የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስና መግደላዊት ማርያም

ምዕራፍ 100 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስና መግደላዊት ማርያም

አራቱም ወንጌሎች ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ ሕያው ሆኖ ያየችው የመጀመሪያዪቱ ሰው መግደላዊት ማርያም እንደ ሆነች በአንድ ቃል ይናገራሉ፤ እርስዋም በገሊላ ባሕር ዳር ካለችው ከመግደላ ከተማ የመጣች ማርያም ናት። ከአንድ ዓመት በፊት ኢየሱስ ክፉ መናፍስትን ያወጣላት ሴት ነበረች፤ ኢየሱስ ስላደረገላት ነገር ከነበራት ፍቅር የተነሣ ተከተለችው፥ ባለ ጠጋ ሴት ነበረችና በስጦታዋም ረዳችው።

ሌሎቹ ሴቶች ከጴጥሮስና ከዮሐንስ ጋር ከመቃብሩ በሄዱ ጊዜ ማርያም እያለቀሰችና እየተንሰቀሰቀች በዚያ ቀረች፤ ኢየሱስ መነሣቱን የተናገረውን መልአክ አላየችም ነበርና፥ ሕያው መሆኑንም አላወቀችም። በመቃብሩ ደጅ ቆማ ስታለቅስ ወደ ውስጥ ተመለከተች። በዚያም የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው ባዶ ስፍራ አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው ሁለት መላእክትን አየች።

«አንቺ ሴት፥» አላት ከመላእክቱ አንዱ፥ «ስለ ምን ታለቅሻለሽ?»

«ጌታዬን ወስደውታልና፥» ብላ መለሰች ማርያም፥ «ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም።»

በዚያን ጊዜ አንዳች ነገር ወደ ኋላ ዘወር እንድትል አደረጋት፤ አንድ ሰውም በአጠገብዋ ቆሞ አየች። ኢየሱስ ነበረ፤ እርስዋ ግን አላወቀችውም፤ ኢየሱስ ከመቃብሩ ከተነሣ በኋላ በልዩ ልዩ መልክ ይገለጥ ነበርና፥ እርሱ እስኪፈቅድላቸውም ድረስ ሰዎች ሊያውቁት አይችሉም ነበር።

«አንቺ ሴት፥» አላት ኢየሱስ፥ «ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?»

ማርያምም ይህ እንግዳ ሰው የአትክልቱ ጠባቂ መሰላት። እንዲህም አለችው፦

«ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፤ እኔ ራሴም እወስደዋለሁ።»

«ማርያም!» አላት ኢየሱስ።

ስምዋንም በጠራ ጊዜ አወቀችው፤ በእግሩም ሥር ወድቃ እግሮቹን በእጆችዋ ያዘች።

«መምህሬ ሆይ!» ከማለት በቀር ምንም ልትናገር አልቻለችም፤ ለመጨረሻ ጊዜ ሞቶ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያየችውን እርሱን እንደ ገና ሕያው ሆኖ በማየትዋ እጅግ ደስ ብሎአት ነበርና።

«አትያዢኝ፤» አለ ኢየሱስ፥ «ገና ተነሥቼ በሰማይ ወዳለው ወደ አባቴ እሄዳለሁና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ወደ ደቀ መዛሙርቴ ሄደሽ በቅርቡ ከምድር ተነሥቼ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፥ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ እንደምሄድ ንገሪአቸው።»

መግደላዊት ማርያም ሄዳ ደቀ መዛሙርቱን አገኘችና «ጌታን አየሁት!» አለቻቸው፤ ያላትንም ደግሞ ነገረቻቸው።

መግደላዊት ማርያም ከመቃብሩ ከሄደች በኋላ ሌሎቹ ሴቶች—የቀለዮጳ ሚስት ማርያም፥ ዮሐና፥ ሰሎሜም—ደቀ መዛሙርቱን አይተው ኢየሱስ እንደ ተነሣ መልአኩ የተናገረውን ነግረዋቸው ተመለሱ። ወደ መቃብሩም በቀረቡ ጊዜ ኢየሱስ ሊገናኛቸው መጣ።

«ደስ ይበላችሁ!» አላቸው ሴቶቹን። እነርሱም ወደ እርሱ ሮጠው በግንባራቸው ወደቁ፥ ልክ ማርያም እንዳደረገችውም እግሮቹን ያዙ፤ ባዩት ጊዜ ደስታና ፍርሃት ተቀላቅሎባቸው ነበርና።

«አትፍሩ፤» አለ ኢየሱስ፥ «ሄዳችሁ ወንድሞቼን ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ንገሩአቸው፤ በዚያም ያዩኛል።»

እነዚህም ሴቶች ኢየሱስ በእውነት ሕያው እንደ ሆነና እነርሱም እንዳዩት የምሥራቹን ሊነግሩአቸው ደቀ መዛሙርቱን ለመፈለግ እንደ ገና ሄዱ። ይህ ሁሉ የሆነው በእሑድ ጠዋት—በመጀመሪያው የትንሣኤ ቀን ነበር።

በዚያው ጠዋት ከመቃብሩ የሸሹት ወታደሮች ከድንጋጤያቸው በተመለሱ ጊዜ ወደ ካህናት አለቆች ሄደው ስለ ምድር መናወጡና ድንጋዩን ስላንከባለለው መልአክ ነገሩአቸው። ካህናቱም ከከተማይቱ አለቆች ጋር ተማከሩ፤ ከዚያም ለወታደሮቹ ብዙ ገንዘብ ሰጥተው ለሰው ሁሉ እንዲህ እንዲሉ አዘዙአቸው፦

«እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው መቃብሩን ሰብረው የኢየሱስን ሥጋ ሰረቁት።»

ወታደር በጥበቃ ላይ ሳለ ሊተኛ መብት እንደሌለው ያውቁ ነበር፤ የሠራዊቱም ሕግ በጥበቃ ስፍራው የተኛ ወታደር ሁሉ እንዲገደል ያዝዝ ነበር። አለቆቹ ግን እንዲህ አሉአቸው፦

«ይህ በገዢው ዘንድ ቢሰማ እኛ እናስረዳዋለን፤ በእናንተም ላይ ምንም ጉዳት እንዳይደርስ እናደርጋለን።»

ወታደሮቹም ገንዘባቸውን ተቀብለው እንደ ተነገራቸው አደረጉ። የኢየሱስም ሥጋ ከመቃብሩ ተሰረቀ የሚለው ወሬ በአይሁድ ሕዝብ መካከል ተወራ፤ እነርሱም አመኑት።


ቀዳሚ ቀጣይ