የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በገንዘቡ ላይ ያለው ምስል

ምዕራፍ 78 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

በገንዘቡ ላይ ያለው ምስል

የኢየሱስ ጠላቶች ምናልባት በአገሩ ላይ በሚገዙት በሮማውያን ገዦች ላይ አንዳች ቃል እንዲናገር ሊያደርጉት እንደሚችሉ አሰቡ። ይህን ቢያደርግ ለሮማዊው አገረ ገዥ ከስሰው ኢየሱስ እንደ ሮም መንግሥት ጠላት እንዲያዝና ወደ ወኅኒ እንዲገባ፥ ወይም እንዲገደል እንኳ ሊያደርጉ ይችሉ ነበር። እነዚህ ካህናትና ፈሪሳውያን አለቆችም ራሳቸው ሮማውያንን ይጠሉ ነበር፤ ቢደፍሩም የሮምን ቀንበር በደስታ ከላያቸው ይጥሉ ነበር፤ ነገር ግን በእነርሱ በኩል ኢየሱስን ማጥፋት ከቻሉ ብቻ ለሮማውያን ጌቶቻቸው ወዳጅ መስለው ለመታየት ፈቃደኞች ነበሩ።

ይህን ዓላማ በልባቸው ይዘው ኢየሱስ በዚያ ማክሰኞ ጠዋት በቤተ መቅደስ ሳለ፥ ኢየሱስ ከዚህ ቀደም አግኝቷቸው የማያውቅ፥ ቅኖችና እውነተኞች የሚመስሉ ሰዎችን ወደ እርሱ ላኩ፤ ራሳቸው ቢመጡ ኢየሱስ ወዲያው ዕቅዳቸውን ተረድቶ ከእነርሱ እንደሚጠነቀቅ ያውቁ ነበርና። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኑ ሁሉን እንደሚያውቅ፥ የሰውንም ልብ ሁሉ መመልከትና አሳባቸውን ሁሉ ማንበብ እንደሚችል አላወቁም ነበር።

ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በቤተ መቅደስ ወደ ኢየሱስ መጡ፤ መጀመሪያም ሞገሱን ለማግኘት የሽንገላ ቃል ሊናገሩት ሞከሩ።

«መምህር ሆይ፥» አሉ፤ «ቅን እንደ ሆንህና እውነትን እንደምትናገር እናውቃለን፤ ማንንም እንደማትፈራ፥ ሰውንም ደስ ለማሰኘት እንደማትሞክር፥ ነገር ግን ትክክል የሆነውን ብቻ እንደምትናገር እናውቃለን። የሚያስጨንቀን አንድ ጥያቄ አለ፤ እንዴት እንደምንመልሰው አናውቅምና። ትክክለኛ መልስ እንደምትሰጠን እናውቃለንና ስለዚህ ወደ አንተ አመጣነው። እንግዲህ ስለ እርሱ ምን እንደምታስብ ንገረን። ሕዝባችን በአገሩ ላይ ለሚገዙት ለሮማውያን ገዦች ግብር መክፈል ተገቢ ነውን? እንክፈል ወይስ አንክፈል?»

ይህ በእርግጥ ለመመለስ ከባድ ጥያቄ ነበረ፤ በተለይም ለማሰብ ጊዜ ሳያገኙ ወዲያው ለመመለስ። ኢየሱስ «ግብሩን አትክፈሉ» ቢል ሮማውያን እንደ መንግሥታቸው ጠላት ይዘው ምናልባትም ይገድሉት ነበርና፤ ግብር ለመክፈል እምቢ በማለታቸው ብቻ ብዙዎችን ይዘው ገድለው ነበርና። በዚያን ጊዜም እንኳ ይህን ግብር ላለመክፈል እየሞከሩ በመቶ የሚቈጠሩ ሰዎች ከሮማውያን ተሸሽገው በዋሻዎችና በጫካዎች ይኖሩ ነበር። በሌላ በኩልም ኢየሱስ «ግብሩን ክፈሉ» ቢል ተራው ሕዝብ ሁሉ ይነሣበት ነበር፤ አይሁድ ሁሉ የሮም ኃይል በላያቸው ላይ እንዳለ ምልክት የሆነውን ይህን ግብር ይጠሉ ነበርና፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ ሰው የሚከፍለው የሮማዊውን አገረ ገዥና የሮማውያንን ወታደሮች ስለ ፈራ ብቻ ነበር።

ኢየሱስ ግን ሴራቸውንና ዕቅዳቸውን ሁሉ ተረዳ፤ መልሱንም አዘጋጅቶ ነበር።

«እናንተ ቅኖች መስላችሁ የምትታዩ፥ ልባችሁ ግን የተንኰል የሆነ ሰዎች!» አለ፤ «በወጥመድ ልትይዙኝ ለምን ትሞክራላችሁ? የግብሩን ገንዘብ አሳዩኝ!»

እነርሱም አንድ የብር ገንዘብ፥ የሮማውያንን ሳንቲም አመጡለት። እርሱም አጥብቆ ተመለከተውና እንዲህ ብሎ ጠየቀ፦

«በዚህ ገንዘብ ላይ የማየው ይህ ምስል የማን ነው? በዙሪያውስ ያሉት ቃላት ምንድን ናቸው?»

«ይህማ የሮማውያን ንጉሠ ነገሥት የጢባርዮስ ቄሣር ምስል ነው፤ እነዚያም ቃላት የማዕረግ ስሙ ናቸው።»

«እንግዲያስ» አለ ኢየሱስ፤ «የቄሣርን ለቄሣር ስጡ፤ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር መስጠትን አትርሱ።»

ለሮም መንግሥት ጠላትነትን ወይም ወዳጅነትን እንደሚያሳይ አድርገው ሊያቀርቡት የሚችሉት ምንም ነገር በዚያ መልስ ውስጥ አልነበረም፤ ኢየሱስንም በሕዝቡ ፊት ለመክሰስ የሚጠቅማቸው አንዳች ነገር አልነበረበትም። እነዚህ ሰዎችም በኢየሱስ መልስ እየተደነቁ ትተውት ሄዱ።


ቀዳሚ ቀጣይ