የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ በሄሮድስ ፊት

ምዕራፍ 94 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ በሄሮድስ ፊት

ጲላጦስ ኢየሱስን የላከለት ሄሮድስ የምድሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሆነችው የገሊላና ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ያለችው የፔሪያ ገዥ ነበረ። ኢየሱስ ዕድሜውን ሁሉ ማለት ይቻላል በገሊላ ኖሮአል፤ በቅርቡም እየሰበከ በፔሪያ አልፎ ነበር፤ ስለዚህ ሄሮድስ ለብዙ ዓመታት የኢየሱስ ገዥ ነበረ። ሄሮድስ በእውነት ንጉሥ አልነበረም። ማዕረጉ «የአራተኛው ክፍል ገዥ» ነበረ፤ ይህም «ከአንድ መንግሥት የአራተኛውን ክፍል የሚገዛ» ማለት ነው። እንዲህ የተባለውም አባቱ ታላቁ ሄሮድስ በሞተ ጊዜ ከአባቱ መንግሥት አንድ አራተኛውን ድርሻው አድርጎ ስለ ተቀበለ ነው። ነገር ግን ሕዝቡ «የንጉሥ ሩብ» ተብሎ ከመታየት ይልቅ እንደ ንጉሥ መቈጠር ደስ እንደሚያሰኘው ያውቁ ስለ ነበር፥ ብዙ ጊዜ «ንጉሡ ሄሮድስ» ተብሎ ይጠራ ነበር። በግብዣው ላይ ለዘፈነችው ብላቴና በገባው ቃል ምክንያት መጥምቁን ዮሐንስን ያስገደለው ይህ ሄሮድስ ነበረ። ይህም ሄሮድስ ምን ዓይነት ሰው እንደ ነበረ ያሳያል፤ ፈቃዱ ደካማ፥ ተድላን የሚወድ፥ ሥራውም ትክክል ይሁን ስሕተት ብዙም የማይገደው ሰው ነበረ።

እንደ ሌሎቹ ሺህ ሰዎች፥ ታላላቆችና ታናናሾች፥ ንጉሡ ሄሮድስም በፋሲካ በዓል ለመካፈል ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሄሮድስ አይሁዳዊ ነበረና የአይሁድን በዓላት ያከብር ነበር፤ የይሁዳ አገረ ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ግን ሮማዊ ነበረ፥ የሮምንም ጣዖታት ያመልክ ነበር። ሄሮድስ ኢየሱስ ለፍርድ ወደ እርሱ በመላኩ እጅግ ደስ አለው፤ ይህም በከፊል የተጐራባች አገሮች ገዦች የሆኑት ጲላጦስና ሄሮድስ ወዳጆች ስላልነበሩ፥ ይህ ሥራ፥ ማለትም ኢየሱስን ለፍርድ መላኩ፥ ጲላጦስ ሄሮድስን ወዳጁ ሊያደርገው እንደ ፈለገ ያሳይ ስለ ነበር ነው። ደግሞም ኢየሱስ በቅፍርናሆም ሲኖርና በገሊላ ሁሉ ሲያስተምር ሄሮድስ ስለ እርሱ ብዙ ሰምቶ ነበር። ከዚህ ቀደም ብሎ ለንጉሡ ሄሮድስ ኢየሱስ ስላደረጋቸው ብዙ ድንቅ ሥራዎች፥ ድውዮችን እንዴት እንደሚፈውስ፥ ለዕውሮች ማየትን እንደሚሰጥ፥ ሙታንንም እንኳ እንደሚያስነሣ በነገሩት ጊዜ ሄሮድስ «ይህ እኔ የገደልሁት መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ ከሙታን ተነሥቶአል» እንዳለ ታስታውሳላችሁ።

ሄሮድስ የሚኖረው በኢየሩሳሌም ሳይሆን በገሊላ ቢሆንም፥ በዚያች ከተማ ቤተ መንግሥት የሚባል ያማረ ቤት ነበረው፤ በኢየሩሳሌም ሳለም በዚህ ቤተ መንግሥት ይቀመጥ ነበር። የጲላጦስ ወታደሮች ኢየሱስን ወደዚህ ቤተ መንግሥት ታላቅ አዳራሽ አመጡት፤ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋም፥ ብዙዎቹ የአይሁድ ካህናትና አለቆችም በኢየሱስ ላይ ሊናገሩ ከእነርሱ ጋር መጡ። ሄሮድስ ብዙ የሰማለትን ነቢዩንና ተአምር አድራጊውን ኢየሱስን በማየቱ እጅግ ደስ አለው። ኢየሱስ ተአምር ሲያደርግ ለማየት ተመኘ፥ እንዲያደርግም አዘዘው፤ ኢየሱስ ለሞትም ሆነ ለሕይወት በእጁ ስለ ሆነ እርሱን ደስ ለማሰኘት እጅግ ይጓጓል ብሎ አስቦ ነበርና።

ነገር ግን እንደምታውቁት፥ ኢየሱስ ተአምራቱን ሰዎች እንዲመለከቱአቸው ብቻ ብሎ ፈጽሞ አያደርግም ነበር። ድውዮችን የሚፈውሳቸው ወይም ለደንቆሮዎች መስማትን የሚሰጣቸው በችግራቸው ስለሚራራላቸው ነበር፤ ሄሮድስ ግን አንድ ድንቅ ሥራ እንዲያደርግ እየጠየቀ በተናገረው ጊዜ ኢየሱስ ዝም ብሎ ቆመ፥ ምንም ሊያደርግም አልወደደም። ሄሮድስ ብዙ ጥያቄ ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን አልመለሰለትም፥ ዝም አለ። ንጉሡ ሕይወቱን ለማዳን እንኳ አንዲት ቃል የማይናገረውን እንዲህ ያለውን እስረኛ ምን እንደሚያደርገው አላወቀም።

ኢየሱስ ዝም ብሎ ሳለ በዚህ ጊዜ ሁሉ ካህናቱና አለቆቹ በዙሪያው ቆመው በልዩ ልዩ ክፋት፥ የአገሩን ሕግ በመተላለፍ፥ በሄሮድስም ገዛ አገር ራሱን ንጉሥ ለማድረግ በመሞከር ይከስሱት ነበር። ኢየሱስ ግን ለከሰሱበት ክስ ሁሉ አንድም አልመለሰም።

ሄሮድስ በኢየሱስ ላይ ሊዘብትበት አሰበ። ኢየሱስ «የአይሁድ ንጉሥ ነኝ» ብሎአል ብለው በሐሰት ይናገሩ ስለ ነበር፥ ሄሮድስ ነገሥታት የሚለብሱትን የመሰለ ያማረ ካባ አስመጥቶ ኢየሱስን አለበሰው። ከዚያም በፊቱ ዝቅ ብለው እየሰገዱ «ንጉሥ» ብለው ጠሩት፤ የንጉሥነት ሥልጣን እንዳለው እንደሚያስመስል ሰው አድርገው አፌዙበት። ነገር ግን በዚያ በሚያፌዙት ሕዝብ መካከል ኢየሱስ ጸጥ ብሎና ረግቶ፥ ምንም ልብ ሳይል፥ ሐሳቡ በሌላ ስፍራ እንዳለ መስሎ ቆሞ ነበር።

ሄሮድስ ኢየሱስ ለሞት የሚያበቃ ምንም እንዳላደረገ፥ ደግና ጕዳት የሌለበት ሰው እንደ ሆነ በሚገባ ያውቅ ነበር። ካህናቱና አለቆቹ ደጋግመው እንዲያደርግ የሚገፋፉትን፥ ኢየሱስ እንዲገደል ማዘዝን፥ አላደረገም። ስለዚህ ለጥቂት ጊዜ ካናቀውና ካዋረደው በኋላ ኢየሱስ የንጉሥ ልብሱን እንደ ለበሰ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው።


ቀዳሚ ቀጣይ