የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የወይን ጠጅ ፈጽሞ ያልቀመሰው ልጅ

ምዕራፍ 7 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

የወይን ጠጅ ፈጽሞ ያልቀመሰው ልጅ

ማርያም ከጎበኘቻቸው ብዙም ሳይቆይ ለዘካርያስና ለኤልሳቤጥ ተስፋ የተሰጠው ልጅ ተወለደ። በአይሁድ ቤተሰቦች ዘንድ ልጅ ወደ ቤት መምጣቱ ሁልጊዜ የታላቅ ደስታ ምክንያት ነበር፤ የዚህ ሕፃን መወለድ ግን ደስታውን ይበልጥ አበዛው፤ ምክንያቱም ይህ የመጀመሪያ ልጃቸው ነበር፤ አባትና እናቱም አርጅተው ነበር። የዘካርያስና የኤልሳቤጥ ወዳጆች ሁሉ ሊጠይቋቸውና እግዚአብሔር በሰጣቸው ልጅ ከእነርሱ ጋር ደስ ሊላቸው መጡ።

ጠያቂዎቹም «በአባቱ ስም ዘካርያስ ተብሎ ሊጠራ ይገባዋል» አሉ።

እናቱም «አይሆንም፤ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል» ብላ መለሰች።

እነርሱም «ይህን ስም ለምን ትሰጪዋለሽ? ከዘመዶችሽ መካከል ዮሐንስ የተባለ አንድም ሰው የለም» አሉ።

ኤልሳቤጥ ግን ልጅዋ ዮሐንስ የሚለውን ስም እንዲይዝ አጥብቃ ተናገረች።

መልአኩ በቤተ መቅደስ ባነጋገረው ጊዜ ዘካርያስ ዲዳ እንደ ሆነ ታስታውሳላችሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ወራት ሁሉ አንድም ቃል አልተናገረም። የሚባለውንም መስማት አይችልም ነበር፤ ስለዚህ የሕፃኑ ስም ማን እንዲሆን ሊጠይቁት በምልክት አነጋገሩት። የመጻፊያ ሰሌዳም አመጡለት፤ እርሱም በላዩ «ስሙ ዮሐንስ ነው» ብሎ ጻፈ። መልአኩ ገብርኤል እንደ ተናገረው የዚህ የተስፋ ልጅ ስም ዮሐንስ ሆነ።

የመጻፊያ ሰሌዳ ምንድር ነው ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። በዚያ ዘመን ወረቀት በጣም ጥቂትና ዋጋው ውድ ነበር፤ ለከባድ ጉዳዮች መጻፊያ ብቻ ይውል ነበር። ለዕለት ተዕለት ጥቅም ግን እያንዳንዱ ቤተሰብ የመጻፊያ ሰሌዳ ነበረው፤ ይህም ቀጭን የሰም ሽፋን የተለበጠበት ሳንቃ ነበር። መጻፍ የፈለጉትን ከብረት ወይም ከአረብ ብረት በተሠራ ሹል ብዕር በዚህ ሰም ላይ ይቀርጹ ነበር። ይህ ዓይነቱ ብዕር ስታይለስ ይባል ነበር። የብዕሩ ሌላኛው ጫፍ እንደ ዝሆን ጥርስ ወረቀት መቁረጫ ጠፍጣፋ ነበር። ከጻፉም በኋላ ሁሉን መልሰው ያለሰልሱት ነበር፤ ሰሙም እንደ ገና ለመጻፊያ ይዘጋጅ ነበር።

ዘካርያስ «ስሙ ዮሐንስ ነው» የሚለውን ቃል እንደ ጻፈ ወዲያውኑ የመስማትና የመናገር ኃይሉ ተመለሰለት። በታላቅ ድምፅም እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመረ፤ የደስታም መዝሙር ዘመረ። ይህ መዝሙር በኋላ ተጽፎአል፤ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል በመጀመሪያው ምዕራፍ መጨረሻ አካባቢ ሊነበብ ይችላል።

ዘካርያስ በዚህ መዝሙሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ ባረከና ከጥንት ጀምሮ በነቢያት ሁሉ አፍ በስሙ የተሰጡትን ተስፋዎች ስለ ጠበቀ አመሰገነው። ነቢያት ምናልባት እንደምታውቁት የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በእግዚአብሔር ኃይል እየተናገሩ ለሕዝቡ የሚያደርሱ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፤ አንዳንድ ጊዜም ገና ሳይደርሱ ብዙ ዘመን አስቀድመው ስለሚሆኑ ታላላቅ ነገሮች ይናገሩ ነበር። እነርሱም እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እንዳየው እንደ ሙሴ፥ እንደ ጠቢቡ ገዥ እንደ ሳሙኤል፥ የእሳት ነቢይ እንደ ሆነው እንደ ኤልያስ፥ የክርስቶስን መምጣት ከዘመኑ ብዙ አስቀድሞ እንደ ተናገረው እንደ ኢሳይያስ ያሉ ሰዎች ነበሩ። በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለሕዝቡ የሚነግር ነቢይ ሁልጊዜ ነበር። ብሉይ ኪዳን ከተፈጸመ ጀምሮ ግን፥ ከዚህ ጊዜ አምስት መቶ ዓመት ያህል አስቀድሞ፥ የጌታን ቃል ይዞ በእስራኤል የተነሣ ነቢይ አልነበረም።

ዘካርያስ ይህ አዲስ የተወለደ ሕፃን አድጎ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ እንደሚያደርስ ያውቅ ነበር። በመዝሙሩም እንዲህ አለ፦

«አንተም ሕፃን ሆይ፥ የእግዚአብሔር ነቢይ ትባላለህ፤
መንገድን ታዘጋጅለት ዘንድ በጌታ በክርስቶስ ፊት ትሄዳለህና፤
ለሕዝቡም የመድኃኒትን የምሥራች ትሰጣለህ፤
የኃጢአታቸውንም ስርየት፥
ከእግዚአብሔር ርኅሩኅ ምሕረት የተነሣ።»

ሕፃኑ ዮሐንስ በዘካርያስና በኤልሳቤጥ ቤት ብርቱና ክቡር ልጅ ሆኖ አደገ። ገና በልጅነቱ ስለ መልአኩ መምጣትና በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ እንዳይቀምስ ስለ ተሰጠው ትእዛዝ ነገሩት። ለእግዚአብሔር ልዩ አገልግሎት በስእለት ወይም በቃል ኪዳን የተለየ ነበር፤ የስእለቱም አንዱ ምልክት የወይን ጠጅ አለመቅመሱ፥ ወይን ፍሬም እንኳ አለመብላቱ ነበር። ሌላው ምልክት ደግሞ ጠጉሩን ሳይቆርጥ ማሳደጉ ነበር። ያየው ሁሉ በእነዚህ ምልክቶች ለእግዚአብሔር ለተለየ አገልግሎት የተሰጠ ሕይወት እንዳለው ያውቅ ነበር።

ዮሐንስ ጎልማሳ በሆነ ጊዜ ከቤቱ ወጥቶ በምድረ በዳ ተቀመጠ፤ በዚያም ከሐሳቡና ከእግዚአብሔር ጋር ብቻውን ኖረ። ብቻውን ለመኖር ከመሄዱ በፊት አባቱና እናቱ ሳይሞቱ አልቀሩም፤ በተወለደበት ጊዜ አረጋውያን ስለ ነበሩ ብዙ ዓመት ሊኖሩ አይችሉም ነበርና።

ዮሐንስ እጅግ ተራ በሆነ ምግብ ይኖር ነበር፤ ይህም ከሜዳ የሚሰበሰበውና ተቀቅሎ ድሆች የሚበሉት አንበጣ ነበር። የበረሀ ንቦች ሠርተው በዛፍ ጉድጓድና በዓለት ስንጥቅ ያከማቹትን ማርም ይበላ ነበር። ዮሐንስ በጉልምስናው ዓመታት ሁሉ እግዚአብሔር ስለ ጠራው ሥራ እያሰበ፥ ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገረና ፈቃዱን እየተማረ ኖረ፤ ይህም ጊዜው ሲደርስ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ ማድረስ እንዲችል ነበር።


ቀዳሚ ቀጣይ