ምዕራፍ 87 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
የጌታ እራት
የፋሲካን ማዕድ እየበሉ ሳሉ ኢየሱስ አንድ እንጀራ አንሥቶ በእጁ ይዞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ ባረከው። ከዚያም ቈርሶ ለእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር አንድ ቍራሽ ሰጠ። ሲሰጣቸውም እንዲህ አለ፦
«እንካችሁ፥ ብሉት፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠውን ሥጋዬን ያመለክታል።»
ከዚያም የወይን ጠጅ ጽዋ አንሥቶ ባረከው፤ ይህንም ደግሞ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ሰጣቸው፦
«ሁላችሁ ከዚህ ጠጡ፤ ይህ ኃጢአታቸውን ሊያስወግድ ስለ ብዙዎች የሚፈሰውን ደሜን፥ የአዲስ ኪዳንን ደም ያመለክታል። እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሮ ከወይን ፍሬ ፈጽሞ አልጠጣም።»
በጥንት ዘመን ስምምነት ወይም ተስፋ «ኪዳን» ይባል ነበር፤ ኪዳን ሲገባም በግ ወይም ፍየል ለመሥዋዕት ታርዶ ሊቃጠል በመሠዊያው ላይ ይቀመጥ ነበር። የመሥዋዕቱ ደም በመሠዊያው ላይ ይፈስ ነበር፤ ይህም «የኪዳኑ ደም» ይባል ነበር። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሊነግራቸው የፈለገው፥ በእርሱ ከሚያምኑት ኃጢአትን ሊያስወግድ እግዚአብሔር ለገባው ተስፋ ምልክት ሆኖ ደሙ በቅርቡ እንደሚፈስ ነው።
በቤተ ክርስቲያን በአንዳንድ አገልግሎቶች ላይ በነጭ ጨርቅ የተሸፈነ ማዕድ አይታችኋል። ጨርቁ ሲነሣም የእንጀራ ሳህኖችንና የወይን ጠጅ ጽዋዎችን አይታችኋል። አገልጋዩ እንጀራውን ለሕዝቡ እየሰጠ የኢየሱስን ቃል፥ «እንካችሁ፥ ብሉ፤ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው» ብሎ ይደግማል። ከዚያም በኋላ የወይን ጠጁ ሲወሰድ፥ «ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ይህ ነውና» ይላል። ይህ አገልግሎት «የጌታ እራት» ይባላል፤ የሚደረገውም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የበላውን የመጨረሻ ማዕድ በልቡናችን እንድናስብ ነው።
ከእራቱም በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ «ውድ ልጆቼ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር የምኖረው ገና ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ ከዚያም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም እንደ ነገርኋቸው አሁን ለእናንተም እላችኋለሁ፤ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም። እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ ይገባችኋል። እርስ በርሳችሁ በመዋደዳችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰው ሁሉ በዚህ ያውቃል።»
«ጌታ ሆይ፥» አለ ስምዖን ጴጥሮስ፥ «ወዴት ትሄዳለህ?»
«እኔ የምሄደው፥» ብሎ መለሰ ኢየሱስ፥ «አሁን ልትከተለኝ ወደማትችልበት ስፍራ ነው፤ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ትከተለኛለህ።»
«መምህር ሆይ፥ አሁን ልከተልህ የማልችለው ስለ ምንድር ነው?» ብሎ ጠየቀ ጴጥሮስ። «ነፍሴን ለመስጠትና ስለ አንተ ለመሞት ተዘጋጅቻለሁ!»
«ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን?» አለ ኢየሱስ። «ጴጥሮስ ሆይ፥ እውነት እልሃለሁ፥ ነገ ጠዋት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ከቶ እንደማታውቀኝ ሦስት ጊዜ ትናገራለህ።»
ጴጥሮስ ግን እንደ ገና አጥብቆ፥ «ከአንተ ጋር መሞት እንኳ ቢያስፈልገኝ ከቶ አልክድህም» አለ።
በዚያም የነበሩት ደቀ መዛሙርት ሁሉ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ጌታቸውን ፈጽሞ እንደማይተዉት ከጴጥሮስ ጋር ተናገሩ።