ምዕራፍ 9 · 9 ደቂቃ ንባብ
ማን ያድነኛል?
«በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? ስለ ምን የወገኔ ሴት ልጅ ጤና አልተመለሰም?»—ኤርምያስ 8:22።
«እናንተ ከዳተኞች ልጆች፥ ተመለሱ፥ ክዳታችሁንም እፈውሳለሁ። እነሆ፥ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና ወደ አንተ መጥተናል።»—ኤርምያስ 3:22።
«አቤቱ፥ ፈውሰኝ፥ እኔም እፈወሳለሁ።»—ኤርምያስ 12:14።
«እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛል።»—ሮሜ 7:24፤ 8:2።
በአንድ ጉባኤያችን ወቅት አንድ ጨዋ ሰው ምክርና እርዳታ ለመጠየቅ ወደ እኔ መጣ። እርሱ በግልጽ ትጉና በሚገባ የተማረ ክርስቲያን ሰው ነበረ። ለክርስቶስ ለመመስከር እየጣረ ለተወሰኑ ዓመታት እጅግ አስቸጋሪ በሆነ አካባቢ ኖሮ ነበር። ውጤቱም የውድቀትና የሐዘን ስሜት ነበር። ምሬቱ ለቃሉ ጣዕም እንደሌለው፣ ቢጸልይም ልቡ በጸሎቱ ውስጥ እንደሌለ ያህል መሆኑ ነበር። ለሌሎች ቢናገር ወይም በራሪ ጽሑፍ ቢሰጥ ይህን የሚያደርገው በግዴታ ስሜት ነበር፤ ፍቅሩና ደስታው አልነበሩም። በእግዚአብሔር መንፈስ ለመሞላት ይናፍቅ ነበር፤ ነገር ግን ይበልጥ በፈለገው ቍጥር ይበልጥ የራቀ ይመስል ነበር። ስለ ሁኔታው ምን ሊያስብ ይገባው ነበር? ከዚህስ የሚወጣበት መንገድ ይኖር ይሆን?
መልሴ፣ ጉዳዩ ሁሉ ለእኔ እጅግ ቀላል መስሎ እንደሚታየኝ ነበር፤ እርሱ ከጸጋ በታች ሳይሆን ከሕግ በታች ይኖር ነበር። እንዲህ እስከ ኖረ ድረስ ምንም ለውጥ ሊኖር አይችልም ነበር። በትኩረት አዳመጠ፤ ነገር ግን ምን ማለቴ እንደ ሆነ በትክክል ሊገባው አልቻለም።
በሕግና በጸጋ መካከል ያለውን ልዩነት፣ ፍጹም ተቃራኒነታቸውን አሳሰብሁት። ሕግ ይጠይቃል፤ ጸጋ ይሰጣል። ሕግ ያዝዛል፤ ለመታዘዝ ግን ብርታት አይሰጥም፤ ጸጋ ተስፋ ይሰጣል፣ ይፈጽማልም፤ ልናደርገው የሚያስፈልገንን ሁሉ ያደርጋል። ሕግ ሸክም ይጭናል፣ ያዋርዳል፣ ይፈርዳልም፤ ጸጋ ያጽናናል፣ ያበረታል፣ ደስም ያሰኛል። ሕግ የቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ራስን ይማጸናል፤ ጸጋ ሁሉን እንዲያደርግ ወደ ክርስቶስ ያመለክታል። ሕግ ወደ ጥረትና ወደ መወጠር ይጠራል፣ ፈጽሞ ልንደርስበት ወደማንችለው ግብ ይገፋፋናል፤ ጸጋ የእግዚአብሔርን የተባረከ ፈቃድ ሁሉ በውስጣችን ይሠራል። የመጀመሪያው እርምጃው ይህን ውድቀት ሁሉ ከመታገል ይልቅ ሙሉ በሙሉ መቀበል፣ እግዚአብሔርም ሊያስተምረው ሲፈልግ የነበረውን የራሱን አቅመ ቢስነት ትምህርት መቀበል፣ በዚህም ኑዛዜ ፈጽሞ ረዳት እንደሌለው ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት መውደቅ እንደ ሆነ አሳየሁት። ጸጋ መዳንንና ብርታትን ካልሰጠው በቀር ካደረገው የተሻለ ፈጽሞ ሊያደርግ እንደማይችል፣ ጸጋም በእርግጥ ሁሉን እንደሚሠራለት የሚማርበት ስፍራ እዚያ ነው። ከሕግ፣ ከራስና ከጥረት በታች ወጥቶ፣ እግዚአብሔር ሁሉን እንዲያደርግ በመፍቀድ፣ ከጸጋ በታች ስፍራውን መያዝ ነበረበት።
በኋላ በነበሩን ንግግሮች የበሽታው ምርመራ ትክክል እንደ ነበረ ነገረኝ። ጸጋ ሁሉን ማድረግ እንዳለበት አመነ። ነገር ግን አንድ ነገር ማድረግ አለብን፣ ቢያንስ የጸጋን ሥራ ለማረጋገጥ ታማኝነታችንን ማምጣት አለብን የሚለው አሳብ እጅግ ጥልቅ ስለ ነበረ፣ ሕይወቱ ብዙም እንደማይለወጥ ፈራ፤ አሁን ወደሚገባባቸው አዲስ ችግሮች ጫና ብቁ እንደማይሆን አሰበ። በዚያ ሁሉ ብርቱ ትጋት መካከል ውስጥ ውስጡን የተስፋ መቍረጥ ድምፅ ነበረ፤ ሊኖር እንደሚገባው እንደሚያውቀው ሊኖር አልቻለም። በአንዳንድ ስብሰባዎቻችን ይህን የተስፋ ቢስነት ድምፅ እንዳስተዋልሁ በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ አስቀድሜ ተናግሬአለሁ። ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ለመኖር፣ «በነገር ሁሉ ደስ እያሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ለመመላለስ» ከሚሹ ነፍሳት ጋር በቅርብ የተገናኘ አገልጋይ ሁሉ ይህ እውነተኛ እድገትን የማይቻል እንደሚያደርገው ያውቃል። በተለይ ስለ ጸሎት ጉድለትና የተሟላ የጸሎት ሕይወት ለመኖር ስላለው ምኞት ብንናገር፣ የሚገጥሙን ችግሮች እንዴት ብዙ ናቸው! አብዝተንና አሻሽለን ለመጸለይ ብዙ ጊዜ ወስነን ወድቀናል። አንዳንዶች እንዳላቸው፣ በአንድ ውሳኔ ዞር ብሎ ልማድን ለመለወጥ የሚያስችል የፈቃድ ብርታት የለንም። የሥራ ግፊት እንደ ቀድሞው ታላቅ ነው፤ ለተጨማሪ ጸሎት ጊዜ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው፤ እንድንጸና የሚያስችለንን በጸሎት ያለውን እውነተኛ ደስታ አይሰማንም፤ እንደሚገባን ለመለመንና ለመማለድ ኃይል የለንም፤ ጸሎታችን ደስታና ብርታት ከመሆን ይልቅ የማያቋርጥ ራስን የመኰነንና የጥርጣሬ ምንጭ ነው። አንዳንድ ጊዜ አዝነናል፣ ተናዝዘናል፣ ወስነናልም፤ ነገር ግን እውነቱን በቅንነት ለመናገር፣ ምንም ታላቅ ለውጥ አንጠብቅም፤ ወደዚያ የሚያደርሰውን መንገድ አናይምና።
ይህ መንፈስ እስካለ ድረስ የመሻሻል ተስፋ እጅግ ጥቂት እንደሚሆን ግልጽ ነው። ተስፋ መቍረጥ ሽንፈትን ማምጣቱ አይቀርም። የሐኪም ቀዳሚ ዓላማዎች አንዱ ሁልጊዜ ተስፋን መቀስቀስ ነው፤ ያለዚህ መድኃኒቶቹ ብዙ ጊዜ እምብዛም እንደማይጠቅሙ ያውቃል። ስውሩ ሹክሹክታ፦ ምንም ተስፋ የለም እያለ ሲሰማ፣ ስለ ተጨማሪ ጸሎት፣ እጅግ ኃይል ስለምታደርግ ጸሎት ግዴታ፣ አስቸኳይ አስፈላጊነትና የተባረከ መብት ከእግዚአብሔር ቃል የሚሰጥ ምንም ትምህርት አይጠቅምም። የመጀመሪያው ጥንቃቄያችን የውድቀቱንና የተስፋ መቍረጡን የተሰወረ ምክንያት ማግኘት፣ ከዚያም መዳን እንዴት በመለኮት የተረጋገጠ እንደ ሆነ ማሳየት ነው። በሁኔታችን ረክተን ልንቀመጥ ካልሆነ በቀር ይህን ጥያቄ ማድመጥና በእርሱም መተባበር አለብን፦ «በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? ስለ ምን የወገኔ ሴት ልጅ ጤና አልተመለሰም?» መለኮታዊውን ተስፋ ከተሰጠው ምላሽ ጋር ማድመጥና በልባችን መቀበል አለብን፦ «እናንተ ከዳተኞች ልጆች፥ ተመለሱ፥ ክዳታችሁንም እፈውሳለሁ። እነሆ፥ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና ወደ አንተ መጥተናል።» በግል ጸሎትና በግል መልስ እንደሚኖር በሚያምን እምነት መምጣት አለብን። ስለ ጸሎት ጉድለት ከአሁኑ ይህን መጠየቅ አንጀምርምን? እግዚአብሔርም እንደሚረዳን አናምንምን? «አቤቱ፥ ፈውሰኝ፥ እኔም እፈወሳለሁ።»
የበሽታን ምልክቶችና በሽታውን ራሱን መለየት ሁልጊዜ አስፈላጊ ነው። በጸሎት መድከምና መውደቅ የመንፈሳዊ ሕይወት ድካም ምልክት ነው። አንድ ሕመምተኛ ደካማ የልብ ትርታውን የሚያነቃቃ ነገር እንዲሰጠው ሐኪምን ቢጠይቅ፣ ይህ እምብዛም እንደማይጠቅመው ይነገረዋል። የልብ ትርታ የልብና የመላ ሰውነት ሁኔታ ጠቋሚ ነው፤ ሐኪሙ ጤና እንዲመለስ ይጥራል። ይበልጥ በታማኝነትና እጅግ ኃይል በምታደርግ ጸሎት ሊጸልይ የሚወድ ሁሉ ሊማረው የሚገባው ይህ ነው፦ መንፈሳዊ ሕይወቱ ሁሉ በሕመም ላይ እንዳለና መፈወስ እንደሚያስፈልገው። የበሽታውን ከባድነት ሙሉ በሙሉ የሚገነዘበው በጸሎት ያለበትን ጉድለት ብቻ ሳይሆን ይህ ምልክቱ የሆነለትን በእምነት ሕይወቱ ያለውን ጉድለት መመልከት ሲጀምር ነው። በዚያን ጊዜ የመንፈሳዊ ሰውነት የልብ ትርታ ብቻ የሆነው የጸሎት ሕይወቱ ጤናንና ብርታትን የሚያመለክት እንዲሆን፣ በሕይወቱና በአመላለሱ ሁሉ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው ያያል። እግዚአብሔር እያንዳንዱ ጤናማ የሰውነት ተግባር ደስታን እንዲያስገኝ አድርጎ ፈጥሮናል። ጸሎት ለጤናማ ሰው እንደ መተንፈስ ወይም እንደ መሥራት ቀላልና ተፈጥሮአዊ እንዲሆን ታስቦአል። የሚሰማን እምቢተኝነትና የምንናዘዘው ውድቀት በሽታችንን እንድናምንና ተስፋ ወደ ሰጠው ፈውስ ወደ እርሱ እንድንመጣ የሚጠራን የእግዚአብሔር የራሱ ድምፅ ነው።
እንግዲህ የጸሎት ጉድለት ምልክቱ የሆነለት በሽታ ምንድን ነው? «ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁም» የሚለው ቃል ከሚያመለክተው የተሻለ መልስ ልናገኝ አንችልም።
እዚህ ሁለት ዓይነት ክርስቲያናዊ ሕይወት ሊኖር እንደሚችል ተጠቁሞአል። በከፊል ከሕግ በታች በከፊልም ከጸጋ በታች የሆነ ሕይወት ሊኖር ይችላል፤ ወይም ከራስ ጥረት ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆኖ ጸጋ ሊሰጠው የሚችለውን መለኮታዊ ብርታት ሙሉ በሙሉ እየተለማመደ ፈጽሞ ከጸጋ በታች የሆነ ሕይወት። እውነተኛ አማኝ ሊፈጽመው የማይችለውን ለማድረግ እየጣረ፣ በራስ ጥረት ኃይል፣ አሁንም በከፊል ከሕግ በታች ሊኖር ይችላል። በክርስቲያናዊ ሕይወቱ የሚናዘዘው የማያቋርጥ ውድቀት በዚህ በአንድ ነገር ምክንያት ነው፦ በራሱ ይታመናል፣ የቻለውንም ያህል ለማድረግ ይሞክራል። በእርግጥ ይጸልያል፣ ለእርዳታም ወደ እግዚአብሔር ይመለከታል፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው አሁንም በእግዚአብሔር እየተረዳ በራሱ ብርታት ያለው እርሱ ነው። ወደ ሮሜ፣ ወደ ቆሮንቶስና ወደ ገላትያ ሰዎች በጻፋቸው መልእክቶች ጳውሎስ ዳግመኛ የባርነትን መንፈስ እንዳልተቀበሉ፣ ከሕግ ነጻ እንደ ሆኑ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ልጆች እንጂ ባሪያዎች እንዳልሆኑ፣ ዳግመኛ በባርነት ቀንበር ከመያዝ ይበልጥ ምንም ነገር እንዳይጠነቀቁ እንዴት እንደሚነግራቸው እናውቃለን። በሁሉም ስፍራ ንጽጽሩ በሕግና በጸጋ መካከል፣ ከሕግ በታች ባለው ሥጋና የጸጋ ስጦታ በሆነው፣ ጸጋም ሥራውን ሁሉ በእርሱ በሚሠራው በመንፈስ መካከል ነው። በዘመናችን፣ ልክ እንደ እነዚያ የመጀመሪያ ዘመናት፣ ታላቁ አደጋ ከሕግ በታች መኖርና እግዚአብሔርን በሥጋ ብርታት ማገልገል ነው። ለአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ዕድሜ ልካቸውን የሚኖሩበት ሁኔታ ይህ ይመስላል። እውነተኛ ቅዱስ ኑሮና በጸሎት ኃይል በዚህ መጠን የጐደሉት ስለዚህ ነው። ውድቀት ሁሉ አንድ ምክንያት ብቻ ሊኖረው እንደሚችል አያውቁም፦ ሰዎች ጸጋ ብቻ በውስጣቸው ሊያደርገው የሚችለውን በራሳቸው ሊያደርጉ ይፈልጋሉ፤ ይህንም ጸጋ በእርግጥ ያደርገዋል።
ብዙዎች ይህ በሽታቸው እንደ ሆነ፣ «ከጸጋ በታች» እንደማይኖሩ ለማመን ዝግጁ አይሆኑም። የማይቻል ነው ይላሉ። «ከልቤ ጥልቀት»፣ ይላል አንድ ክርስቲያን፣ «በእኔ ምንም መልካም ነገር እንደሌለ፣ ሁሉንም ለጸጋ ብቻ ባለ ዕዳ እንደ ሆንሁ አምናለሁ፣ አውቃለሁም።» «ሕይወቴን ያሳለፍሁት»፣ ይላል አንድ አገልጋይ፣ «የነጻ ጸጋን ትምህርቶች በመስበክና ከፍ ከፍ በማድረግ ነው፤ ክብሬንም ያገኘሁት በዚሁ ነው።» «እኔስ»፣ ይመልሳል አንድ ሚስዮናዊ፣ «ብቸኛ መተማመኛዬ ባመጣሁት መልእክትና በታመንሁበት በእግዚአብሔር የተትረፈረፈ ጸጋ ኃይል ባይሆን ኖሮ አሕዛብ ሲድኑ ለማየት እንዴት ላስብ እችል ነበር?» በጸሎት ያለብን ውድቀት—በሐዘንም እንናዘዘዋለን—«ከጸጋ በታች» ባለመኖራችን ምክንያት ነው ልትሉ በእርግጥ አትችሉም። ይህ በሽታችን ሊሆን አይችልም።
ሰው ሳያውቀው በበሽታ ሊሠቃይ እንደሚችል ምን ያህል ጊዜ እንደሚሆን እናውቃለን። ቀላል ሕመም አድርጎ የቈጠረው አደገኛ በሽታ ሆኖ ይገኛል። ፈጽሞ «ከጸጋ በታች» እንደምንኖር ራሳችንን እየቈጠርን፣ በብዙ መጠን አሁንም «ከሕግ በታች» እንደማንኖር እጅግ እርግጠኞች አንሁን። ለዚህ ስሕተት ብዙ ጊዜ ምክንያቱ «ጸጋ» ለሚለው ቃል የሚሰጠው ውሱን ትርጉም ነው። ስለ እግዚአብሔር ባለን ጥቂት ወይም እምነት የጐደለው አሳብ እግዚአብሔርን ራሱን እንደምንወስነው፣ እንዲሁ እንደ «የጸጋ ባለ ጠግነት»፣ «አብልጦ የበዛ ጸጋ» ባሉ አገላለጾች ደስ በሚለን ቅጽበት ጸጋውን እንወስነዋለን። ከቡንያን መጽሐፍ ጀምሮ «የበዛ ጸጋ» የሚለው አገላለጽ ራሱ ለክፉዎቹ ኃጢአተኞች እንኳ ሁልጊዜ በሚታደስ ይቅርታና በዘላለም ክብር ወደሚገኘው የነጻ መጽደቅ ታላቅና የተባረከ እውነት ብቻ ተወስኖ፣ በመቀደስ ረገድ ያለው «የበዛ ጸጋ» የሚለው ሌላው እኩል የተባረከ እውነት በሚገባ ሳይታወቅ አልቀረምን? ጳውሎስ፦ «ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ» ብሎ ይጽፋል። ያ በሕይወት መንገሥ፣ በኃጢአት ላይ እንደ ድል አድራጊ መንገሥ፣ እዚህ በምድር ላይ እንኳ ነው። በልብና በሕይወት «ኃጢአት በበዛበት»፣ በአማኙ ሕይወትና ማንነት ሁሉ ውስጥ «ጸጋ እጅግ አብልጦ በዛ፤ ጸጋ ደግሞ በጽድቅ ይነግሥ ዘንድ»። ጳውሎስ፦ «ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን?» ብሎ የሚጠይቀውና «አይደለም።» ብሎ የሚመልሰው በነፍስ ውስጥ ስላለው ስለዚህ የጸጋ ንግሥና ነው። ጸጋ የኃጢአት ይቅርታ ብቻ ሳይሆን በኃጢአት ላይ ኃይልም ነው፤ ጸጋ ኃጢአት በሕይወት ውስጥ የነበረውን ስፍራ ይወስዳል፤ ኃጢአት በሞት ኃይል በውስጥ እንደ ነገሠ፣ ጸጋም በክርስቶስ ሕይወት ኃይል ሊነግሥ ኃላፊነቱን ይወስዳል። ክርስቶስ፦ «ጸጋዬ ይበቃሃል» ብሎ የተናገረው፣ ጳውሎስም፦ «በድካሜ ልመካ እወዳለሁ፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና» ብሎ የመለሰው ስለዚህ ጸጋ ነው። ራሳችንን ፈጽሞ አቅመ ቢሶችና ረዳት የሌለን መሆናችንን ለመናዘዝ ፈቃደኞች ስንሆን ገብቶ ሁሉን በውስጣችን ስለሚሠራው ስለዚህ ጸጋ ጳውሎስ በሌላ ስፍራ እንዲህ ያስተምራል፦ «እግዚአብሔርም በሁሉ ሁልጊዜ ብቃትን ሁሉ እያላችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትበዙ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።»
እግዚአብሔርንና መዳንን የሚፈልግ ሰው መጽሐፍ ቅዱሱን ለረጅም ጊዜ አንብቦ፣ በእምነት የሚገኘውን የነጻ፣ የሙሉና የወዲያውኑ መጽደቅ እውነት ፈጽሞ ሳያይ መቅረቱ ብዙ ጊዜ ሆኖአል። አንድ ጊዜ ዓይኖቹ ሲከፈቱና ሲቀበለው በሁሉም ስፍራ ማግኘቱ አስደነቀው። እንዲሁም ለይቅርታ የሚሠራውን የነጻ ጸጋ ትምህርት የሚይዙ ብዙ አማኞች፣ ጸጋ ሕይወታችንን ሁሉ በውስጣችን ለመሥራት ኃላፊነት ሲወስድና አብ እንድንሆንና እንድናደርግ ለሚወደው ሁሉ በየደቂቃው በእርግጥ ብርታትን ሲሰጠን ያለውን አስደናቂ ትርጉሙን ፈጽሞ አላዩም። የእግዚአብሔር ብርሃን በዚህ የተባረከ እውነት ወደ ልባችን ሲያበራ ጳውሎስ፦ «ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም» ሲል ምን ማለቱ እንደ ሆነ እናውቃለን። እዚህም ደግሞ ሁለቱን ዓይነት ክርስቲያናዊ ሕይወት ታገኛለህ። አንደኛው ያ «እኔ አይደለሁም»—እኔ ምንም አይደለሁም፣ ምንም ማድረግ አልችልም—ገና እውነት ያልሆነበት ነው። ሌላኛው ያ አስደናቂ ልውውጥ የተደረገበት፣ ጸጋ የጥረታችንን ስፍራ የወሰደበትና፦ «እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል» ብለን የምንናገርበትና የምናውቅበት ነው። ያን ጊዜ ይህ የዕድሜ ልክ ተሞክሮ ሊሆን ይችላል፦ «የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ።»
የተወደድህ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ! ምን ይመስልሃል? በሕይወትህ የጐደለው፣ በጸሎት የመውደቅህ ምክንያት ይህ ሳይሆን አይቀርምን? ሕይወትህ ሁሉ አንድ ጊዜ በኃይሉ ሥር ቢሆን ጸጋ እንድትጸልይ እንዴት እንደሚያስችልህ አላወቅህም ነበር። በጸሎት ያለብህን እምቢተኝነት ወይም መደንዘዝ በብርቱ ጥረት ለማሸነፍ ፈለግህ፤ ነገር ግን ወደቅህ። ልታስበው በቻልኸው በማንኛውም የኀፍረት ወይም የፍቅር ምክንያት ራስህን ለማነሣሣት ታገልህ፤ ነገር ግን አልረዳህም። እንደ አገልጋዩ የማመጣልህ መልእክት ከምታስበው ይልቅ ለአንተ እውነት ሊሆን ይችል እንደ ሆነ ጌታን መጠየቅ አይገባህምን? የጸሎትህ ጉድለት በሕይወትህ የበሽታ ሁኔታ ምክንያት ነው፤ በሽታውም ይህ እንጂ ሌላ አይደለም፦ ቃሉ የሚያመጣውን ሙሉ መዳን ለዕለት ኑሮና ለእያንዳንዱ ተግባር አልተቀበልህም፦ «ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁም።» የጸጋ ዝግጅትና በሕይወት እንድንነግሥ የሚያደርግበት ኃይል እንደ ሕግ ፍላጎትና እንደ ኃጢአት ንግሥና ሁሉን የሚያጠቃልልና ጥልቅ የሚደርስ ነው፤ እንዲያውም እጅግ አብልጦ የበዛ ነው። (ማስታወሻ ለ።)
ጳውሎስ፦ «ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁም» ብሎ ከጻፈበት ምዕራፍ በሚቀጥለው ምዕራፍ ከሕግ በታች ያለውን የአማኝ ሕይወት ሥዕልና የሚያበቃበትን መራራ ተሞክሮ ይሰጠናል፦ «እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?» ለጥያቄው የሰጠው መልስ፣ «በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።»፣ በከንቱ በተታገሏቸው ክፉ ልማዶች ሥር ተማርኮ ከተያዘ ሕይወት መዳን እንዳለ ያሳያል። ያ መዳን የክርስቶስ ሕይወት በውስጣችን ሊሠራው የሚችለውን ሙሉ ተሞክሮ በሚሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ነው፦ «በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛል።» የእግዚአብሔር ሕግ ሊያደርግ የሚችለው ለኃጢአትና ለሞት ሕግ ኃይል አሳልፎ መስጠት ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ ወደ መንፈስ ነጻነት ሊያመጣንና በዚያም ሊጠብቀን ይችላል። የምንወደውን እንዳናደርግ ማርኮ ይዞን ከነበረው ኃይል በታች ካለው ከአሳዛኙ ሕይወት ነጻ ልንወጣ እንችላለን። በክርስቶስ ያለው የሕይወት መንፈስ ከማያቋርጠው የጸሎት ውድቀታችን ነጻ ሊያወጣን፣ በዚህም ደግሞ በነገር ሁሉ ደስ እያሰኘን ለጌታ እንደሚገባ እንድንመላለስ ሊያስችለን ይችላል።
ኦ! ተስፋ አትቍረጥ፣ አትታክት፤ በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት አለ፤ በዚያ ሐኪም አለ፤ ለሕመማችን ፈውስ አለ። በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል። ልታደርገው የምትችልበትን መንገድ የማታየውን ጸጋ ያደርገዋል። በሽታውን ተናዘዝ፤ በሐኪሙ ታመን፤ ፈውሱን ጠይቅ፤ የእምነትን ጸሎት፦ «ፈውሰኝ፥ እኔም እፈወሳለሁ» ብለህ ጸልይ። አንተም የጸሎት ሰው ልትሆን፣ እጅግ ኃይል የምታደርገውን ጸሎት ልትጸልይ ትችላለህ።
ለተጨማሪ ጸሎት የቀረበ ልመና
ምዕራፍ 9 ተጠናቋል
ማን ያድነኛል?