ምዕራፍ 79 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ሰባት ባሎች ያገባችው ሴት
በዚህ ታሪክ ውስጥ ስለ ፈሪሳውያን ብዙ ሰምተናል፤ እነርሱም ዘወትር ወደ ጸሎት ቤት ስለሚሄዱ፥ የጸሎት ቤቱን ግብር ስለሚከፍሉና አንዳንዶቹ ሕጎች ምንም ያህል የሞኝነት ቢመስሉ ሕጎቹን ሁሉ ስለሚጠብቁ በሃይማኖት ረገድ የሕዝቡ መሪዎች ተደርገው ይታዩ ነበር። እነዚህ ፈሪሳውያን፥ እንደምታውቁት፥ የኢየሱስ መራራ ጠላቶች ነበሩ፤ በየስፍራውም ሕዝቡን በእርሱ ላይ ያነሣሡ ነበር።
ነገር ግን በአይሁድ መካከል እስከ አሁን ያልጠቀስነው ሌላ ወገን ነበረ፤ እነርሱም ሰዱቃውያን ናቸው። እነዚህ ሰዎች ፈሪሳውያንንም ኢየሱስንም እኩል ይቃወሙ ነበር። ለጸሎት ቤቱ ሕጎች ብዙም ግድ የማይሰጣቸው፥ ምቾትን የሚወዱ ሰዎች ነበሩ፤ እንዲያውም፥ እንደምታውቁት «ምኵራብ» ተብሎ ወደሚጠራው የጸሎት ቤት አዘውትረው አይሄዱም ነበር። በልዩ ልዩ ከተሞች ለሚገኙት የጸሎት ቤቶች ብዙም ግድ ባይኖራቸውም፥ በኢየሩሳሌም ላለው ቤተ መቅደስ ግን እጅግ ያስቡ ነበር፤ በቤተ መቅደሱ ከነበሩት ካህናት አብዛኞቹ፥ በአይሁድ ታላቁ ሸንጎ ከነበሩት አለቆችም ብዙዎቹ ሰዱቃውያን ነበሩና።
ሰዱቃውያን በሰው ውስጥ ነፍስ እንዳለች፥ ከዚህ ሕይወት በኋላ ሌላ ሕይወት እንዳለ፥ መላእክት እንዳሉ፥ ወደ ፊት ሙታን እንደሚነሡ፥ መንግሥተ ሰማያትም ሆነ ሲኦል እንዳለ አያምኑም ነበር። ሰው ሞቶ ሲቀበር ያ ለዘላለም ፍጻሜው እንደ ሆነ ያምኑ ነበር።
ከእነዚህ ሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ኢየሱስን በጥያቄ ሊያደናግሩት ሞከሩ። በዚያ ማክሰኞ ቀን ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ በቤተ መቅደስ ወደ እርሱ መጡ።
«መምህር ሆይ፥» አሉት፥ «በሙሴ ሕግ አንድ ሰው ልጆች ሳይኖሩት ሚስቱን ትቶ ቢሞት፥ ወንድሙ መበለቲቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲያቆም እንደ ታዘዘ ታስታውሳለህ። እንግዲህ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። ታላቁ ሚስት አገባ፤ ከጊዜም በኋላ ልጅ ሳይተው ሞተ። ሁለተኛውም አገባት፤ እርሱም ደግሞ ልጅ ሳይኖረው ሞተ። ሦስተኛውም ወሰዳትና ሞተ፥ አራተኛውም እንዲሁ፤ ከሰባቱም የቀሩት ሁሉ ልጅ ሳይተዉ ሞቱ። በመጨረሻም ሴቲቱ ራስዋ ሞተች። አንተ ሙታን ወደ ሕይወት የሚነሡበት ቀን እንደሚመጣ ስታስተምር ቆይተሃል። ያ ቀን ሲደርስ፥ ይህችን ሴት ያገቡ እነዚህ ሰባት ሰዎች በሚነሡበት ጊዜ፥ ሁሉም ተራ በተራ አግብተዋታልና ከሁሉም ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?»
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ «የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ስለማታስተውሉ፥ ሙታንንም በአንድ ቃል ወደ ሕይወት ሊጠራ የሚችለው የእግዚአብሔር ኃይል ምን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ ስለማታውቁ ትስታላችሁ። በዚህ ዓለም ወንዶችና ሴቶች የሚጋቡት በምድር ላይ የሚኖሩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ስለ ሆነና ከእነርሱ በኋላ የሚኖሩ ቤተሰቦች ሊኖሯቸው ስለሚገባ ነው። ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ግን እንደ ባልና ሚስት አይነሡም፤ በሚመጣውም ዓለም አያገቡም፤ በእነርሱ ስፍራ የሚተኩ ቤተሰቦችን ማፍራት አያስፈልጋቸውምና። በዚያች አገር ሁሉ እንደ እግዚአብሔር መላእክት ለዘላለም ይኖራሉ። ስለ ትንሣኤ ሙታን ደግሞ፥ ማለትም ከሙታን ስለ መነሣት፥ እግዚአብሔር በሚነደው ቍጥቋጦ ዘንድ ለሙሴ የተናገረውን ቃል አላነበባችሁምን?»
«‹እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ።›»
«እንግዲህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። ሰዎች ሁሉ በምድር ላይ ከሞቱ በኋላ እንኳ በእግዚአብሔር ፊት ሕያዋን ናቸውና።»
ኢየሱስ እነዚህን ጥያቄዎች ሲመልስ—ማለትም በቤተ መቅደስ ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን ለማስወጣት ስለ ነበረው መብት የቤተ መቅደሱ አለቆች ያቀረቡትን፥ ግብር ስለ መክፈል ፈሪሳውያን ያቀረቡትን፥ ስለ ትንሣኤ ሙታን ማለትም ከሙታን ስለ መነሣት ሰዱቃውያን ያቀረቡትን ጥያቄ ሲመልስ—ሕዝቡ በዙሪያው ቆመው ያዳምጡ ነበር። አለቆቹ የኢየሱስ ጠላቶች ቢሆኑም ተራው ሕዝብ ግን ይወደው ነበር፤ በደስታም ይሰሙት ነበር። መልሱ ምን ያህል ፈጣንና ተገቢ እንደ ሆነ አዩ፤ የኢየሱስም ጠላቶች በፊቱ ሲዋረዱ በማየታቸው እጅግ ደስ አላቸው።