የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ ወደ ቀራንዮ ተወሰደ

ምዕራፍ 96 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ ወደ ቀራንዮ ተወሰደ

በእኛ ዘመንና በሥርዓት በሚተዳደሩ አገሮች ሁሉ አንድ ሰው ሞት ሲፈረድበት ለመሞት ይዘጋጅ ዘንድ ወደ እስር ቤት ተወስዶ ለጥቂት ቀናት በጥንቃቄ ይጠበቃል። ማንም እንዲጐዳው አይፈቀድም፤ የሚበላው መልካም ምግብ ይሰጠዋል፤ የመጨረሻ ቀኖቹንም በሰላም እንዲኖር ይፈቀድለታል። ነገር ግን በጥንት ዘመን፥ ኢየሱስ በሰዎች መካከል በነበረበት ጊዜ፥ ሞት የተፈረደባቸው እስረኞች እጅግ በጭካኔ ይያዙ ነበር። ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ይዘበትባቸው፥ ይደበደቡ፥ ይተፋባቸውም ነበር፤ ከዚያም ለሞት ይወሰዱ ነበር።

በዚያ ቀን በኢየሱስም ላይ እንዲሁ ሆነ። ወታደሮቹ በአሳፋሪ ሁኔታ ካንገላቱት በኋላ ቀዩን ልብስ ገፍፈው የራሱን ልብስ አለበሱት። ከዚያም በቈሰሉት ትከሻዎቹ ላይ የመስቀሉን ከባድ ግንድ ጫኑበት፤ ከጲላጦስ ቤተ መንግሥትም በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች በኩል ከከተማይቱ ቅጥር ውጭ ወዳለ ኮረብታ ወሰዱት። ይህ ኮረብታ በአይሁድ ሕዝብ ቋንቋ በዕብራይስጥ «ጎልጎታ» ይባል ነበር፤ ትርጓሜውም «የራስ ቅል ስፍራ» ማለት ነው። በሮማውያን ቋንቋ «የራስ ቅል ስፍራ» የሚለው ቃል «ካልቫርያ» ነበረ፤ ከዚህም ቃል የተነሣ ኢየሱስ የተሰቀለበት ስፍራ «የቀራንዮ ተራራ» ተብሎ ተጠርቶአል።

እውነተኛው የቀራንዮ ተራራ፥ የክርስቶስ መስቀል የቆመበት ስፍራ፥ የት እንደ ነበረ በእርግጥ አይታወቅም። ለረጅም ጊዜ በከተማይቱ በስተ ምዕራብ ያለ ትንሽ ኮረብታ እንደ ሆነ ይታመን ነበር፤ በዚያም ኮረብታ ላይ በኋለኞቹ ዓመታት «የቅዱስ መቃብር ቤተ ክርስቲያን» የተባለ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ተሠራ፤ እንዲህ የተባለውም በዚያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች መስቀሉ ቆሞበታል ብለው ያሰቡትን ስፍራ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ የተቀበረበትን መቃብርም ስለሚያሳዩ ነው። መድኃኒቱ የሞተበትንና የተቀበረበትን ትክክለኛውን ስፍራ ማየት የሚችሉ መስሎአቸው በየዓመቱ በሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች ወደዚህ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ።

ነገር ግን ስለ ኢየሩሳሌም ከተማና በዙሪያዋ ስላሉት ኮረብቶች ሊታወቅ የሚቻለውን ሁሉ በጥንቃቄ ያጠኑት አብዛኞቹ ሰዎች እውነተኛው ቀራንዮ ታላቁ የቅዱስ መቃብር ቤተ ክርስቲያን አሁን ባለበት ስፍራ ሳይሆን በሌላ ስፍራ እንደ ነበረ ያምናሉ። ብዙዎች ከከተማይቱ በስተ ሰሜን ልክ ከቅጥሩ ውጭ ያለ፥ ክብ ቅርጽ ያለውና ሣር የለበሰ ትንሽ ኮረብታ እንደ ነበረ ያስባሉ። የዚህ ኮረብታ ወደ ከተማይቱ የሚመለከተው ጐኑ እጅግ ገደላማ ነው፤ በእርሱም ውስጥ ሁለት ታላላቅ ዋሻዎች አሉ። አንድ ሰው በከተማይቱ ቅጥር ላይ ቆሞ ሁለት ጕድጓዶች ያሉበትን ይህን ክብ ኮረብታ ሲመለከት የራስ ቅልን ያስታውሰዋል፤ የራስ ቅል ማለት ቆዳና ሥጋ የሌለበት፥ ሁለት የዓይን ጕድጓዶችም ያሉበት የሰው ራስ ነው። ይህ ኮረብታ የራስ ቅልን እጅግ ስለሚመስል «የራስ ቅል ስፍራ» ተብሎ ተጠርቶ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ የተሰቀለው የራስ ቅልን በሚመስለው በዚህ ኮረብታ ላይ ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስ የመስቀሉን ከባድ ግንድ በትከሻዎቹ ላይ ተሸክሞ በከተማይቱ ጎዳናዎች ተጓዘ። ወታደሮቹ እየጐተቱት፥ አንዳንዶቹም እየመቱ ወደ ፊት ይነዱት ነበር፤ ድንገትም በመከራ ደክሞ፥ ከደም መፍሰስና ከምግብ እጦት የተነሣ ዝሎ፥ ሸክሙን ከዚያ በላይ መሸከም አቅቶት በምድር ላይ ወደቀ። በዚያን ጊዜ አንድ ሰው ከገጠር ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ወታደሮቹንና ከኢየሱስ ጋር የነበረውን ሕዝብ አገኘ። የዚህ ሰው ስም ስምዖን ነበረ። እርሱ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ስምዖን ጴጥሮስ አልነበረም፤ በአፍሪካ ርቃ ከምትገኝ ቀሬና ከምትባል ከተማ የመጣ ሌላ ስምዖን ነበረ እንጂ። ወታደሮቹ ይህን ሰው ያዙት፥ ወደ ቀራንዮም እስኪደርሱ ድረስ መስቀሉን በመሸከም ኢየሱስን እንዲረዳው አስገደዱት።

ኢየሱስን እንዲሰቅሉ የታዘዙትን ወታደሮች ተከትለው የአይሁድ ካህናትና የሕግ መምህራን የሆኑ ጻፎች፥ ከሕዝቡም እጅግ የተዋረዱት ብዙ ሰዎች ይጓዙ ነበር፤ ሁሉም ኢየሱስ በምድሪቱ ሁሉ ካሉት ሰዎች እጅግ ክፉው እንደ ነበረ ያህል ሊገደል በመሆኑ ደስታቸውን በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ይገልጹ ነበር። ነገር ግን በመካከላቸው ጥቂት የኢየሱስ ወዳጆችና የሚያውቁትና የሚወዱት አንዳንድ ሴቶች ነበሩ፤ እነርሱም በእርሱ ላይ በደረሰው በደል ያለቅሱ ነበር።

ኢየሱስ ዘወር ብሎ እነዚህን ሴቶች እንዲህ አላቸው፦

«እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ! ‹መከራ የሚቀበሉና የሚሞቱ ልጆች የሌሉአቸው ብፁዓን ናቸው› የሚሉበት ጊዜ ይመጣልና። በዚያን ወራት ተራራዎችን ‹በላያችን ውደቁ›፥ ኮረብቶችንም ‹ሰውሩን› ይላሉ። አሁን በመጀመሪያው እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ ያን ጊዜ በመጨረሻው ምን ያደርጉ ይሆን?»

በዚያ በአስፈሪው ሰዓት እንኳ ኢየሱስ ያሰበው ስለ ራሱና ስለ ገዛ መከራው ሳይሆን ብዙም ሳይቆይ በሌሎች ላይ ስለሚመጣው ኀዘን ነበር።

ኢየሱስ ወደ ቀራንዮ ሲሄድ በመንገድ ላይ ስለ ሆነው የሚነገር አንድ ታሪክ አለ፤ ይህ ታሪክ በየትኛውም ወንጌል ውስጥ አይገኝም፤ እውነት ላይሆንም ይችላል። ኢየሱስ በዚያ ሲያልፍ ቬሮኒካ የምትባል አንዲት ደግ ሴት በመንገዱ ዳር ቆማ ነበር ይባላል። ፊቱ በላብ፥ በአቧራና በደም ተሸፍኖ ባየች ጊዜ ወደ እርሱ ሄዳ ፊቱን በመሐረብ ጠረገችለት። መሐረቧንም ስትመለከት የኢየሱስ መልክ በላዩ ታትሞ አገኘች፤ ከዚያም ወዲህ እንደ ታላቅ ሀብቷ አድርጋ ጠበቀችው።

ኢየሱስን በከተማይቱ ቅጥር ካለው በር አውጥተው፥ ያ ኮረብታ የትም ይሁን የት፥ በቀራንዮ ኮረብታ ጐን ወደ ላይ ወሰዱት። በዚያም መስቀሉን በምድር ላይ አጋደሙት፤ ኢየሱስንም በላዩ ዘረጉት። ሥጋውን ከመስቀሉ ጋር ለማያያዝ በእጆቹና በእግሮቹ ችንካሮችን መቱ። ከዚያም ኢየሱስ በላዩ እንዳለ መስቀሉን አንሥተው ቀጥ ብሎ እንዲቆም የታችኛውን ጫፉን ወደ ጕድጓድ ጣሉት።

ከኢየሱስ ጋር ወንበዴዎች የነበሩና በመስቀል እንዲሞቱ የተፈረደባቸውን ሌሎች ሁለት ሰዎች አምጥተው ነበር። እነዚህን ሁለት ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ሰቀሉአቸው፤ አንዱን በቀኙ ሌላውንም በግራው፥ ኢየሱስንም ከሦስቱ እጅግ ክፉው እንደ ሆነ ያህል በመካከላቸው ሰቀሉት።

ኢየሱስ ወደ መስቀሉ የቸነከሩት የሮም ወታደሮች እንደ አይሁድ ጠላቶቹ እንዳልነበሩ፥ ነገር ግን አለቆቻቸው የሰጡአቸውን ትእዛዝ ብቻ እንደሚፈጽሙ ያውቅ ነበር። ስለ እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

«አባት ሆይ» አለ ኢየሱስ፥ «የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!»

ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ዓርብ ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት ነበረ፤ እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓትም ድረስ ለስድስት አስጨናቂ ሰዓታት በሕይወት ሳለ በዚያ ተሰቅሎ ቆየ።


ቀዳሚ ቀጣይ