ምዕራፍ 84 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
የመክሊቱ ምሳሌ
ኢየሱስ በደብረ ዘይት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ያደረገውን ረጅም ንግግር ከደመደመባቸው ከሦስቱ ምሳሌዎች ሁለተኛው «የመክሊቱ ምሳሌ» ነበር። ይህም ከአንድ ሳምንት በፊት ብቻ በኢያሪኮ ለሕዝቡ ከተነገረው ከ«ምናኑ ምሳሌ» ጋር በአንዳንድ ክፍሉ ይመሳሰል ነበር፤ በሌላ ክፍሉ ግን ይለያል። በዚያኛው ምሳሌ መንግሥትን ሊቀበል ወደ ሩቅ ከተማ የሚሄድ ንጉሥ ነበረ። በዚህኛው ምሳሌ ግን ረጅም ጕዞ የሚሄድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ። በምናኑ ምሳሌ ባሮቹ ሁሉ በእኩል ገንዘብ ጀመሩ፤ በዚህኛው ምሳሌ ግን የተለያየ መጠን ተቀበሉ፤ አንዱም ሌላው ከተቀበለው አምስት እጥፍ ተቀበለ። በምናኑ ምሳሌ አንዱ የተሰጠውን ዐሥር እጥፍ፥ ሌላውም አምስት እጥፍ አተረፈ፤ የተለያየ ዋጋም አገኙ፤ አንዱ በዐሥር ከተሞች፥ ሌላውም በአምስት ከተሞች ላይ ተሾመ። በመክሊቱ ምሳሌ ግን እያንዳንዱ ታማኝ ባሪያ የተቀበለውን እጥፍ አደረገ፤ ሁለቱም አንድ ዓይነት ዋጋ አገኙ። እንግዲህ የመክሊቱን ምሳሌ እንሰጣለን፤ ከምናኑ ምሳሌ እንዴት እንደሚለይም ታያላችሁ። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦
«የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ ወደ ሩቅ አገር ከሄደበት ጕዞ እንደ ተመለሰ ሰው ይሆናል። ይህ ሰው ጕዞውን ከመጀመሩ በፊት ባሮቹን በአንድነት ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ሰጣቸው። ለአንዱ አምስት መክሊት፥ ለሌላው ሁለት፥ ለሌላውም አንድ ሰጠ። እያንዳንዱ መክሊት ሁለት ሺህ ዶላር ያህል ዋጋ ነበረው፤ ስለዚህ የመጀመሪያው ባሪያ ዐሥር ሺህ ዶላር፥ ሁለተኛው አራት ሺህ ዶላር፥ ሦስተኛውም ሁለት ሺህ ዶላር ነበራቸው። ለእያንዳንዱም ጌታው ሊጠብቀው ይችላል ብሎ ያሰበውን ያህል ተሰጠው። ጌታቸው ወደ ቤቱ እስኪመለስ ድረስ ገንዘቡን ሥራ ላይ አውለው እንዲያተርፉበት፥ በዚያን ጊዜም ከትርፉ ጋር እንዲያመጡለት ነበር። ሰውዬውም ገንዘቡን ካካፈለ በኋላ ሄደ።»
«አምስቱን መክሊት ወይም ዐሥሩን ሺህ ዶላር የተቀበለው ባሪያ ወዲያው ሄዶ በገንዘቡ ነገደ፤ በእርሱም ሌላ ዐሥር ሺህ ዶላር አተረፈ፤ በጠቅላላም ሃያ ሺህ ዶላር ሆነ። ሁለት መክሊት ወይም አራት ሺህ ዶላር የነበረው ሁለተኛው ባሪያም ገንዘቡን በጥንቃቄ ሥራ ላይ አውሎ እጥፍ አደረገው፤ ስምንት ሺህ ዶላርም አደረሰው። አንድ መክሊት ወይም ሁለት ሺህ ዶላር የተሰጠው ሦስተኛው ባሪያ ግን የጌታውን ገንዘብ ሥራ ላይ ከማዋል ይልቅ ሄዶ በምድር ጕድጓድ ቈፈረ፤ መክሊቱንም በጕድጓዱ ውስጥ አኑሮ በዚያ ተወው።»
«ከብዙ ጊዜም በኋላ የባሮቹ ጌታ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ እያንዳንዱም ምን እንዳተረፈ ለማየት ባሮቹን ጠራ። አምስቱን መክሊት የተቀበለው በክንዱ የወርቅ ከረጢቶችን ይዞ መጣ። እንዲህም አለ፦»
«‹ጌታዬ ሆይ፥ ዐሥር ሺህ ዶላር ሰጥተኸኝ ነበር። እነሆ፥ እርሱና በገንዘብህ ያተረፍሁት ሌላ ዐሥር ሺህ ዶላር።›»
«ጌታውም ‹መልካም አደረግህ፥ አንተ በጎ ባሪያ!› አለው። ‹በጥቂቱ መልካም አድርገሃል፤ አሁን ታላቅ ነገር እሰጥሃለሁ፤ ግባ፥ የጌታህን ግብዣ ተካፈል!›»
«ከዚያም ሁለት መክሊት የተሰጠው ሁለተኛው ባሪያ መጣ።»
«‹ጌታዬ ሆይ፥› አለ፥ ‹አራት ሺህ ዶላር በአደራ ሰጥተኸኝ ነበር። እነሆ፥ ለአንተ ካተረፍሁት ከሌላው አራት ሺህ ዶላር ጋር!›»
«ጌታውም ‹መልካም አደረግህ፥ አንተ በጎ ባሪያ› አለው። ‹አንተም በጥቂቱ መልካም አድርገሃል፤ አሁን ታላቅ ነገር እሰጥሃለሁ፤ ግባ፥ ከእኔ ጋር ግብዣውን ተካፈል!›»
«ከዚያም አንድ መክሊት፥ ሁለት ሺህ ዶላር የተሰጠው ባሪያ መጣ። በእጁም የተቀበለው ያው የወርቅ ከረጢት ነበረ፤ ከዚያም የበለጠ አልነበረም።»
«‹ጌታ ሆይ፥› አለ፥ ‹ካልዘራህበት የምታጭድ፥ ያልሰበሰብኸውንም እህል የምትወስድ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቅ ነበር። ስለዚህ ፈራሁ፥ ገንዘብህንም በምድር ውስጥ ሸሸግሁት። እነሆ፥ የአንተ የሆነው ይኸውልህ።›»
«ጌታውም ‹አንተ ሃኬተኛና የማትረባ ባሪያ!› አለው። ‹ካልዘራሁበት እንደማጭድ፥ ያልሰበሰብሁትንም እህል እንደምወስድ ታውቅ ነበርን? እንደዚህ ያለ ሰው መሆኔን ካወቅህ ገንዘቤን በባንክ ታስቀምጠው ዘንድ በተገባህ ነበር፤ ቢያንስ የራሴን ገንዘብ ከጥቂት ትርፍ ጋር ባገኘሁ ነበር።›»
«ጌታውም ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ ‹ስለዚህ መክሊቱን ከዚህ ሰው ውሰዱና ዐሥሩን መክሊት፥ ሃያውን ሺህ ዶላር ላመጣልኝ ስጡት፤ ይህ ሊጠብቀው የሚገባው መሆኑን ያሳያልና። ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፤ ይበዛለትማል። ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።›»
«‹ያንንም የማይረባ ባሪያ ከግብዣው ደጅ አውጡት፤ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ ወደ ግብዣው መግባት የማይችሉት በዚያ ያለቅሳሉ፥ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ።›»
ከዚህ ምሳሌና ከምናኑ ምሳሌ ጌታ «ላለው ሁሉ» ሲል «ያለውን ለሚንከባከብና ሥራ ላይ ለሚያውለው ሁሉ» ማለቱ፥ «ከሌለው» ሲልም «ያለውን ሥራ ላይ የማያውለው» ማለቱ ግልጥ ነው። ያለውን—ገንዘብም ቢሆን፥ ዕውቀትም ቢሆን፥ የአእምሮ ችሎታም ቢሆን፥ መልካም የማድረግ ዕድልም ቢሆን—በትክክል የሚጠቀምበት ሁሉ ከዚያው ይበልጥ እየበዛለት ያገኛል፤ ያለውን ቸል የሚል ሁሉ ግን በእርግጥ ያጣዋል።