ምዕራፍ 82 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
ኢየሱስ ስለሚመጡት የጨለማ ቀናት ሲናገር
ኢየሱስ የቤተ መቅደሱ ታላቁ የውጭ አደባባይ የሆነውን የአሕዛብን ወይም የእንግዶችን አደባባይ አቋርጦ ወደ ደብረ ዘይት አመራ። በዚያ በኩል ባለው አደባባይ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበረ፤ ይህም በሁለት ረድፍ የቆሙ ዓምዶች ሲሆን ከፀሐይ እንዲከልል በላዩ ጣራ ነበረው። ከዚህ መመላለሻ ሥር በእብነ በረድ ደረጃ ወርደው «የወርቁ በር» በሚባለው ደጅ በኩል ከቤተ መቅደሱ ግቢ ወጡ። ወደዚህ በር በቀረቡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ በግንቡ ውስጥ ያሉትን ታላላቅ ድንጋዮች፥ ዓምዶቹንና በዙሪያው ያሉትን ያማሩ ሕንጻዎች እንዲመለከት አሳዩት።
ኢየሱስም «እነዚህን ድንጋዮችና ሕንጻዎች ትመለከታላችሁን?» አለ። «እነሆ እላችኋለሁ፥ እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ የሚፈራርሱበት ጊዜ ይመጣል፤ ሩቅም አይደለም፤ ከእነዚህ ያማሩ ሕንጻዎችም በስፍራው ቆሞ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ አይኖርም፤ ሁሉ ይፈርሳል!»
ደቀ መዛሙርቱ ይህን ቃል በድንጋጤና በኀዘን ሰሙ። ጌታቸው እንደ ነቢይ እንደሚናገርና የተናገረው ሁሉ በእርግጥ እንደሚፈጸም ያውቁ ነበር። ነገር ግን ኢየሩሳሌምን እንደ ቅድስት ከተማ፥ ቤተ መቅደሱንም እንደ እግዚአብሔር ቤት ይመለከቱ ነበር። ለእነርሱ የከተማዪቱና የቤተ መቅደሱ መውደቅ እንደ ዓለም ሁሉ ፍጻሜ መሰላቸው። ዝም ብለው ኢየሱስን ተከትለው የቄድሮንን ወንዝ ሸለቆ ተሻገሩ፤ የደብረ ዘይትንም ገደላማ ዳገት ወጡ። በራሱም ላይ ሊያርፉ ተቀመጡ፤ ከሸለቆውም ማዶ ማማዎቿና ጣራዎቿ ፊት ለፊታቸው ከፍ ብለው የሚታዩትን ከተማ ተመለከቱ። በተራራው ላይ ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስና እንድርያስ ከወንድማማቾቹ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ አሉት፦
«መምህር ሆይ፥ የቃልህ ትርጉም ምን እንደ ሆነ፥ እነዚህም አስፈሪ ነገሮች መቼ እንደሚፈጸሙ ንገረን። ትሄድና ደግሞ ትመለሳለህን? አንተን መቼ እንደምንጠብቅ በምን እናውቃለን?»
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ከበውት በተራራው ላይ ተቀምጦ ሳለ ስለሚመጡት ነገሮች ረጅም ትምህርት ሰጣቸው። በመጀመሪያም ክርስቶስ፥ የእስራኤል ንጉሥ ነን የሚሉ ሰዎችን እንዳይከተሉ አስጠነቀቃቸው።
«ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ» አለ። «ብዙዎች ‹እኔ ክርስቶስ፥ የእስራኤል ንጉሥ ነኝ› እያሉ ይመጣሉና፤ ብዙ ሰዎችንም ያስታሉ። ነገር ግን ከእነዚህ ሐሰተኞች ክርስቶሶች አንዱንም አትከተሉ።»
«የተነሡትን ጦርነቶች ወሬና የሚመጡትንም ጦርነቶች ወሬ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አትደንግጡ። እነዚህ ሊሆኑ ግድ ነው፤ ዳሩ ግን መጨረሻው አይደሉም። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይዋጋል፤ በብዙ ስፍራም የምድር መናወጥ ትሰማላችሁ፤ የተራቡም የሚበሉት እንጀራ የማያገኙበት ጊዜ ይመጣል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የመከራው መጀመሪያ ብቻ ናቸው፤ የባሰው ገና ይመጣል።»
«እነዚህ ከመሆናቸው በፊት ግን ደቀ መዛሙርቴ ስለ ሆናችሁ የምትቀበሏቸው ሌሎች መከራዎች አሉ። ጠላቶች በእናንተ ላይ ይነሣሉ። ልትዳኙ በሸንጎዎችና በፍርድ ቤቶች ፊት ትቀርባላችሁ፤ ትያዛላችሁ፥ በአይሁድም ምኵራቦች ትገረፋላችሁ፤ ተከታዮቼ በመሆናችሁ ስለ ራሳችሁ መልስ ልትሰጡ በአገረ ገዦችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። ይዘው ለፍርድ ባቀረቧችሁ ጊዜ ግን ምን እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ በዚያች የፍርድ ሰዓት ተገቢው ቃል ይሰጣችኋልና። የሚናገረው በእናንተ በኩል የሚናገር የእግዚአብሔር መንፈስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁም።»
«በዚያ የመከራ ዘመን አባቶችና እናቶች በልጆቻቸው ላይ ይነሣሉ፤ ወንድሞችም በእኔ የሚያምኑትን ወንድሞቻቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ። ከእናንተም አንዳንዶቹ በዚያ ዘመን ይገደላሉ። ደቀ መዛሙርቴም ስለ ሆናችሁ ሰው ሁሉ ይጠላችኋል። ነገር ግን እስከ መጨረሻው፥ እስከ ሞትም ድረስ ታማኞች ብትሆኑ ለዘላለም ሕይወት ትድናላችሁ።»
ከዚያም ኢየሱስ በኢየሩሳሌምና በአይሁድ ምድር ላይ ስለሚመጣው አስፈሪ ዘመን ተናገረ። እንዲህም አለ፦
«ታላላቅ ሠራዊት በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉት በእነዚህ ኮረብቶች ላይ ሰፍረው ስታዩ፥ ከተማዪቱና ቤተ መቅደሱ የሚጠፉበት ጊዜ እንደ ደረሰ እወቁ። ይህም በይሁዳ ላለ ሰው ሁሉ ወደ ተራሮች ሸሽቶ እንዲሸሸግ ምልክት ይሁን። በዚያን ጊዜ በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ሰው ከቤቱ አንዳች ሊወስድ አይውረድ፤ በእርሻም ያለ ሰው መደረቢያውን ሊወስድ ወደ ቤቱ አይመለስ፤ ነገር ግን እንዳለ፥ በላዩ ባለው ልብስ ብቻ ፈጥኖ ይሽሽ፤ የሚሸሸግበትንም ደኅና ስፍራ ይፈልግ።»
«በዚያን ጊዜ ማንም ‹ክርስቶስ እነሆ በዚህ አለ!› ወይም ‹እነሆ በዚያ አለ!› ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ የእግዚአብሔርን የራሱን ሕዝብ እንኳ አንዳንዶቹን እስኪያስቱ ድረስ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እውነት እላችኋለሁ፥ አሁን በሕይወት ካሉት ብዙዎቹ ይህ ሁሉ ሲፈጸም ያያሉ።»
ኢየሱስ በቅርቡ ትቷቸው እንደሚሄድ፥ በራሱ ጊዜ ግን እንደ ገና እንደሚመጣ ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ ነግሯቸው ነበር። አሁንም ስለ «ዳግመኛ መምጣቱ» ተናገረ።
«ስለ ሰው ልጅ መምጣት ግን ያችን ቀንና ያችን ሰዓት የሚያውቅ የለም፤ መቼ እንደሚሆን ሰውም፥ መላእክትም፥ ልጁ ራሱ እንኳ አያውቅም፤ የሚያውቅ አብ ብቻ ነው። በዚያን ጊዜ በኖኅ ዘመን እንደ ነበረው ይሆናል፤ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ይበሉና ይጠጡ፥ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን ጠራርጎ እስኪወስዳቸው ድረስ ልብ አላሉም።»
«የሰው ልጅ ሲመጣም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ አብረው ይሠራሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፥ አንዱም ይቀራል። ሁለት ሴቶች በእጅ ወፍጮ እህል ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች፥ አንዲቱም ትቀራለች። ጌታ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና እንግዲህ ዘወትር ንቁ። ይህን እወቁ፤ የቤቱ ባለቤት ሌባው ከሌሊቱ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ይጠብቀው ነበር፤ ቤቱም እንዲቈፈር ፈጽሞ አይተውም ነበር። ስለዚህ ሁልጊዜ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና።»