ምዕራፍ 81 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ከሁሉ የሚበልጠው ስጦታ፤ ከሩቅ አገር የመጡት እንግዶች
ኢየሱስ የሕዝብ ትምህርቱ የመጨረሻ ቀን በሆነው በዚያ ማክሰኞ የተናገረበት በቤተ መቅደስ ያለው ክፍል «መዝገብ ቤት» ይባል ነበር፤ በግድግዳዎቹ አጠገብ ለአምልኮ የሚመጡ ሰዎች ለድሆች መሥዋዕት መክፈያ እንዲሆን ስጦታቸውን የሚጥሉባቸው ሣጥኖች ነበሩና። ኢየሱስ ከክፍሉ ሊወጣ ሲነሣ ሰዎች ገንዘባቸውን ወደ እነዚህ ሣጥኖች ሲጥሉ ተመለከተ። አንዳንድ ባለ ጠጎች ብዙ ገንዘብ እንደሚሰጡ ለማሳየት ገንዘቡን አንድ በአንድ ቀስ ብለው ወደ ሣጥኑ እየጣሉ እንዲንኳኳ ያደርጉ ነበር።
አንዲት ድሀ ሴት መጣች፤ ልብስዋም መበለት መሆንዋን ያሳይ ነበር፤ እርስዋም ሁለቱ ተደምረው የአንድ ሳንቲም ሩብ ብቻ የሚያወጡ ሁለት ትናንሽ የናስ ሳንቲሞች በሣጥኑ ውስጥ ጣለች። ኢየሱስም አያት፤ ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦
«እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር ፊት ይህች ድሀ መበለት ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ አብልጣ በሣጥኑ ውስጥ ጣለች። ሌሎቹ ሁሉ የጣሉት ከትርፋቸው ያልፈለጉትን ገንዘብ ነው። እርስዋ ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ፥ ትዳርዋን ሁሉ ሰጠች!»
ከዚያም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከመዝገብ ቤቱ በምሥራቅ በኩል ባለው ደጅ ወጣ፤ ያም ደጅ እጅግ ያጌጠ ስለ ነበረ «ውብ» የተባለው ደጅ ተብሎ ይጠራ ነበር። ወደ አሕዛብ አደባባይ ወረዱ፤ በደረጃዎቹም ግርጌ መልካቸውና አለባበሳቸው አይሁድ ሳይሆኑ የውጭ አገር ሰዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ጥቂት ሰዎች አገኙ። እነዚህ ሰዎች ከሩቅ አገር የመጡ ግሪኮች ነበሩ። አይሁድ ባለ መሆናቸው ወደ ቤተ መቅደሱ የውስጥ አደባባዮች መግባት ተከልክለው ስለ ነበር በደረጃዎቹ ግርጌ ኢየሱስን ይጠብቁ ነበር።
እነዚህ ግሪኮች ከገሊላ ሰሜን ከቤተ ሳይዳ ወደ መጣውና ቋንቋቸውን መናገር ወደሚችለው ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ቀረቡ።
«ጌታ ሆይ፥» አሉት ፊልጶስን፥ «ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን።»
ፊልጶስ መምህሩ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ይሆን እንደ ሆነ እርግጠኛ አልነበረም፤ አይሁድ አሕዛብን ወይም የውጭ አገር ሰዎችን ያርቁ ነበርና፤ ከእነርሱ ጋር ፈጽሞ አይበሉም፥ ሊያነጋግሯቸውም አይወዱም ነበር። ፊልጶስ የጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እነዚህን ሰዎች ወደ ኢየሱስ ማምጣት ይገባ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ያውቅ ይሆናል ብሎ አሰበ፤ ስለዚህ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስም ግሪኮቹን ይዞ ወደ ኢየሱስ በመምጣት ቀዳሚ ሆነ።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ «የሰው ልጅ ከፍ ከፍ የሚልበትና የሚሞትበት ሰዓት አሁን ደርሶአል። ፍሬ ማፍራት የምችለው በመሞት ብቻ ነውና። የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ በወደቀች ጊዜ የውጭው ቅርፊትዋ ካልሞተ ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ዘር ሆና ብዙ የስንዴ ቅንጣቶችን መከር ታስገኛለች። ነፍሱን የሚወድና የሚጠብቃት ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ለነፍሱ የማይሳሳ ግን ለዘላለም ያገኛታል። የሚያገለግለኝ ሊሆን የወደደ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም በምሄድበት አገልጋዬ ከእኔ ጋር በዚያ ይሆናል። ማንም አገልጋዬ ቢሆን አባቴ ያከብረዋል።»
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከሦስት ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሞቶ በመስቀል ላይ እንደሚንጠለጠል ትዝ አለው። ይህ ሐሳብ ለቅጽበት አሳዘነው። ኢየሱስም አለ፦ «ነፍሴ እጅግ ታውካለች፥ በልቤም ኀዘን አለ፤ ምንስ እላለሁ? ‹አባት ሆይ፥ በቶሎ ከሚመጣው ከዚህ ሰዓት አድነኝ› ልበልን? አይደለም፤ ይህን አልልም፤ እስከ አሁን የኖርሁት በመስቀል ላይ ለሚሆነው ለዚያ የሞት ሰዓት ነውና። ‹አባት ሆይ፥ የራስህን ስም አክብር!› እላለሁ።»
በዚያን ጊዜ «አከበርሁት፥ ደግሞም አከብረዋለሁ» የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።
በዙሪያው ቆመው የነበሩት ሕዝብ «ይህ አሁን የነጐድጓድ ድምፅ ነው» አሉ።
ሌሎችም «አይደለም፤ መልአክ ይህን ሰው ተናገረው!» አሉ።
ኢየሱስም «ይህ ድምፅ የመጣው ስለ እናንተ ነው እንጂ ስለ እኔ አይደለም፤» አለ፤ «እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ላይ የሚፈርድበት ሰዓት በቶሎ ይመጣል፤ ይህን ዓለም የሚገዛው የክፋት አለቃም ወደ ውጭ ይጣላል።»
ከዚያም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለሚሆነው ሞቱ አሰበ፤ ሞቱ ለዓለም ምን እንደሚያመጣ፥ ከሞቱም በኋላ በየስፍራው አይሁድ ብቻ ሳይሆኑ ግሪኮችና የአገሩ ሁሉ ሰዎች እንደ ጌታቸውና መድኃኒታቸው በእርሱ እንደሚያምኑ አሰበ፤ እንዲህም አለ፦
«እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።»
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቈይ ኢየሱስ ዳግመኛ እግሩን ወደዚያ ላይረግጥ ከቤተ መቅደስ ወጣ።