ምዕራፍ 1 · 3 ደቂቃ ንባብ
መቅድም
«በእኔ ኑሩ» ከሚለው ትእዛዝ ጋር ከተያያዙት ተስፋዎች ሁሉ፣ ከዚህኛው የሚበልጥ፣ «አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም» የሚለውንም ኑዛዜ ከእርሱ ይልቅ ፈጥኖ የሚያስገኝ ምንም የለም፤ እርሱም ይህ ነው፦ «በእኔ ብትኖሩ … የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።» በእግዚአብሔር ፊት ኃይል ማግኘት፣ ሙሉ በሙሉ በእርሱ የመኖር ሕይወት ከሚደርስባቸው ከፍታዎች ሁሉ የላቀው ነው።
ክርስቶስን ከሚመስል ሕይወት ባሕርያት ሁሉ ደግሞ፣ እርሱ አሁን በአብ ፊት ያለማቋረጥ በተያዘበት ሥራ፣ ማለትም ሁሉን በሚያሸንፈው ምልጃው፣ እርሱን ከመምሰል የሚበልጥና የሚከብር የለም። በእርሱ ይበልጥ በኖርንና እርሱን ወደ መምሰል ባደግን መጠን፣ የካህንነት ሕይወቱ በእኛ ውስጥ በብርቱ ይሠራል፤ ሕይወታችንም እንደ እርሱ ሕይወት ይሆናል፤ ይኸውም ስለ ሰዎች ዘወትር የሚማልድና የሚያሸንፍ ሕይወት ነው።
«ለአምላካችን ነገሥታትና ካህናት አደረግኸን።» በንጉሥም በካህንም ዘንድ ዋናው ነገር ኃይል፣ ተጽዕኖና በረከት ነው። በንጉሥ ዘንድ ኃይሉ ወደ ታች ይወርዳል፤ በካህን ዘንድ ግን ኃይሉ ወደ ላይ ይወጣል፣ በእግዚአብሔርም ፊት ያሸንፋል። ብሩክ ካህናችንና ንጉሣችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የንግሥናው ኃይል በክህነቱ ላይ የተመሠረተ ነው፦ «ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና … ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።» የእርሱ ካህናትና ነገሥታት በሆንነው በእኛም ዘንድ ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛውን ኃይልዋን የምታገኘውና የምትጠቀምበት በምልጃ ነው፤ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ብልትም ከእስራኤል መወለዱን የሚያረጋግጠው በዚሁ ነው፤ እስራኤል እንደ አለቃ ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ኃይል ነበረው፣ አሸንፎአልም።
ይህ መጽሐፍ የተጻፈው፣ በክርስትና ሕይወት ውስጥ የጸሎት ስፍራና ኃይል በሚገባ አልተረዳም የሚል ጥልቅ ስሜት ስላደረብኝ ነው። ጸሎትን በዋናነት የራሳችንን የክርስትና ሕይወት የምንጠብቅበት መንገድ አድርገን እስከ ተመለከትነው ድረስ፣ ምን እንዲሆን እንደ ታሰበ በሙላት እንደማናውቅ እርግጠኛ ነኝ። ነገር ግን ለእኛ በአደራ ከተሰጠን ሥራ ሁሉ ከፍተኛው ክፍል፣ የሌላውም ሥራ ሁሉ ሥርና ብርታት አድርገን ልንመለከተው ስንማር፣ በትክክል የመጸለይን ጥበብ ያህል ልናጠናውና ልንለማመደው የሚያስፈልገን ምንም ነገር እንደሌለ እናያለን። ጌታችን ስለ ጸሎት የሰጠውን ደረጃ በደረጃ የሚያድግ ትምህርት፣ እንዲሁም የመጨረሻዪቱ ሌሊት ድንቅ ተስፋዎች (ዮሐንስ 14:16) በስሙ ልንሠራቸው ከሚገቡን ሥራዎች፣ ከሚበልጡትም ሥራዎች፣ ብዙ ፍሬ ከማፍራትም ጋር ያላቸውን ግልጽ ግንኙነት በመጠኑም ቢሆን ለማሳየት ተሳክቶልኝ ከሆነ፣ የክርስቶስ ኃይል ለቤተ ክርስቲያን ሲገለጥ ልንጠብቅ የምንችለው ቤተ ክርስቲያን ራስዋን ለዚህ ቅዱስ የምልጃ ሥራ አሳልፋ ስትሰጥ ብቻ መሆኑን ሁላችንም እንቀበላለን። እግዚአብሔር ልጆቹ እንዲይዙት የሚጠብቀውን፣ የደከመውም ዓለም ደግሞ የሚጠብቀውን ያንን ድንቅ የኃይልና የተጽዕኖ ስፍራ ለአንዳንድ ልጆቹ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ይህችን ትንሽ መጽሐፍ እንዲጠቀምባት ጸሎቴ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ የኢየሱስን የጸሎት ትምህርት ሳጠና በሚደንቅ ግልጽነት ወደ እኔ የመጣ ሌላ እውነት አለ። እርሱም ይህ ነው፦ አብ እያንዳንዱን የእምነት ጸሎት ሊሰማ፣ የምንወደውንና በኢየሱስ ስም የምንለምነውን ሁሉ ሊሰጠን ይጠብቃል። የአምላካችንን ድንቅ ፍቅርና ሰፊ ተስፋዎች መገደብን እጅግ ስለ ለመድን፣ የጌታችንን እጅግ ቀላልና ግልጽ ቃላት እንኳ፣ በምንጠብቃቸውና በምንተረጕማቸው ገዳቢ ሐረጎች ሳናጅብ ማንበብ አንችልም። ቤተ ክርስቲያን ልትማረው የሚያስፈልጋት አንድ ነገር አለ ብዬ የማስበው ቢኖር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ጸሎት መልስ እንዲያገኝ ያስባል፤ ጸሎቱ እንደሚሰማ ለማመን ራሱን ለሰጠ ልጁ እግዚአብሔር የሚያደርግለትም ነገር በሰውም ልብ ያልታሰበው ነው። እግዚአብሔር ጸሎትን ይሰማል፤ ይህ በሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እውነት ነው፤ ነገር ግን ትርጕሙን የሚረዱት ወይም ኃይሉን የሚለማመዱት እጅግ ጥቂቶች ናቸው። የጻፍሁት ነገር አንባቢዬን ወደ መምህሩ ቃላት እንዲሄድና ድንቅ ተስፋዎቹን እንደ ተጻፉ በቀላሉና ቃል በቃል እንዲቀበል ቢያነሣሣው፣ ዓላማዬ ተፈጽሞአል።
ደግሞም አንድ ነገር ብቻ ልጨምር። በእነዚህ የመጨረሻ ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ክርስቶስ እንዴት ፈጽሞ ሕይወታችን እንደ ሆነ፣ በእኛም ውስጥ የሚያስፈልገንን ሁሉ ለመሆንና ለማድረግ እንዴት ኃላፊነት እንደሚወስድ በመማር የማይነገር በረከት አግኝተዋል። ይህን እውነት በጸሎት ሕይወታችን ላይ ተግባራዊ ማድረግን ገና እንደ ተማርን አላውቅም። ብዙዎች በእምነት ለመጸለይ፣ ውጤታማውን፣ በሥራዋ እጅግ ኃይል የምታደርገውን ጸሎት ለመጸለይ ኃይል እንደሌላቸው ያማርራሉ። ላደርስላቸው የምመኘው መልእክት ይህ ነው፦ ብሩኩ ኢየሱስ ይህን ሊያስተምራቸው ይጠብቃል፣ ይናፍቃልም። ክርስቶስ ሕይወታችን ነው፤ በሰማይ ዘወትር ሊጸልይ በሕይወት ይኖራል፤ በእርሱ ብቻ ብንታመን፣ በእኛ ውስጥ ያለው ሕይወቱ ዘወትር የሚጸልይ ሕይወት ነው። ክርስቶስ እንድንጸልይ የሚያስተምረን በምሳሌ፣ በትምህርት፣ በትእዛዝ፣ በተስፋዎች ብቻ ሳይሆን፣ ራሱን ለእኛ በማሳየትም ነው፤ ራሱን፣ ዘወትር በሕይወት የሚኖረውን አማላጅ፣ ሕይወታችን አድርጎ። ይህን ስናምን፣ ለጸሎት ሕይወታችንም ቢሆን ሄደን በእርሱ ስንኖር፣ በትክክል መጸለይ አንችልም የሚለው ፍርሃታችን ይጠፋል፤ ጌታችንም እንድንጸልይ እንዲያስተምረን፣ ራሱም የጸሎታችን ሕይወትና ኃይል እንዲሆን በደስታና በድል አድራጊነት እንታመንበታለን።
የንጉሥ ካህናት እንደ መሆናችን የተለየንለት ቅዱስ የምልጃ አገልግሎት ምን እንደ ሆነ ለማየት እግዚአብሔር ዓይኖቻችንን ይክፈት። ጸሎታችን ምን ያህል ታላቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ለማመን ሰፊና ብርቱ ልብ ይስጠን። ዘወትር ሊጸልይ በሕይወት የሚኖረውን፣ በእኛም ውስጥ ሊጸልይ የሚኖረውን፣ ለጸሎት ሕይወታችንም ዋስ የቆመውን ኢየሱስን ስናይ፣ ጥሪያችንን መፈጸም አንችልም የሚለው ፍርሃት ሁሉ ይወገድ።
አንድሪው መሪ
ዌሊንግተን፣ ኦክቶበር 28ኛ ቀን 1885
ምዕራፍ 1 ተጠናቋል
መቅድም