የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ በሮማዊው አገረ ገዥ ፊት

ምዕራፍ 93 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ በሮማዊው አገረ ገዥ ፊት

የአይሁድ ታላቁ ሸንጎ ኢየሱስ እንዲገደል ቢፈርድበትም፥ ያለ ሮማዊው አገረ ገዥ ያለ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ፈቃድ ሊገድሉት አይችሉም ነበር፤ ሮማውያን ማንንም ሰው የመግደልን መብት ከዚህ ብዙ ጊዜ በፊት ከአይሁድ ወስደው ነበርና። ስለዚህ የካህናት አለቆችና አለቆቹ በማለዳ ፀሐይ ሳይወጣ ኢየሱስን አገረ ገዡ ወደሚኖርበት ግንብ አመጡት። የእርሱ መኖሪያ ስድሳ ማይል ያህል ርቃ በባሕር ዳርቻ ባለችው በቂሣርያ ከተማ ነበረ፤ ነገር ግን በፋሲካ ጊዜ፥ ከተማይቱ ከየአገሩ ክፍል በመጡ ሰዎች በምትጨናነቅበት ወቅት፥ ጸጥታና ሥርዓት እንዲጠበቅ ለመቈጣጠር ብዙውን ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣ ነበር፤ በዚህም ጊዜ ከቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን «የአንቶኒያ ግንብ» በሚባል ምሽግ ውስጥ ይኖር ነበር።

አይሁድ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ የፈረዱት እንደሚሉት «እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ» ብሎአል በማለት ነበር፤ ይህም በሕጋቸው ሞት የሚገባው ከባድ ወንጀል ነበር። ኢየሱስ በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ፤ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኑም ሊያከብሩትና ትምህርቱን ሊታዘዙ ይገባቸው ነበር። ነገር ግን ጲላጦስ ለሕጋቸው ግድ እንደማይለው፥ ኢየሱስም «የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ» ስላለ ብቻ እንዲገደል እንደማያዝዝ በሚገባ ያውቁ ነበር። ስለዚህ ከሮማውያን ሕግ ጋር የሚቃረን አንድ ነገር በኢየሱስ ላይ ለማግኘት ተነሡ፤ ሊያቀርቡትም የወሰኑት ክስ ኢየሱስ በሮማውያን አገዛዝ ላይ ተናግሮአል፥ ራሱንም የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሎአል የሚል ነበረ። እርሱ በእርግጥ ንጉሥ ነበረ፤ ነገር ግን ሮማውያንንና መንግሥታቸውን የሚቃወም ዓይነት ንጉሥ አልነበረም።

አይሁድ ወደ ግንቡ መጥተው በውጭ ቆሙ፤ ጲላጦስም ከተኛበት ክፍል ወጥቶ ወደ እርሱ ባመጡት ሕግ ተላላፊ ላይ እንዲፈርድ ጠሩት። ጲላጦስ ነገሩን በጥንቃቄ ሳይመረምር እንደ ፈቃዳቸው ያደርጋል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። እርሱም ወርዶ እንደ ዳኛ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠና እንዲህ አለ፦

«በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?»

እነርሱም «ይህ ሰው ሕግን የጣሰ ክፉ ሰው ባይሆን ኖሮ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር» ብለው መለሱ።

ጲላጦስም «እንግዲያስ የአገሩን ሕግ ጥሶ ከሆነ ወደ ራሳችሁ ፍርድ ቤት ወስዳችሁ ቅጡት» አለ።

የአይሁድ አለቆችም እንዲህ አሉ፤ «ይህ ሰው በየስፍራው ሕዝቡን ከገዦቻቸው ሲያስኰበልል አገኘነው። ለሮማውያን ንጉሠ ነገሥት ለቄሣር ግብር እንዳይከፍሉ ይከለክላቸዋል፤ እኔ ክርስቶስ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሎ ለሕዝቡ ይነግራቸዋል። ሕዝቡን በመንግሥት ላይ ስላነሣሣ ሊገደል ይገባዋል፤ በእርሱም ላይ እንድትፈርድበት እንለምንሃለን።»

ጲላጦስ ወዲያውኑ በእነዚህ የአይሁድ አለቆች ላይ እጅግ ይጠራጠራቸው ጀመር። እነርሱ ራሳቸው የሮማውያንን ኃይል እንደሚጠሉና የሚቃወመውን ማንንም ሰው ለማስቀጣት ፈጽሞ እንደማይሹ ያውቅ ነበር። በመካከላቸው ታስሮና ረዳት አጥቶ የቆመውን ኢየሱስን ተመለከተ፤ ይህም ሰው አደገኛ ጠላት ሊሆን እንደማይችል አሰበ። ጲላጦስም እንዲህ አላቸው፦

«ይህን ሰው ወደ እኔ አምጡት። ላነጋግረው እፈልጋለሁ።»

ኢየሱስም ወደ ጲላጦስ የፍርድ ዙፋን ደረጃዎች ግርጌ ቀረበ፤ ጲላጦስም ጠየቀው፤

«የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?»

ኢየሱስም ለአገረ ገዡ «አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ንጉሥ እንደ ሆንሁ ነገሩህን?» ብሎ መለሰለት።

ጲላጦስም «እኔ አይሁዳዊ ይመስልሃለሁን?» ብሎ ጠየቀ። «የገዛ ወገኖችህና ካህናቱ ንጉሥ ነኝ ብለሃል ብለው ወደ እኔ አቀረቡህ። እንግዲህ ንገረኝ፥ ምን አድርገሃል?»

ኢየሱስም «ንጉሥ ሆኜ የምገዛው አገዛዝ የዚህ ዓለም አይደለም» አለ። «መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ለአይሁድ እንዳልሰጥ ሰዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ መንግሥቴ ግን እዚህ በምድር ላይ አይደለችም።»

ጲላጦስም «እንግዲያ አንተ ንጉሥ ነህ!» አለ።

ኢየሱስም «እውነት ተናገርህ፥ እኔ ንጉሥ ነኝ» አለ። «ለዚህ ተወልጃለሁ፤ ስለ እውነት እመሰክር ዘንድ ለዚህ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ከእውነት ወገን የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማል።»

ጲላጦስም «እውነት! እውነት ምንድር ነው?» አለ። ከዚያም ከአዳራሹ ወጥቶ ለአይሁድ አለቆች እንዲህ አላቸው፦

«በዚህ ሰው ላይ አንዳች በደል አላገኘሁበትም።»

ይህ የጲላጦስ ውሳኔ አይሁድን እጅግ አስቈጣቸው፤ ብዙ ጥያቄ ሳይጠይቅ ፍርዳቸውን ያጸድቃል ብለው ተስፋ አድርገው ነበርና፤ አሁን ግን ኢየሱስን ሊፈታው ፈቃደኛ እንደ ሆነ አዩ። ጲላጦስ ኢየሱስ ምንም ጉዳት የማያደርስ ሰው እንደ ሆነ፥ ምናልባትም ንጉሥ ነኝ ብሎ በማመኑ አእምሮው ፍጹም ጤነኛ እንዳልሆነ አሰበ።

አለቆቹ ግን በኢየሱስ ላይ መክሰሳቸውን አላቋረጡም። ጲላጦስንም «ይህ ሰው በየስፍራው ሕዝቡን ያነሣሣል፤ ሁከትም ያስነሣል። በገሊላ ጀመረ፤ አሁንም ወደዚህ መጥቶአል» አሉት።

ጲላጦስም «ምን? ይህ ሰው ከገሊላ ነውን?» አለ። «እንግዲያስ የንጉሥ ሄሮድስ ግዛት ነው፤ ሄሮድስም አሁን እዚህ በኢየሩሳሌም አለ። ወደ ሄሮድስ ውሰዱት፤ ሄሮድስም ጉዳዩን ይወስን።»

ጲላጦስ ይህን ያለው ራሱ ከመወሰን ለመሸሽ ስለ ፈለገ ብቻ ነበር። ኢየሱስ አንድም ሕግ እንዳልጣሰና ሊፈታ እንደሚገባው ያውቅ ነበር፤ ነገር ግን የአይሁድን አለቆች ማስቀየም አልፈለገም፤ ኢየሱስንም በገሊላ ገዥ በሄሮድስ ፊት እንዲፈረድበት በመላክ ከጉዳዩ ራሱን ነጻ ለማድረግ አሰበ።


ቀዳሚ ቀጣይ