ምዕራፍ 89 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃሎች
ኢየሱስ ከእራቱ በኋላ በዚያው ክፍል ውስጥ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የሚያደርገውን የመጨረሻውን ንግግሩን ቀጠለ። ከተናገራቸውም ብዙ ነገሮች መካከል እንዲህ አለ።
«ይህች ለእናንተ የምሰጣችሁ የመጨረሻዪቱ ትእዛዜ ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት የሚበልጥ የፍቅር ማስረጃ ሊያሳይ የሚችል ማንም የለም። እኔ የማዝዛችሁን ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ‹ባሮች› ብዬ አልጠራችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ነገር ግን ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ስለ ነገርኋችሁ ‹ወዳጆች› ብዬ ጠርቻችኋለሁ። እኔን የመረጣችሁኝ እናንተ አይደላችሁም፤ እኔ ግን መረጥኋችሁ፤ በስሜም ከአብ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ሄዳችሁ የሚኖር ፍሬ እንድታፈሩ ሾምኋችሁ።»
«እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዝዛችኋለሁ። ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ አስታውሱ። ከዓለም ብትሆኑ ዓለም የራሱን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መርጫችኋለሁና ከዓለም ስላልሆናችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ‹ባርያ ከጌታው አይበልጥም› ያልኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን ሊጐዱኝ ከሞከሩ እናንተንም ደግሞ ሊጐዱአችሁ ይሞክራሉ። ቃሌን ከጠበቁ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። በቅዱስ መጽሐፍ ‹በከንቱ ጠሉኝ› ተብሎ ተጽፎአል፤ ያም ቃል በእኔ ላይ ተፈጽሞአል፤ ምንም ምክንያት ሳይኖር በእውነት ጠልተውኛልና። ነገር ግን እኔ ወደ እናንተ የምልከው ያ አጽናኝ፥ ከአብ የሚወጣው የእውነት መንፈስ፥ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ጀምሮ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ስለ እኔ ትመሰክራላችሁ።»
«በሚመጣው ዘመን ይህን ነገር አውቃችሁ እንዳትደክሙና እንዳትሰናከሉ ይህን አሁን ነግሬአችኋለሁ። ከምኵራቦቻቸው ያወጡአችኋል፤ እንዲያውም የሚገድላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሚያቀርብ የሚመስለው ጊዜ ይመጣል። ይህንም የሚያደርጉት አባቴንም እኔንም በእውነት ስላላወቁ ነው። ነገር ግን ጊዜው በደረሰ ጊዜ፥ አለቆቹና ሕዝቡ ጠላቶቻችሁ ሆነው ስታገኙአቸው፥ እኔ እንደ ነገርኋችሁ እንድታስታውሱና ለዚህ ሁሉ ተዘጋጅታችሁ እንድትገኙ ይህን አሁን እነግራችኋለሁ።»
«እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ባልሄድ ያ አጽናኝ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ፥ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚመጣውንም ነገር ያስታውቃችኋል። ጥቂት ጊዜ ነው፥ ከእንግዲህም ወዲህ አታዩኝም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ዳግመኛም ታዩኛላችሁ።»
እነዚህ ቃሎች ለደቀ መዛሙርቱ ለመረዳት አስቸጋሪ መሰሉአቸው። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ።
«‹ጥቂት ጊዜ ነው አታዩኝም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ ነው ታዩኛላችሁ›፥ ደግሞም ‹ወደ አብ እሄዳለሁ› ብሎ የሚነግረን ምን ማለቱ ነው? ‹ጥቂት ጊዜ› የሚለውስ ምን ማለቱ ነው?»
ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ዐወቀ፤ እንዲህም አላቸው። «‹ጥቂት ጊዜ ነው አታዩኝም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ ነው ታዩኛላችሁ› ስል ምን ማለቴ እንደ ሆነ ለማወቅ ትጠያየቃላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ በጣም ጥቂት ጊዜ ቆይታችሁ እናንተ ታለቅሳላችሁ ታዝኑማላችሁ፤ በዙሪያችሁ ያለው ዓለም ግን ደስ ይለዋል። ደግሞም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል፤ እንደ ገና ታዩኛላችሁና፥ ደስታችሁንም ከእናንተ የሚወስድ ማንም የለም።»
ኢየሱስ ይህን ሲል ደቀ መዛሙርቱ እንዲረዱ የፈለገው ነገር ይህ ነበር፤ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከእነርሱ ተወስዶ እንዲሞት በመስቀል ላይ እንደሚሰቀል፥ እንደሚቀበርም፥ ይህም ሁሉ ሕመምና ኀዘን እንደሚያመጣባቸው ነው። ነገር ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ ከመቃብር ዳግመኛ ይነሣል፤ ከዚያም በኋላ ምንም እንኳ እንደ ገና ትቶአቸው ወደ አብ ቢሄድ፥ ከቶ በማያልፍ ደስታ ደስ ይላቸዋል፥ ሐሤትም ያደርጋሉ።
ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ እጆቹን ወደ እግዚአብሔር አንሥቶ ጸለየ። በጸሎቱም እንዲሠራው የተሰጠውን ሥራ ለመፈጸም ስለ ቻለ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ደግሞም ስለ ደቀ መዛሙርቱ ጸለየ፤ ሁሉም በልባቸው አንድ እንዲሆኑ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲዋደዱ፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ታማኞች ሆነው እንዲጠበቁ ለመነ። ደግሞም ስለ እነዚህ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን፥ በቃላቸው አማካይነት የዓለም መድኃኒት አድርገው በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ ጸለየ፤ እርስ በርሳቸው እየተዋደዱ ሁሉም በአንድ ልብ እንዲሆኑ፥ ከኢየሱስና ከአባቱም ጋር አንድ እንዲሆኑ ለመነ።
ኢየሱስ ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ ሁሉም በአንድነት መዝሙር ዘመሩ፤ ከእራቱም ክፍል ወጥተው ፀጥ ወዳሉት ወደ ከተማይቱ መንገዶች ሄዱ። ከሰዓት በኋላ ወደ መጡባት ወደ ቢታንያ የሚመለሱ መስለው ወደ ደብረ ዘይት አቅጣጫ ተጓዙ።
ከቤቱ በወጡ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ የሚባል አንድ ጐበዝ ነበረ። እርሱ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እራት የበሉበት ቤት ባለቤት ልጅ ሳይሆን አይቀርም። ይህ እውነት ከሆነ የእናቱ ስም እንደ ኢየሱስ እናት ስም ማርያም ነበረ፤ ነገር ግን እርስዋ ያች ሴት አልነበረችም። ከብዙ ዘመን በኋላ ይህ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ የኢየሱስን ሕይወት የሚተርኩትን ከአራቱ ወንጌሎች አንዱን፥ «የማርቆስ ወንጌል» የተባለውን፥ ጻፈ።