ምዕራፍ 73 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
የአልባስጥሮሱ ቢልቃጥ
ከኢያሪኮ ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስደው መንገድ በጣም አቀበታማ ሆኖ ተራራውን ወደ ላይ የሚወጣ የዐሥራ አምስት ማይል ጕዞ ነበር፤ በመንገዱም ዳር በዓለቶቹ መካከል ተሸሽገው በሚቀመጡት ወንበዴዎች ምክንያት ብዙ ጊዜ አደገኛ ነበር። በፋሲካ ጊዜ ግን ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች ወደ በዓሉ ስለሚወጡ፥ ሕዝቡ በአንድነት በብዛት ይጓዝ ስለ ነበረ መንገዱ የሰላም ነበር። ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱና ወደ ፋሲካ ከሚሄዱ ከብዙ ሕዝብ ጋር በዚህ መንገድ ወጣ። ነገር ግን በቀጥታ ወደ ኢየሩሳሌም አልሄደም፤ ወደ ከተማዪቱ በቀረበ ጊዜ ፈቀቅ ብሎ ወዳጆቹን ማርታንና ማርያምን አልዓዛርንም ለመጐብኘት በቢታንያ መንደር ዐረፈ። ኢየሱስን አሁን በማየታቸው እጅግ በጣም ደስ አላቸው፤ ከጥቂት ወራት በፊት በመጨረሻ በጐበኛቸው ጊዜ አልዓዛርን ዳግመኛ በሕይወት እንዲኖር ከመቃብሩ እንደ ጠራው ታስታውሳላችሁ።
ኢየሱስ ወደ ቢታንያ የመጣው ፋሲካ ሊከበር ስድስት ቀን ሲቀረው በዓርብ ቀን ነበር። በዚያም ስምዖን በተባለ ሰው ቤት ለኢየሱስ ክብር እራት ተዘጋጀ። ይህ ስምዖን ለምጻም ነበረ፤ ኢየሱስ ግን ፈውሶት ነበር፤ ስለዚህ ለኢየሱስ ፍቅሩንና ክብሩን የሚያሳይበት የራሱ ምክንያት ነበረው። በእራቱም ላይ እንግዶቹ ራሳቸውን ወደ ማዕዱ፥ እግራቸውን ደግሞ ከማዕዱ ወደ ውጭ አድርገው በመደገፊያዎች ላይ ተደግፈው ተቀመጡ፤ የሚያገለግሉትም ምግቡንና መጠጡን ለእንግዶቹ ያዞሩ ነበር። በማዕዱ ከሚያገለግሉት መካከል የአልዓዛር እኅት ማርታ ነበረች።
በማዕዱ ራስ ባለው መደገፊያ ላይ በመካከል ግብዣውን ያዘጋጀው ስምዖን ተደግፎ ነበር። በቀኙ በክብር ስፍራ ኢየሱስ ነበረ፤ በግራውም አልዓዛር ነበረ። በጐን ባሉት ማዕዶች ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና ሌሎች እንግዶች ተደግፈው ነበር።
ድንገትም የአልዓዛር እኅት ማርያም ወደ ቤቱ ገባች። አልባስጥሮስ የሚባለውን ዓይነት ከእብነ በረድ የተሠራ ቢልቃጥ በእቅፍዋ ይዛ ነበር። መክደኛው የታተመ ነበር፤ ማርያም ግን ማኅተሙን ሰበረች፤ ወዲያውም ብርቱ መዓዛ በአየሩ ላይ ተነሣ፤ በግብዣው አዳራሽ ብቻ ሳይሆን በቤቱ ሁሉ ተሰራጨ፤ ቢልቃጡ እጅግ መልካም መዓዛ ባለውና ውድ በሆነ ሽቱ ተሞልቶ ነበርና። ማርያምም እንግዶቹ በተደገፉባቸው በማዕዶቹና በመደገፊያዎቹ መካከል ባለው መተላለፊያ ወደ ፊት ሄደች። በኢየሱስ ፊት ለፊት ደርሳ ከሽቱው ጥቂቱን በራሱ ላይ አፈሰሰች፤ ከዚያም መደገፊያውን ዞራ የቀረውን በእግሩ ላይ አፈሰሰች፥ በትከሻዋ ላይ በተዘረጋው ረጅም ጠጕርዋም እግሩን አበሰች።
በቤቱ የነበረ ሁሉ ማርያም ባደረገችው ነገር ተደነቀ፤ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦
«ይህ እንዴት ያለ ጥፋት ነው? ያ የሽቱ ቢልቃጥ ቢያንስ ሃምሳ ዶላር ያወጣ ነበር እኮ! ተሽጦ ገንዘቡ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበር!»
ይህን የተናገረው ጌታውን ለጠላቶቹ ለካህናት አለቆችና ለአለቆቹ አሳልፎ ለመስጠት አስቀድሞ ያሰበው ክፉው ደቀ መዝሙር የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበር። ይሁዳ የኢየሱስና የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ገንዘብ ያዥ ነበር። ሁሉም እንደ አንድ ቤተ ሰብ ይኖሩ ነበር፤ ገንዘባቸውንና ደግሞ ወዳጆቹ ለኢየሱስ የሰጡትን ገንዘብ ሁሉ በአንድ ከረጢት ያኖሩ ነበር። ይህን ከረጢት ይሁዳ ይይዝ ነበር፤ እርሱ ግን ሌባ ነበረ፤ ለራሱም ሊጠቀምበት ከገንዘቡ ይሰርቅ ነበር። ይሁዳ ያ ሁሉ ውድ ሽቱ በኢየሱስ ራስና እግር ላይ ሲፈስ ባየ ጊዜ ተቈጣ፤ ለራሱ ሊያስቀረው ይችል የነበረ ገንዘብ እንደ ባከነ አድርጎ ቈጥሮታልና።
ኢየሱስም፦ «ይህችን ሴት ስለ ምን ትነቅፉአታላችሁ?» አለ። «ለእኔ መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። ይህን ሽቱ በሥጋዬ ላይ ባፈሰሰች ጊዜ በቅርብ ለሚሆነው ለመቃብሬ አደረገችው። እላችኋለሁ፥ ወንጌሌ በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት ስፍራ ሁሉ የዚህች ሴት ሥራ ይነገራል፤ በእርሱም ምክንያት ትታሰባለች።»
የኢየሱስ ወዳጆች ሁሉ በቅርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ መንግሥቱን እንዲያቆምና እንዲገዛ ይጠብቁ ነበር። ስለ መሞቱና ከሙታን ስለ መነሣቱ የተናገረውን ቃል አላስተዋሉም ነበር። ከሁሉም መካከል ግን ማርያም ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚሞት ዐወቀች፤ ይህንም ያደረገችው ወንድምዋን ወደ ሕይወት ስለ መለሰላት ፍቅርዋን ለማሳየት ብቻ አልነበረም፤ በቃል የማትናገረውን፥ ጌታዋ በቅርቡ እንደሚሞትና እንደሚቀበር የሚገልጠውን ነገር በእጅግ ርኅራኄ በሥራ ለማሳየት ነበር።
ከዚህ እራት በኋላ ማርያምንና ስጦታዋን የነቀፈው ደቀ መዝሙር የአስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን ለጠላቶቹ አሳልፎ ሊሰጥ በልቡ በጸጥታ ወሰነ። ኢየሱስ እርሱ እንደ ተመኘው ያለ ንጉሥ እንደማይሆን አየ፤ ደግሞም ስርቆቱ እንደ ታወቀ ወይም ቢያንስ እንደ ተጠረጠረ መፍራት ጀምሮ ነበር። በስውርም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ አለቆቹ ሄዶ እንዲህ አላቸው፦
«ኢየሱስን በእጃችሁ አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትከፍሉኛላችሁ?»
እነርሱም ይህን በመስማታቸው ደስ አላቸውና፦ «ሠላሳ ብር እንሰጥሃለን» አሉት።
ይህም በእኛ ገንዘብ ከሃያ ዶላር ጥቂት የሚያንስ ነበር፤ ለአንድ ባሪያም የሚከፈል ዋጋ ነበር። እስቲ አስቡት፤ የምድር ሁሉ ጌታ በባሪያ ዋጋ ከመረጣቸው ተከታዮቹ በአንዱ ተሸጠ!
ይሁዳ ከካህናቱ ጋር በሚደራደርበት ጊዜ ብልጥ ነበር። ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጣቸው በኋላ ገንዘቡን እንዳያታልሉት ፈራ። ስለዚህ እንዲህ አለ፦
«ገንዘቡን አሁን ክፈሉኝ፤ ጊዜው ሲደርስ የናዝሬቱን ኢየሱስን እንዴት እንደምትይዙት አሳያችኋለሁ።»
ሠላሳውንም ብር ለይሁዳ ሰጡት፤ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ይሁዳ ኢየሱስን በጠላቶቹ እጅ አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።