ምዕራፍ 91 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ኢየሱስ በሐና ፊት
ኢየሱስን ይዘው ያሰሩት ሰዎች የቤተ መቅደሱ ዘበኞች ነበሩ፤ አለቃቸውም ይመራቸው ነበር። ከእነርሱም ጋር ከካህናቱና ከሎሌዎቹ አንዳንዶች ነበሩ፤ አለቆቹም ከየጎዳናው የሰበሰቧቸው እጅግ የተዋረዱ ሰዎች ብዙ ሕዝብ ሆነው አብረዋቸው ነበሩ። እነዚህ ሁሉ በአንድነት የሚጮኽና ሥርዓት የሌለው ሁከተኛ ሕዝብ ሆነው ኢየሱስን ከጌቴሴማኒ አትክልት እየጐተቱ አውጥተው በጽዮን ተራራ ላይ ወዳለችው ከተማ አስገቡት። ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስ፥ ተከተሉ፤ ወደ ሕዝቡ ተጠግተው ነገር ግን ከመካከሉ ሳይገቡ ይሄዱ ነበር፤ ልባቸውም ስለ መምህራቸው በፍርሃት ተሞልቶ ነበር።
የቤተ መቅደሱ ዘበኞች ኢየሱስን በገመድና በሰንሰለት ታስሮ ሳለ በጽዮን ተራራ ላይ በከተማው ቅጥር ውስጥ ወዳለው ቤት አመጡት፤ በዚያም ሐና የሚባል ከካህናት አለቆች አንዱ ይኖር ነበር። ሐና በአንድ ወቅት ሊቀ ካህናት ነበረ፤ ማለትም በካህናት ሁሉ ራስ ላይ የቆመ ታላቅ ካህን ነበረ፤ ነገር ግን የአገሩ ሮማውያን ገዦች ሹመቱን ከእርሱ ወስደው የሐና ልጅ ባል የሆነውን ቀያፋን በእርሱ ፋንታ ሊቀ ካህናት አደረጉት። ከሕዝቡ ብዙዎች ሮማውያን ሹመቱን ከሐና ለመውሰድ መብት እንዳልነበራቸው ያምኑ ነበር፤ አሁንም እርሱን እንደ እውነተኛና ትክክለኛ ሊቀ ካህናት ይቈጥሩት ነበር። ሐና ብዙዎች የሚፈሩት ታላቅ ኃይል ያለው ሰው ነበረ፤ ስለዚህ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች አስቀድመው ወደ ሐና ቤት አመጡት። በቤቱም ውስጥ ከታላላቆቹ አለቆችና ከአይሁድ ታላቁ ሸንጎ አባላት ብዙዎች ተሰብስበው ነበር። ኢየሱስም በሁሉም ፊት ቀረበ። ሐናም ያስተማረውን ምን እንደ ሆነና ደቀ መዛሙርቱ እነማን እንደ ሆኑ እንዲነግረው ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት፦
«ትምህርቴ በስውር ከቶ አልነበረም፤ ሁልጊዜ በግልጥና በሕዝብ ፊት ተናገርሁ። ሕዝቡ ለአምልኮ በሚሄዱባቸው በየምኵራቡና በቤተ መቅደስ በሁሉ ስፍራ ተናገርሁ። የተናገርሁትን ስለ ምን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ሰዎች ጠይቅ፤ እነርሱ የተናገርሁትን ያውቃሉ።»
ኢየሱስ ይህን ሲናገር በአጠገቡ ቆሞ ከነበሩት ዘበኞች አንዱ ኢየሱስን በእጁ በብርቱ መታውና እንዲህ አለ፦
«ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?»
ኢየሱስም በእርጋታ መለሰለት፤ «እውነት ያልሆነ ነገር ተናግሬ እንደ ሆነ አስረዳ፤ እውነትን ተናግሬ እንደ ሆነ ግን ስለ ምን ትመታኛለህ?»
ኢየሱስ ወደ ሐና ቤት በገባ ጊዜ ዮሐንስ ሕዝቡን ተከትሎ ወደ ውስጥ ገባ፤ ዮሐንስ ሊቀ ካህናቱን ያውቀው ነበርና ወደ ቤቱ ለመግባት አልፈራም። ጴጥሮስ ግን በውጭ በጎዳናው ላይ ቆሞ ነበር። ዮሐንስም በሩን ትጠብቅ የነበረችውን ሴት አነጋግሮ በውጭ የቆመውን ሰው እንድታስገባው ለመናት፤ እርስዋም በሩን ለጴጥሮስ ከፈተችለት። የቤቱ ክፍሎች በአንድ ገላጣ ግቢ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ ጴጥሮስም በግቢው ውስጥ በአገልጋዮቹና በዘበኞቹ መካከል ቆመ። ብርድ ነበረና በማንደጃ ውስጥ የከሰል እሳት አንድደው ነበር፤ ማንደጃ ማለት በሦስት ወይም በአራት እግሮች ላይ የሚቆም የብረት ሳሕን ነው። ሰዎቹም በዚህ እሳት ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ ጴጥሮስም በግቢው ውስጥ በመካከላቸው ቆሞ ይሞቅ ዘንድ እጆቹን በእሳቱ ላይ ዘርግቶ ነበር። በሩን የምትጠብቀው ሴትም ጴጥሮስን አትኵራ ተመለከተችውና እንዲህ አለች፦
«አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?»
ጴጥሮስ በኢየሱስ ጠላቶች መካከል ብቻውን ነበረ፤ ዮሐንስ ኢየሱስ በሐናና በሌሎቹ አለቆች ፊት ወደ ቆመበት ክፍል ገብቶ ነበርና። ጴጥሮስም ድንገት ፍርሃት ያዘው፤ ለዚህችም ሴት ጥያቄ እንዲህ ብሎ መለሰ፦
«አይደለሁም!»
ምስኪን ጴጥሮስ! ጌታውን መካድ ገና አሁኑኑ ጀምሮ ነበር!
ሐና በኢየሱስ ላይ ፈራጅ ሆኖ ለመሥራት መብት እንደሌለው ያውቅ ነበር። ሊያደርግ የሚችለው ሁሉ ኢየሱስን መመርመር፥ የሚናገረውን መስማት፥ ጠላቶቹም በእርሱ ላይ ክስ የሚያቀርቡበትን ምክንያት ከቃሉ ውስጥ ለማግኘት መሞከር ብቻ ነበር። ስለዚህ ጥቂት ቆይቶ ሐና ኢየሱስን እንደ ታሰረ በሕግ ሊቀ ካህናት ወደ ነበረው ወደ ቀያፋ ሰደደው።