ምዕራፍ 80 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ከትእዛዛት ሁሉ የምትበልጠው ትእዛዝ
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ እየተናገረና እነዚህን ጥያቄዎች ሁሉ እየመለሰ ሳለ አንድ የሕግ መምህር በአጠገቡ ቆሞ ያዳምጥ ነበር። ኢየሱስ የቀረቡለትን ጥያቄዎች ሁሉ እንዴት መልካም አድርጎ እንደ መለሰ አየ፤ ወደ እርሱም ቀርቦ እንዲህ አለው፦
«መምህር ሆይ፥ ከትእዛዛት ሁሉ ፊተኛይቱ የትኛይቱ ናት?»
ስለ ዐሥርቱ ትእዛዛት እየተናገረ ከእነርሱ የትኛዋ እጅግ እንደምትበልጥ የሚጠይቅ ይመስለን ይሆናል። ዓላማው ግን ይህ አልነበረም። ያሰበው በእግዚአብሔር ስለ ተሰጡት ትእዛዛት ሳይሆን ጻፎች ስላወጧቸው ሕጎች ነበር። አንዱ መምህር ሰንበትን ስለ መጠበቅ የወጡት ሕጎች ከሁሉ ይበልጣሉ ይል ነበር፤ ሌላው ስለ መታጠብ የወጡት ሕጎች ፊተኞች ናቸው ይል ነበር፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ጻፊ ወይም መምህር አንዱን የሕግ ዓይነት ከሌላው አብልጦ ያጸና ነበር። ኢየሱስ ግን ሰዎች ያወጧቸውን እነዚህን ጥቃቅን ሕጎች ሁሉ እንደ ከንቱ ይቈጥራቸው ነበር፤ ጥያቄውን ላቀረበለት ጻፊም የሰጠው መልስ ይህ ነበር፦
«ከትእዛዛት ሁሉ ፊተኛይቱና ታላቂቱ ይህች ናት፤ ‹እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ።› ሁለተኛይቱም ትእዛዝ ይህች ናት፤ ‹ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።› ከእነዚህ ከሁለቱ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።»
እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ መውደድ ማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ግድ ስለ ሆነብን ሳይሆን ማድረግ ስለምንወድና በማድረጉም ደስ ስለሚለን ማድረግ ነው። ባልንጀራችንን መውደድ ማለትም ለወገኖቻችን ማሰብና እነርሱ እንዲያደርጉልን የምንወደውን ሁሉ ለእነርሱ ማድረግ ነው።
ጻፊውም ለኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፦ «መምህር ሆይ፥ መልካም ተናገርህ! አንተ እንዳልህ አንድ አምላክ መኖሩ እውነት ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም። እግዚአብሔርንም በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ኃይልም መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ—ይህ በመሠዊያ ላይ ከሚቀርበው መሥዋዕት ሁሉ እጅግ ይበልጣል!»
ኢየሱስም የዚህ ሰው ቃል እውነተኛና መልካም እንደ ሆነ፥ ለእግዚአብሔርና ለወገኖቻችን ስላለብን ግዴታ ትክክለኛ ሐሳብ እንዳለው አየ። እንዲህም አለው፦
«አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም።»
ይህ ለኢየሱስ የቀረበለት የመጨረሻው ጥያቄ ነበር። ድንቅ መልሱን ስለ ፈሩ ከዚያ በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። የካህናት አለቆችና ሹማምንቱ ከቀድሞው ይበልጥ ተቈጡበት፤ ተራው ሕዝብ ግን በፈቃዱ ያዳምጠው ነበር።
ኢየሱስ በማስተማር ላይ ሳለ እርሱ በበኩሉ ፈሪሳውያንንና የሕግ መምህራንን አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው።
«እስቲ ንገሩኝ፤» አለ፥ «ይመጣል ተብሎ ተስፋ ስለ ተሰጠው ስለ እስራኤል ንጉሥ ስለ መሲሕ-ክርስቶስ ምን ታስባላችሁ? የማን ልጅ ነው?»
እነርሱም ወዲያው «የዳዊት ልጅ ነው» ብለው መለሱ።
ኢየሱስም ደግሞ «ታዲያ ዳዊት በአንዱ መዝሙር ‹ጌታ› ብሎ የሚጠራው እንዴት ነው?» ሲል ጠየቀ።
«ጌታ ጌታዬን እንዲህ አለው፦ ‹በቀኜ ተቀመጥ፥
ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ።›»
«ዳዊት ይህን የሚመጣውን ክርስቶስ ‹ጌታዬ› ብሎ ከጠራው፥ እንዴት የዳዊት ልጅ ይሆናል?»
ይህን ሊመልሱ አልቻሉም፤ ከዚያም ወዲያ ኢየሱስን ምንም ሊጠይቁት አልደፈሩም። እኛ ግን ክርስቶስ በሰውነቱ ከዳዊት ዘር እንደ ተወለደ፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኑ ግን የዳዊት ጌታ እንደ ሆነ ከአዲስ ኪዳን ቃል እናውቃለን።
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ካህናቱን፥ ጻፎቹንና አለቆቹን ስለ ሕይወታቸው ክፋት፥ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ማሳታቸው፥ እርሱንም ለመግደል ስላሰቡት ግፈኛና ጨካኝ ዓላማ አጥብቆ ገሠጻቸው። ስለ እነርሱና ስለ ሕዝባቸው ኃጢአት ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ፥ የኢየሩሳሌም ከተማ እንደምትጠፋ፥ አገሪቱም ባድማ እንደምትሆን ነገራቸው። እነዚህ የመጨረሻ ቃሎቹ ነበሩ፤ ተናግሮም ከጨረሰ በኋላ ከቤተ መቅደስ ሊወጣ ተነሣ።