ምዕራፍ 8 · 6 ደቂቃ ንባብ · 7 ደቂቃ ማዳመጥ
ሕፃኑ ንጉሥ በግርግም አልጋው
ዮሴፍና ማርያም ከተጋቡ በኋላ ለጥቂት ወራት በናዝሬት ባለችው ትንሽ ቤታቸው ኖሩ። ዮሴፍ በአናጢነት ሙያው ይሠራ ነበር፤ ማርያም ደግሞ ቤትዋን ትጠብቅ ነበር፤ ለቤቱም የሚያስፈልገውን ውኃ በመንደሩ መካከል ካለው ጕድጓድ እንስራዋን ሞልታ በራስዋ ላይ ተሸክማ ታመጣ ነበር።
አንድ ቀን ዮሴፍ ወደ ቤት መጥቶ ቤተሰባቸው ወደ ተገኘበት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄድ እንደ ተጠራ ለሚስቱ ነገራት። ቀደም ብለን እንዳየነው ዮሴፍም ማርያምም ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት በቤተ ልሔም ከተወለደው ከታላቁ ንጉሥ ከዳዊት ዘር የወጡ ነበሩ። ከዳዊት ዘር የሆነ ሁሉ የትም ቢኖር ቤተ ልሔምን የቤተሰቡ የትውልድ ከተማ አድርጎ ይቈጥራት ነበር።
በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛውና ከይሁዳ ንጉሥ ከሄሮድስ በላይ የነበረው በሮም ያለው አውግስጦስ ቄሳር በሰፊው ግዛቱ ያሉ ቤተሰቦች ሁሉ እንዲቈጠሩ ትእዛዝ አወጣ። በእያንዳንዱ ቤተሰብ ላይ ግብር ሊጥል ፈልጎ ነበር፤ ይህም ለሹማምንቱ፥ ለሠራዊቱና ለቤተ መንግሥቱ መተዳደሪያ እያንዳንዱ ቤተሰብ ገንዘብ እንዲከፍል ማዘዝ ማለት ነው፤ ግብሩንም ለመወሰን የሕዝቡ ሁሉ ስም ተጽፎ ሊኖረው ያስፈልገው ነበር።
በእኛ አገር እንዲህ ያለው መዝገብ በየአሥር ዓመቱ ይዘጋጃል፤ የሕዝብ ቈጠራም ይባላል። በእኛ ዘንድ በየከተማውና በየመንደሩ ሰዎች ተመርጠው ሕዝቡ ወደሚኖርበት ቦታ እየሄዱ ስማቸውን ይመዘግባሉ። ከአገሪቱ ግዛቶች ሁሉ እነዚህ መዝገቦች ወደ አንድ መሥሪያ ቤት ይላካሉ፤ በዚያም ስሞቹ በሥርዓት ይደራጃሉ።
በዚያን ጊዜ ዓለምን ይገዙ የነበሩት ሮማውያን ግን ይህን ታላቅ መዝገብ ለማዘጋጀት ለራሳቸው አነስተኛ ድካም የሚያመጣውን መንገድ መረጡ፤ ምንም እንኳ ከበታቻቸው ላሉት ሕዝብ እጅግ የበዛ ድካም ቢያመጣና ረጅም መንገድ እንዲጓዙ ቢያስገድዳቸውም። በየቦታው ሰዎችን በሚኖሩበት ስፍራ የሚመዘግብ ሹም ከመሾም ይልቅ፥ እያንዳንዱ ቤተሰብ እነርሱ ወይም አባቶቻቸው ወደ ወጡበት ከተማ ወይም መንደር እንዲሄድና በዚያ የሕዝቡን መዝገብ ለሚያዘጋጁት ሹማምንት ስሙን እንዲሰጥ ሕግ አወጡ። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሆነው ከሴኬም ወይም ከኢዮጴ ወይም ከቂሣርያ የመጡ ሰዎች ከእነዚህ ስፍራዎች ወደ አንዱ ሄደው በዚያ መመዝገብ ነበረባቸው፤ በናዝሬት የሚኖሩ ሆነው እነርሱ ወይም ወላጆቻቸው ከሌላ ስፍራ የመጡ ሰዎችም ምንም ያህል ሩቅ ቢሆን ወደ ትውልድ ከተማቸው ሄደው በዚያ መመዝገብ ወይም በስሞች መዝገብ ላይ መጻፍ ነበረባቸው።
ማርያም ምንም እንኳ ራስዋ ከዳዊት ቤተሰብ የወጣች ብትሆን ከባልዋ ጋር ወደ ቤተ ልሔም እንድትሄድ ተገድዳ ነበር ብለን የምናስብበት ምክንያት የለም። የሮማውያን ሕግ ግብር የሚከፍሉ ባለጠጎች ካልሆኑ በቀር ሴቶችን ብዙም አይመለከትም ነበር። ዮሴፍ ብቻውን ወደ ቤተ ልሔም ሄዶ የሁለቱንም ስም በመዝገቡ ላይ ሊያስጽፍ ይችል ነበር። ማርያም ግን ወዲያውኑ አንድ ሐሳብ መጣላትና ባልዋን እንዲህ አለችው፦
«ወደ ቤተ ልሔም ብቻህን አትሄድም፤ እኔም ከአንተ ጋር እሄዳለሁ።»
ወጣቷ ሚስት ከባልዋ ጋር ረጅሙን መንገድ ለመሄድ ለምን እንደ ቈረጠች አልተነገረንም፤ ምክንያቱ ግን ይህ ሊሆን ይችላል፦ ማርያም ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ታውቅ ነበር፤ የሚወለድበትም ጊዜ ቀርቦ ነበር። ልጅዋ የዳዊት ልጅና የእስራኤል ንጉሥ እንደሚሆን፥ በዳዊትም ዙፋን እንደሚቀመጥ ታውቅ ነበር። ስለዚህ በገሊላ ባለችው በናዝሬት መንደር ሳይሆን በዳዊት ከተማ በቤተ ልሔም እንዲወለድ ፈለገች። እርሱ ከንጉሣዊው ዘር የሚወጣ ነበርና ልጅዋ ዳዊት ከኖረባት ከንጉሣዊቱ ከተማ እንዲወጣ አስቸጋሪና አድካሚ ጕዞን ለመታገሥ፥ መከራንም እንኳ ለመቀበል ፈቃደኛ ነበረች። ማርያም የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት አንብባ ነበር፤ በእነዚያም መጻሕፍት እግዚአብሔር የተናገራቸው ነቢያት መሲሕና ክርስቶስ ብለው የጠሩት ይህ ንጉሥ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ እንደ ጻፉ ታውቅ ነበር። ማርያም ከባልዋ ጋር ወደ አባቶቻቸው ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ለመሄድ ፈጥና የወሰነችው በእነዚህ ምክንያቶች ነበር።
ስለዚህ ዮሴፍ የአናጢነት ሱቁን ዘጋ፤ ሚስቱንም በአህያ ላይ አስቀምጦ በትሩን ይዞ በአጠገብዋ እየሄደ ተራራውን ተሻግሮ በሸለቆው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወረደ፤ ከዚያም ወንዙን ተከትሎ በሮማውያን መንገድ ተጓዘ፤ ይህም ማርያም ከጥቂት ወራት በፊት ከተጓዦች ወይም ከፒልግሪሞች ቡድን ጋር የሄደችበት ያው ረጅም መንገድ ነበር። ዮሴፍ በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም በዓላት ሲወጣ በዚያ መንገድ ብዙ ጊዜ ሄዶ ስለ ነበር የሚያልፉባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ያውቅ ነበር፤ በጕዞአቸውም ተራሮቹና ከተሞቹ በፊታቸው ሲታዩ ስለ ሕዝባቸውና በዚያ ስለ ተፈጸሙት ታላላቅ ነገሮች ለማርያም ታሪክ ይነግራት ነበር።
በሙት ባሕር ራስ አጠገብ ባለችው በኢያሪኮ ቆሙ፤ ከዚያም ወደ ምዕራብ ተመልሰው ወንበዴዎች በሚያዘወትሩበት መንገድ ተራሮቹን እየወጡ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ምናልባት በዚህች ከተማ አንድ ወይም ሁለት ቀን አርፈው ይሆናል፤ ከዚያም በቢታንያ መንደር አልፈው ወደ ደብረ ዘይት ተሻገሩ፤ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ስድስት ማይል ያህል ሄደውም በቤተ ልሔም በር ገቡ።
በቤተ ልሔም የሚያርፉበት ወዳጅ ስላልነበራቸው የእንግዶች ማረፊያውን፥ ማለትም ካን የሚባለውን ፈለጉ። ይህ በግቢ ዙሪያ ክፍሎች ያሉት ትልቅ ሕንፃ ነበር። እንስሶቹና ጓዙ በግቢው ውስጥ ይቀመጡ ነበር፤ እንግዶቹ ደግሞ በዙሪያው ባሉት ክፍሎች ያርፉ ነበር። ነገር ግን ለግብሩ ስማቸውን ለማስመዝገብ ወደ ቤተ ልሔም የመጡት ዮሴፍና ማርያም ብቻ አልነበሩም። ሌሎች ከእነርሱ አስቀድመው ማረፊያው ደርሰው ነበር። እነርሱ በደረሱ ጊዜ ግቢው በአህዮች፥ በግመሎች፥ በሰረገሎችና በጓዝ ተሞልቶ ነበር፤ በዙሪያው ያሉት ክፍሎችም ሁሉ በእንግዶች ተጨናንቀው ነበር። ዮሴፍ ሚስቱ ከረጅሙና ከአድካሚው ጕዞ በኋላ የምታርፍበትን ስፍራ በማረፊያው ቅጥር ውስጥ አላገኘም።
በመጨረሻ ግን ዮሴፍ ሌሊቱንና ጥቂት ቀናትን የሚያድሩበት ስፍራ አገኘ። ይህም በኮረብታው ጎን የተፈለፈለ ለከብቶች በረት የሚሆን ዋሻ ብቻ ነበር፤ ምንም እንኳ የተጐሳቈለ ቢሆን ማርያም በገለባው ላይ ተኝታ በማረፍዋ ደስ አላት። በዚያም በረት ዋሻ ውስጥ የማርያም ልጅ ተወለደ። ሕፃንዋንም በእጅዋ ባገኘችው ጨርቅ ጠቀለለችው፤ ለመጀመሪያ እንቅልፉም በሬዎች በሚበሉበት ግርግም አስተኛችው። የዳዊት ልጅ፥ በምድር ሁሉ ላይ የሚነግሠው ንጉሥ፥ ያልተከበረ አልጋ ይህ ነበር! ንጉሥ ሄሮድስ በቤተ መንግሥቱ አላወቀም፤ በሮም ያለው አውግስጦስ ቄሳርም አላለመም፤ በቤተ ልሔም ባለው ትሑት በረት ውስጥ ከይሁዳና ከሮም መንግሥት እጅግ በሚበልጥ ግዛት ላይ የሚነግሥ ልዑል ተኝቶ እንደ ነበረ፥ ዓለምም ሁሉ ዓመታቱን ያ ሕፃን ከተወለደበት ዓመት ጀምሮ እንደሚቈጥር፥ ስማቸውም ከተረሳ ብዙ ዘመን በኋላ ስሙ እንደሚመሰገን አላወቁም።
ንጉሥ ሄሮድስም ሆነ አውግስጦስ ቄሳር፥ ወይም በኢየሩሳሌም ያሉት ሊቀ ካህናቱና አለቆቹ አዲስ የተወለደውን ንጉሣቸውን ለመቀበል በዚያ ባይገኙም፥ በግርግም አልጋው አጠገብ አንዳንድ ጎብኚዎች ነበሩ። በቤተ ልሔም ዙሪያ ባለው መስክ ሌሊት መንጋቸውን የሚጠብቁ እረኞች ነበሩ፤ ልክ ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት በዚያው መስክ ብላቴናው እረኛ ዳዊት በጎቹን ከምድረ በዳ አራዊትና ከወንበዴዎች እየጠበቀ ይንከባከባቸው እንደ ነበረ።
ድንገትም ታላቅና የሚያንጸባርቅ ብርሃን በእረኞቹ ላይ በራ፤ ዘካርያስ በመሠዊያው አጠገብ እንዳየ፥ ማርያምም በናዝሬት እንዳየች፥ ክቡር መልአክ በፊታቸው ቆሞ አዩ። እረኞቹም በፍርሃት ተሞልተው የሚያበራውን መልክ ቀና ብለው ለማየት ሳይደፍሩ በግምባራቸው በምድር ላይ ወደቁ። መልአኩ ግን በደግነትና በቸርነት እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦
«አትፍሩ፤ ደስ የሚያሰኛችሁን የምሥራች ይዤ መጥቻለሁና፤ ይህም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ የሚሆን ዜና ነው። በዚህች ሌሊት በዚያች በዳዊት ከተማ መድኃኒት የሚሆን እርሱም ክርስቶስ ጌታችሁና ንጉሣችሁ ተወልዶአል። ሄዳችሁ ይህን ሕፃን ማየት ትወዳላችሁን? እንዴት እንደምታገኙት እነግራችኋለሁ። ሕፃናት በሚለብሱት ጨርቅ ተጠቅልሎ፥ በቤት ውስጥ በአልጋ ሳይሆን በሬዎችና አህዮች በሚታሰሩበት በረት ግርግም ውስጥ ተኝቶ ያለ አዲስ የተወለደ ሕፃን ፈልጉ። በዚያ የምድር ሁሉ ንጉሥ የሚሆነውን ሕፃን ታገኛላችሁ!»
እረኞቹ የዚህን መልአክ ቃል ሲሰሙ ሳሉ በላያቸው ያለው የእኩለ ሌሊት ሰማይ ሁሉ በብዙ የሰማይ ሠራዊት ተሞልቶ አዩ። እረኞቹም እንዲህ ሲዘምሩ ሰሙአቸው፦
«ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን
ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ።»
ከዚያም ራእዩ ጠፋ፤ የመላእክት ሠራዊትም ከዓይናቸው ተሰወሩ፤ በጨለማውም ሰማይ ከበላያቸው ከዋክብት ብቻ ያበሩ ነበር። እረኞቹም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦
«በጎቻችንን ለጥቂት ጊዜ እዚህ ትተን ወደ መንደሩ እንሂድ፤ የሆነውንም ይህን ድንቅ ነገር እንይ። ንጉሣችንን በመጀመሪያ እንድናይ ጌታ ይህን ቃል ለእኛ መስጠቱ እንዴት መልካም ነው!»
ቤተ ልሔም በዚያን ጊዜ ትንሽ መንደር ብቻ ስለ ነበረች እረኞቹ ትክክለኛውን በረትና ግርግሙን ለማግኘት ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። መጥተው በሩን ከፈቱ፤ መልአኩም እንደሚያዩ የነገራቸውን ልክ እንደዚያው አገኙ፤ አንድ ትንሽ ሕፃን በግርግም ተኝቶ፥ እናቱ አጠገቡ ሆና፥ ዮሴፍም ሁለቱን በፍቅር እየጠበቀ።
ንጉሣዊውን ሕፃን አዩ፤ በግርግም አልጋውም ዙሪያ ዝቅ ብለው ሰገዱ፤ ከዚያም ለረጅም ዘመን ተስፋ የተሰጠውን ንጉሥ በመላኩ ስለ ቸርነቱ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ መንጋቸው ወደ መስኩ ተመለሱ። እረኞቹ ይህን ታሪክ የነገሩአቸው ሰዎች ያምኑ ወይም አያምኑ እንደ ሆነ ሳያውቁ ተደነቁ፤ የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ይመጣል ብለው አልጠበቁም ነበርና። እነርሱ በቤተ መንግሥት የሚወለድ ልዑል እንጂ ከብቶች በሚታሰሩበት ጨለማ ዋሻ ውስጥ የሚወለድ የሠራተኛ ሴት ልጅ አልጠበቁም ነበር።
ማርያም ግን በልጅዋ ደስ ብሏት ወደ ልብዋ አቀፈችው፤ በናዝሬት ስለ መጣላት መልአክና ስለዚህ ሕፃን ስለ ተሰጣት ተስፋ ለማንም ምንም አልተናገረችም። ሕፃኑ ስም የሚወጣለት ቀን በደረሰ ጊዜ «ስሙ ኢየሱስ ይባላል» ብቻ አለች፤ ስሙ ለምን እንደ ተሰጠው ግን ለማንም አልነገረችም። በአይሁድ ዘንድ የተለመደ ስም ስለ ነበረ በስሙ የተደነቀ ማንም አልነበረም። ነገር ግን ይህ ሕፃን ምን እንደሚሆን ከስሙ ከ«ኢየሱስ» የበለጠ የሚገልጥ ቃል አልነበረም፤ ኢየሱስ የሚለው ቃል «መድኃኒት» ማለት ነውና።