ምዕራፍ 85 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
ታላቁ የመጨረሻ ቀን
ኢየሱስ ስለ «ቈነጃጅቱ» እና ስለ «መክሊቶቹ» ሁለቱን ምሳሌዎች ከተናገረ በኋላ፥ ገና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በደብረ ዘይት ላይ ሳለ አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ሰጠ፤ ይህም የ«ታላቁ የመጨረሻ ቀን» ሥዕል ነበር። እንዲህም አለ፦
«የሰው ልጅ በንጉሥነቱ ክብር ሁሉ፥ የእግዚአብሔርም መላእክት ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆነው ዳግመኛ ወደ ምድር በሚመጣበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ በንጉሣዊ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል፤ በዓለም ያሉ ሰዎች ሁሉ ሊፈረድባቸው በፊቱ ይሰበሰባሉ። በዚያን ጊዜ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም እረኛ መንጋውን እንደሚለይ፥ በጎቹን በቀኙ ፍየሎቹንም በግራው እያቆሙ ያን ታላቅ ሕዝብ ለሁለት ይለያሉ። ከዚያም ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦»
«‹እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ኑና ውሰዱ። ተርቤ ሳለሁ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ ሳለሁ አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳ ሆኜ ሳለሁ ደጃችሁን ከፍታችሁ ወደ ቤታችሁ አስገብታችሁኛልና፤ ምንም ልብስ ባልነበረኝ ጊዜ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜ ሳለሁ ተንከባክባችሁኛልና፤ በወኅኒ ሳለሁ ልትጠይቁኝ መጥታችኋልና።›»
«በዚያን ጊዜ ደጎቹ እንዲህ ብለው ይመልሳሉ፦ ‹ተርበህ አግኝተንህ ያበላንህ መቼ ነው? ወይስ ተጠምተህ ያጠጣንህ? እንግዳ ሆነህ አይተንህ ወደ ቤታችን ያስገባንህ መቼ ነው? ወይስ ልብስ ሳይኖርህ ያለበስንህ? ታመህ ወይም ታስረህ አይተንህ ልንጠይቅህ የመጣነው መቼ ነው?›»
«ንጉሡም እንዲህ ብሎ ይመልስላቸዋል፦ ‹እላችኋለሁ፥ በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ፥ ከሁሉ ለሚያንሰው እንኳ፥ ከእነዚህ ነገሮች አንዱን ባደረጋችሁለት ቍጥር ለእኔ አደረጋችሁት።›»
«ከዚያም ንጉሡ በግራው ወዳሉት ዘወር ብሎ እንዲህ ይላቸዋል፦»
«‹እናንተ እግዚአብሔር የረገማችሁ፥ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ፥ ማለትም ለክፉ መናፍስት ወደ ተነደደው ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ለዘላለም መኖሪያችሁ በዚያ ይሆናል! ተርቤ ነበርሁ፥ እናንተ ግን ፈጽሞ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ ነበርሁ፥ እናንተ ግን ፈጽሞ አላጠጣችሁኝም፤ እንግዳ ነበርሁ፥ እናንተ ግን ደጃችሁን ፈጽሞ አልከፈታችሁልኝም፤ ልብስ አስፈልጎኝ ነበር፥ እናንተ ግን ምንም አልሰጣችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ ነበር፥ እናንተ ግን ፈጽሞ ግድ አልሰጣችሁኝም።›»
«እነርሱም እንዲህ ብለው ይመልሱለታል፦»
«‹ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይም ተጠምተህ ወይም እንግዳ ሆነህ ወይም ልብስ አጥተህ ወይም ታመህ ወይም ታስረህ አይተንህ ያልረዳንህ መቼ ነው?›»
«እርሱም እንዲህ ብሎ ይመልስላቸዋል፦ ‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምኑትን እነዚህን ወንድሞቼን፥ ከሁሉ የሚያንሱትን እንኳ፥ በችግራቸው ባልረዳችኋቸው ቍጥር እኔን አልረዳችሁኝም።› እነዚህም ለዘላለም ቅጣት ይሄዳሉ፤ መልካም ያደረጉት ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።»
አሁን ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ቀኑ መሽቶ ነበር፤ ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከደብረ ዘይት ተራራ ወደ ቢታንያ ወረደ። በመንገድም እንዲህ አላቸው፦
«ከሁለት ቀን በኋላ የፋሲካ በዓል እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። በዚያ ቀን የሰው ልጅ ለጠላቶቹ አልፎ ይሰጣል፤ በመስቀልም ላይ ይገድሉታል።»
ነገር ግን ይህን ብዙ ጊዜ ቢነግራቸውም፥ አሁንም እንኳ ሊያምኑት አልቻሉም። አብረውም ወደ ቢታንያ፥ ወደ ማርታና ወደ ማርያም ወደ አልዓዛርም ቤት ሄዱ።