የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ በቀያፋ ፊት

ምዕራፍ 92 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ በቀያፋ ፊት

ኢየሱስ አሁን በሥርዓት ለመፈረድ የቀረበበት ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ለብዙ ዓመታት በሹመቱ ላይ ቆይቶ ነበር። እርሱ ብልጥና ተንኰለኛ ሰው ነበረ፤ ለትክክልም ሆነ ለስሕተት እምብዛም ግድ አልነበረውም፤ ነገር ግን የሮማውያንን ገዦች ሳያስቈጣ የአይሁድን መሪዎች ደስ የሚያሰኘውን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ሁልጊዜ የተዘጋጀ ነበረ።

ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ካስነሣው በኋላ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ባመኑ ጊዜ፥ ይህ ቀያፋ እንዲህ እንዳለ ታስታውሳላችሁ፤ «ኢየሱስ ንጹሕ ቢሆንም በደለኛ ቢሆንም፥ ደግ ቢሆንም ክፉ ቢሆንም፥ ከችግር ለማምለጥ የሚቀልልን መንገድ እርሱን መግደል ነው፤ ይህንንም ማድረግ አለብን።» ይህም የሊቀ ካህናቱን የቀያፋን መንፈስ ያሳያል።

የሐናና የቀያፋ ቤቶች እርስ በርሳቸው ብዙም አይራራቁም ነበር፤ ምናልባትም በጽዮን ተራራ ላይ በአንድ የሕንፃዎች ስብስብ ውስጥ ሳይሆኑ አይቀሩም። ሎሌዎቹና ዘበኞቹ ኢየሱስን በሊቀ ካህናቱ ቤት ወዳለው ሰፊ አዳራሽ አስገቡት፤ በዚያም በዚህ ድንገተኛ ጊዜ ሊሰበሰቡ የቻሉት የአይሁድ ሸንጎ አባላት ሁሉ ተሰብስበው ነበር። ኢየሱስ በአትክልቱ ውስጥ የተያዘው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጥቂት አለፍ ብሎ ነበር፤ ኢየሱስ በቀያፋና በሸንጎው ፊት የቆመው ዓርብ ጠዋት ከሌሊቱ በአሥር ሰዓትና በአሥራ አንድ ሰዓት መካከል ሳይሆን አይቀርም።

ጴጥሮስ ከሕዝቡ ጋር መጥቶ በሊቀ ካህናቱ ቤት ግቢ ውስጥ ነበረ። ዮሐንስ በዚያ አልነበረም፤ ነገር ግን ልጅዋ በጠላቶቹ እጅ እንደ ወደቀ የሚገልጸውን አስጨናቂ ወሬ ለማድረስና ሊያጽናናትም ለመሞከር የኢየሱስ እናት ማርያም ወደምትኖርበት በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤት ሄዶ ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስ እንደ ገና ኢየሱስን በሚቃወሙ ብዙ ሰዎች መካከል ብቻውን ቀረ።

በአይሁድ ሕግ ሁለት ሰዎች ተገኝተው ያ ሰው ሲያደርግ ያዩትን ክፉ ሥራ ወይም ሲናገር የሰሙትን ክፉ ቃል ካልመሰከሩበት በቀር ማንም ሊገደል አይችልም ነበር፤ ደግሞም የእነዚህ የሁለቱ ምስክሮች ቃል መስማማት ነበረበት። አለቆቹም መጥተው ስላዩትና ስለ ሰሙት በኢየሱስ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮችን ፈለጉ። እነዚህ በኢየሱስ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮች እውነትን ቢናገሩም ሐሰትን ቢናገሩም ግድ አልነበራቸውም፤ የፈለጉት ሁሉ በቃላቸው እንዲስማሙ ብቻ ነበር። በኢየሱስ ላይ በሐሰት የመሰከሩ ብዙዎች ነበሩ፤ ነገር ግን የተናገሩት አልተስማማም። ከጊዜ በኋላ ሁለት ሰዎች ተነሥተው እንዲህ አሉ፦

«ይህ ሰው በቤተ መቅደስ ‹ይህን በሰው እጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሳለሁ፤ በሦስት ቀንም በእጅ ያልተሠራውን ሌላ እሠራለሁ› ሲል እኛ ራሳችን ሰምተነዋል።»

ነገር ግን እነዚያ ምስክሮች እንኳ ኢየሱስ ተናገረ ስለሚሉት ነገር ቃላቸው አልተስማማም። ከሦስት ዓመት በፊት ኢየሱስ በቤተ መቅደስ «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ» ማለቱን ታስታውሳላችሁ። እርሱ ግን የተናገረው ስለ አይሁድ ቤተ መቅደስ ሳይሆን የጌታ ቤተ መቅደስ ስለ ሆነው ስለ ራሱ፥ ስለ ሞቱና ከመቃብር ስለ መነሣቱ ነበር። እነዚህ ሰዎች የኢየሱስን ቃል ሲተርኩት እንዴት እንደ ለወጡት ታያላችሁ።

አይሁድ ማንም ሰው የእግዚአብሔርን ቤት ስለ ማፍረስ መናገሩ እጅግ ክፉ ነገር እንደ ሆነ፥ እንዲህ ያለውን ነገር የሚናገርም ሁሉ መገደል እንዳለበት ተስማምተው ነበር። ስለዚህ የእነዚህ የሁለቱ ሰዎች ቃል ባይስማማና ሐሰት ቢሆንም፥ ቀያፋና ሸንጎው ኢየሱስን የመግደል ዓላማቸውን የሚፈጽሙበት አጋጣሚ በዚህ አገኙ።

ሊቀ ካህናቱ ቀያፋም ተነሥቶ በታላቅ ድምፅና በቍጣ እንዲህ አለው፦

«እነዚህ ምስክሮች ስለ ተናገሩት ነገር ምን ትላለህ? አንዳች መልስ የለህምን?»

ኢየሱስ ግን ዝም ብሎ ቆመ፤ አንዲትም ቃል አልተናገረም። የሚለው ምንም ቢሆን ሊገድሉት ቈርጠው ነበርና መናገሩ እንደማይጠቅመው ያውቅ ነበር። ጥቂት ከጠበቀ በኋላ ቀያፋ እንደ ገና ተናገረ።

«አንተ ክርስቶስ ነህን?» ብሎ ጠየቀ፤ «የዚያ የቡሩክ ልጅ ነህን?»

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በግልጥ ተናገረ፦

«እኔ ነኝ» ብሎ መለሰ፤ «ከዚህም በላይ የሰው ልጅ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ሁላችሁ ታያላችሁ!»

በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ እጅግ ተቈጣ። በቍጣውም ልብሱን ቀደደ፤ እጆቹንም ወደ ላይ ወርውሮ ጮኸ፦

«ምን ያለ አስፈሪ፥ አስፈሪ ቃል ነው!» ብሎ ሊቀ ካህናቱ ጮኸ። «ይህ ሰው ራሱን ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር እኩል ያደርጋል! ከእንግዲህ ምስክሮች አያስፈልጉንም፤ በራሱ ላይ ፍርዱን ራሱ ተናግሮአል። ራሱን አምላክ ብሎ በሚጠራ ሰው ላይ ምን ይደረግ?»

በዚያን ጊዜ ሸንጎው ሁሉ በአንድ ድምፅ «ሞት ይገባዋል» አሉ፤ በኢየሱስም ላይ የሞት ፍርድ ተፈረደ።

በዚያን ጊዜ በፊቱ ይተፉበትና ይመቱት ጀመር። ፊቱንም በልብስ ሸፍነው ከመቱት በኋላ «ነቢይ ነህን? እንግዲያስ የመታህ ማን እንደ ሆነ ንገረን!» ይሉት ነበር።

በዚህ ጊዜ ሁሉ ጴጥሮስ በሕንፃው ግቢ ውስጥ ነበረ፤ በተከፈተውም በር በኩል ኢየሱስ በውስጠኛው ክፍል ቆሞ ያየው ነበር። ከገረዶቹም አንዲቱ ጴጥሮስን አትኵራ ተመለከተችውና በመጨረሻ እንዲህ አለች፦

«አንተ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ ነህ!»

ጴጥሮስም «የምትዪውን አላውቅም» ብሎ መለሰ፤ ከሰዎቹም ተለይቶ በውጭ ወዳለው መተላለፊያ ሄደ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ፤ ጴጥሮስም ሰማው።

ያስተዋለችውም ሴት ደግሞ በአጠገብ ለቆሙት «ያ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው!» እያለች ትነግራቸው ጀመር። እርሱ ግን እንደ ገና ካደ። ጥቂት ቆይቶ ሌላ ሰው ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦

«አንተ በእርግጥ ከዚህ ሰው ወገን ነህ! አነጋገርህ እንኳ ከገሊላ እንደ መጣህ ያሳያል! ቃልህን የምትናገረው እንደ ገሊላ ሰው ነው!»

ጴጥሮስም ይረገምና ይምል ጀመር፤ «የምትሉትን ሰው አላውቀውም፤ ከቶም አይቼው አላውቅም!» አለ።

ጴጥሮስ ይህን ሲናገር ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። በዚያችም ቅጽበት ጌታ ኢየሱስ በውስጠኛው ክፍል ሆኖ ዘወር ብሎ ከተከፈተው በር ውጭ የቆመውን ጴጥሮስን ተመለከተው። ያን ጊዜ ጌታው በፊተኛው ምሽት «ነገ ጠዋት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ከቶ እንዳላወቅኸኝ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ» ያለው ቃል ድንገት ወደ ጴጥሮስ አእምሮ መጣ። ጴጥሮስም ወጥቶ ሄደ፤ ስለ ነገሩ ሁሉ ባሰበ ጊዜ በኀዘን ተሞልቶ መራራ እንባ አለቀሰ።

ነገር ግን በዚያች ጠዋት በችግር ላይ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ብቻ አልነበረም። ችግሩ እጅግ የጠለቀ አንድ ሰው ነበረ። ያም ሰው ጌታውን በገንዘብ የሸጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበረ። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ እንደ ፈረዱ ባወቀ ጊዜ፥ ይሁዳ እርሱ ምን ያህል ክፉ እንደ ነበረና በበደለኛ ሥራው ምክንያት ኢየሱስ ሊገደል እንደ ሆነ አየ። የተሰጠውንም ሠላሳውን ብር ወደ ቤተ መቅደስ መልሶ አምጥቶ በወለሉ ላይ ጣለውና እንዲህ አለ፦

«ንጹሕ ሰው አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ! ገንዘባችሁን መልሳችሁ ውሰዱ!»

ካህናቱም «እኛስ ምን አግዶን?» ብለው መለሱ፤ «ያ የአንተ ጉዳይ ነው እንጂ የእኛ አይደለም።»

ይሁዳም ሄደ፤ በኀዘኑም ተረብሾ ታንቆ ራሱን ገደለ። በማግሥቱም ተሰቅሎ ሞቶ ተገኘ። የካህናት አለቆችም እርሱ መልሶ ያመጣውን ገንዘብ ምን እንደሚያደርጉት አላወቁም። እንዲህም አሉ፦

«የደም ዋጋ ነውና ያንን ገንዘብ ሕዝቡ ለቤተ መቅደስ ከሰጡት መባ ጋር መጨመር ከቶ አይገባም።»

በመጨረሻም ገንዘቡን ወስደው በከተማው ለሚሞቱ እንግዶች መቃብር የሚሆን መሬት ገዙበት። መሬቱን የገዙት ከሸክላ ማሰሮዎችና እንስራዎች ከሚሠራ ሰው ነበር፤ ስሙም «የሸክላ ሠሪው መሬት» ተባለ። ሕዝቡ ሁሉ ግን ከዚያ ወዲህ «የደም መሬት» ብለው ጠሩት።


ቀዳሚ ቀጣይ