የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በጌቴሴማኒ አትክልት

ምዕራፍ 90 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

በጌቴሴማኒ አትክልት

በፋሲካ ሳምንት የኢየሩሳሌም ከተማ ከወትሮው ሦስት ወይም አራት እጥፍ የሚሆን ሕዝብ ትይዝ ስለ ነበረ፥ በቅጥሮቿ ያሉት በሮች ቀንና ሌሊት ተከፍተው ይቆዩ ነበር፤ በዓመቱ አብዛኛው ጊዜ ግን ፀሐይ ስትጠልቅ ይዘጉ ነበር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከእራቱ ክፍል ወጥተው ከቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን አጠገብ ባለው በምሥራቁ ቅጥር በኩል ባለ በር ሲያልፉ ሐሙስ ሌሊት እኩለ ሌሊት ሊሆን ተቃርቦ ነበር። ወደ ቄድሮን ወንዝ ሸለቆ ወረዱ፥ ወንዙንም በድልድይ ላይ ተሻገሩ። በሸለቆው ማዶ ጌቴሴማኒ የተባለ የወይራ ዛፎች አትክልት ቦታ ደረሱ። ኢየሱስ ይህን አትክልት ብዙ ጊዜ ይጐበኘው ነበር፤ ፀጥ ያለ ስፍራ ነበረና፤ በወይራ ዛፎቹም ጥላ ሥር መጸለይ ይወድ ነበር። አትክልቱ በዙሪያው ቅጥር ነበረው፤ በበሩም ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው።

«ወደ አትክልቱ ውስጥ ገብቼ እስክጸልይ ድረስ እዚህ ተቀመጡ።»

ከደቀ መዛሙርቱም ሦስቱን፥ ስምዖን ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ይዞ ከእነዚህ ሦስቱ ጋር ወደ አትክልቱ ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ጌታቸው በኀዘን እንደ ተሞላ ሆኖ የጥልቅ ትካዜ ምልክት ማሳየቱን ያስተውሉ ጀመር። ሦስቱንም ደቀ መዛሙርት እንዲህ አላቸው።

«ልቤ አዝኖአል፤ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኖአል፤ በዚህ ቆዩ፥ ትጉም።»

ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በግንባሩ በምድር ላይ ወደቀ፥ ወደ አብም ጸለየ።

«አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ!» ብሎ ጮኸ። «አንተ ሁሉን ማድረግ ትችላለህ! እባክህ ይህችን ጽዋ ከእኔ አርቃት! ነገር ግን አንተ የምትወደውን ብቻ እንጂ የእኔን ፈቃድ እንዲሆን አልለምንም።»

ኢየሱስ የተናገረለት «ጽዋ» እጅግ በቅርብ ጊዜ ይደርስበት የነበረው አስጨናቂ መከራ ነበረ። በእነዚያ የመጨረሻ ጊዜያት ፍርዱና ሞቱ እንደ ጥቁር ደመና ሲቀርቡ ባየ ጊዜ መንፈሱ ተጨነቀ። ጸሎቱም እጅግ ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ ላቡ እንደ ደም ጠብታ በፊቱ ላይ ታየ። በዚያን ጊዜ መልአክ ከሰማይ መጥቶ ሊያበረታውና ሊረዳው በአጠገቡ ቆመ።

ከዚያም ተነሥቶ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት ወደ ተዋቸው ስፍራ ሄደ። እነርሱም ጌታቸውን በቅርቡ እንደሚያጡ በማወቃቸው በተሰማቸው ጭንቀት ተሸንፈው እንቅልፍ ወስዶአቸው ነበር። ኢየሱስም ጴጥሮስን እንዲህ አለው።

«ስምዖን ሆይ፥ ትተኛለህን? አንድ ሰዓት ስንኳ ከእኔ ጋር ልትተጋ አልቻልህምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ሁላችሁም ትጉና ጸልዩ። መንፈሳችሁ ዝግጁ እንደ ሆነ አውቃለሁ፥ ሥጋችሁ ግን ደካማ ነው።»

ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ብሎ ጸለየ።

«አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! አንተ ሁሉን ማድረግ ትችላለህ! ይህችን ጽዋ ከእኔ አርቃት! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ እንጂ የእኔ ፈቃድ እንዲሆን አልሻም።»

ተመልሶም ሲመጣ ዓይኖቻቸው ከብደው ስለ ነበረና ሊገልጡአቸው ስላልቻሉ እንደ ገና ተኝተው አገኛቸው። በቀሰቀሳቸውም ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ ተኝተው በመገኘታቸው አፍረው ስለ ነበረ የሚመልሱለትን አላወቁም። ኢየሱስም ትቶአቸው ለሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። በዚህም ጸሎት እንዲህ አለ።

«አባቴ ሆይ፥ ይህች ጽዋ ልትወገድ ባትችል፥ ልጠጣትም ግድ ቢሆንብኝ፥ እንግዲያስ ፈቃድህ ይሁን!»

ደግሞም ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ሄዶ እንደ ቀድሞው ተኝተው አገኛቸው። አሁንም እንዲህ አላቸው።

«ከዚህ በኋላ ልትረዱኝ ጊዜው አልፎአልና አሁን ተኙ፥ ዕረፉም። ሰዓቴ ደርሶአል! የሰው ልጅ በክፉ ሰዎች እጅ ተሰጥቶአል። ኑ፥ ተነሡ፥ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል!»

ይህንም ቃል ሲናገር በዚያው ቅጽበት አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ሰይፍና ዱላ ከያዙ ብዙ ሰዎች ጋር ወደ አትክልቱ ዘሎ ገባ። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን እንዲይዙ በካህናት አለቆችና በሹማምንቱ የተላኩ ነበሩ። ኢየሱስ ከእራት በኋላ ሲናገር ሰላዮች በቤቱ አጠገብ ይጠብቁ ነበር፤ ሌሎችም ኢየሱስ በበሩ ሲወጣ በዚያ ይጠብቁ ነበር። ኢየሱስ በአትክልቱ ውስጥ እንዳለ ለካህናት አለቆች ወሬ ተላከ፤ እርሱም ወደ አባቱ ሲጸልይ እነዚህ ሰዎች በአስቆሮቱ ይሁዳ እየተመሩ ኢየሱስን ለመያዝ ወደዚያ ስፍራ ይቻኮሉ ነበር።

ኢየሱስን ሊይዙት የመጡት ሰዎች ሙሉ ጨረቃ ብታበራም እንኳ በሌሊት ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ለይተው ሊያውቁት እንደሚችሉ እርግጠኞች አልነበሩም። ስለዚህ ይሁዳን እንዲህ አሉት።

«በጨለማ፥ በዛፎቹም ሥር፥ እስረኛ አድርገን የምንይዘው ማን እንደ ሆነ እንዴት እናውቃለን?»

ይሁዳም። «እኔን ተመልከቱ፤ ቀርቤ አንድን ሰው በሳምሁ ጊዜ ያዙት፤ የምስመው እርሱ የምትፈልጉት ሰው ነውና» አላቸው።

ስለዚህ ይሁዳ ወደ አትክልቱ ገባ፤ በዚያን ጊዜ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሁሉ በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው ነበር። ይሁዳም እየሮጠ ቀርቦ «መምህር ሆይ! መምህር ሆይ!» እያለ እርሱን በማየቱ ደስ እንዳለው ሰው ሆኖ ሳመው።

ኢየሱስም። «ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?» አለው።

ከዚያም ፋኖሶቻቸውንና ችቦዎቻቸውን፥ ሰይፎቻቸውንና ጦሮቻቸውን ይዘው ወደ ቆሙት ሰዎች ወደ ፊት ቀረበ።

እነዚህንም ሰዎች። «ማንን ትፈልጋላችሁ?» አላቸው።

እነርሱም። «የናዝሬቱን ኢየሱስን» ብለው መለሱለት።

ኢየሱስም። «እኔ ነኝ» አላቸው። ይህን ባለ ቅጽበት እንደ ፈሩ ሆነው ወደ ኋላ አፈገፈጉ፥ በምድርም ላይ በግንባራቸው ወደቁ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ደግሞ እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው።

«ማንን ትፈልጋላችሁ?»

እነርሱም ደግሞ። «የናዝሬቱን ኢየሱስን» ብለው መለሱ።

ኢየሱስም። «እኔ እንደ ሆንሁ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው ይሂዱ» አለ።

ኢየሱስ በዚያች ሰዓት እንኳ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ያስብ ነበር እንጂ ስለ ራሱ ደኅንነት አላሰበም። የጥቂት ጊዜ መዘግየትም ለደቀ መዛሙርቱ ጥቂት ድፍረት ሰጣቸው። እንዲህም ብለው ይጠይቁ ጀመር።

«ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታን?»

ስምዖን ጴጥሮስም ከኢየሱስ መልስ ሳይጠብቅ ይዞት የመጣውን ሰይፍ መዘዘ፥ ማልኮስ የተባለውን የሊቀ ካህናቱን ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ በዚያን ጊዜ ሰዎቹ ከወደቁበት ተነሥተው እየቀረቡ ነበርና። ኢየሱስም እንዲህ አለ።

«ቢያንስ ይህን ላድርግ፤» ጆሮውንም ዳሰሰው፤ ወዲያውም ጆሮው እንደ ገና ዳነ።

ኢየሱስም ጴጥሮስን። «ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና። በአንድ ቃል አባቴን ብለምነው አሁን እንኳ በደኅና እንዲጠብቁኝ ዐሥራ ሁለት ሠራዊት መላእክትን እንደሚልክልኝ አታውቅምን? አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን?» አለው።

ከዚያም ሊይዙት ወደ መጡት ሰዎች ዘወር አለ።

«ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ልታስሩኝ ወጣችሁን? ዕለት ዕለት በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር ነበርሁ፥ እጃችሁንም አልጫናችሁብኝም። አሁን ግን ሰዓታችሁ ደርሶአል፥ የጨለማውም ኃይል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል።»

ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስን ለመከላከል ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ባዩ ጊዜ ትተውት ብቻውን ሸሹ። የሰዎቹም ቡድን ኢየሱስን በሰንሰለት አስረው ወሰዱት።

ነገር ግን ዮሐንስ፥ ጴጥሮስም ደግሞ፥ በጌታቸው ላይ የሚደረገውን ለማየት ተጨንቀው ቡድኑን ተከተሉ። ማርቆስ የተባለው ጐበዙ ዮሐንስም እርሱን እየተከተለ ሳለ ከቡድኑ አንዱ ልብሱን ይዞ ሊይዘው ሞከረ። እርሱም ተጠቅልሎበት የነበረውን የበፍታ ልብስ በሰውየው እጅ ትቶ ውስጥ ልብሱን ብቻ ለብሶ አምልጦ ሄደ።


ቀዳሚ ቀጣይ