ምዕራፍ 9 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ወደ ቤተ መቅደስ የቀረበው ሕፃን
ኢየሱስ በበረት ቢወለድና በግርግም ቢተኛም በዚያ ስፍራ ብዙ አልቈየም። ከጥቂት ቀናት በኋላ ዮሴፍ ወጣቷ እናትና ሕፃንዋ የሚወሰዱበት ይበልጥ የተመቸ ቤት ማግኘት ቻለ። አይሁድ ከወገናቸው ለሆኑ እንግዶች እጅግ ደጎች ነበሩ፤ በከተሞቻቸው በሚያልፉበትም ጊዜ በቤታቸው ይቀበሉአቸው ነበር።
ዮሴፍና ቤተሰቡ በቤተ ልሔም ለጥቂት ሳምንታት፥ ምናልባትም ለጥቂት ወራት ቈዩ። ቤተ ልሔምን መኖሪያቸው ለማድረግና ይህን ሕፃን፥ የዳዊትን ልጅ፥ በዳዊት ከተማ ለማሳደግ አስበው ይሆናል፤ በዚያም ሕይወቱ ምንም ይሁን ምን ከገጠሪቱ መንደር ከናዝሬት ይልቅ ለሚመጣው ሕይወቱ የተሻለ ትምህርት ሊያገኝ ይችል ነበር።
ኢየሱስ አርባ ቀን በሆነው ጊዜ ከእናቱ ጋር ከቤተ ልሔም ስድስት ማይል ብቻ ወደምትርቀው ወደ ኢየሩሳሌም ተወሰደ። በዚያም ለእግዚአብሔር እንደ ተሰጠና የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ እንደሚያድግ ለሚያሳይ ሥርዓት ወደ ቤተ መቅደስ ቀረበ። በአይሁድ ዘንድ የመጀመሪያው ልጅ ለቤተሰብ ሲወለድ ስለ እርሱ በቤተ መቅደስ መሠዊያ ላይ መሥዋዕት እንዲቀርብና ጸሎት እንዲደረግ ሥርዓት ነበር። ባለጠጋ ቤተሰብ ለመጀመሪያ ልጁ በግ ያቀርብ ነበር፤ በጉም ታርዶ በልጁ ፈንታ ለእግዚአብሔር ስጦታ ሆኖ በመሠዊያው ላይ ይቃጠል ነበር። ቤተሰቡ ድሀ ወይም ከሠራተኛው ሕዝብ ወገን ከሆነ ግን ወላጆቹ ሁለት ዋኖሶች ወይም ርግቦች ያቀርቡ ነበር። ዮሴፍና ማርያም ሁለት ዋኖሶች አመጡ፤ እነዚህም በመሠዊያው ላይ ሲቃጠሉ ማርያም ሕፃንዋን በክንድዋ ታቅፋ በአጠገቡ ቆሙ።
በዚያን ጊዜ በቤተ መቅደስ ስምዖን የሚባል አንድ ሽማግሌ ነበረ። እርሱም ደግ ሰው ነበረ፤ በነቢያት አማካይነት ከጥንት ጀምሮ ተስፋ የተሰጠውን የእስራኤልን መሲሕ ንጉሥ፥ የእግዚአብሔርን ክርስቶስ፥ እስኪያይ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ወደ እግዚአብሔር አጥብቆ ይጸልይ ነበር። እግዚአብሔርም ክርስቶስን ሳያይ እንደማይሞት ለስምዖን ነግሮት ነበር። በዚያች ጠዋት «ወደ ቤተ መቅደስ ሂድ» የሚለው ድምፅ የተናገረው መሰለው። በዚያች ቀን ወደዚያ ስፍራ ለምን እንደ ተላከ ሳያውቅ ታዘዘ።
ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደስ ሲያስገቡ የጌታ ድምፅ እንደ ገና ለስምዖን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦
«ይህ ሕፃን የዳዊት ልጅ፥ የእስራኤል ንጉሥ ነው።»
ሽማግሌውም ቀርቦ እጆቹን ዘረጋ፤ ሕፃኑንም ተቀብሎ ወደ ብብቱ አቀፈው፤ ዓይኖቹንም ወደ ሰማይ አንሥቶ በዕብራይስጥ ቅኔ እንዲህ አለ፦
«ጌታ ሆይ፥ አሁን ባሪያህን
እንደ ቃልህ በሰላም ታሰናብተዋለህ፤
እነዚህ ዓይኖቼ መድኃኒትህን አይተዋልና፤
ለሕዝብ ሁሉ የላክኸውን፥
ለአሕዛብ የሚያበራ ብርሃን፥
ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር።»
ዮሴፍና ማርያም ከዚህ በፊት አይተውት በማያውቁትና በማያውቁት ሽማግሌ ሥራና ቃል እጅግ ተደነቁ። እርሱ ግን ሕፃኑን መልሶ በእጃቸው ሲያኖር ለዮሴፍና ለማርያም የእግዚአብሔርን በረከት ጸለየላቸው።
እንዲህም አለ፦ «ስሙ፤ ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መውደቅና መነሣት ምክንያት ይሆናል። የእግዚአብሔር የምሕረት ምልክት ይሆናል፤ ብዙዎች ግን ይቃወሙታል። እናት ሆይ፥ በአንቺም ነፍስ ደግሞ ኀዘን እንደ ሰይፍ ያልፋል፤ የብዙ ልብ አሳብም ይገለጣል።»
እነዚያ ቃላት በዚያን ጊዜ እጅግ እንግዳ መሰሉ፤ ከብዙ ዘመን በኋላ ግን ኢየሱስ አድጎ ሰው በሆነ ጊዜ፥ ማርያም ጠላቶች በልጅዋ ላይ ሲሰበሰቡ ባየች ጊዜና በመጨረሻም በመስቀል ላይ ሲሞት በተመለከተች ጊዜ ቃሉ ምን ያህል እውነት እንደ ነበረ አወቀች። በዚያን ጊዜ በእውነት ሰይፍ በማርያም ነፍስ አለፈ።
በዚያው ቅጽበት አንዲት ሴት ወደ ትንሹ ቡድን ቀረበች። እርስዋም እጅግ አሮጊት ነበረች፤ ዕድሜዋም ከዘጠና ዓመት በላይ ነበር፤ መበለትና እግዚአብሔርን የምትፈራ አምላኪ ስለ ነበረች ዘመንዋን ሁሉ በቤተ መቅደስ እየጸለየች ትኖር ነበር። እግዚአብሔር ለእርስዋም ስለሚመጣው ክርስቶስ፥ ስለ መድኃኒቱና ስለ ንጉሡ ተስፋ ነግሮአት ነበር። እርስዋም በዚህ ትንሽ ሕፃን ተስፋ የተሰጠውን መሲሕ አየች፤ በታላቅ ድምፅም እግዚአብሔርን አመሰገነች አከበረችም። የሰሙአት ሁሉ በቃልዋ ተደነቁ፤ ተራ ልብስ የለበሱትን እነዚህን አባትና እናት ከሕፃናቸው ጋር ሲመለከቱ ይበልጥ ተደነቁ፤ ሁሉም ከገጠር እንደ መጡ ግልጥ ነበር፤ የዮሴፍና የማርያም አነጋገርም ከሩቅ ሰሜን ከገሊላ እንደ መጡ ያሳይ ነበር።
እንዲሁም ኢየሱስ ገና የአርባ ቀን ብቻ ሕፃን ሳለ፥ በዚህ በኢየሩሳሌም ጥቂት ሰዎች አይተውት ስለሚመጣው የእስራኤል ንጉሥ ተናገሩለት።
ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ይዘው በቤተ ልሔም ወዳለው አዲሱ ቤታቸው ተመለሱ፤ ማርያምም ከዚያች በቤተ መቅደስ ከዋለችበት ቀን በኋላ ለረጅም ጊዜ በዝምተኛ ልብዋ የምትሰውረው ብዙ አሳብ ነበራት።