ምዕራፍ 88 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
የወይን ግንዱና ቅርንጫፎቹ
ኢየሱስ እነርሱ ከእርሱ ጋር አብረውት ሊሄዱ ወደማይችሉበት ስፍራ እንደሚሄድና በጠላቶቹ መካከል ብቻቸውን እንደሚተዋቸው ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ በበተናገረው ቃል እጅግ ታውከው እንደ ተረበሹ አየ፤ ይልቁንም ጴጥሮስ በቅርቡ ጌታውን እንደሚክድና የቀሩትም ደቀ መዛሙርት ሁሉ ብቻውን መከራ እንዲቀበል ትተውት እንደሚሄዱ ስለ ነገራቸው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በፍርሃታቸውና በኀዘናቸው ውስጥ ሳሉ ሊያጽናናቸውና ልባቸውን ሊያበረታ ሞከረ።
«ልባችሁ አይታወክ፤» አላቸው፤ «በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔና በቃሌም እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ። ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ፤ ባዘጋጀሁም ጊዜ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ተመልሼ እመጣለሁ፥ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚወስደውን መንገድ ታውቃላችሁ።»
ቶማስም። «ጌታ ሆይ፥ አንተ ወዴት እንደምትሄድ እኛ አናውቅም፤ መንገዱንስ እንዴት እናውቃለን?» አለው።
ኢየሱስም። «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤» ብሎ መለሰ። «በእኔ በቀር ወደ አብ በሌላ መንገድ የሚመጣ ማንም የለም። እኔን ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፥ አይታችሁትማል፤ እኔን አይታችኋልና።»
ፊልጶስም። «ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየን፤ እኛ የምንፈልገው ከዚህ ሌላ ምንም አይደለም» አለው።
ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት። «ፊልጶስ ሆይ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል። እንግዲህ ‹አብን አሳየን› ስትል ምን ማለትህ ነው? አብና እኔ አንድ እንደ ሆንን፥ ማለትም እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምናገረው ቃል የአባቴ ቃል ነው፤ የማደርገውም ሥራ የአባቴ ሥራ ነው። እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ሥራ እንኳ ያደርጋል። እኔ ወደ አብ እሄዳለሁ፤ አብም በወልድ ይከበር ዘንድ በስሜ አብን የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።»
ኢየሱስም ቀጥሎ። «ብትወዱኝ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ታደርጋላችሁ፤» አለ፤ «እኔም አብን እለምናለሁ፥ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል። ያም አጽናኝ የእውነት መንፈስ ነው። የዚህ ዓለም ሰዎች ይህን መንፈስ ሊቀበሉት ከቶ አይችሉም፤ አያዩትምና አያውቁትምም። እናንተ ግን ታውቁታላችሁ፤ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራልና፥ በውስጣችሁም ይሆናልና። በኀዘናችሁ ብቻችሁን አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ገና ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርቷል፥ ዓለምም ከእንግዲህ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተም ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። ትእዛዛቴን ይዞ በልቡ የሚጠብቃቸው እርሱ የሚወደኝ ነው፤ የሚወደኝም በአባቴ ይወደዳል፤ እኔም እወደዋለሁ፥ ራሴንም እገልጥለታለሁ።»
ከዚያም ይሁዳ የተባለው ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ሳይሆን (እርሱ ቀድሞ ወጥቶ ነበርና)፥ የያዕቆብ ወንድም የሆነው ሌላው ይሁዳ። «ጌታ ሆይ፥ ራስህን ለዓለም ሳይሆን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?» አለው።
ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ። «የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም እንመጣለን፥ በእርሱም ዘንድ መኖሪያችንን እናደርጋለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ቃል ነው እንጂ የእኔ አይደለም። ይህን ሁሉ እኔ ገና ከእናንተ ጋር ሳለሁ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን አብ በእኔ ፋንታ የሚልክላችሁ አጽናኝ፥ መንፈስ ቅዱስ፥ እርሱ ማወቅ የሚገባችሁን ሁሉ ያስተምራችኋል፥ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላም ለእናንተ ይሁን! የራሴን ሰላም እሰጣችኋለሁ። ሰላሜን የምሰጣችሁ ዓለም ‹ሰላሙን› እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ፤ አትፍሩም።»
«እሄዳለሁ ወደ እናንተም ቶሎ እመለሳለሁ ስል ሰምታችኋል። በሙሉ ልባችሁ በእውነት ብትወዱኝስ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ አብ ከእኔ ይበልጣልና። ይህን ሁሉ፥ ማለትም እንደምሄድ፥ ሳይሆን አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ በሆነ ጊዜ፥ በቅርቡም ይሆናልና፥ አሁንም በእኔ እንድታምኑ፥ ዳግመኛም እንደምመጣ እንድታምኑ ነው።»
ከዚያም በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ «የወይን ግንዱና ቅርንጫፎቹ» የተባለውን ሌላ ምሳሌ ሰጣቸው። እንዲህም አለ።
«እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ አባቴም ገበሬው፥ የወይኑ አትክልት ጌታ ነው። እናንተ ደቀ መዛሙርቴና በእኔ የሚያምኑ ሁሉ የወይኑ ቅርንጫፎች ናችሁ። ገበሬው በወይኑ ግንድ ላይ ፍሬ የማያፈሩ ቅርንጫፎችን ቢያገኝ ይቈርጣቸዋል፤ ለምንም ነገር አይጠቅሙምና። ፍሬ የሚያፈሩትንም ቢያገኝ ከፊቱ የተሻለ ፍሬ እንዲያፈሩ ይገርዛቸዋል፥ ያጠራቸዋልም። እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ። ከእኔ ከወይኑ ግንድ ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ተጣብቄ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ ከወይኑ ግንድ ተለይቶ ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንደማይችል፥ እንዲሁ እናንተም ከእኔ ጋር ተጣብቃችሁ ባትኖሩ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም።»
«አስታውሱ፥ እኔ የወይን ግንድ ነኝ፥ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ራሱን ከእኔ ጋር አንድ አድርጎ የሚኖር፥ እኔንም ከራሱ ጋር አንድ አድርጎ የሚጠብቅ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ያለ እኔ ግን ምንም ልታደርጉ አትችሉም። ከእኔ ጋር ተጣብቆ የማይኖር ቢኖር እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል፥ ይደርቃልም፤ ከዚያም የማይረቡትንና የደረቁትን ቅርንጫፎች ሰዎች ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሏቸዋል፥ ይቃጠሉማል።»
«ከእኔ ጋር ተጣብቃችሁ ብትኖሩ ትምህርቴም በልባችሁ ቢኖር፥ የምትፈልጉትን ሁሉ ለምኑ፥ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ስታፈሩና በዚህም ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ስታሳዩ አባቴ በዚህ ይከበራል። አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ እንዲሁ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። እኔ የአባቴን ትእዛዛት በልቤ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ እናንተም ትእዛዛቴን በልባችሁ ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።»