የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ

ምዕራፍ 86 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ

ቀደም ብለን እንዳየነው ማክሰኞ ለኢየሱስ ሥራ የበዛበት ቀን ነበር፤ ረቡዕ ግን ጸጥ ያለ ቀን ሳይሆን አይቀርም፤ ከአራቱ ወንጌሎች አንዱም እንኳ በዚያ ቀን ስለ ተፈጸመ ነገር አይነግረንምና። ኢየሱስ በሁለት ቀን ውስጥ መከራው እንደሚጀምር ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ የመጨረሻዋ ሙሉ ቀኑ የሆነችውን ረቡዕን ለማረፍና በሰማይ ካለው አባቱ ጋር ለመነጋገር ያስፈልገው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በረቡዕ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብዙም ሳይነጋገር ከእግዚአብሔር ጋር ብቻውን ነበረ።

ሐሙስ ማታ አይሁድ ሁሉ ታላቁን የፋሲካ በዓል ሊያከብሩ ነበር። ይህ በዓል ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ አስቀድሞ እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው ነጻ ሕዝብ የሆኑበትን ቀን የሚያስታውስ ነበር። በዚያን ጊዜ በግብፅ የነበረ እያንዳንዱ የእስራኤል ቤተሰብ አንድ በግ አርዶ ጠብሶ በላው፤ ይህም በግብፅ የበሉት የመጨረሻ ምግብ ነበር፤ ከእርሱም ጋር «ቂጣ»ን ማለትም ያለ እርሾ የተጋገረውን እንደ ደረቅ ብስኩት ያለ እንጀራ በሉ። ያን ቀን ለማስታወስ የእስራኤል ቤተሰቦች በየዓመቱ በጸደይ ወራት ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው የተጠበሰ በግ ከቂጣ ጋር ይበሉ ነበር፤ ይህንም «የፋሲካ በዓል» ብለው ይጠሩት ነበር፤ ምክንያቱም በዚያች ሌሊት በግብፅ የሞት መልአክ በግብፃውያን ቤተሰቦች ላይ ሞትን ሲያመጣ የእስራኤላውያንን ቤቶች «አልፎአቸው» ሄዶ ነበርና።

ሐሙስ ጠዋት ጴጥሮስና ዮሐንስ በቢታንያ ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ አሉት፦

«መምህር ሆይ፥ የፋሲካን ራት የምናዘጋጅልህ ወዴት ነው?»

«ወደ ከተማ ሂዱ፤» አለ ኢየሱስ፥ «ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ ተከተሉት፤ ወደሚገባበትም ቤት ገብታችሁ በዚያ የሚኖረውን ሰው ‹መምህሩ፦ ዛሬ ማታ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ መብላት አለብኝ፤ አዳራሼ ወዴት ነው? ይላል› በሉት። ይህም ሰው በደርብ ላይ ያለ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም ለእራቱ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጁ።»

ጴጥሮስና ዮሐንስ እንደ ታዘዙት ከቢታንያ ወደ ከተማ ሄዱ፤ ማድጋ የተሸከመውንም ሰው አግኝተው እስከ ቤቱ ድረስ ተከተሉት። በዚያም የቤቱን ባለቤት አግኝተው ኢየሱስ እንዳላቸው ነገሩት። ይህ ሰው የኢየሱስ ተከታይ ሳይሆን አይቀርም፤ ጌታው በቤቱ ማዕድ በመቅረቡ ደስ ብሎት ይሆናል። እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ደርቡ ወደ አንድ ታላቅ አዳራሽ አወጣቸው፤ በዚያም ማዕዶች ተዘርግተው ነበር፤ በዙሪያቸውም ለእንግዶቹ መደገፊያዎች ነበሩ።

ከዚያም ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ገበያ ሄደው አንድ በግ ገዙ። በትከሻቸውም ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት። በዚያም ታረደ፤ ደሙም በታላቁ መሠዊያ እግር ሥር ፈሰሰ። ከዚያም በጉ በምድጃ ተጠበሰ፤ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላም ወደ እራቱ አዳራሽ መጥቶ በማዕዱ ላይ ተቀመጠ። ከጎኑም ጠፍጣፋ ቂጣዎች፥ ደግሞም ከበጉ ጋር የሚበሉ ጣዕማቸው ጥቂት የሚመርር አትክልቶች ነበሩ።

ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ቀኑ ሲመሽ ኢየሱስና የቀሩት ደቀ መዛሙርቱ ቢታንያን ለቀው ወጡ። ይህ ያን ቤትና በዚያ የሚኖሩትን አፍቃሪ ሰዎች የሚሰናበትበት የመጨረሻ ጊዜ እንደ ሆነ ያወቀ ኢየሱስ ብቻ ነበር፤ ነገር ግን እንዳያስደነግጣቸው ምንም አልተናገረም። በዚያ ከሰዓት በኋላ ከተከታዮቹ መካከል የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበረ፤ እርሱም ጌታውን ለጠላቶቹ እንደ ሸጠውና ሠላሳው ብር በዚያን ጊዜም በገንዘብ ከረጢቱ ውስጥ እንዳለ ያውቅ ነበር። ኢየሱስም ይህን ያውቅ ነበር፤ ነገር ግን ለይሁዳም ሆነ ለደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር አንዲት ቃል እንኳ አልተናገረም።

ደብረ ዘይትን ዞረው ሸለቆውን ተሻገሩ፤ በአንዱም በር በኩል ወደ ከተማ ገቡ፤ ከዚያም በጽዮን ተራራ ላይ ባሉት መንገዶች መካከል አልፈው እራቱ ተዘጋጅቶ ወደሚጠብቃቸው ደርብ ወዳለው ቤት ደረሱ። በዚህም ቀደም ብሎ ብዙ ጊዜ እንደ ሆነው፥ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ማን ከኢየሱስ ጋር በእንግዳው ማዕድ ይቀመጥ በሚለው ጥያቄ ላይ ትንሽ ክርክር ተነሣ፤ ያ ማዕድ የክብር ስፍራ ነበርና። ኢየሱስም ቀደም ብሎ የነገራቸውን እንደ ገና በመናገር ክርክሩን አቆመው፦

«ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ ዝቅተኛውን ስፍራ ይያዝ፤ አለቃ ሊሆን የሚወድም አገልጋያችሁ ይሁን። ነገር ግን ስለ ስፍራ መጨነቅ አያስፈልጋችሁም። በፈተናዎቼ ሁሉ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ ቆማችኋል፤ በመንግሥቴም ለሁላችሁ ከፍ ያለ ስፍራ እሰጣችኋለሁ፤ በዐሥራ ሁለት ዙፋኖች ላይ ትቀመጣላችሁና፤ እያንዳንዳችሁም በአንዱ የእስራኤል ነገድ ላይ ትሾማላችሁ።»

ነገር ግን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የልብ ትሕትናንና ራስ ወዳድ አለመሆንን ሲያስተምራቸው በቃል ብቻ አላቆመም። ያስደነቃቸውን አንድ ሥራ በማድረግ አስተማራቸው። ልክ ከእራቱ በፊት ከተደገፈበት መደገፊያ ተነሣ፤ ልብሱንና መደረቢያውን አወለቀ፤ ከዚያም ማበሻ ጨርቅ በወገቡ ታጠቀ፤ በመታጠቢያውም ውኃ ጨመረ፤ ደቀ መዛሙርቱም ራሳቸውን ወደ ማዕዱ እግራቸውንም ከማዕዱ ወደ ውጭ አድርገው በማዕዱ ዙሪያ ተደግፈው ሳሉ እግራቸውን ማጠብ ጀመረ። ኢየሱስ በመጀመሪያ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ መጥቶ የውኃውን መታጠቢያ ይዞ በእግሩ አጠገብ ቆመ። ጴጥሮስም ቀና ብሎ አየውና መድኃኒቱ እግሩን ሊያጥብ መዘጋጀቱን ተረዳ።

«መምህር ሆይ፥ ምነው!» አለ ጴጥሮስ። «አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?»

«ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ አሁን አታስተውልም፤» አለ ኢየሱስ፥ «ከጊዜ በኋላ ግን ታውቀዋለህ።»

«ጌታዬ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም!» አለ ጴጥሮስ።

«ካላጠብሁህ፥» ብሎ መለሰ ኢየሱስ፥ «የእኔ አይደለህም።»

«እንግዲያስ መምህር ሆይ፥» አለ ጴጥሮስ፥ «እንዲህ ከሆነ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንና ራሴንም እጠበኝ!»

«አስቀድሞ የታጠበ፥» አለ ኢየሱስ፥ «ንጹሕ ነው፤ እግሩን ብቻ መታጠብ ያስፈልገዋል። እናንተም ንጹሐን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም።»

«ሁላችሁ አይደላችሁም» ባለው ቃል ከሌሎቹ ጋር በዚያ ስለ ነበረው ስለ ከሃዲው ስለ ይሁዳ ያስብ ነበር።

እንዲሁ ኢየሱስ የጴጥሮስን እግር አጥቦ በወገቡ በታጠቀው ማበሻ አደረቀው፤ በመደገፊያዎቹም ዙሪያ እየዞረ የደቀ መዛሙርቱን ሁሉ እግር አጠበ፤ የክፉውን የይሁዳን እግር እንኳ አጠበ። ከጨረሰም በኋላ ማበሻውን ፈታ፤ መደረቢያውንም ለብሶ እንደ ገና በማዕዱ ስፍራውን ያዘ።

«ያደረግሁላችሁን ትርጕም ታስተውላላችሁን?» አለ ኢየሱስ። «እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ ልክ ናችሁ፤ መምህርም ጌታም ነኝና። እንግዲህ እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ሆኜ እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተም ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። ይህን ሁሉ ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።»

ኢየሱስም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ «‹እናንተ› ስል ሁላችሁን ማለቴ አይደለም፤ አሁን ከእኔ ጋር የሚበላ ከእናንተ አንዱ ለጠላቶቼ አሳልፎ ይሰጠኛልና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል!»

ኢየሱስ ይህን ሲናገር በጥልቅ ጭንቀት ውስጥ እንዳለ ፊቱ ያሳይ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ስለ ማን እንደሚናገር ሳያውቁ እርስ በርሳቸው ተያዩ። እነርሱም በኀዘን ተሞሉ፤ በማዕዱም ዙሪያ ያሉት ሁሉ፥ «ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን?» ይሉት ጀመር።

«ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ የሚያጠልቅ፥» ብሎ መለሰ ኢየሱስ፥ «አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ ከምድር ይሄዳል፤ ነገር ግን ጌታውን አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፥ ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር!»

በማዕዱ በኢየሱስ አጠገብ ኢየሱስ እጅግ ይወደው የነበረው ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ዮሐንስ ተደግፎ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስም «ስለ ማን እንደሚናገር ጠይቀህ እወቅ» ማለት የሆነውን ምልክት ለዮሐንስ ጠቀሰው።

ስለዚህ ዮሐንስ ወደ ኋላ በኢየሱስ ትከሻ ላይ ተጠግቶ በሹክሹክታ እንዲህ አለው፦

«መምህር ሆይ፥ ማን ነው?»

«ይህን የእንጀራ ቍራሽ በወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው፥» ብሎ መለሰ ኢየሱስ፥ «እርሱ ነው።»

ኢየሱስም ቍራሹን የተጠበሰው በግ ባለበት ወጭት አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው። በዚያን ቅጽበት የክፋት መንፈስ ፈጽሞ ወደ ይሁዳ ልብ ገባ። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦

«የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ።»

ነገር ግን በማዕዱ ከተቀመጡት ይህ ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ያስተዋለ አንድም አልነበረም። ይሁዳ የማኅበሩን ከረጢት ይይዝ ስለ ነበረ፥ ኢየሱስ ለበዓሉ አንዳንድ ነገሮችን እንዲገዛ ወይም ምናልባት ለድሆች ጥቂት ገንዘብ እንዲሰጥ የነገረው መሰላቸው። ይሁዳም ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወደ ሌሊቱ ጨለማ ወጣ።


ቀዳሚ ቀጣይ