በጸሎት የሚገኝ ኃይል
ቀኑን በጸሎት ጀምር

ምዕራፍ 9 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ቀኑን በጸሎት ጀምር

ማንንም ሰው ከማየቴ በፊት መጸለይ ይገባኛል። ብዙ ጊዜ ረጅም ስተኛ ወይም በማለዳ ከሌሎች ጋር ስገናኝ፣ የስውር ጸሎት የምጀምረው ከቀኑ አምስት ወይም ስድስት ሰዓት ላይ ነው። ይህ አሳዛኝ አሠራር ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። ክርስቶስ ገና ሌሊት ሳለ ተነሥቶ ወደ ብቸኛ ስፍራ ሄደ። ዳዊት፦ «ወደ አንተ እገሠግሣለሁ»፤ «በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ» ይላል። የቤተሰብ ጸሎት ብዙ ኃይሉንና ጣዕሙን ያጣል፤ እኔን ፈልገው ለሚመጡትም ምንም መልካም ነገር ላደርግላቸው አልችልም። ሕሊና በደለኛነት ይሰማዋል፤ ነፍስ ሳትመገብ ትቀራለች፤ መብራቱም ሳይዘጋጅ ይቀራል። ከዚያም በስውር ጸሎት ጊዜ ነፍስ ብዙ ጊዜ ከቅኝቷ ስትወጣ፣ በእግዚአብሔር መጀመር እጅግ የተሻለ እንደ ሆነ ይሰማኛል—ፊቱን አስቀድሞ ማየት፣ ነፍሴን ወደ ሌላ ሰው ከማቅረቤ በፊት ወደ እርሱ ማቅረብ።—ሮበርት መሪ ማክሼን

በዚህ ዓለም ለእግዚአብሔር ብዙ ነገር ያደረጉ ሰዎች በማለዳ በጉልበታቸው የሚንበረከኩ ነበሩ። የማለዳውን ጊዜ፣ ዕድሉንና ትኩስነቱን እግዚአብሔርን ከመፈለግ ውጪ በሆኑ ሌሎች ጉዳዮች የሚያባክን ሰው በቀሪው ቀን እርሱን በመፈለግ ብዙ አይራመድም። እግዚአብሔር በማለዳ በአሳባችንና በጥረታችን የመጀመሪያውን ስፍራ ካልያዘ፣ በቀሪው ቀን የመጨረሻውን ስፍራ ይይዛል።

ከዚህ በማለዳ መነሣትና በማለዳ መጸለይ በስተጀርባ ወደዚህ እግዚአብሔርን የመፈለግ ጉዞ የሚገፋን የሚቃጠል ምኞት አለ። የማለዳ ስልቹነት የስልቹ ልብ ምልክት ነው። እግዚአብሔርን በማለዳ ለመፈለግ የሚዘገይ ልብ የእግዚአብሔርን ጣዕም አጥቷል። የዳዊት ልብ እግዚአብሔርን በብርቱ ይናፍቅ ነበር። እግዚአብሔርን ተራበ፣ ተጠማም፤ ስለዚህ ገና ሳይነጋ በማለዳ እግዚአብሔርን ፈለገ። አልጋና እንቅልፍ እግዚአብሔርን ለማግኘት የጓጓችውን ነፍሱን ሊያስሩአት አልቻሉም። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ ይናፍቅ ነበር፤ ስለዚህ ገና ሌሊት ሳለ ተነሥቶ ለመጸለይ ወደ ተራራ ይወጣ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ፈጽመው ሲነቁና ራሳቸውን በማስደሰታቸው ሲያፍሩ፣ እርሱን የት እንደሚያገኙት ያውቁ ነበር። ዓለምን ለእግዚአብሔር በብርቱ የነኩትን ሰዎች ዝርዝር ብንመለከት፣ ሁሉም እግዚአብሔርን በማለዳ የሚፈልጉ እንደ ነበሩ እናገኛለን።

የእንቅልፍን ሰንሰለት መበጠስ የማይችል የእግዚአብሔር ናፍቆት ደካማ ነገር ነው፤ ራሱን እስኪጠግብ ካስደሰተ በኋላም ለእግዚአብሔር የሚያደርገው መልካም ነገር እጅግ ጥቂት ነው። በቀኑ መጀመሪያ ከዲያብሎስና ከዓለም ይህን ያህል ወደ ኋላ የሚቀር የእግዚአብሔር ናፍቆት ፈጽሞ ሊደርስባቸው አይችልም።

ሰዎችን ወደ ፊት የሚያወጣቸውና በእግዚአብሔር ሠራዊት ውስጥ የጦር አዛዦች የሚያደርጋቸው መነሣቱ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ራስን የማስደሰትን ሰንሰለቶች ሁሉ የሚያነቃቃውና የሚበጥሰው የሚቃጠል ምኞት ነው። ነገር ግን መነሣቱ ለምኞቱ መውጫ፣ ጭማሪና ብርታት ይሰጠዋል። በአልጋቸው ላይ ተኝተው ራሳቸውን ቢያስደስቱ ኖሮ ምኞቱ በጠፋ ነበር። ምኞቱ ቀሰቀሳቸው፤ ለእግዚአብሔርም ሙሉ ኃይላቸውን እንዲዘረጉ አደረጋቸው፤ ይህንን ጥሪ መስማታቸውና በእርሱም መሠረት መሥራታቸው እምነታቸው እግዚአብሔርን አጥብቆ እንዲይዝ አደረገ፤ ለልባቸውም እጅግ ጣፋጩንና ሙሉውን የእግዚአብሔርን መገለጥ ሰጣቸው፤ ይህ የእምነት ብርታትና የመገለጥ ሙላትም የላቁ ቅዱሳን አደረጋቸው፤ የቅድስናቸውም ብርሃን እስከ እኛ ደርሷል፤ እኛም የድሎቻቸውን ደስታ ወርሰናል። እኛ ግን የምንጠግበው በመደሰት እንጂ በማፍራት አይደለም። መቃብሮቻቸውን እንሠራለን፣ በመቃብር ድንጋዮቻቸውም ላይ የመታሰቢያ ጽሑፍ እንጽፋለን፤ ነገር ግን ምሳሌነታቸውን ላለመከተል እንጠነቀቃለን።

እግዚአብሔርን የሚፈልጉ፣ በማለዳም የሚፈልጉት የሰባኪዎች ትውልድ ያስፈልገናል፤ የጥረታቸውን ትኩስነትና ጠል ለእግዚአብሔር የሚሰጡ፣ በምላሹም በቀኑ ሙቀትና ድካም ሁሉ እርሱ ራሱ ደስታና ብርታት የተሞላ ጠል እንዲሆንላቸው የኃይሉን ትኩስነትና ሙላት የሚቀበሉ ሰባኪዎች ያስፈልጉናል። እግዚአብሔርን በመፈለግ ረገድ ያለብን ስንፍና የሚጮኸው ኃጢአታችን ነው። የዚህ ዓለም ልጆች ከእኛ እጅግ ልባሞች ናቸው። በማለዳም በማታም በሥራቸው ላይ ናቸው። እኛ ግን እግዚአብሔርን በብርቱ ፍላጎትና በትጋት አንፈልገውም። እግዚአብሔርን አጥብቆ የማይከተል ማንም ሰው እግዚአብሔርን አያገኝም፤ በማለዳም እርሱን የማይፈልግ ነፍስ እግዚአብሔርን አጥብቃ አትከተልም።

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ