዲጸልዩ መጠየቁ እንግዳ ነገር አይደለምን? እርሱ ራሱ መጸለይ አይችልምን? ከእነርሱ ሺህ ጸሎት ይልቅ የእርሱ አንድ ጸሎት አይበልጥምን? የመከሩ ጌታ እግዚአብሔርስ ችግሩን አላየውምን? ያለ እነርሱ ጸሎትስ በራሱ መልካም ጊዜ ሠራተኞችን አይልክምን? እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች ወደ ጸሎት ጥልቅ ምሥጢራትና በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ወዳለው ኃይሉ ያደርሱናል። ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ ጸሎት በእርግጥ ኃይል መሆኑን፣ የመከሩ መሰብሰብና የመንግሥቱ መምጣትም በእውነት በእርሱ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ያሳምነናል።

ጸሎት ሥርዓት ወይም ለታይታ የሚደረግ ነገር አይደለም። ጌታ ኢየሱስ ራሱ እውነት ነበረ፤ የተናገረው ሁሉ ጥልቅ እውነት ነበረ። (ቁጥር 36ን ተመልከት) «ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው»፤ በዚያን ጊዜ ነበር ደቀ መዛሙርቱን ሠራተኞች ወደ እነርሱ እንዲላኩ እንዲጸልዩ የጠራቸው። ይህን ያደረገው ጸሎታቸው በእርግጥ እንደሚያስፈልግና እንደሚረዳ ስላመነ ነው። የማይታየውን ዓለም ከእኛ እጅግ የሚሰውረው መጋረጃ ለኢየሱስ ቅዱስ ሰብአዊ ነፍስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ግልጽ ነበረ። በመንፈሳዊው ዓለም ያለውን የተሰወረ የምክንያትና የውጤት ትስስር ለረጅም ጊዜ፣ በጥልቀትና አርቆ ተመልክቶት ነበር። እግዚአብሔር እንደ አብርሃምና ሙሴ፣ እንደ ኢያሱ፣ ሳሙኤልና ዳንኤል ያሉትን ሰዎች በጠራና በስሙ በሰዎች ላይ ሥልጣን በሰጣቸው ጊዜ፣ በዚያው ጊዜ የሰማይን ኃይላት በሚያስፈልጓቸው ጊዜ ለእርዳታቸው የመጥራት ሥልጣንና መብት እንደ ሰጣቸው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ አስተውሎ ነበር። የእግዚአብሔር ሥራ ለእነዚያ የቀድሞ ሰዎች፣ ለራሱም ለጥቂት ጊዜ እዚህ በምድር ላይ እንደ ተሰጠ፣ አሁን ደግሞ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እጅ ሊተላለፍ መሆኑን ያውቅ ነበር። ይህ ሥራ በአደራ በተሰጣቸው ጊዜ ሥርዓት ወይም ለታይታ ብቻ የሚደረግ ነገር እንደማይሆን፣ ይልቁንም የሥራው መከናወን በእርግጥ በእነርሱና በታማኝነታቸው ወይም ባለመታመናቸው ላይ እንደሚመሠረት ያውቅ ነበር። ኢየሱስ በሰው አካልና በሰው ሕይወት ገደብ ውስጥ እንዳለ አንድ ግለ ሰብ፣ በዙሪያው በሚያያቸው በእነዚህ በሚቅበዘበዙ በጎች መካከል አጭር ጉብኝት ምን ያህል ጥቂት ሊፈጽም እንደሚችል ይሰማዋል፤ በሚገባም እንዲጠበቁ እርዳታን ይናፍቃል። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱን አሁኑኑ መጸለይ እንዲጀምሩ፣ ሥራውንም በምድር ላይ ከእርሱ በተረከቡ ጊዜ ይህን ከጸሎታቸው ዋና ዋና ልመናዎች አንዱ እንዲያደርጉት ይነግራቸዋል፦ የመከሩ ጌታ ራሱ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ። ሥራውን በአደራ የሰጣቸውና በዚህ ያህል መጠን በእነርሱ ላይ እንዲመሠረት ያደረገው እግዚአብሔር፣ የሚረዱ ሠራተኞችን ከእርሱ እንዲለምኑ ሥልጣን ይሰጣቸዋል፤ የሠራተኞቹም መገኘት በጸሎታቸው ላይ እንዲመሠረት ያደርጋል።

ለመከር በነጡት በዓለም እርሻዎች ውስጥ ያለውን የሠራተኞች እጦት ክርስቲያኖች በእውነት የሚሰማቸውና የሚያዝኑበት ምንኛ ጥቂት ነው! የሠራተኞቻችን መገኘት በጸሎት ላይ እንደሚመሠረት፣ ጸሎትም በእርግጥ «የሚፈልገውን ሁሉ» እንደሚያስገኝ የሚያምኑትስ ምንኛ ጥቂት ናቸው! የሠራተኞች እጥረት አይታወቅም ወይም አይወራበትም ማለት አይደለም። ጕድለቱን ለመሙላት አንዳንድ ጊዜ ጥረት አይደረግም ማለትም አይደለም። ነገር ግን የመከሩ ጌታ ለጸሎት መልስ ሠራተኞችን እንደሚልክ በሚያምን እምነት፣ ያለዚህ ጸሎትም ለማጨድ የደረሱ እርሻዎች ጠፍተው እንደሚቀሩ በሚያውቅ ጥልቅ እርግጠኝነት፣ እረኛ እንደሌላቸው የሚቅበዘበዙ በጎች ሸክም በእውነት የሚሸከሙት ምንኛ ጥቂት ናቸው! ሆኖም ነገሩ እንዲሁ ነው። ሥራውን ለቤተ ክርስቲያኑ እጅ መስጠቱ እጅግ ድንቅ ነው፤ ጌታ ሥራው በእነርሱ ብቻ ሊሠራ በሚችልበት አካሉ በሆኑት በእነርሱ ላይ ራሱን እጅግ ጥገኛ አድርጓል፤ ጌታ በሰማይና በምድር እንዲጠቀሙበት ለሕዝቡ የሰጠው ኃይልም እጅግ እውነተኛ ነው፤ ስለዚህ የሠራተኞቹ ቁጥርና የመከሩ መጠን በእርግጥ በጸሎታቸው ላይ የተመሠረተ ነው።

እንዴት ያለ ከባድ ሐሳብ ነው! ታዲያ የጌታን ትእዛዝ በሙሉ ልባችን የማንታዘዘውና ስለ ሠራተኞች አጥብቀን የማንጮኸው ለምንድን ነው? ለዚህ ሁለት ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው፦ ይህን የጸሎት ጥያቄ የወለደው የኢየሱስ ርኅራኄ ይጎድለናል። አማኞች ባልንጀራቸውን እንደ ራሳቸው መውደድ፣ በሰዎችም መካከል ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ክብር መኖር አብ ለተቤዣቸው ልጆቹ የሰጠው የመጀመሪያ ትእዛዝ መሆኑን ሲማሩ፣ የሚጠፉትን ጌታቸው በአደራ የሰጣቸው ኃላፊነት አድርገው ይቀበሏቸዋል። እነርሱንም የሥራ መስክ ብቻ ሳይሆን የፍቅራዊ እንክብካቤና የትኩረት ተቀባዮች አድርገው ሲቀበሏቸው፣ ተስፋ ቢስ ሆነው ለሚጠፉት ያለው ርኅራኄ ልባቸውን ሊነካ ብዙ አይቆይም፤ እስከዚያን ጊዜም ድረስ ባልታወቀ ትጋት፦ ጌታ ሆይ! ሠራተኞችን ላክ የሚል ጩኸት ወደ ላይ ይወጣል። ትእዛዙን ቸል ለማለታችን ሁለተኛው ምክንያት የሆነው የእምነት ጕድለት ከዚያ በኋላ ይታወቃል፤ ርኅራኄያችን ለእርዳታ ሲማልድ ግን ይሸነፋል። የተወሰነ ውጤት ለማምጣት ባለው የጸሎት ኃይል የምናምነው እጅግ ጥቂት ነው። ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጥ በዚህ መተማመን እንድንችል፣ ወደ እግዚአብሔር በበቂ ሁኔታ ተጠግተን አንኖርም፤ ለአገልግሎቱና ለመንግሥቱም ሙሉ በሙሉ በበቂ ሁኔታ ራሳችንን አልሰጠንም። እንግዲህ ርኅራኄው ወደ እኛ እንዲፈስስ፣ መንፈሱም ጸሎታችን እንደሚጠቅም ሊያረጋግጥልን እንዲችል ከክርስቶስ ጋር አንድ ለሆነ ሕይወት እንጸልይ።

እንዲህ ያለው ጸሎት ሁለት እጥፍ በረከትን ይለምናል፣ ያገኛልም። በመጀመሪያ ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሰጡ ሰዎች እንዲበዙ ይመኛል። ለጌታ አገልግሎት እንደ አገልጋዮች፣ ሚስዮናውያን ወይም የእግዚአብሔር ቃል አስተማሪዎች የሚሆኑ ሰዎች በእርግጥ የማይገኙበት ጊዜ መኖሩ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያለ አስከፊ ነውር ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ይህን ለራሳቸው ክበብ ወይም ቤተ ክርስቲያን የልመና ጕዳይ ሲያደርጉት ይሰጣል። ጌታ ኢየሱስ አሁን የመከሩ ጌታ ነው። ስጦታዎችን ይሰጥ ዘንድ ከፍ ከፍ ብሏል—የመንፈስን ስጦታዎች። ዋነኞቹ ስጦታዎቹም በመንፈስ የተሞሉ ሰዎች ናቸው። የስጦታዎቹ መገኘትና መከፋፈል ግን በራስና በብልቶች ኅብረት ሥራ ላይ የተመሠረተ ነው። ወደዚህ ዓይነቱ ኅብረት ሥራ የሚመራው ጸሎት ነው፤ በእምነት የሚለምኑትም ለሥራው ሰዎችንና ገንዘብን እንዲያገኙ ይነቃቃሉ።

የሚለመነው ሁለተኛው በረከትም ያነሰ አይደለም። እያንዳንዱ አማኝ ሠራተኛ ነው፤ ለአገልግሎት ያልተዋጀና የሚጠብቀው ሥራ የሌለው አንድም የእግዚአብሔር ልጅ የለም። በወይኑ አትክልት ውስጥ አንድ እንኳ ሥራ ፈትቶ ቆሞ እንዳይገኝ ጌታ ሕዝቡን ሁሉ በመሰጠት መንፈስ እንዲሞላ ጸሎታችን ሊሆን ይገባል። በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ ረዳቶች ወይም ብቁ ረዳቶች ጠፍተዋል የሚል ቅሬታ ባለበት ሁሉ፣ ጸሎት የመገኘታቸው ተስፋ አለው። እግዚአብሔር ለማቅረብ ያልተዘጋጀበትና የማይችልበት የሰንበት ትምህርት ቤት ወይም የቤት ለቤት ጉብኝት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወይም የማዳን ሥራ የለም። ጊዜና ንዝነዛ ሊያስፈልግ ይችላል፤ የመከሩን ጌታ እንድንለምን የክርስቶስ ትእዛዝ ግን ጸሎቱ እንደሚሰማ ዋስትና ነው፦ «እላችኋለሁ፥ … ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።»

እንዴት ያለ ከባድና የተባረከ ሐሳብ ነው! የዓለምን ችግር ለማሟላት፣ ለእግዚአብሔር ሥራም አገልጋዮችን ለማግኘት ይህ ኃይል በጸሎት ተሰጥቶናል። የመከሩ ጌታ ይሰማል። በተለየ ሁኔታ እንዲህ እንድንጸልይ የጠራን ክርስቶስ በስሙና ለእርሱ ጕዳይ የምናቀርባቸውን ጸሎቶቻችንን ይደግፋል። ጊዜ ለይተን ለዚህ የምልጃ ሥራችን ክፍል ራሳችንን እንስጥ። ጸሎታችንን እንዲጠይቅ ወደ ገፋፋው ወደዚያ ርኅሩኅ ልቡ ኅብረት ያስገባናል። ፈቃዳቸው በታላቁ እግዚአብሔር ዘንድ ለመንግሥቱ መስፋፋት ዋጋ እንዳለው ሰዎች፣ ንጉሣዊ ስፍራችንን ወደማስተዋል ከፍ ያደርገናል። በሥራው ድርሻ በእውነትና በቁም ነገር በአደራ የተሰጠን፣ በምድር ላይ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ መሆናችንን በእውነት እንዲሰማን ያደርገናል። ለጸሎታችን መልስ፣ ያለ እርሱ ባልመጣ ነበር በረከት እንደ ተሰጠ ስናውቅ፣ በኢየሱስ የነፍስ ምጥ ብቻ ሳይሆን በነፍሱ እርካታም ተካፋዮች ያደርገናል።

«ጌታ ሆይ፥ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን።»

ብሩክ ጌታ ሆይ! ዛሬም እንደ ገና ከድንቅ ትምህርቶችህ ሌላውን እንድንማር ሰጠኸን። በትሕትና እንለምንሃለን፦ ስትናገርባቸው የነበሩትን መንፈሳዊ እውነታዎች በትክክል እንድናይ ስጠን። ያ እጅግ ሰፊ የሆነውና የሚጠፋው መከር አለ፤ ሠራተኞች እንዲመጡ ምልክት እንዲሰጡ የሚያንቀላፉትን ደቀ መዛሙርት ይጠብቃል። ጌታ ሆይ፥ በርኅራኄና በሐዘኔታ በተነካ ልብ እንድንመለከተው አስተምረን። እጅግ ጥቂቶች የሆኑት ሠራተኞች አሉ። ጌታ ሆይ፥ ይህ ምልክቱ የሆነው የጸሎትና የእምነት ጕድለት ኃጢአት ምን ያህል አስከፊ እንደ ሆነ አሳየን። ሊልካቸውም የሚችለውና የተዘጋጀው የመከሩ ጌታ አለ። ጌታ ሆይ፥ መልሱን ያቈራኘበትን ጸሎት በእርግጥ እንዴት እንደሚጠብቅ አሳየን። የመጸለይ አደራ የተሰጣቸው ደቀ መዛሙርትም አሉ፦ ጌታ ሆይ፥ ርኅራኄህና በተስፋ ቃልህ ያለው እምነት ወደማያቋርጥና ወደሚያሸንፍ ጸሎት እንዲያነቃቸው መንፈስህን እንዴት በእነርሱ ላይ ልታፈስስና እፍ ልትልባቸው እንደምትችል አሳየን።

ጌታችን ሆይ! እንደዚህ ያለውን ሥራ በአደራ እንዴት እንደምትሰጥ፣ እንዲህ ያለውንም ኃይል እጅግ ለሰነፉና ታማኝ ላልሆኑ ሰዎች እንዴት እንደምትሰጥ ልናስተውል አንችልም። ሠራተኞች እንዲላኩ ቀንና ሌሊት እንዲጮኹ ለምታስተምራቸው ሁሉ እናመሰግንሃለን። ጌታ ሆይ፥ ለዚህ ለአንድ ነገር ብቻ—ለጌታቸው መንግሥትና ክብር—መኖርን እንዲማሩ፣ ጸሎታቸው ምን ሊፈጽም እንደሚችል ወደሚያምኑበት እምነትም ፈጽመው እንዲነቁ፣ የራስህን መንፈስ በልጆችህ ሁሉ ላይ እፍ በል። በሕያው እግዚአብሔር ላይ በፍቅራዊ እምነት የሚቀርብ ጸሎት እርግጠኛና የተትረፈረፈ መልስ እንደሚያመጣ በዚህም እንደ ሌላው ልመና ሁሉ ልባችን ሁሉ በመተማመን ይሞላ። አሜን።

ገጽ 1 / 1 · 6 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል