ምዕራፍ 99 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
የተነሣው ክርስቶስና ባዶው መቃብር
ዓርብ ማታ ፀሐይ ስትጠልቅ ነበረ፤ ኢየሱስ በመስቀሉ ላይ ከሞተ ገና ሦስት ሰዓት ብቻ ነበረ፤ ያን ጊዜ በመቃብሩ ደጃፍ ያለው ድንጋይ ወደ ደጃፉ ተንከባለለ፤ የኢየሱስም ሥጋ በማረፊያው ስፍራ ብቻውን ቀረ። የአይሁድ ሰንበት በሆነው በቅዳሜ ቀኑን ሁሉ፥ በዚያም ሌሊት ሁሉ፥ ሥጋው በሮማውያን ወታደሮች እየተጠበቀ በመቃብሩ ውስጥ ተኛ። ነገር ግን እሑድ በማለዳ ፀሐይ ሳትወጣ፥ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ ታይቶ የማያውቅና ከዚያ ቀን ወዲህም ዳግመኛ ያልታየ አስደናቂ ነገር ሆነ።
አንድ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ በመቃብሩ ዙሪያ ያለውን ምድር ያናወጠ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ። ፊቱና መልኩ እንደ መብረቅ በሚያንጸባርቅ ብርሃን አበራ፤ ልብሱም በፀሐይ እንደሚያብረቀርቅ በረዶ ነጭ ነበረ። ዘብ የቆሙት ወታደሮች መልአኩን ባዩ ጊዜ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ ሞቱም ሆነው በምድር ላይ ወደቁ፤ ጥቂት ቆይተውም ተነሥተው በፍርሃታቸው ተሹለክልከው ከአትክልቱ ወጥተው ሄዱ።
ብሩሁ መልአክ በላዩ ያለውን ማኅተም ከምንም ሳይቈጥር በመቃብሩ ደጃፍ ባለው ድንጋይ ላይ እጁን አኖረ፥ ድንጋዩንም አንከባለለው። በተከፈተውም የመቃብሩ ደጃፍ ቆሞ ሳለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚያ ወጣ፤ ከእንግዲህ ሙት ሳይሆን ሕያው ነበረ፥ ዳግመኛም ላይሞት ሕያው ሆኖ ይኖር ነበር። መግነዙ አሁን በሥጋው ዙሪያ አልተጠቀለለም፤ ጨርቁም ከፊቱ ተወስዶ ነበር።
የሮማ ወታደሮች ገና በዚያ ቢሆኑ እንኳ ኢየሱስን ሊያዩት አይችሉም ነበር፤ በእርሱ ላይ ለውጥ መጥቶበት ነበርና፤ አሁን የሚታየው እንዲያዩት ለወደዳቸው ብቻ ነበረ እንጂ ለሌሎች አልነበረም። እንደ ወደደም ድንገት ሊገለጥና ሊሰወር ይችል ነበር። በአንድ ስፍራ ድንገት ይታይና ከአፍታ በኋላ ብዙ ማይሎች ርቆ በሌላ ስፍራ እንዲሁ ድንገት ሊታይ ይችል ነበር። የተዘጉትን በሮች እንደ ተከፈቱ ሆነው ሊያልፍባቸው ይችል ነበር፤ ለወዳጆቹም ከታየ በኋላ ከዓይናቸው ሊሰወር ይችል ነበር።
ከምድር መናወጡ ጥቂት ቆይቶ፥ የተነሣውም ክርስቶስ ከመቃብሩ ከወጣ በኋላ፥ ጥቂት ሴቶች በሥጋው ዙሪያ የሚያኖሩት ተጨማሪ ሽቱና መልካም መዓዛ ይዘው ከከተማ ወደ መቃብሩ መጡ። እነዚህ ሴቶች መግደላዊት ማርያም፥ የቀለዮጳ ሚስት ማርያም፥ ሰሎሜ፥ ዮሐና የተባለች ሴትና ምናልባትም ሌሎች ነበሩ። የምድሩን መናወጥ ሳይሰማቸው አልቀረም፤ ነገር ግን የሆኑትን አስደናቂ ነገሮች አላወቁም ነበር፤ የኢየሱስም ሥጋ በመቃብሩ ውስጥ ያለ መሰላቸው። በቀረቡም ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦
«ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?»
ወደ መቃብሩ በደረሱ ጊዜ ግን ድንጋዩ አስቀድሞ ተንከባሎ መቃብሩም ተከፍቶ አገኙት። መግደላዊት ማርያም ከሌሎቹ ጥቂት ቀድማ መጣች፤ መቃብሩ እንደ ተከፈተ መጀመሪያ ያየችውም እርሷ ነበረች፤ ወደ ውስጥም ብትመለከት ባዶ እንደ ሆነ አየች። አንድ ጊዜ ብቻ ተመለከተች፤ ከዚያም ሌሎቹን ሳትጠብቅ መቃብሩ እንደ ተከፈተና የኢየሱስ ሥጋ እንደ ተወሰደ ለአንዳንድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ልትነግር እየሮጠች ሄደች፤ ኢየሱስ እንደ ተነሣና ሕያው እንደ ሆነ አላወቀችም ነበርና።
መግደላዊት ማርያም ከሄደች ከአፍታ በኋላ ሌሎቹ ሴቶች ወደ መቃብሩ መጡ። እነርሱም ደግሞ ድንጋዩ እንደ ተንከባለለ፥ መቃብሩ እንደ ተከፈተ፥ የኢየሱስም ሥጋ በዚያ እንደሌለ አዩ። ነገር ግን እነዚህ ሴቶች መግደላዊት ማርያም ያላየችውን አዩ፤ ይኸውም የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው ስፍራ በቀኝ በኩል የተቀመጠ፥ ፊቱ የሚያበራና ረጅም ነጭ ልብስ የለበሰ ጎልማሳ ነው። ሲመለከቱትም ፈሩ፤ ይህ ጎልማሳ ድንጋዩን ያንከባለለው መልአክ ነበረና። እርሱ ግን እንዲህ ብሎ ፍርሃታቸውን አበረደላቸው፦
«አትፍሩ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ። ተነሥቶአል፤ በዚህ የለም! እዩ፤ ሥጋውን ያኖሩበት ስፍራ ይህ ነው፤ ባዶ እንደ ሆነም ታያላችሁ! ነገር ግን ሂዱ፥ ደቀ መዛሙርቱንና ጴጥሮስን ፈልጋችሁ ወደ ገሊላ ወደ ተራሮቹ እንደሚቀድማችሁ ንገሩአቸው። ከመሞቱ በፊት እንደ ነገራቸው በዚያ ያዩታል።»
እነዚህ ሴቶችም ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት እንደ ሄደችው እንደ መግደላዊት ማርያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን ሊፈልጉ ከመቃብሩ ሄዱ። ጴጥሮስንና ዮሐንስንም አግኝተው መልአኩ የነገራቸውን ወሬ ነገሩአቸው።
ጴጥሮስና ዮሐንስ ወዲያው ወደ መቃብሩ ተጣደፉ። ዮሐንስ ከጴጥሮስ ያንስ ነበር፤ አስቀድሞም ወደ መቃብሩ ደረሰ። ድንጋዩ እንደ ተንከባለለና መቃብሩ እንደ ተከፈተ አየ፤ ወደ መቃብሩ ይግባ ወይም አይግባ ሳያውቅ እያመነታ በደጃፉ ቆመ። ከአፍታ በኋላ የመጣው ጴጥሮስ ግን አላመነታም። ዮሐንስን አልፎ ወደ መቃብሩ ገባ፤ ባዶ እንደ ሆነም አየ። አሳቢ የነበረው ዮሐንስ በመቃብሩ ደጃፍ መጠበቁ፥ ፈጣንና ችኩል የነበረው ጴጥሮስም በቀጥታ ወደ መቃብሩ መግባቱ የባሕርያቸው ምልክት ነበረ። ጴጥሮስ ወደ መቃብሩ ከገባ በኋላ ዮሐንስ ተከትሎት ወደ ውስጥ ገባ። መቀበሪያው ስፍራ ባዶ እንደ ሆነ አዩ፤ መልአክ ግን አላዩም። ዮሐንስ ኢየሱስ ረጃጅሞቹን ቍራጮች ሳይፈታ ሹልክ ብሎ እንደ ወጣባቸው መግነዙ በወለሉ ላይ ተከምሮ እንደ ተኛ፥ በፊቱም ታስሮ ያየው ጨርቅ በጥንቃቄ ተጠቅልሎ ለብቻው እንደ ተቀመጠ ተመለከተ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ሥጋው በድንገት ወይም በችኮላ እንዳልተወሰደ ያሳዩ ነበር።
ስሜታዊው ጴጥሮስ አሳቢ አልነበረም፤ እነዚህን ነገሮች አይቶ ብቻ ተደነቀ። አሳቢው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ ግን እነዚህን ነገሮች ተመለከተ፤ ማኅተሙ ተሰብሮ የተንከባለለውን ድንጋይ፥ ባዶውን መቃብር፥ በሥርዓት የተከመረውን መግነዝ፥ በጥንቃቄም የተጠቀለለውን ጨርቅ። ያን ጊዜ ጌታው ከመቃብር ሕያው ሆኖ እንደ ተነሣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአእምሮው ላይ ብልጭ አለ! በዚያም ቅጽበት ኢየሱስ ሊሞት እንዳለበትና በሦስተኛው ቀን ከሞት ወደ ሕይወት እንደሚነሣ ከአንድ ጊዜ በላይ የተናገራቸው ቃላት ትዝ አሉት። ከኢየሱስ ዐሥራ አንድ ደቀ መዛሙርት ሁሉ፥ ይሁዳ ስለ ሞተ ከእንግዲህ ዐሥራ ሁለት ሳይሆኑ ዐሥራ አንድ ነበሩና፥ ኢየሱስ አብልጦ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ ኢየሱስ እንደ ተነሣ ያመነ የመጀመሪያው ሰው ነበረ፤ ሕያው ጌታውንም ገና ሳያይ አመነ።
እስከዚያ ጊዜ ድረስ ኢየሱስን ሕያው ሆኖ ያየው ማንም አልነበረም። ሁለት ደቀ መዛሙርት ባዶውን መቃብር ተመልክተው ነበር፤ ሴቶቹም ከመግደላዊት ማርያም በቀር መልአኩን አይተው ነበር፤ ነገር ግን ከእነርሱ ማንም ኢየሱስን አላየም ነበር፤ ከመግደላዊት ማርያም በቀር ሁሉም እየተደነቁና ምን እንደሚያስቡ እንኳ ሳያውቁ ሄዱ።