የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ በመስቀል ላይ

ምዕራፍ 97 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ በመስቀል ላይ

ሮማውያን አንድን ሰው በመስቀል ላይ ሰቅለው ሲገድሉ፥ የሰውየውን ወንጀል የሚገልጽ ጽሕፈት ከራሱ በላይ በመስቀሉ ላይ ማኖር ልማዳቸው ነበር። ጲላጦስም ከኢየሱስ ራስ በላይ የሚኖረው ጽሕፈት እንዲህ የሚል እንዲሆን አዘዘ፦

ይህ የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው።

ጽሕፈቱ በሦስት የተለያዩ ሕዝቦች ቋንቋ ተጽፎ ነበር፤ አይሁድ በሚናገሩት በዕብራይስጥ፥ የሮማውያን ቋንቋ በሆነው በሮማይስጥ፥ በዚያም የዓለም ክፍል አይሁድ ያልሆኑት ሁሉ በሚናገሩት በግሪክ። እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ንጉሥ እንደ ሆነ ታላቅ እውነትን ተናገሩ፤ በዚያን ጊዜ ያመኑት እጅግ ጥቂቶች ቢሆኑም ለምድር ሁሉ ተናገሩት። ዛሬ ግን በዓለም ሁሉ ኢየሱስን እንደ ጌታና እንደ ንጉሥ የሚያገለግሉ እጅግ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች አሉ።

የአይሁድ ካህናትና አለቆች ይህን በመስቀሉ ላይ ያለውን ጽሕፈት ባነበቡ ጊዜ እጅግ ተቈጡ፤ ኢየሱስ ንጉሥ ተብሎ እንዲጠራ አልወደዱምና። ካህናቱም በቤተ መንግሥቱ ወዳለው ወደ ጲላጦስ ሄደው እንዲህ አሉት፦

«በዚያ ሰው መስቀል ላይ ያለውን ጽሕፈት አትለውጥምን? ‹የአይሁድ ንጉሥ› አይሁን። እባክህ፥ ‹እርሱ፥ «የአይሁድ ንጉሥ ነኝ» አለ› ብለህ ለውጠው።»

ጲላጦስ ግን «የጻፍሁትን ጽፌአለሁ» ብሎ መለሰላቸው። ይህም በመስቀሉ ላይ ያኖረው ሁሉ ሳይለወጥ በዚያ መቆየት አለበት ማለቱ ነበር።

ደግሞም አንድ ሰው በተሰቀለ ጊዜ ልብሱን በመስቀል ላይ ለቸነከሩት ወታደሮች መስጠት የሮማውያን ልማድ ነበር። መስቀሉን የሚጠብቁ አራት ወታደሮች ነበሩ። እነዚህም እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ልብስ እየወሰዱ የኢየሱስን ልብሶች ተካፈሉ። ነገር ግን አንድ ልብስ ቀረ፤ ይኸውም የኢየሱስ እጀ ጠባብ ነበረ። ይህ ሳይሰፋ ሁሉ በአንድነት የተሸመነ ነበረ፤ ስለዚህ ወታደሮቹ እንዲህ ተባባሉ፦

«አንቅደደው፤ ነገር ግን የማን እንደሚሆን ለመወሰን ዕጣ እንጣጣልበት።»

ነጠብጣብ ያለባቸውን ትንንሽ አራት ማዕዘን የዝሆን ጥርስ ቍርጥራጮች መሬት ላይ ወረወሩ። እነዚህ ቍርጥራጮች ዳይስ ይባሉ ነበር። እያንዳንዱ ወታደር አንድ አንድ ቍርጥራጭ ወረወረ፤ ወደ ላይ የዞረውንም ገጽ ነጠብጣቦች ቈጠሩ። ቍርጥራጩ ከፍተኛውን ቍጥር ያሳየው ወታደር የኢየሱስን እጀ ጠባብ የራሱ አድርጎ ወሰደ። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ በአጠገቡ ቆሞ ወታደሮቹ የኢየሱስን ልብሶች ሲከፋፈሉ አየ፤ በክርስቶስ ላይ የሚደርሰውን አስቀድሞ እንደ ተናገረ ትንቢት በሃያ ሁለተኛው መዝሙር ያሉትን ቃላት አሰበ። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የተጻፉት የመዝሙሩ ቃላት እነዚህ ነበሩ፦

«ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፥
በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት።»

ወታደሮቹ ሥራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ሊጠብቁት በመስቀሉ ዙሪያ ተቀመጡ። ብዙ ካህናት፥ ጻፎችና ሕዝብ በመስቀሉ ዙሪያ ቆመው በዚያ ተሰቅሎ ያለውን ኢየሱስን ይመለከቱ ነበር። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ራሳቸውን እየነቀነቁ እንዲህ ያሉትን ቃላት በክፋት ይናገሩት ነበር፦

«ዋ! ቤተ መቅደሱን አፍርሰህ በሦስት ቀን መልሰህ ልትሠራው ነበር፤ አይደለም? እንግዲያስ ከቻልህ ከመስቀሉ ወርደህ ራስህን አድን!»

ከካህናቱና ከጻፎቹም አንዳንዶቹ እንዲህ ብለው ጮኹ፦ «ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ሊያድን አይችልም! እርሱ እንዳለው ‹ክርስቶስ፥ የእስራኤል ንጉሥ› ከሆነ አሁን በፊታችን ከመስቀሉ ይውረድ። ያን ጊዜ እናምንበታለን።»

ሌሎችም «በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‹የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ› ብሎአልና እግዚአብሔር ቢወድ አሁን ይርዳው» አሉ።

ከኢየሱስ ጋር በመስቀሎች ላይ ተሰቅለው ከነበሩት ከሁለቱ ወንበዴዎች አንዱ ከሰዳቢዎቹ ጋር ተባብሮ እንዲህ ብሎ ጮኸበት፦

«አንተ ክርስቶስ፥ የእስራኤል ንጉሥ አይደለህምን? ከሆንህስ ራስህንና እኛን ከአንተ ጋር ለምን አታድንም?»

በኢየሱስ በሌላው ወገን የተሰቀለው ሰው ግን ገሠጸው፦

«ጻድቅ የሆነውን እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን?» አለው። «አንተ ይህ ሰው የተፈረደበትን ፍርድ እየተቀበልህ ነው። እኔና አንተስ ስለ ሥራችን የሚገባንን ብቻ እንቀበላለን፤ ይህ ግን ምንም ክፉ አላደረገም።»

ከዚያም ይህ ሰው ከመስቀሉ ሆኖ ኢየሱስን «ኢየሱስ ሆይ፥ ወደ መንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አትርሳኝ» አለው።

ኢየሱስም «እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በሰማያዊው አገር ትሆናለህ» ብሎ መለሰለት።

በዚህ ጊዜ በኢየሱስ መስቀል አጠገብ ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ፥ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ያ ደቀ መዝሙር፥ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የኢየሱስ እናት ማርያም፥ እኅቷም፥ ማርያም የተባሉ ሌሎች ሁለት ሴቶችም ነበሩ፤ እነርሱም የቀለዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም፥ ማለትም የመግደላዋ ማርያም ናቸው። ኢየሱስም እናቱንና በአጠገቧ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ባየ ጊዜ ከመስቀሉ ሆኖ እርሷን እንዲህ አላት፦

«አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ።»

ከዚያም ዮሐንስን እንዲህ አለው፦

«ልጄ ሆይ፥ እናትህ እነኋት።»

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ የኢየሱስ እናት ማርያም እንደ ገዛ ልጇ ከደቀ መዝሙሩ ከዮሐንስ ጋር ኖረች።

አሁን ቀትር ሆኖ ነበር፤ ኢየሱስ ፀሐይ በራሱ ላይ እየጋለበት ሦስት ረጃጅምና አስጨናቂ ሰዓታት በመስቀል ላይ ቆይቶ ነበር። ልክ በቀትር ድንገት ጨለማ ሰማዩንና ምድሩን ሸፈነ፤ ጨለማውም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አላለፈም። ይህ ጨለማ ሕዝቡን አስደነገጠ፤ ኢየሱስን የንቀት ቃል ይናገሩት የነበሩትም አሁን በፍርሃት ተሞልተው ዝም ብለው ቆሙ።

በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ እነዚህን ቃላት ጮኸ፦

«አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?»

እነዚህ ቃላት ክርስቶስ የሚቀበለውን መከራ አስቀድሞ እንደ ትንቢት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የተጻፈው የሃያ ሁለተኛው መዝሙር መክፈቻ ቃላት ናቸው። ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው መከራው ሁሉ ከብዙ ጊዜ በፊት አስቀድሞ እንደ ተነገረ ለማሳየት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ሲናገር መዝሙሩ በተጻፈበት በጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ ተናገረ። በጥንቱ ዕብራይስጥ «አምላኬ! አምላኬ!» የሚሉት ቃላት «ኤሎሄ! ኤሎሄ!» ነበሩ። ነገር ግን መዝሙራቱ ከተጻፉበት ጊዜ ጀምሮ ቋንቋው እጅግ ተለውጦ ስለ ነበረ የሰሙት ሰዎች ቃላቱን አላስተዋሉም። አንዳንዶቹም «ይረዳው ዘንድ ነቢዩን ኤልያስን ይጠራል!» አሉ።

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦

«ተጠማሁ።»

በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ማሰሮ ተቀምጦ ነበር። ከሰዎቹ አንዱ ሰፍነግ ወስዶ በሆምጣጤው ነከረው፤ በበትር ጫፍ ላይ አሰረውና ወደ ኢየሱስ ከንፈር አቀረበው። ይህም ደግሞ በስድሳ ዘጠነኛው መዝሙር እንዲህ በሚሉት ቃላት አስቀድሞ ተነግሮ ነበር፦

«በጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ።»

ኢየሱስ ሆምጣጤውን እንደ ቀመሰ እንዲህ አለ፦

«ተፈጸመ።»

ከዚያም ጥቂት ቆይቶ በታላቅ ድምፅ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦

«አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ!»

በእነዚህም ቃላት ራሱ ወደ ፊት አዘነበለ፤ ኢየሱስም በመስቀሉ ላይ ሞቶ ተንጠልጥሎ ነበር።

ልክ ኢየሱስ በሞተበት ቅጽበት ድንገት የምድር መናወጥ ሆነ፤ ምድር ተናወጠች፥ ዓለቶች ተሰነጠቁ፥ በኢየሩሳሌም ዙሪያ የነበሩ ብዙ መቃብሮችም ተከፈቱ። በሞሪያ ተራራ ላይ ባለው ቤተ መቅደስ ደግሞ አንድ አስደናቂ ነገር ታየ። በቅድስትና በቅድስተ ቅዱሳን መካከል ተንጠልጥሎ የነበረው ታላቁ መጋረጃ በማይታይ ኃያል እጅ የተቀደደ ይመስል ድንገት ከላይ እስከ ታች ተቀደደ፤ ስለዚህ በቤተ መቅደስ የነበሩት ካህናት ከሊቀ ካህናቱ በቀር ከእነርሱ ማንም ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀውን፥ የቅድስተ ቅዱሳንን ውስጥ ማየት ቻሉ።

በቀራንዮ ኮረብታ ላይ ቆመው የሚሞተውን ኢየሱስን ይመለከቱ የነበሩት ሰዎች በፍርሃት ተሞሉ። ደረታቸውን በእጃቸው እየደቁ ከጨለማውና ከምድር መናወጡ የተነሣ በድንጋጤ ወደ ከተማ ተመለሱ። በመስቀሉ ዙሪያ ያሉትን ወታደሮች ይመራ የነበረው ሮማዊው የመቶ አለቃም እንዲህ አለ፦

«በእውነት ይህ ሰው ደግ ሰው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ!»

በአይሁድ ዘንድ ሰንበት በሳምንቱ በሰባተኛው ቀን ይጠበቅ እንደ ነበረና ሁልጊዜም ከዋዜማው ፀሐይ ስትጠልቅ ይጀምር እንደ ነበረ ታውቃላችሁ። ኢየሱስ የተሰቀለው ዓርብ ዕለት ነበረ፤ ጊዜውም የዚያ ቀን ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ነበረ። አይሁድ በሦስቱ መስቀሎች ላይ ያሉት ሰዎች በሰንበት በዚያ ተሰቅለው እንዲቆዩ አልፈለጉም፤ ያ ቀን የፋሲካ ሰንበት ስለ ነበረ በተለየ ሁኔታ የተቀደሰ ሆኖ ይጠበቅ ነበርና።

የአይሁድ አለቆችም ወደ ጲላጦስ መጥተው ሰዎቹ በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይቀሩ፥ ነገር ግን እንዲገደሉና ሥጋቸው እንዲወሰድ ለመኑት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደ ሞተ አላወቁም ነበር። ጲላጦስም ሰዎቹን እንዲገድሉ ለወታደሮቹ ትእዛዝ ሰጠ። ይህንም ያደረጉት በመስቀሎቹ ላይ ተሰቅለው ሳሉ ጭናቸውን በመስበር ነበር። ኢየሱስ ግን በሕይወት እንደሌለ ባዩ ጊዜ ጭኑን አልሰበሩም። ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ መሞቱን ለማረጋገጥ ልቡን ለመምታት ጦሩን በኢየሱስ ጎን ሰደደ። ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ እስከ መጨረሻው ድረስ በመስቀሉ አጠገብ ቆሞ ይመለከት ነበር፤ ከብዙ ዓመታትም በኋላ በጦሩ ከተወጋው ቍስል ከኢየሱስ ጎን ውኃና ደም ሲፈስ እንዳየ በወንጌሉ ጻፈ።


ቀዳሚ ቀጣይ