ምዕራፍ 10 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
ኮከቡን የተከተሉ ሰዎች
ዮሴፍና ማርያም ከሕፃኑ ከኢየሱስ ጋር ገና በቤተ ልሔም ሳሉ ከሩቅ አገር የመጡ አንዳንድ ሰዎች እንግዳ ጥያቄ ይዘው በመምጣታቸው የኢየሩሳሌም ከተማ ታወከች። እነዚህ ሰዎች አይሁድ አልነበሩም፤ አሕዛብ ነበሩ። አሕዛብ አይሁድ ከራሳቸው በቀር ለሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የሰጡት ስም ነው። ሮማውያንን፥ ግሪኮችን፥ ግብፃውያንንና ከወገናቸው ያልሆኑትን ሌሎችን ሁሉ አይሁድ «አሕዛብ» ብለው ይጠሩአቸው ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት እነዚህ የአሕዛብ እንግዶች ያገኙትን ሰው ሁሉ እንዲህ ብለው ይጠይቁ ነበር፦
«የአይሁድ ንጉሥ ሊሆን የተወለደው ሕፃን የት እንደሚገኝ ልትነግሩን ትችላላችሁን? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልናከብረው መጥተናል።»
እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ? ያዩትስ ኮከብ ምን ነበር?
አገራቸው የትኛው እንደ ሆነ በእርግጥ አናውቅም፤ ነገር ግን ብዙዎች ዛሬ ፋርስ የሚባለው፥ በዚያን ጊዜ ግን ጳርቴ ተብሎ ይታወቅ የነበረው፥ ከይሁዳ በምሥራቅ አንድ ሺህ ማይል ያህል የሚርቀው አገር እንደ ሆነ ያስባሉ። በዚያ አገር አንዳንድ አይሁድ ይኖሩ ነበር፤ አይሁድ እንደ ዛሬው ያን ጊዜም በየአገሩ በተለይም በታላላቅ ከተሞች ይገኙ ነበርና። የጳርቴ ሕዝብ ግን አይሁድ አልነበሩም፤ አይሁድ እንደሚጠሩአቸው አሕዛብ ነበሩ። ከአይሁድ ወገን ባይሆኑም በአንድ ነገር አይሁድን ይመስሉ ነበር፤ ሰው ለሠራው ጣዖት ፈጽሞ አይሰግዱም ነበር። የምድርን ሁሉ አንዱን አምላክ ያመልኩ ነበር፤ ፊታቸውንም ወደ ፀሐይ መልሰው ይጸልዩ ነበር። ፀሐይን ሳይሆን ፀሐይን የሚመስለውን፥ የዓለም ብርሃን የሆነውን አንዱን አምላክ እናመልካለን ይሉ ነበር።
ከእነዚህ የጳርቴ ሰዎች መካከል በሌሊት በሰማይ ያሉትን ከዋክብት የሚመረምሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ዛሬ ከዋክብትን የሚመለከቱ ሰዎች እንዳላቸው ጨረቃንና ፕላኔቶችን ከዋክብትንም የሚያቀርብ መነጽር አልነበራቸውም፤ በገዛ ዓይናቸው ብቻ ይመለከቱ ነበር። ነገር ግን ለረጅም ጊዜ በማጥናት ስለ ከዋክብት ብዙ ተምረው ነበር፤ አካሄዳቸውንም ሊናገሩ፥ እያንዳንዱንም በሰማይ የት እንደሚያገኙት ሊያውቁ ይችሉ ነበር። ሕይወታቸውን ለዚህ የከዋክብት ጥናት የሰጡ ሰዎች ሰብአ ሰገል ይባሉ ነበር፤ ትርጓሜውም «ጥበበኞች» ማለት ነው። ስለዚህ በኢየሩሳሌም ሕፃኑን ንጉሥ ይፈልጉ የነበሩት እነዚህ እንግዶች አንዳንድ ጊዜ «ጥበበኞቹ»፥ አንዳንድ ጊዜም «ሰብአ ሰገል» ይባላሉ።
የዚያን ዘመን ሰዎች ታላላቅ ነገሥታት ሲወለዱ ወይም ከመሞታቸው በፊት እንግዳ ከዋክብት በድንገት በሰማይ እንደሚታዩ፥ ለጊዜውም አብርተው እንደዚሁ በድንገት እንደሚሰወሩ ያምኑ ነበር። ኢየሱስ በቤተ ልሔም ከመወለዱ አንድ ወይም ምናልባት ሁለት ዓመት በፊት ከዚያ ቀደም ታይቶ የማያውቅ እንዲህ ያለ እጅግ ብሩህ ኮከብ ማብራት ጀመረ። እነዚህ ሰዎችም ይህ ኮከብ በአገሮች ሁሉ ላይ የሚነግሥና በይሁዳ ምድር የሚገኝ ታላቅ ንጉሥ መምጣቱን እንደሚያመለክት በሆነ መንገድ በልባቸው ታወቃቸው።
እነዚህ ጥበበኞች ወዲያውኑ ወደ ይሁዳ ምድር ሄደው ይህን ሕፃን ንጉሥ ለማየት ቈረጡ። ከአንድ ሺህ ማይል የሚበልጥ ረጅምና አስቸጋሪ መንገድ ነበር። ከጳርቴ ደጋማ ሜዳዎች ወደ ባቢሎን ቈላ መውረድ፥ ሁለቱን ታላላቅ ወንዞች ጤግሮስንና ኤፍራጥስን የሚሻገሩበትን መንገድ መፈለግ ነበረባቸው። ከዚያም ምንም የማይበቅልበትና ውኃ የሌለበት መንገድ የማይታይበት ሰፊ ምድረ በዳ ያገኛሉ። ይህን ምድረ በዳ ለመዞር ቢሹ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ወደ ሰሜን ርቀው መሄድ፥ ከዚያም በረጃጅም ተራሮች ጥላ ሥር ወደ ደቡብ መጓዝ ነበረባቸው፤ በመጨረሻም ወደ ይሁዳና ወደ ታላቂቱ ከተማዋ ወደ ኢየሩሳሌም ይደርሳሉ። አንድ ዓመት በሚፈጀው በዚያ ረጅምና አድካሚ ጕዞ ሁሉ፥ አብዛኛውን መንገድ በግመሎች ላይ ሆነው ሲጓዙ፥ ያ ድንቅ ኮከብ በሰማይ እየመራቸው ይመስል ነበር።
በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ከተጻፈው ታሪክ እንደምንረዳው እነዚህ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ኮከቡ ከእንግዲህ አያበራም ነበር። ነገር ግን አሁን በንጉሡ በራሱ አገር ስለ ነበሩ ኮከቡ መጥፋቱ ብዙም አያሳስብም ነበር፤ በዚያ አገር በተለይም በኢየሩሳሌም ከተማ ያለ ሰው ሁሉ ልዑላቸው እንደ ተወለደ ያውቃል ብለው አስበው ነበርና። ነገር ግን የሚያስደንቅ ሆኖ ስለ አዲሱ ንጉሥ መወለድ የሰማ አንድም ሰው አልተገኘም። ኢየሱስ በተወለደባት ሌሊት መልአኩን ያዩትን የቤተ ልሔም እረኞች አላገኙም፤ ከአንድ ወር ወይም ከዚያ በላይ በፊት ሕፃኑን ክርስቶስን ያዩትን ሽማግሌውን ስምዖንንና ሐናንም አልሰሙም። ንጉሡ እንደ መጣ የሚያውቁት እጅግ በጣም ጥቂቶች ነበሩ፤ እነዚህ እንግዶችም ከእነዚያ ጥቂቶች አንዱንም በአጋጣሚ አላገኙም።
ይህን ወጣት ልዑል የት እንደሚፈልጉት በእርግጥ የሚያውቁበት አንድ ስፍራ እንዳለ አሰቡ፤ ይህም በኢየሩሳሌም ያለው የንጉሡ ቤተ መንግሥት ነበር። ሄሮድስ ያረጀና እጅግ የደከመ ቢሆንም ገና በሕይወት ነበረ፤ እንደ ቀድሞውም ጨካኝና አረመኔ ነበረ። ምናልባት የሚፈልጉት ልዑል የንጉሡ ልጅ ወይም የልጅ ልጅ ሊሆን ይችላል ብለው አስበው ይሆናል። ሄሮድስ በኢየሩሳሌም አይኖርም ነበር፤ ሕዝቧን አይወድም ነበርና፥ ሕዝቧም ምን ያህል እንደሚጠሉት ያውቅ ነበርና። ነገር ግን በከተማዋ ቤተ መንግሥት ነበረው፤ ለአጭር ጊዜም ብዙ ጊዜ ይመጣበት ነበር። ጥበበኞቹ በመጡ ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበረ ይሆናል፤ ወይም ሄሮድስን አብዛኛውን ጊዜ በሚኖርባት ሀያ ማይል ርቃ በምትገኘው በኢያሪኮ ፈልገውት ይሆናል።
አረጋዊው ንጉሥ የእነዚህን እንግዶች ጥያቄ እንደ ሰማና በኮከብ ተመርተው ወደ አገሩ እንደ መጡ እንደ ተረዳ እጅግ ደነገጠ። የአይሁድ ንጉሥ ሊሆን የተወለደ ሕፃን፥ እንዲህ ያለ ሕፃን ካለ፥ የሄሮድስ ዙፋንና ዘውድ ምን ይሆናሉ? ይህ ሕፃን የት እንዳለ ቢያገኝ ኖሮ መንግሥቱን ሊወስዱበት ይፈልጋሉ ብሎ የጠረጠራቸውን ብዙዎችን እንደ ገደለ፥ ወታደሮቹን ወደዚያ ልኮ ፈጥኖ ባስገደለው ነበር። ሄሮድስ ግን ክፉ አሳቡን ሰውሮ ስለ መጡበት ጕዳይ ለእንግዶቹ በደግነት ተናገራቸው። ኮከቡ መቼ እንደ ታየ፥ ምን እንደሚመስል፥ ንጉሥ መወለዱን እንደሚያሳይ እንዴት እንዳወቁ ጠየቃቸው።
ከዚያም ሄሮድስ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን በአገሩ ካሉት ሁሉ ይልቅ ጥበበኞች የሆኑትን የሕግ መምህራን አስጠራ። ሕዝቡ ሁሉ ክርስቶስ ብለውም የሚጠሩትን የመሲሕ ንጉሣቸውን መምጣት ይጠባበቁ እንደ ነበር ያውቅ ነበር።
ሄሮድስም «ይህ ታላቅ ንጉሥ፥ መሲሕ ወይም ክርስቶስ፥ በየትኛው ስፍራ እንደሚወለድ ልትነግሩኝ ትችላላችሁን?» ብሎ ጠየቀ።
ሊቃውንቱም መልሳቸውን አዘጋጅተው ነበር፤ እንዲህም አሉ፦
«ከዳዊት ዘር የሚወጣው ይህ ንጉሥ በዳዊት ከተማ በይሁዳ ቤተ ልሔም ይወለዳል። የጥንት ነቢያት ያሉት ይህ ነው።»
ንጉሡ ከቤተ ልሔም እንደሚወጣ የሚናገረውን ከነቢያት ተስፋዎች አንዱንም አነበቡለት።
ከዚያም ሄሮድስ ጥበበኞቹን እንደ ገና አስጠርቶ ኮከቡን መጀመሪያ ያዩበትን ትክክለኛ ጊዜ እንዲነግሩት ጠየቃቸው። ጊዜውንም በተረዳ ጊዜ ይህ ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የኖረው ንጉሥ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ በፊት በቤተ ልሔም ተወልዶ መሆን አለበት ብሎ ወዲያው አሰበ።
ሄሮድስ ጥበበኞቹን «ወደ ቤተ ልሔም ሂዱ፤ ይህን ሕፃን እስክታገኙት ድረስ ከተማዋን ሁሉ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ መጥታችሁ ንገሩኝ፤ እኔም ለዚህ ንጉሥ ክብር ልሰጠው እወዳለሁና» አላቸው።
ሄሮድስ የተናገረው ይህ ነበር፤ ሊያደርግ ያሰበው ግን ወደ ፊት እንደምናየው እጅግ ሌላ ነገር ነበር።
ጥበበኞቹም ከኢየሩሳሌም ስድስት ማይል ብቻ ወደምትርቀው ወደ ቤተ ልሔም ወዲያው ተነሡ። አንዱን ተራራ አልፈው በሄዱ ጊዜ አንዱ ሌላውን እንዲህ አለው፦
«እነሆ፥ ኮከቡ እንደ ገና ታየ! ልክ በፊታችን በሰማይ ተመልከቱት!»
ኮከቡ ወደ ቤተ ልሔም በሚወስደው መንገድ ላይ ቆሞ ነበር፤ እነርሱም እንደ ገና ደስ እያላቸው ተከተሉት። በቀጥታ ወደ ከተማዋ፥ ከዚያም ወደ አንድ ቤት መራቸው፤ በዚያ ቤት ላይም የቆመ መሰለ። በሩንም አንኳኩ፤ በተከፈተም ጊዜ ወደ አንዲት ክፍል ገቡ፤ በዚያም በወጣቷ እናቱ እቅፍ ውስጥ የተኛ ሕፃን አገኙ።
እነዚህ ጥበበኞች ለረጅም ጊዜ የፈለጉትና ብዙ መንገድ የተጓዙለት ንጉሥ ይህ እንደ ሆነ ወዲያው አወቁ። ምን ያህል እንደሚያከብሩት ለማሳየት በፊቱ እስከ ምድር ድረስ ሰገዱ። ከዚያም ከአገራቸው ያመጡትን ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ለነገሥታት የሚቀርብ ዓይነት ውድ ስጦታ ሰጡት። ወርቅን፥ ነጭ ዕጣንንና ከርቤን ሰጡት፤ እነዚህም ለመሥዋዕት የሚያገለግሉና እጅግ ውድ የሆኑ መዓዛ ያላቸው ሙጫዎች ናቸው። እንዲህም በገዛ አገሩ በንጉሣቸው መምጣት ደስታቸውን ያሳዩ ጥቂት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ፥ ከሩቅ አገር የመጡ እንግዶች ግን ክብር ሊሰጡት መጡ። ንጉሡ የት እንደ ተወለደ ለንጉሡ ለሄሮድስ ሊነግሩት የቻሉ ከተማሩት አይሁድ አንዳንዶቹ ሊያዩት ከጥበበኞቹ ጋር ይመጡ ነበር ብለን እናስብ ነበር። ነገር ግን እነዚህ ታላላቅ ሊቃውንት በእውነት ለኢየሱስ ብዙም ግድ አልነበራቸውም። በቤታቸው ተቀመጡ፤ የምሥራቅ ሰዎችንም፥ ጕዞአቸውንና ጥያቄአቸውንም ብዙም ሳይቈዩ ረሱ።