የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ ሞት ተፈረደበት

ምዕራፍ 95 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ ሞት ተፈረደበት

ጲላጦስ ኢየሱስን ወደ ንጉሡ ሄሮድስ በላከው ጊዜ እፎይ አለ፤ በአንድ በኩል ንጹሕ ሰው የሆነውን ኢየሱስን እንዲገደል ማዘዝ አልፈለገም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስን በመፍታት የአይሁድን አለቆች ማስቀየም አልፈለገም። ከችግሩ ያመለጠ መስሎት ነበር፤ ድንገት ግን ኢየሱስ ተመልሶ ወደ እርሱ ሲመጣ፥ ካህናቱም እንደ ቀድሞው እንዲገደል ሲጮኹ አገኘ።

ጲላጦስ የኢየሱስን ፍርድ ዳግመኛ ለመስማት ተገድዶ፥ በጉዳዩም ላይ ውሳኔ ከመስጠት ማምለጥ ተስኖት ሳይወድ በዙፋኑ ላይ እንደ ገና ተቀመጠ። የኢየሱስን አዲስ ፍርድ ሊጀምር ሲል ጭንቀቱንና ፍርሃቱን የሚያበዛ መልእክት ከሚስቱ መጣለት። የጲላጦስ ሚስት ይህን ቃል ላከችበት፦

«ባሌ ሆይ፥ በዚያ ደግ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር እንዲደርስበት እንዳትፈቅድ እለምንሃለሁ፤ ዛሬ ስለ እርሱ ባየሁት ሕልም እጅግ ተጨንቄአለሁና።»

ይህ መልእክት ጲላጦስ ለአይሁድ እጅ ሰጥቶ ኢየሱስን እንዳያስገድል ይበልጥ እንዲፈልግ አደረገው። የኢየሱስን ሕይወት የሚያድንበት አዲስ ዘዴ አሰበ፤ ይህንም በልቡ ይዞ ለካህናት አለቆችና ለመሪዎቹ እንዲህ አላቸው፦

«ይህን ሰው ሕዝቡን በመንግሥት ላይ እንዲያምፁ ሊያነሣሣ ሞክሮአል ብላችሁ ከስሳችሁ ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እኔም ጉዳዩን መርምሬ ክሱ ሐሰት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የምትከስሱትን ነገር አላደረገም፤ እኔ እስከማየው ድረስ በሥራውም ምንም ክፋት የለበትም። ሄሮድስም ምንም በደል አላገኘበትም፤ መልሶ ልኮታልና። ለሞት የሚያበቃ ምንም አላደረገም። ነገር ግን ይህን ሁሉ ሁከትና ሽብር ስላስነሣ ጥቂት ቅጣት ይገባዋል። በሚገባ እንዲገረፍ አዝዤ እፈታዋለሁ።»

ነገር ግን ሁሉም በአንድ ድምፅ «ይህን አስወግድ! ወደ መስቀል ውሰደው! አትፍታው፤ በርባንን ፍታልን!» ብለው ጮኹ።

በፋሲካ በዓል የዘመኑን ደስታ ለማሳየት ሕዝቡ የሚለምኑትን፥ በእስር ቤት ያለውን ማንኛውንም ሰው፥ አንድ እስረኛ መፍታት ልማድ ነበረ። በዚያን ጊዜ በእስር ቤት በሮማውያን ገዦች ላይ የአይሁድን ጭፍራ መርቶ በውጊያውም ሰው የገደለ በርባን የሚባል ሰው ነበረ። ሞት ተፈርዶበት ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ እነርሱም የሚጠሉአቸውን፥ ኃይላቸውንም ባይፈሩ ኖሮ በደስታ ከአገሩ የሚያባርሩአቸውን ሮማውያንን ስለ ተዋጋ በእርሱ ላይ ያላቸው አክብሮት አልቀነሰም ነበር። ሕዝቡም በየዓመቱ ይደረግ እንደ ነበረ እንዲያደርግና አንድ እስረኛ እንዲፈታ ወደ ጲላጦስ ይጮኹ ጀመር።

«ፈቃዳችሁ ነውን» አለ ጲላጦስ፥ «ይህን ሰው፥ የአይሁድን ንጉሥ ኢየሱስን፥ እንድፈታላችሁ?»

ነገር ግን የካህናት አለቆችና የአይሁድ አለቆች በሕዝቡ መካከል እየተዘዋወሩ ከኢየሱስ ይልቅ በርባንን እንዲለምኑ አግባቡአቸው። ሕዝቡም ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው እንዲህ ብለው ጮኹ፦

«ይህን ሰው አንፈልግም፤ በርባንን እንፈልጋለን!»

ጲላጦስ የጠበቀው ይህን አልነበረም። እንደ በዓሉ ልማድ ኢየሱስን ፈትቶ ሕዝቡንም ደስ ሊያሰኝ እንደሚችል አስቦ ነበር። ሕዝቡንም እንዲህ አላቸው፦

«እንግዲያስ ክርስቶስ የሚሉትን ሰው ኢየሱስን ምን ላድርገው?»

«ወደ መስቀል ስደደው! በመስቀል ላይ ይሙት!» ብለው በሙሉ ኃይላቸው አገሱ።

«ለምን? ምን ክፉ ነገር አደረገ?» ብሎ ጲላጦስ ሕዝቡን ጠየቀ። «ለሞት የሚያበቃ ምንም በደል አላገኘሁበትም። አስገርፌ እለቀዋለሁ!»

ከዚያም በጲላጦስ ትእዛዝ ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ ዘበኞች ክፍል ወሰዱት። ልብሱን ሁሉ ገፈፉት፥ ከአንዱ ምሰሶ ጋር አሰሩት፥ ሥጋውንም በሚቦጭቁ ከባድ ጅራፎች ገረፉት። ራሱን «ንጉሥ» ብሎ እንደሚጠራ ሰው ሊያፌዙበት ቀይ መጐናጸፊያ አለበሱት፤ የእሾህ አክሊል ጐንጕነው ደሙ እስኪፈስስ ድረስ በራሱ ላይ ጫኑበት፤ ንጉሥ እንደሚይዘው በትረ መንግሥት አድርገው በእጁ መቃ አስያዙት፤ በፊቱም ተንበርክከው «የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ!» አሉት። ደጋግመው በጥፊ መቱት፤ በመቃውም መቱት፤ በፊቱም ተፉበት።

ጲላጦስ ሕዝቡ ኢየሱስን የእሾህ አክሊል ደፍቶ በደምም ተሸፍኖ እንዳለ ቢያዩት ያዝኑለታል፥ እንዲገደልም አይጮኹም ብሎ አሰበ። አይሁድንም እንዲህ አላቸው፦

«እንድታዩት ወደ ውጭ አወጣዋለሁ፤ ነገር ግን በእርሱ ምንም በደል እንዳላገኘሁበት እወቁ።»

ከዚያም ኢየሱስን ወደ ቤተ መንግሥቱ ደረጃዎች አወጡት። ፊቱ በደም ተበክሎ ነበር፤ በራሱ ላይ የእሾህ አክሊል ነበረ፤ በትከሻዎቹም ላይ ቀዩ መጐናጸፊያ ነበረ። ጲላጦስም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦

«እነሆ፥ ሰውዬው!»

ነገር ግን ጲላጦስ እንዲህ ያለውን እጅግ አሳዛኝና ኀዘን የሞላበትን የኢየሱስን መልክ ማየት የሕዝቡን ርኅራኄ ያነሣሣል ብሎ ተስፋ አድርጎ ከሆነ፥ ብዙም ሳይቆይ እንደ ተሳሳተ አወቀ። በካህናት አለቆችና በሎሌዎቻቸው እየተመሩ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ብለው ጮኹ፦

«ወደ መስቀል ውሰደው! ይሰቀል!»

መሰቀል ማለት በመስቀል ላይ በችንካር መቸንከር ነው፤ መስቀሉም ቀጥ ተደርጎ ይተከልና የሚሠቃየው ሰው እስኪሞት ድረስ ቆሞ ይተው ነበር። በጲላጦስ ቤተ መንግሥት ፊት የነበሩት የአይሁድ ሕዝብ ምንም ጕዳት ሳያደርስ መልካምን ብቻ ባደረገው በኢየሱስ ላይ እንዲያደርግበት የለመኑት ይህን ነበር!

ጲላጦስም «ከፈለጋችሁ እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት። እኔ በዚህ ነገር ምንም ድርሻ አይኖረኝም፤ ምንም ክፋት እንዳደረገ አላገኘሁምና» ብሎ መለሰላቸው።

የአይሁድ አለቆችም «እኛ ግን ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና እንደ ሕጋችን ሊሞት ይገባዋል!» ብለው ለጲላጦስ መለሱለት።

ጲላጦስ ይህን በሰማ ጊዜ በዚህ ሰው በኢየሱስ ላይ አንዳች እንግዳ ነገር ያለ ስለ መሰለው ይበልጥ ፈራ። ምን እንደሚያደርግ አላወቀም። ወደ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገባ፥ ኢየሱስንም ይዞት ገባ።

ጲላጦስ ኢየሱስን «አንተ ከወዴት ነህ?» አለው።

ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። ጲላጦስም እንዲህ አለው፦

«አትነግረኝምን? ልፈታህም ሆነ ወደ መስቀል ልሰድድህ እንደ ፈቀድሁ ሥልጣን በእጄ እንዳለ አታውቅምን?»

«ከላይ ካልተሰጠህ በቀር» አለ ኢየሱስ፥ «በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም። እግዚአብሔር ያንን ሥልጣን የሰጠህ ለቅን ነገር እንድትጠቀምበት እንጂ ለክፉ አይደለም። ከአንተ ይልቅ ኃጢአቱ የባሰ አንድ ሰው አለ፤ እርሱም ወደ አንተ ያመጣኝ ሊቀ ካህናቱ ነው!» ኢየሱስ ጲላጦስ ለሊቀ ካህናቱ ፈቃድ የሚገዛ ደካማ ሰው ብቻ እንደ ሆነ፥ እርሱ ግን አገረ ገዥ እንደ መሆኑ የራሱ ሐሳብ ሊኖረውና በእግዚአብሔር ፊት ቅን የሆነውን ብቻ ሊያደርግ እንደሚገባው እንዲያስተውል ፈልጎ ነበር።

ይህ ሁሉ ጲላጦስ ኢየሱስን ከመግደል ይልቅ ሊፈታው ይበልጥ እንዲጓጓ አደረገው። የአይሁድ አለቆች ግን ጮኸው እንዲህ አሉት፦

«ራሱን ንጉሥ ያደረገውን ይህን ሰው ብትፈታው በሮም ላለው ንጉሠ ነገሥት ለቄሣር ወዳጅ አይደለህም! ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ በሁላችን ላይ ካለው ከንጉሠ ነገሥቱ በላይ ራሱን ያደርጋል!»

ጲላጦስ ንጉሠ ነገሥቱ ቄሣር እጅግ ቀናተኛ እንደ ሆነ፥ ማንም ሰው ራሱን ንጉሥ ሊያደርግ እንደሚሞክር ቢያውቅ እጅግ እንደሚቈጣ ያውቅ ነበር። ጲላጦስ በሮም ያለውን ንጉሠ ነገሥት ጠላቱ ከማድረግ ይልቅ ኢየሱስ እንዲገደል መተው ለራሱ የሚሻል እንደ ሆነ እጅግ ሳይወድ ቈረጠ። ስለዚህ ጲላጦስ እንደ ገና በዙፋኑ ተቀመጠ፥ ኢየሱስንም በፊቱ አስቀረበው። ጊዜውም ፀሐይ የምትወጣበት፥ ከንጋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ነበረ። ጲላጦስም አይሁድን እንዲህ አላቸው፦

«እነሆ ንጉሣችሁ!»

«ግደለው! ግደለው!» ብለው አይሁድ ጮኹ። «ስቀለው! ስቀለው!»

«ይህ ሰው ንጉሣችን አይደለም» ብለው ካህናቱና አለቆቹ ጮኹ። «ከንጉሠ ነገሥቱ ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም!»

ጲላጦስ ኢየሱስን የመግደሉ ሥራ የእነርሱ እንጂ የእርሱ እንዳልሆነ ለአይሁድ ሊያሳያቸው ሞከረ። በሳሕን ውኃ አስመጥቶ በሁሉም ፊት እጁን ታጠበ። ከዚያም እጆቹን ዘርግቶ ለሕዝቡ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦

«እጆቼ ከዚህ ደግ ሰው ደም ንጹሓን ናቸው! ለሞት የሚያበቃ ምንም እንዳላደረገ እነግራችኋለሁ! ይህ የእናንተ ሥራ ነው እንጂ የእኔ አይደለም!»

«ይህ ደም በእኛና ከእኛ በኋላ በሚመጡት በልጆቻችን ላይ ይሁን» ብለው አይሁድ መለሱ።

ከዚያም ጲላጦስ በዙፋኑ ተቀምጦ እንደ ፈለጉት እንዲሆን፥ ወንበዴና ነፍሰ ገዳይ የሆነው በርባን እንዲፈታ፥ ምንም ጕዳት ሳያደርስ መልካምን ብቻ ያደረገው ኢየሱስ ግን ወደ መስቀል እንዲሰደድ ፈረደ።


ቀዳሚ ቀጣይ