ምዕራፍ 1 · 1 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
መቅድም
የቅዱስ አባታችን የአባ እንጦንስ ሕይወትና ኑሮ፤ በቅዱሳን መካከል አባታችን በሆነው በእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶስ በአትናቴዎስ ተጽፎ በውጭ አገር ላሉ መነኮሳት የተላከ።
ኤጲስ ቆጶሱ አትናቴዎስ በውጭ አገር ለሚገኙ ወንድሞች።
በበጎነት መንገድ በምታደርጉት ተጋድሎ የግብፅን መነኮሳት ለመስተካከል አልያም ለመብለጥ ቈርጣችሁ በመነሣታችሁ ከእነርሱ ጋር መልካም ፉክክር ጀምራችኋል። አሁን በመካከላችሁ ገዳማት አሉና፤ የመነኩሴም ስም በሕዝብ ዘንድ ታውቋል። ስለዚህ ይህን ቍርጥ ሐሳባችሁን ሰዎች ሁሉ በምክንያት ያመሰግኑታል፤ እግዚአብሔርም ለጸሎታችሁ መልስ አድርጎ ፍጻሜውን ይሰጣችኋል። እንግዲህ ስለ ብፁዕ እንጦንስ አኗኗር እንድነግራችሁ ለመናችሁኝ፤ ተጋድሎውን እንዴት እንደ ጀመረ፣ ከዚያ በፊት ማንና ምን ዓይነት ሰው እንደ ነበረ፣ ሕይወቱን እንዴት እንደ ፈጸመ፣ ስለ እርሱ የሚነገረውም እውነት እንደ ሆነ ልታውቁ ትሻላችሁ፤ ይህም እናንተ ደግሞ እርሱን ለመምሰል ትችሉ ዘንድ ነው። እኔም ትእዛዛችሁን በደስታ ተቀበልሁ፤ አባ እንጦንስን ማስታወስ ብቻ ለእኔም ታላቅ ርዳታ ነውና። እናንተም በሰማችሁ ጊዜ ሰውየውን ከማድነቃችሁ በተጨማሪ ቍርጥ ሐሳቡን ልትከተሉ እንደምትመኙ አውቃለሁ፤ የአባ እንጦንስ ሕይወት ለመነኮሳት በቂ የተጋድሎ አርአያ ነውና። ስለዚህ ስለ እርሱ ወሬ ካመጡላችሁ ሰዎች የሰማችሁትን አትጠራጠሩ፤ ይልቁንም የነገሯችሁ ጥቂቱን ብቻ እንደ ሆነ አስቡ፤ ይህን ያህል ታላቅ ነገር በዝርዝር ሊነግሯችሁ ከቶ አይችሉምና። እኔም በጥያቄያችሁ መሠረት ስለ እርሱ ጥቂት ነገሮችን አስታውሼ የምችለውን ያህል በደብዳቤ ስለምልክላችሁ፣ ከዚህ በመርከብ የሚሄዱትን መጠየቅ ቸል አትበሉ፤ ሁሉም የሚያውቁትን ቢናገሩ እንኳ ታሪኩ ከክብሩ ጋር የሚመጣጠን ላይሆን ይችላልና። ስለዚህም ደብዳቤያችሁ በደረሰኝ ጊዜ አንዳንድ መነኮሳትን፣ በተለይም ከእርሱ ጋር አዘውትረው ይኖሩ የነበሩትን አስጠርቼ አዲስ ነገር ብሰማ ልልክላችሁ ፈልጌ ነበር። ነገር ግን የመርከብ ጉዞ ወራት ሊያልቅ ስለ ደረሰና ደብዳቤ አድራሹም ስለ ቸኰለ፣ እኔ ራሴ የማውቀውን፣ ብዙ ጊዜ አይቼዋለሁና፣ ከእርሱም ለመማር የቻልሁትን ለቅድስናችሁ ለመጻፍ ፈጠንሁ፤ ለረጅም ጊዜ አገልጋዩ ነበርሁና፤ በእጆቹም ላይ ውኃ አፈስስ ነበር። በሁሉም ነገር እውነትን አስቤአለሁ፤ ይህም ማንም ከመጠን በላይ ሰምቶ እንዳይጠራጠር፣ በሌላ በኩልም ጥቂት ብቻ ሰምቶ ሰውየውን እንዳይንቅ ነው።
ምዕራፍ 1 ተጠናቋል
መቅድም