ምዕራፍ 76 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ማክሰኞ ጠዋት በቤተ መቅደስ
በዚያች ታላቅ ሳምንት፥ ማለትም መድኃኒታችን በምድር ላይ በኖረበት የመጨረሻው ሳምንት፥ ማክሰኞ ጠዋት ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከቢታንያ ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። በደብረ ዘይት ላይ ሲወጡም ኢየሱስ በቀደመው ቀን ጠዋት ወደ ተናገራት በለስ ደረሱ። በኮረብታው ጥግ ቆማ ነበር፤ ነገር ግን ደርቃና ሞታ ነበር፤ የደረቁ ቅጠሎቿም ወደ ቢጫነት ተለውጠው በነፋስ ይንኰሻኰሹ ነበር።
«መምህር ሆይ፥ ተመልከት!» አለ ጴጥሮስ፤ «ትናንት እነዚያን ቃላት የተናገርሃት በለስ ፈጽሞ ደርቃለች!»
«በእግዚአብሔር እመኑ» ብሎ ኢየሱስ መለሰ። «እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ማንም በፊታችን ያለውን ይህን ተራራ ‹ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር› ቢለው፥ በልቡም ሳይጠራጠር የሚለው እንደሚሆን ቢያምን ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ እግዚአብሔርን የምትለምኑትን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጣችሁ እመኑ፤ የእናንተም ይሆናል። ነገር ግን ይህን ደግሞ በልባችሁ ያዙ፤ ለጸሎት በቆማችሁ ጊዜ ሁሉ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። ያን ጊዜ፥ ያን ጊዜ ብቻ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ በእርሱ ላይ የሠራችሁትን ኃጢአት ይቅር ይላችኋል።»
ደግሞም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ የአሕዛብንም አደባባይ አቋርጠው አለፉ። አደባባዩ አሁን ጸጥ ያለና ከቀደመው ቀን ጠዋት ሁከት የጸዳ ነበር፤ መግዛት፥ መሸጥ፥ ወደ ከተማውም ሸክም ተሸክሞ በዚያ ማለፍ አልነበረም። ኢየሱስ በቀደመው ቀን ወዳስተማረበትና ወደ ፈወሰበት ወደ መዝገብ ቤት ገቡ፤ የታላቁን መምህር ቃል እንደ ገና ለመስማት ተስፋ አድርገው በተሰበሰቡ ሰዎች አስቀድሞ ተሞልቶ አገኙት።
ነገር ግን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለኢየሱስ ወዳጆች የሆኑና እርሱን ለመስማት የጓጉ ሰዎች ብቻ አልነበሩም፤ የካህናት አለቆች፥ የሕግ መምህራንና የታላቁ ሸንጎ አባላትም በዚያ ነበሩ፤ በእርሱም ላይ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተው ነበር። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ በቀደመው ቀን ባደረገው ነገር እጅግ ተቈጥተውበት ነበር። ሕዝቡን እየገፉ ወደ ኢየሱስ ቀረቡ፤ በጌትነት መልክም እንዲህ አሉት፦
«እዚህ መጥተህ እንደ ገዥ የምታደርገው በምን መብት ነው? ትናንት ያደረግኸውን ታደርግ ዘንድ ይህን መብት ማን ሰጠህ?»
«እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ» ብሎ ኢየሱስ ወዲያው መለሰ፤ «ያንን ብትመልሱልኝ እኔም እዚህ በቤተ መቅደስ ያደረግሁትን አደርግ ዘንድ መብት የሰጠኝ ማን እንደ ሆነ እነግራችኋለሁ። ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ምን ትላላችሁ? የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መልእክተኛው ሆኖ ተናገረን? ወይስ ከእግዚአብሔር ሥልጣንና ኃይል ሳይኖረው የራሱን ቃል ብቻ ተናገረ? ያንን ጥያቄ መልሱልኝ!»
በዚህ በኢየሱስ መልስ ደነገጡ፤ በዙሪያቸውም ያለው ሕዝብ እየተመለከታቸው እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር።
«ምን እንበል?» ብለው እርስ በርሳቸው ተንሾካሾኩ። «‹መጥምቁ ዮሐንስ ከእግዚአብሔር ተናገረ› ብንል፥ ‹እንግዲያስ ስለ ምን ቃሉን አላመናችሁም፥ አልታዘዛችሁለትምም?› ይለናል። አይሆንም፤ ‹ከእግዚአብሔር ሥልጣንና ኃይል ሳይኖረው እንደ ሰው ብቻ ተናገረ› እንበል። ነገር ግን ያንን ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደ ነበረ ያምናሉና በድንጋይ ይወግሩናል።»
ስለዚህ ጥቂት ቆይተው እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን «ጥያቄህን ልንመልስ አንችልም። ዮሐንስ የተናገረው የእግዚአብሔርን ቃል ወይም የራሱን ቃል እንደ ሆነ አናውቅም» አሉት።
ኢየሱስም «እኔም እነዚህን ነገሮች አደርግ ዘንድ ኃይልን የሰጠኝ ማን እንደ ሆነ አልነግራችሁም» አለ።
እነዚህ ሰዎች መጥምቁ ዮሐንስ «ጌታ እንዲህ ይላል» ባለ ጊዜ ካላመኑ፥ እርሱ «አባቴ እንዳደርግ የሚነግረኝን ብቻ አደርጋለሁ» ሲል እንደማያምኑት ኢየሱስ በሚገባ ያውቅ ነበርና።