የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የዐሥሩ ቆነጃጅት ምሳሌ

ምዕራፍ 83 · 1 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

የዐሥሩ ቆነጃጅት ምሳሌ

ኢየሱስ በደብረ ዘይት ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያደረገውን ረጅም ንግግር ሲጨርስ ሦስት ምሳሌዎችን ሰጠ። የመጀመሪያው ምሳሌ ተከታዮቹ ድንገት ለሚሆነው መምጣቱ ነቅተውና ተዘጋጅተው መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያሳይ ነበር። ይህም «የዐሥሩ ቆነጃጅት ምሳሌ» ነው።

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ «ጌታ በመንግሥቱ የሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ በሰርግ ላይ ሚዜዎች የሆኑ ዐሥር ቆነጃጅት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ከወዳጆቹ ጋር ሊቀበሉና ከእነርሱም ጋር ወደ ሙሽራይቱ ቤት ሊሄዱ ወጡ። ከእነዚህም ቆነጃጅት አምስቱ ሰነፎችና ግድ የለሾች ነበሩ፤ አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ ቆነጃጅት መብራታቸውን ይዘው መጡ፤ ነገር ግን መብራታቸውን እንደ ገና ለመሙላት ተጨማሪ ዘይት እንደሚያስፈልጋቸው ፈጽሞ አላሰቡም። ከአምስቱ ልባሞች ቆነጃጅት እያንዳንዲቱ ግን ባስፈለጋት ጊዜ መብራቷን እንደ ገና የምትሞላበት ትንሽ የዘይት ማሰሮ ይዛ ነበር።»

«ሙሽራው፥ ማለት የሚያገባው ጐበዝ፥ በዘገየ ጊዜ ዐሥሩ ቆነጃጅት እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸው፤ በመጨረሻም ሁሉም ተኙ። እስከ እኩለ ሌሊትም ተኙ፤ በዚያን ጊዜ ድንገት ‹እነሆ ሙሽራው ይመጣል! ልትቀበሉት ውጡ!› የሚል ጩኸት ቀሰቀሳቸው።»

«በዚያን ጊዜ ቆነጃጅቱ ሁሉ ተነሥተው መብራታቸውን ያዘጋጁ ጀመር። ግድ የለሾቹና ሰነፎቹ ልባሞቹንና አስተዋዮቹን እንዲህ አሉአቸው፦»

«‹እባካችሁ ከዘይታችሁ ስጡን፤ መብራታችን ሊጠፋብን ነው።›»

«ልባሞቹ ቆነጃጅት ግን መልሰው እንዲህ አሉአቸው፦ ‹አይሆንም፤ እያንዳንዳችን ለራሳችን መብራት የሚበቃ ዘይት ብቻ ነው ያመጣነው። ዘይታችንን ከእናንተ ጋር ብንካፈል ከእኛ አንዲቱም መብራቷን የምታበራበት በቂ ዘይት አይኖራትም፤ ሁላችንም በአንድነት በጨለማ እንሆናለን። ወደ ገበያ ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ!›»

«ስለዚህ ሙሽራው በሚመጣበት ጊዜ፥ በሌሊቱ እኩሌታ፥ እነዚያ ሰነፎች ሴቶች ወደ ከተማ ሄደው ዘይት ሻጮችን ቀስቅሰው ተጨማሪ ዘይት መግዛት ግድ ሆነባቸው። ዘይት ሊገዙ በመንገድ ሳሉም ሙሽራውና አጃቢዎቹ መጡ፤ ተዘጋጅተው የነበሩትም ቆነጃጅት ከእነርሱ ጋር ወደ ሰርጉ ግብዣ ገቡ። ሁሉም ወደ ክፍሉ ከገቡ በኋላ መግባት መብት የሌላቸው እንግዶች እንዳይገቡ ደጁ ተዘጋ።»

«ከጥቂት ጊዜም በኋላ የቀሩቱ ቆነጃጅት መጥተው ደጁ ተዘግቶ አገኙት። ሙሽራውንም እንዲህ ብለው ጠሩት፦»

«‹ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ! እባክህ ደጁን ክፈትልን!›»

«እርሱ ግን መልሶ ‹እላችኋለሁ፥ ማን እንደ ሆናችሁ አላውቅም!› አላቸው።»

ኢየሱስም «ስለዚህ» አለ፥ «እላችኋለሁ፥ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀኒቱንም ሆነ ሰዓቲቱን አታውቁምና ንቁ፤ ሁልጊዜም ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።»


ቀዳሚ ቀጣይ