የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በአትክልቱ ውስጥ ያለው መቃብር

ምዕራፍ 98 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

በአትክልቱ ውስጥ ያለው መቃብር

ኢየሱስ ዓርብ ዕለት በማለዳ ከጌቴሴማኒ አትክልት ወደ አይሁድ ታላቁ ሸንጎ ለፍርድ እንደ ቀረበ፥ ሸንጎውም ክርስቶስ የእስራኤል ንጉሥ ነኝ ብሎ በሐሰት እንደ ተናገረ ሰው እንዲገደል እንደ ወሰነ ታስታውሳላችሁ። ነገር ግን የዚህ ሸንጎ አባላት ሁሉ የኢየሱስ ጠላቶች አልነበሩም። ከእነርሱ ጥቂቶቹ ወዳጆቹ ነበሩ፤ ዳሩ ግን አለቆቹንና ሕዝቡን ስለ ፈሩ ስለ እርሱ ለመናገርም ሆነ ለእርሱ ድምፅ ለመስጠት ሳይደፍሩ በስውር ወዳጆቹ ነበሩ።

ከእነዚህ ከኢየሱስ ስውር ወዳጆች አንዱ ከሦስት ዓመት በፊት ኢየሱስ መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ በሌሊት ሊያየው የመጣው አለቃ ኒቆዲሞስ ነበረ። ሌላውም ከኢየሩሳሌም ጥቂት ማይሎች ርቆ በገጠር በምትገኝ አርማትያስ በምትባል ስፍራ የሚኖር ዮሴፍ የተባለ ደግ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ። ይህ የአርማትያስ ሰው ዮሴፍ እጅግ ደፋር ነገር አደረገ። በቤተ መንግሥቱ ወዳለው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ከመስቀል አውርዶ ይቀብረው ዘንድ እንዲፈቅድለት ለመነው። ይህ ለእኛ የጀግንነት ሥራ ላይመስለን ይችላል፤ ነገር ግን ነበረ፤ የሮማ ገዦች ለሞት የተፈረደበትን ሰው ወዳጅ መስሎ የሚታየውን ማንኛውንም ሰው እጅግ ይጠረጥሩ ነበርና። ከዚህ ጥቂት ጊዜ አስቀድሞ አንድ ሰው የተገደለውን ሰው ሥጋ አገረ ገዡን በለመነ ጊዜ፥ አገረ ገዡ ያንንም ወዳጅ የሮማውያንና የአገረ ገዡ ጠላት እንደ ሆነ አድርጎ እንዲገደል አዘዘ። ስለዚህ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ጲላጦስን በለመነ ጊዜ «ነፍሱን በእጁ ይዞ ነበር» ማለት ይቻላል።

ጲላጦስ ግን በዮሴፍ አልተቈጣም፤ በልቡም የኢየሱስ ጠላት አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በመስቀል ላይ በአስከፊ ሥቃይ ብዙ ቀናት በሕይወት ይቆዩ ስለ ነበረ ጲላጦስ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ ተደነቀ። በመስቀሉ ላይ ኃላፊ የነበረውን ሮማዊውን የመቶ አለቃ አስጠርቶ የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደ ሞተ ጠየቀው። የመቶ አለቃውም ኢየሱስ እንደ ሞተ በነገረው ጊዜ ዮሴፍ ሥጋውን ወስዶ እንደ ወደደ ያደርገው ዘንድ ፈቀደለት።

ከዚያም ዮሴፍ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ ጋር ሆኖ የኢየሱስን ሥጋ በጥንቃቄና በርኅራኄ ከመስቀል አወረደ፤ በዚያም ዘመን እንደ ነበረው እንደ አይሁድ አቀባበር ልማድ በረጃጅም የተልባ እግር ልብስ ቍራጮች ዙሪያውን ጠቀለሉት። በኢየሱስም ፊት ላይ ጨርቅ አሰሩ። ኒቆዲሞስም ለቀብሩ ሊረዳ መጣ፤ መቶ ፓውንድ የሚመዝን መዓዛው ያማረና ዋጋው የከበረ ሽቱ፥ እሬትና ከርቤ ይዞ መጣ፤ ይህንም በሥጋው ዙሪያ በተልባ እግሩ ልብስ ውስጥ አኖሩ።

ኢየሱስ በተሰቀለበት ስፍራ አጠገብ የአርማትያሱ ዮሴፍ የሆነ አትክልት ነበረ፤ በዓለታማውም ኮረብታ ጎን ዮሴፍ ለራሱ መቃብር እንዲሆን ያስወቀረው ዋሻ ነበረ። በዚህ መቃብር ማንም ሙት ገና አልተቀበረበትም ነበር፤ በዚያም የኢየሱስን ሥጋ አኖሩ። ከዚያም ታላቅ ድንጋይ ወደ መቃብሩ ደጃፍ አንከባለው ትተውት ሄዱ።

በዚያን ጊዜ በአጠገቡ ከኢየሱስ ጋር ከገሊላ ከመጡት ሴቶች አንዳንዶቹ ነበሩ፤ እጅግ የወደዱት የኢየሱስ ሥጋ በመቃብሩ ሲኖር ይመለከቱ ነበር። ከእነዚህ ሴቶች አንዲቱ መግደላዊት ማርያም፥ ማለትም በገሊላ ባሕር አጠገብ ያለችው «የመግደላዋ ማርያም» ነበረች፤ እርሷም ከአንድ ዓመት በላይ አስቀድሞ ኢየሱስ ክፉ መናፍስትን ያወጣላት ሴት ነበረች። ሌላዋ የቀለዮጳ ሚስት ማርያም ነበረች፤ ሌላዋም ሰሎሜ የተባለች ነበረች፤ እርሷም የደቀ መዛሙርቱ የያዕቆብና የዮሐንስ እናት፥ የዓሣ አጥማጁ የዘብዴዎስ ሚስት ሳትሆን አትቀርም። እነዚህ ሴቶች የኢየሱስ ሥጋ የተቀበረበትን ስፍራ በጥንቃቄ ተመለከቱ።

በማግሥቱ ጠዋት፥ ይኸውም የአይሁድ ሰንበት ቀን፥ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ታላላቅ ሰዎች ወደ ጲላጦስ መጥተው እንዲህ አሉት፦

«ጌታ ሆይ፥ ያ ሕዝቡን ያሳተ ሰው በሕይወቱ ሳለ ‹በመቃብር ከሦስት ቀን በኋላ እንደ ገና እነሣለሁ› እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ የተቀበረበት መቃብር ለሦስት ቀን እንዲጠበቅ እዘዝ። ካልተጠበቀ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው ሥጋውን ከመቃብሩ ሰርቀው ይደብቁታል፤ ከዚያም ለሕዝቡ ‹ከሙታን ተነሣ› ይሉታል፤ ይህም የኋለኛው የሐሰት ወሬ የእስራኤል ንጉሥ ነበረ ከሚለው ከፊተኛው ይልቅ የከፋ ጉዳት ያደርጋል።»

ጲላጦስም «የወታደሮች ጠባቂ ውሰዱ፤ እንደ ቻላችሁም አስጠብቁት» አላቸው።

እነርሱም ሄደው በደጃፉ ባለው በታላቁ ድንጋይ ላይ ማኅተም አድርገው መቃብሩን አጸኑት። ደግሞም ለሦስት ቀን በዚያ እንዲቆዩ አዝዘው በመቃብሩ ፊት የወታደሮች ጠባቂ አኖሩ።

ኢየሱስ የተሰቀለበት ቀራንዮ ሊሆን በሚችለው የራስ ቅል በሚመስለው ክብ ኮረብታ በአንዱ ጎን እጅግ ጥንታዊ የሆነ መቃብር ተገኝቷል፤ ይህም የመድኃኒታችን መቀበሪያ ሳይሆን አይቀርም። ይህን ማንም በእርግጥ ሊያውቅ አይችልም፤ ነገር ግን ኢየሱስ በዚህ መቃብር ወይም ብዙም በማይርቅ እንደዚህ ባለ መቃብር እንደ ተቀበረ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።


ቀዳሚ ቀጣይ