የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ሦስት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች

ምዕራፍ 77 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

ሦስት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች

ኢየሱስ ለካህናቱና ለአለቆቹ ጥያቄ መልስ ከሰጠ በኋላ ወዲያው አንዱን ከሌላው አስከትሎ ሦስት ምሳሌዎችን ተናገረ፤ ሁሉም ወደ ጠላቶቹ ያነጣጠሩ ነበሩ። የመጀመሪያው «የሁለቱ ልጆች ምሳሌ» ነበር።

«ምን ይመስላችኋል?» አለ ኢየሱስ። «ሁለት ልጆች የነበሩት አንድ ሰው ነበረ። ወደ ታላቁ ልጅ ሄዶ ‹ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሄደህ በወይኑ አትክልት ሥራ› አለው። ጐበዙም ‹እሺ ጌታዬ፤ እሄዳለሁ› አለ። ነገር ግን ሊሄድ ቃል ቢገባም ቃሉን አፈረሰ፤ አልሄደምና።»

«ከዚያም አባቱ ለፊተኛው እንደ ተናገረ ሁለተኛውን ልጁን እንዲሁ ተናገረው፦ ‹ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሄደህ በወይኑ አትክልት ሥራ።› ይኸኛው ግን አባቱን ‹አልሄድም› አለው። በኋላ ግን ተጸጸተ፤ ሊሠራም ወደ ወይኑ አትክልት ሄደ። እንግዲህ ንገሩኝ፤ ከእነዚህ ከሁለቱ ልጆች አባቱ እንዳዘዘው ያደረገ የትኛው ነው?»

እነርሱም «ሁለተኛው» ብለው መለሱለት።

«እውነት እላችኋለሁ» አለ ኢየሱስ፤ «ከሌሎች ይልቅ እንደምትሻሉ ራሳችሁን የምትቈጥሩ እናንተ ሳትሆኑ ቀራጮችና ክፉ ሴቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እየገቡ ነው። መጥምቁ ዮሐንስ መጥቶ እንዴት እንደምትኖሩ አሳያችሁ፤ እናንተ ግን አላመናችሁትም፤ እንዳለውም አላደረጋችሁም። ቀራጮችና ክፉ ሴቶች ግን አመኑት፤ ከክፉ መንገዳቸውም ተመልሰው ወደ እግዚአብሔር ዞሩ። እናንተም ከክፉ ወደ መልካም ሲመለሱ ባያችሁ ጊዜ እንኳ እነርሱን ተከትላችሁ እግዚአብሔርን ልትፈልጉና የዮሐንስን ቃል ልትከተሉ አልወደዳችሁም።»

ከዚያም ኢየሱስ ለእነዚህ አለቆች «የክፉዎቹ ገበሬዎች ምሳሌ» የተባለውን ሌላ ምሳሌ ነገራቸው።

«ሌላ ምሳሌ ስሙ» አለ። «መሬት የነበረው አንድ ሰው በላዩ የወይን አትክልት ተከለ። በዙሪያውም አጥር አጠረ፤ በውስጡም መጭመቂያ ቈፈረ፤ ጠባቂም ከሌቦች ይጠብቅ ዘንድ በአትክልቱ መካከል ግንብ ሠራ። ከዚያም እንዲንከባከቡት ለገበሬዎች አከራየው፤ ወይኑ በሚበስልበትም ጊዜ ከፍሬው ድርሻውን ወይም ዋጋውን በገንዘብ እንዲልኩለት ተዋዋለ። አትክልቱንም ካከራየ በኋላ ወደ ሌላ አገር ሄደ።»

«የወይን መከር ጊዜ፥ ማለትም ወይኑ የሚለቀምበት ጊዜ በቀረበ ጊዜ፥ ከፍሬው ድርሻውን እንዲቀበሉ ባሪያዎቹን ላከ። ገበሬዎቹ ግን የእርሱ የሆነውን ከመስጠት ይልቅ ባሪያዎቹን ያዙ። አንዱን ባሪያ ገርፈው አባረሩት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሦስተኛውንም በድንጋይ ወገሩት። ባለቤቱም ሁለተኛ ጊዜ ከፊተኞቹ የበዙ ሌሎችን ባሪያዎች ላከ፤ ገበሬዎቹም እንዲሁ አደረጉባቸው። ከብዙ ሌሎችም ጋር እንዲሁ ሆነ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ፥ አንዳንዶቹንም ገደሉ።»

«የወይኑ አትክልት ባለቤት እጅግ አድርጎ የሚወደው አንድ ጐበዝ ልጅ ነበረው። በመጨረሻም ‹ልጄንስ በእርግጥ ያከብሩታል፤ ባሪያዎቹንም እንዳደረጉባቸው አያደርጉበትም› ብሎ ይህን ልጁን ወደ እነርሱ ላከ።»

«እነዚያ ሰዎች ግን ባዩት ጊዜ ‹አባቱ ሲሞት የወይኑ አትክልት ባለቤት የሚሆን ይህ ነው። ኑ እንግደለው፤ የወይኑም አትክልት የእኛ ይሆናል› ተባባሉ። ስለዚህ በመጣ ጊዜ ይዘው ገደሉት፤ ሬሳውንም ከወይኑ አትክልት ውጭ ጣሉት።»

«እንግዲህ እጠይቃችኋለሁ» አለ ኢየሱስ፤ «የዚያ የወይን አትክልት ባለቤት በመጣ ጊዜ በእነዚያ ገበሬዎች ላይ ምን ያደርግባቸዋል?»

እነርሱም «እነዚያን ክፉዎችና ጨካኞች ሰዎች ፈጽሞ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት በየዓመቱ ከፍሬው ድርሻውን ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራየዋል» ብለው መለሱለት።

ኢየሱስም «ይህን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?» አለ፦

«ግንበኞች የናቁት ድንጋይ
እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤
ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥
ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው።»

«እላችኋለሁ» ብሎ ኢየሱስ ጨመረ፤ «የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች፤ ፍሬዋንም ለእግዚአብሔር ለሚያመጣ ሕዝብ ትሰጣለች። አዎን፥ በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል!»

የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን አለቆችም እነዚህን ምሳሌዎች በሰሙ ጊዜ በእነርሱ ላይ እንደ ተነገሩ ወዲያው ዐወቁ። ኢየሱስንም ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ተራው ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚናገር ነቢይ ይቈጥሩት ነበርና በዙሪያው ያለውን ሕዝብ ፈሩ።

ኢየሱስ ሦስተኛ ምሳሌ ሰጠ፤ እርሱም «የንጉሡ ልጅ ሰርግ» የሚለው ነው። ይህ በቤተ መቅደስ የተነገረው ምሳሌ በአንዳንድ ክፍሎቹ ቀደም ብሎ በፔሪያ የሰጠውን «የታላቁ ግብዣ ምሳሌ» የተባለውን ሌላ ምሳሌ ይመስል ነበር፤ ሌሎቹ ክፍሎቹ ግን፥ እንደምናየው፥ ከዚያ ምሳሌ የተለዩ ነበሩ።

«ለልጁ ሰርግ ታላቅ ግብዣ ያደረገ አንድ ንጉሥ ነበረ» አለ ኢየሱስ። «ወደ ግብዣው የተጠሩትን እንዲጠሩ ባሪያዎቹን ላከ፤ እነርሱ ግን ሊመጡ አልወደዱም። ደግሞም ሌሎችን ባሪያዎች ልኮ ለተጠሩት እንዲህ በሉ አላቸው፦»

«‹እነሆ፥ ግብዣዬ ተዘጋጅቷል፤ በሬዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ተዘጋጅቷል፤ ወደ ሰርጉ ኑ።›»

«እነርሱ ግን ቃሉን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው ሌላውም ወደ ንግዱ ሄዱ። አንዳንዶቹም ባሪያዎቹን ይዘው አንገላቱአቸው፤ እስከ መግደልም ደረሱ። ይህም ንጉሡን እጅግ አስቈጣው። ሠራዊቱንም ልኮ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።»

«ከዚያም ንጉሡ ባሪያዎቹን ‹የሰርጉ ግብዣ ተዘጋጅቷል፤ የተጠሩት ግን የሚገባቸው አልነበሩም። ወደ ከተማው ጎዳናዎችና ወደ አገሩ መንገዶች ውጡ፤ ያገኛችሁትንም ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ› አላቸው። ባሪያዎቹም ወደ መንገዶች ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም ደጎችንም ወደ ግብዣው አመጡ። እንዲሁም የሰርጉ ግብዣ በብዙ እንግዶች ተሞላ።»

«ንጉሡም እንግዶቹን ሊያይ በገባ ጊዜ በመካከላቸው የሰርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየ። እያንዳንዱ እንግዳ ወደ ቤቱ ሲመጣ በግብዣው ላይ የሚለብሰው ያማረ ልብስ ይሰጠው ነበርና።»

«ንጉሡም ይህን ሰው ‹ወዳጄ ሆይ፥ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?› አለው።»

«ሰውየውም የሚለው ስላልነበረው ዝም አለ። ንጉሡም ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦»

«‹ይህን ሰው እጁንና እግሩን አስራችሁ ከቤት ውጭ ወደ ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት። በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና እላችኋለሁ።›»


ቀዳሚ ቀጣይ